በጣም ዘግይተሻል ወያኔ! [ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው]

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

“You are late!” ይላል ፈረንጅ በመዘግየቱ ያለቀለት ነገር ሲያጋጥመው፡፡ አንዳንድ ጓደኞቸ የሰሞኑን የብሔራዊውና ወያኔ ክልል በማለት የሚጠራው የሀገር ክፍል የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ (ነርሃላዊ) የብዙኃን መገናኛዎች የሚያቀርቧቸውን ነገሥታትንና ታሪካችንን አወዳሽ፣ ዘካሪ፣ አክባሪ ዝግጅቶች እያዳመጡ “ዝግጅቶቹን እንዴት አገኘሀቸው?” ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ሲመስለኝ እነኝህ ዝግጅቶች እየቀረቡ ያሉት በአማርኛ በሚቀርበው የብሔራዊው ጣቢያ ዝግጅቶችና ወያኔ የአማራ ክልል በማለት በሚጠራው የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የመንግሥት ሬዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ጣቢያዎች ላይ ነው፡፡ እንደ ኦሮምኛና ትግርኛ በመሳሰሉ ቋንቋዎች በሚያቀርቡ ጣቢያዎች ተመሳሳይ ዝግጅቶች መቅረባቸውን በእጅጉ እጠራጠራለሁ፡፡

እኔ የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች ከመገናኛ ብዙኃን መርሖ (Principle) እና ሥነ ምግባር (Ethics) ውጭ ከሚዛናዊነት ጋር ተቆራርጠው የሀገሪቱንና የሕዝቧን ጥቅም እጅግ በሚጎዳ አቅጣጫ አጥብቀው በመንጎድ ከሀገርና ሕዝብ ጥቅም በተፃራሪ የቆመውን የወያኔን ዕኩይና ነውረኛ ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ለፋፊ ቱልቱላ ሆነው መቅረታቸውን ከተረዳሁ ወዲህ አዳምጨም ተከታትየም አላውቅምና የሆነውን ነገር ለመረዳት እነሱኑ መልሸ መጠየቅ ነበረብኝ፡፡

ለካ ወያኔ ሆየ ሰሞኑን በብዙኃን መገናኛዎች ለ26ዓመታት አርቃ ለመቅበር ጥልቅ ጉድጓድ ስትቆፍርለት የኖረችውን፣ ከትምህርት ሥርዓቱም አሽቀንጥራ የጣለችውን የታሪክን ነገር በጥሩ ጥሩ ዝግጅቶች ስታዜምና ስትተርክ ሰንብታ ኖሯል፤ ሰውም ይሄ መሆኑ ገርሞት ነው መጠያየቁ፡፡ አንዳንድ ተላሎች ወገኖቻችንም በእነኝህ ዝግጅቶች በመደሰት የቀረቡ ዝግጅቶችን በመጽሐፈ ገጽ መዝገባቸው (በፌስቡክ አካውንታቸው) ላይ ተጋርተው ለጥፈውታል፡፡ መቸስ ይገርማል! እንግዲህ ወያኔ በጥልቅ ስለታደሰች በጥልቅ መታደሷ ያመጣው ለውጥ ይሆናላii ኪኪኪኪኪ…

መስሏቹሀል! ከወያኔ ይሄንን የምትጠብቅ ጅልና ተላላ ዜጋ ካለህ ሳትበላ ብትነቃ ይሻልሀል!! በብዙኃን መገናኛዎች የቀረቡት አንዳንዶቹ ዝግጅቶችማ የምር ወያኔ የተፀፀተና ለመታረምም የቆረጠ የሚያስመስል ነው፡፡ ወያኔ ሲናዘዝ “በትውልዱ ላይ ለደረሰው የሞራል (የቅስም) ዝቅጠት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት መጥፋት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ (ብሔረሰቦች) መሀከል ለተፈጠረው የእርስበርስ ጥላቻና መለያየት፣ በጠላትነት መፈላለግ መተያየት፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት መጥፋት ወዘተረፈ. ተጠያቂው እኔ ነኝ!፣ ይህ ውጤት እንዲፈጠር አድርጌአያለሁ!፣ ሕዝብን እንዲህ በቁጣ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ያደረገው ለዘመናት ሲደርስበት ሲፈጸምበት የቆየው የአሥተዳደር በደል ነውና ተቃውሞውን ማሰማቱ አግባብ ነው!” ወዘተረፈ. እስከማለት መድረሳቸውን ላየ ከልብ መፀፀታቸውንና መመለሳቸውን ለማመን ሳይዳዳው የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ቆይ እንጅ እኔ የምለው! የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን ማኅበራዊና የማንነት ቀውስ ወያኔ እንዲያስመዘግብ፣ በደል እንደጉድ እንዲፈጽም ነበር በ26 ዓመታት ውስጥ አምስት ጊዜ በተደረጉ እንከን የለሽና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ምርጫዎች በተደጋጋሚ ሲመርጠው የኖረው ማለት ነው??? መቸም እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ካልሆነ ደግሞ ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአምስቱም ምርጫዎች “እኔን መርጧል!” ማለቱ ሐሰት ነበር ማለት ነው፡፡

እኔ የሚገርመኝ ወያኔ ይሄንን ሁሉ ቀውስና ኪሳራ በማስመዝገቡ በሕዝብ እንደተጠላና እንዳልተፈለገ ካወቀው ታዲያ ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላም እንዴት ሆኖ ነው “አሁንም እኔው እቀጥላለሁ እንጅ ለሌላ አላስረክብም!” ሊል የሚችለው? እስከፈለገበት ጊዜ ድረስ ረግጦ ቀጥቅጦ እንዲገዛ ሥልጣንን በዓጽመ ርሥትነት ለወያኔ ማን ነው የሰጠው? የኢትዮጵያ ሕዝብ “በቃኸኝ! አልፈልግህም!” እያለ ባለበትም ሰዓት መንግሥት የመቀየር፣ ሌላ የማየት መብትና ሥልጣን የለውም ማለት ነው? “ሌላ እፈልጋለሁ!” ማለት አይችልም ማለት ነው? ማን ነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይሄንን ሊለው የሚችለው? በምንስ አግባብ? አገዛዙ በስብሻለሁ! እያለም ሕዝቡ እንደበሰበሰ እያወቀ በበሰበሰና በገማ አገዛዝ የመገዛት ግዴታ አለበት ማለት ነው? እኮ በምን አግባብነት ያለው ምክንያት? በበሰበሰና በገማ አሥተዳደር የመገዛት ግዴታን በዚህ ሕዝብ ላይ የጣለበት ማን ነው? ሕዝብስ ይሄንን ጉዳይ በጸጋ መቀበል አለበት?

ተላሎች ሆይ! ይሄ የሰሞኑ የብዙኃን መገናኛዎች አቀራረብ እውነተኛና ዘላቂ እንዳይመስላቹህ! በምንም ተአምር ከወያኔ ይሄንን እንዳትጠብቁ! ወያኔን ከእኩይነት መለየት ማጥራት ማለት ከሰልን አጥቦ ከጥቁረቱ እንደማጥራት እንደመለየት ማለት ነው! ይቻላል እንዴ? ይህች ይህች የሰሞኑ መቅለስለስ ከጭንቀት የመጣች ናት እንጅ በፍጹም በፍጹም ከመፀፀትና ከመታረም የመጣች አይደለችም!

እንደምታስታውሱት ከዓመታት በፊት “ወያኔ አፍጥጦ ከመጣበት ጥፋት ለመዳን የማያደርገው ነገር፣ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ነግሬያቹህ ነበረ፡፡ ወያኔ ፍላጎቱን ለማሳካት፣ ጥቅሙን ለማስከበር፣ ህልውናውን ለማስቀጠል ሲችል እንደወንድ ተንቀባሮ ተጀንኖ በማስገደድ፤ ሳይችል ደግሞ እንደውሻ ከእግር ስር ተልከስክሶ ተልሞስሙሶ በመቅለስለስ ህልውናውን ለማስጠበቅ፣ ጥቅሙን ለማስከበር የማያደርገው ነገር የለም! ብያቹህ ነበረ፡፡

የኦባማ አሥተዳደር ከወያኔ ጋር ሲበሻቀጥ ከርሞ በቅርቡ በተደረገው ምርጫ ፈጽሞ ፈጽሞ  ያልጠበቀው ሽንፈት አጋጥሞት በወያኔ እንደረከሰ ነጩን ቤተመንግሥት መልቀቁ ሞት ሆኖበት፣ ለታሪኩ አስቀያሚ ጠባሳ ሆኖበት፣ ይሄም እጅግ አሳስቦት ባለቀ ሰዓት ወያኔን አስጨንቆ ይዞታል፡፡ ወያኔ እንደምንም ብላ ጥር ለመድረስ ጥረት እያደረገች ነው፡፡ “ጥር ላይ ግን የኦባማ አሥተዳደር ለተመራጮቹ ለነ ትራምፕ ሥልጣኑን አስረክቦ ተጠራርጎ ውልቅ ስለሚል ከዚያ በኋላ ምንም ሊያመጣ አይችልምና አሁን አንዳንድ ትዕዛዞቹን እየፈጸምኩና በዚያ እየደለልኩ ጥር ላይ ልድረስ!” በማለት እየዶለተች ትገኛለች፡፡ የኦባማ አሥተዳደር ምን ያህል እንደሚሳካለት እናያለን፡፡

እንግዲህ ወያኔ እያሳየው ያለው መቅለስለስና መለማመጥ እነ ኦባማ ስለጨከኑባት አማራጭ ስላጣች ነው እንጅ የተጠያቂነት ስሜት ወይም ተፈጥሮ ኖሯት “ሕዝቡ እምቢ! ካለ ምን አደርጋለሁ? ጨርሸ አልፈጀው ነገር!” ብላ ለሕዝብ እምቢተኝነት እጅ ሰጥታ እራሷን ስላረመች አይደለም እየተቅለሰለሰችና እየተለማመጠች ያለችው፡፡

እራሷን አዋርዳ እግራቸው ስር እንደ ውሻ እየተልሞሰሞሰች ከጎኗ እንዲቆሙ ያደረገቻቸው መንግሥታት በወራዳና ኢሰብአዊ ግፏ ትልቅ ትዝብት ላይ ስለጣለቻቸው፣ ስላጋለጠቻቸው ለስማቸው፣ ለታሪካቸው ሲሉ ጨከን ስላሉባትና ፊት ስለነሷት ነው አሁን ልትደልልና አፍጥጦ ከመጣባት ጥፋት እራሷን ለማዳን ለከት ባልነበረው ንቀትና ጥላቻ ስትረግጠው፣ ግፍ ስትሰፍርበት ከኖረችው የኢትዮጵያ ሕዝብ እግር ስር እንደውሻ እየተልሞሰሞሰች የምትገኘው፡፡ ገና ከዚህም የከፋ ጭንቅና መጋለጥ ቢያጋጥማት ያለ አንዳች ሐፍረትና መሸማቀቅ ዓይኗን በጨው አጥባ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንጀት ለመብላት “በፍጹም ምሕረት የማይገባኝ ወራዳ ወንበዴ ነኝና ፍረዱብኝ!” እስከማለት ሁሉ ልትደርስ ትችላለች፡፡ በእነሱ ቤት እነሱ ብቻ ናቸው ብልጥ እኮ!

እንጅ በፍጹም በፍጹም ወያኔ የሚማር፣ የሚመከር፣ የሚፀፀት ልብ ኖሮት ተምሮ፣ ተመክሮ፣ ተፀፅቶ አይደለም!!! ይሄ ላለመሆኑ ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለኝም! ወያኔ ይታረማል፣ ሰው ይሆናል ብለሽ ተስፋ የምታደርጊ ቂላቂል ካለሽ ቁርጥሽን እወቂ! በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ እንደጻፍኩበት ሁሉ ወያኔ እንዳይታረም ሦስት ነገሮች ያግዱታልና ይሄንን ተስፋ ማድረግ ከንቱ ቅዠት ነው፡፡ የሚያግዱት የሚከለክሉት ነገሮች 1ኛ. የሚከተለው ርዕዮተዓለም 2ኛ. ዕኩይ ተፈጥሮው 3ኛ. ለይቅርታና ምሕረት የማይመቹ በሀገርና በሕዝብ ላይ የፈጸማቸው ግፍ፣ በደልና ክህደት ናቸው፡፡

እናም ወያኔን በተመለከተ የተለወጠና ወደፊትም የሚለወጥ፣ ተስፋ የተጣለበትና ወደፊትም የሚጣልበት ምንም ነገር የለም አይኖርምምና ምንም የሚያስቆም ወይም ወደኋላ የሚያስብል ነገር የለም! ትግልህን አጠንክረህ ግፋ! ነው መልእክቴ ወገኔ!

እስከ አሁን ድረስ “የትም አይደርሱም! ተቀጥቅጠው አጉል የትም ለመቅረት፣ ለማለቅ ነው! በከንቱ ለመጥፋት ነው!” እያልክ ሕዝባዊ ትግሉ የትም እንደማይደርስ እየለፈፍክ ዳር ተመልካች የሆንክ ያልነቃህ ዜጋ ሁሉ እባክህን ልብ ግዛና ጊዜ ሳታባክን ቢረፍድብህም ሳይመሽብህ ሕዝባዊ ትግሉን ተቀላቀል! የሚጠበቅብህንም ታሪካዊና የዜግነት ግዴታህን በብርታት ተወጣ! በየት ሀገር ነው ያለመሥዋዕትነት ድል ተገኝቶ የሚያውቀው? ሌላው ቢቀር ማንነትህ ወንጀል ተደርጎብህ በሚታወቅም በማይታወቅም የዘር ማጥፋት ጥቃቶች ተለቅመህ ማለቅህ ካልቀረ ጠላትን ተበቅሎ ማለፍ ብቻ በራሱ ለድል የሚያቀርብ ተግባርና ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሞት ካልቀረ ተዋርዶ ከመሞት ለክብሩ ለነጻነቱ ታግሎ የክብር ሞት መሞት ትልቅ ጀብድ ነው፡፡ እናም እባካቹህ ዳር ተመልካቾች ሆይ ኧረ ንቁ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.