የዘመን መለወጫ እና የጌታ ልደት ቀናት ለምን በአንድ ቀን ሳይውሉ ቀሩ? አዲስ ዓመትስ የሚገባው ስንት ሰዓት ላይ ነው? – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 

ሳተናው
By ሳተናው September 10, 2017 01:33

ምንም እንኳ ሰላምም፣ ጤናም ምንም በሀገር ባይኖር ከዚህች ሀገርና ሕዝቧ ጠላት ቅስፈት ሠውሮ ጠብቆ ለዚህ ዓመት ያደረሰንን አምላክ ማመስገን ይኖርብናልና እንኳን ለ፳፻፲ (2010) ዓ.ም. በሰላም አደረሳቹህ! ፈጣሪ አምላክ መድኃኔዓለም ክርስቶስ አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የድል፣ የነጻነት፣ የእድገት፣ የብልጽግና ያድርግልን አሜን!!!

በርእሱ መጀሪያ ላይ ያነሣሁት ጥያቄ ብዙ ጊዜ ይነሣል፡፡ ቀጥሎ ያለው ጥያቄ ደግሞ ተራቀቅን የሚሉ ሰዎች የተሳሳተ መላምታቸውን ለማስተላለፍ ሲሉ የሚያነሡት ጥያቄ ነው፡፡ የዘመን መለወጫ እና የጌታ ልደት ቀናት ለምን በአንድ ቀን ሳይውሉ ቀሩ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ተብሎ የሚቀርበው ምላሽም “ሊቃውንቱ ቀናቱን ከወቅቶች ጋር ለማስማማት ሲሉ በዓላቶችን አሁን በምናከብራቸው ቀናት ላይ እንዲውሉ አድርገዋቸዋል!” የሚል ሲሆን ይሄ ምላሽ ደግሞ ከሁለቱ በዓላት አንዱ ማለትም ወይ ዘመን መለወጫ ወይ ደግሞ የጌታ ልደት ቀን ቀናቸው ባልሆነ ቀን ላይ እንዲውል ተደርጓል የሚል መረዳትን ወይም ግምትን ፈጥሯል፡፡ ይሁንና የተሰጠው ምላሽም ይሁን ምላሹ የፈጠረው ግምትም ትክክል ነው ብየ አላምንም፡፡ ዘመን መለወጫም ሆነ የጌታ ልደት ቀን በትክክለኛ ቀናቸው ነው እየተከበሩ ያሉት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ጽሑፍ እንዴት? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ ይሁንና ይህ መልሴ ይሆናል ብየ የገመትኩት ነው እንጅ “ቀናቱ የተለያዩበት ምክንያቱ ይሄ ነው ሌላ ምንም ምክንያት የለም!” ብየ በእርግጠኝነት መናገሬ እንዳልሆነ ልብ ይሏል!

ነገሩ እንዲህ ነው፦ ጥያቄው “ጌታ የተወለደው ልክ ዓለም ከተፈጠረ 5500 ዘመንን ቆጥሮ ከዕለቷ ዕለትን ከሰዓቷ ሰዓትን ሳያሳልፍ ከሆነና የእኛ የዘመን አቆጣጠርም ትክክለኛ ከሆነ የጌታ የልደት ቀን እንዴት መስከረም አንድ ቀን ሳይሆን ቀረ? ለምን ታኅሣሥ 29 ሆነ?” የሚል ነው፡፡ መነሣት ያለበትም ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጥያቄ የዘመን መለወጫን ወይም የጌታን ልደት ቀን ከሁለቱ አንዱን የተሳሳተ ያስመሰለው እራሱ ጥያቄው በተሳሳተ አረዳድ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑ ነው ስሕተቱ የሚጀምረው፡፡ ነገ ለምሳሌ በእኛ አቆጣጠር የ2010ዓ.ም. መባቻ ነው፡፡ ከላይ ያነሣነውን ጥያቄ በሌላም መልክ ስናቀርበው “ዓመተ ምሕረትን የምንቆጥረው የጌታን ልደት ቀን መነሻ በማድረግ ከሆነ ለምንድነው ታዲያ ዓመተ ምሕረታችንን በጌታ ልደት ቀን የማንቀይረው? ለምን መስከረም አንድ ቀን እንቀይራለን?” የሚልም ነው፡፡

የጥያቄው ስሕተት ምንድን ነው? ካላቹህ ዓመተ ዓለምን በዚህም ላይ ተመሥርቶ ዓመተ ምሕረትን ለመቁጠር መሠረት ሆኖ የሚያገለግለው የጌታ ልደት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም በአምስት ቀን ተኩል (5500) ዘመን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገብቶለት ስለነበረ ከጌታ ልደት በፊት ያለው ዘመን ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዓመት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ጥያቄው ታዲያ ይሄንን የዓመተ ዓለም የዘመን ልኬት በተሳሳተ አረዳድ በመያዝ የሚሰነዘር በመሆኑ ነው ነገሩን የተሳከረ ያደረገው፡፡

እንዴት? እንዴትማ ጥያቄው የሚጠየቀው ይህ እግዚአብሔር ለአዳም “በአምስት ቀን ተኩል (በ5500) ዘመን!” ብሎ የተናገረውን ስፍረ ዘመን ዓለም ከመፈጠሯ ቅጽበት ጀምሮ የተቆጠረ ዘመን እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር መሰንዘሩ ነው ስሕተቱ፡፡ እንደኔ እምነት የአምስት ቀን ተኩሉ (የ5500) ዘመን ቁጥሩ መነሻ እግዚአብሔር ለአዳም “በአምስት ቀን ተኩል (በ5500) ድንግል ከምትሆን ከልጅ ልጅህ ተወልጀ አድንሀለሁ!” ብሎ ቃል ኪዳን ከገባለት ቅጽበት ነው የሚጀመረው ወይም የሚነሣው እንጅ 7 ዓመት ከወራት ወደኋላ ተመልሶ ዓለም ከተፈጠረችበት ቅጽበት አይደለም የሚጀመረው ወይም የሚነሣው ባይ ነኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የዓመተ ዓለም ወይም የዘመን መለወጫ መባቻና የጌታ ልደት ወይም የዓመተ ምሕረት መባቻ ቀናት ሊለያዩ የቻሉት እንጅ በዓላቱን ከወቅቶች ጋር ለማጣጣም ሲባል ትክክለኛ ቀናቸው ስለተቀየረ አይደለም፡፡

የዘመን መለወጫ ወይም የዓመተ ዓለም (እኛ በዘልማድ ዓመተ ምሕረትን የምንቀይርበት) ቀን የሚቀየረው መስከረም አንድ ነው፡፡ የጌታ ልደት ቀን ወይም ዓመተ ምሕረት የሚቀየረው ደግሞ በታኅሣሥ 29 ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በየአብያተክርስቲያናቱ መስከረም አንድ ቀን አዋጁን ሲያውጁ “ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ዛሬ ይሄንን ያህል ዘመን ሆኗል!” ብለው ነው እንጅ የሚያውጁት “ጌታ ከተወለደ ዛሬ ይሄንን ያህል ዘመን ሆነ!” ብለው አይደለም፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ዓመተ ዓለምን ትተን ዓመተ ምሕረትን መስከረም አንድ ላይ እየቆጠርን የምናብተው ወይም የምንጀምረው? ከተባለ እኛ ኢትዮጵያውያን መስከረም አንድ ላይ ዘመን መለወጥን የጀመርነው ጌታ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ ነው “ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ይሄንን ያህል ዘመን ሆነ!” እንል የነበረው፡፡ ይሄ የዘመን ቀመርም ትክክለኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ሊቃውንቱ ታዲያ “ይሄንን ለሽዎች ዓመታት ስንቆጥር ስናብተው የኖርነውን የዓመተ ዓለም መባቻ በዓል መስከረም አንድ ቀንን እና አዲሱን ስፍረ ዘመን የጌታን የልደት ቀን ወይም ዓመተ ምሕረትን በታኅሣሥ 29 ቀን እያባትን ወይም እያስገባን አዲስ የስፍረ ዘመን በዓል በመጨመር በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት የዘመን መለወጫ በዓል እያከበርን ሰውን ግራ ከምናጋባው የጌታን ልደት ወይም ዓመተ ምሕረትን ሕዝቡ በዘመን መለወጫነቱ በሚያውቀው በነባሩ ዓመተ ዓለም ስንቀይርበት በነበረው በዓል መስከረም አንድ ዕለት እንቁጠርበት!” ብለው ሊቃውንቱ በመወሰን የጌታን ልደት ቀን ወይም ዓመተ ምሕረት ከሚብትበት አራት ወራት ቀድሞ መስከረም አንድ ቀን እየባተ እንዲቆጠር አደረጉ፡፡ ይሁንና ዘመኑን ከላይ በገለጽኩት ምክንያት መስከረም ላይ መጥቶ እንዲቆጠር ያድርጉ እንጅ እንደሚታወቀው የጌታ ልደት በዓል የሚከበረው ግን በታኅሣሥ 29 ነው፡፡ በዘመነ ዮሐንስ ግን የዘመነ ሉቃስ ጳጉሜ 6 ስለምትሆንና አንድ ቀን ስለምትስብ የጌታ ልደት በ28 ይሆናል፡፡

በመሆኑም ዓመተ ምሕረት ወደ ዓመተ ዓለም ተወስዶ መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር የተደረገበት ምክንያት ከላይ የነገርኳቹህ እንዳለ ሆኖ ሁለቱም ማለትም መስከረም አንድ የምናብተው የዓመተ ዓለም ስፍረ ዘመን መባቻ እና የጌታ ልደት ቀን በየትክክለኛ ቀናቸው ነው እየተከበሩ ያሉት ማለቴ ነው፡፡ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው እግዚአብሔር ለአዳም ቃል ኪዳን ከገባለት ቅጽበት ጀምሮ ነው እንጅ ወደኋላ ተመልሶ ዓለም ከተፈጠረችበት ቅጽበት ጀምሮ አይደለም የሚቆጠረው፡፡ ይሄ መሆኑ ነው ዓመተ ዓለምንና ዓመተ ምሕረትን በተለያዩ ቀናት ላይ እንዲውሉ ያደረጋቸው፡፡ በመሆኑም ከጌታ ልደት በፊት ያለውን የዓመተ ዓለምን ስፍረ ዘመን መናገር ካስፈለገ አዳም የስድስተኛው ቀን ፍጥረት ነውና 6 ቀናት + አዳም ገነት ከመግባቱ በፊት ከተፈጠረበት ደብር ቅዱስ የቆየበት 40 ቀናት + አጥፍቶ እስኪባረር ድረስ ገነት የቆየበት 7 ዓመታት ከ 1ወር ከ17 ቀናት + ከገነት ተባሮ ሱባኤ ገብቶ አምላክ ተገልጾለት ቃል ኪዳን እስከገባለት ቀን ድረስ 41 ቀናት = ድምሩ 7 ዓመታት ከ4 ወራት ከ14 ቀናትን ከ5500 ስፍረ ዘመን ላይ ጨምሮ መናገር ይገባል ማለት ነው፡፡ ይሁንና ይህ 7 ዓመት ከወራት እየተዘነጋ ዓመተ ዓለም ሲነገር የሚነገረው 5500 ዘመኑ ብቻ ነውና ሊቃውንቱ ይህችን ዓመት ባይዘነጓት መልካም ነው፡፡ ባሕረ ሐሳቡ የበዓላቱንና የአጽዋማቱን መባቻ የሚያወጣው ስፍረ ሰዓትን፣ አበቅቴን፣ መጥቅንና አዕዋዳትን በመጠቀም በመሆኑ የዚህች የተዘነጋች ሰባት ዓመት ተጨምራ መነገሯ የሚፈጥረው ችግር አይኖርም፡፡ አይ አይደለም! የሚለኝ ቢኖር ሁለቱ ስፍረ ዘመን ለምንና እንዴት በተለያዩ ቀናት ሊከበሩ ወይም ሊውሉ እንደቻሉ በሚገባ አብራርቶ ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡

በነገራችን ላይ የዚህ 5500 ስፍረ ዘመን ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ይሄ ብቻ ነው ብለን በዘልማድ በምንጠቅሰው መጽሐፍ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ገላ.4፥4 ላይ “… ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ!” በማለት እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው ስፍረ ዘመን እንዳለ ከመጠቆሙ በስተቀር የተገለጸ ነገር የለም፡፡ መናፍቃን ከየት አምጥተው እግዚአብሔር ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት 5500 ዘመኑ ሲፈጸም ጌታ እንደተወለደ ሊያምኑ እንደቻሉ ይገርመኛል፡፡ ይህ ነገር ከነዝርዝር ታሪኩ የተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ ከሚያደርጉት የቤተክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት (መጽሐፍ ቅዱሶች) አንዱ በሆነው አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ደግሞ መናፍቃኑ ከማይቀበሏቸው የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ታዲያ ጌታና አዳም የተባባሉትን፣ ጌታ ከአዳም ጋር ምን ስለተባባሉ 5500 ዘመኑን ቆጥሮ ሊወለድ እንደቻለ ከየት አምጥተው አሟልተውት ነው ሊያምኑ የቻሉት? ካመኑ የቤተክርስቲያንን ቅዱሳት መጻሕፍትን ተቀብለው አሟልተው ማመን ነው፡፡ ካላመኑ ደግሞ አለማመን ነው፡፡ ምንድን ነው እንደዚህ መውለብድበድ?

አዲስ ዓመት የሚገባው ወይም የሚብተው ስንት ሰዓት ላይ ነው?

አንዳንድ መምህራንና ዕውቅና ያለቸው ሰዎች እኛ ዘመንን የምንቆጥርበት ዓውደ ዓመት የፀሐይ ማለትም 365 ቀናት ከ 15 ኬክሮስ (6 ሰዓት) መሆኑን በማውሳት “የአዲስ ዓመት መግቢያ ሰዓት በአንድ የተወሰነ ሰዓት ላይ ሳይሆን በየዓመቱ የስድስት የስድስት ሰዓታት ልዩነት ሊኖረው ይገባል!” በማለት እየተቀባበሉ በየድረ ገጹ ጽሑፍ እየጻፉ ሲያራግቡት ተመልክቻለሁ፡፡ ይሄም ማለት ለምሳሌ ዘንድ ከንጋቱ 12 ሰዓት ገብቶ ከሆነ ከርሞ ደግሞ ከቀኑ 6 ሰዓት የሚቀጥለው ደግሞ ከምሽቱ 12 ሰዓት ለይ እንደገና የሚቀጥለው ደግሞ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ መሆን አለበት ማለታቸው ነው፡፡

ነገር ግን ይህ አባባላቸው ስሕተት ነው፡፡ እንዲህማ ከተደረገ እኮ ጳጉሜ በየ አራት ዓመቱ በዘመነ ሉቃስ ስድስት መሆኗ ይቀራል እኮ! ጳጉሜን በየ አራት ዓመቱ 6 እያደረግን የምንቆጥረው እኮ ዓመቱን በ365ኛ ቀኑ ያለ ተጨማሪው ስድስት ሰዓታት በተመሳሳይ ሰዓት እያስገባን ወይም እያባትን የየዓመቱን ተጨማሪ ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኬክሮስ ወይም ስድስት ስድስት ሰዓታት አጠራቅመን ስለምንመጣ እኮ ነው በአራተኛ ዓመቱ አንድ ቀን ወይም 24 ሰዓታት ሲሞላ ጳጉሜን 6 የምናደርገው፡፡ ከስድስት ሰዓትም የቅጽበት ያህል የምትተርፍ በጣም ጥቂት ሰዓት አለች በስድስት መቶ ዓመታት ተጠራቅማ 24 ሰዓት የምትሞላ፡፡ ያን ጊዜ ጳጉሜ 7 ትሆናለች፡፡

በየዓመቱ ስድስት ስድስት ሰዓታቱን ትተን በ365ኛው ቀን በተመሳሳይ ሰዓት ዓመቱን ማባት ትተን ስድስት ስድስት ሰዓታቱን ጨምረን በመቁጠር ስድስት ስድስት ሰዓታት ወደፊት እየገፋን ዓመቱን የምናስገባ ወይም የምናብትና የምንቆጥር ከሆነማ ጳጉሜን 6 ማድረግ አንችልም አኮ፡፡ ምክንያቱም መጠራቀም የነበረበትን ስድስት ስድስት ሰዓታት ሳናጠራቅመው ከየዓመቱ ጋር ቆጥረን አሳልፈነዋልና ነው፡፡ ቆጥረን ካሳለፍነው ደግሞ የሚጠራቀምና በአራተኛ ዓመቱ አንድ ቀን የሚሞላ ስድስት ስድስት ሰዓታት አይኖረንም ማለት ነው፡፡ ከሌለን ደግሞ በአራት ዓመታት አንዴ ጳጉሜን ስድስት ማድረግ አንችልም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚያ መምህራን እየተቀባበሉ ከላይ የተናገሩት በየ ድረገጹ የጻፉት ነገር ሳያስተውሉ የተሳሳቱት አስተሳሰብ በመሆኑ ሊከተላቸው ያሰበ ሰው ቢኖር ከእርምጃው ይቆጠብ፡፡ እንዲያ እያሉ ተቀባብለው ያናፈሱ አንዳንድ መምህራንና አንዳንድ ታዋቂ ሰዎችም ስሕተታቸውን ተረድተው ታርመው እንዲቀመጡ እጠይቃለሁ፡፡

ታዲያ አዲስ ዓመቱ የሚገባው ስንት ሰዓት ነው ከተባለ የአላፊው ዓመት የጳጉሜ 5 ወይም 6 ምሽት 12 ሰዓት መጠናቀቂያና የአንድ ሰዓቱ መግቢያ የመጀመሪያ አሐዲት (ሰከንድ) ላይ ነው የሚገባው፡፡ ያም ማለት 12:00 ላይ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለም ሲፈጠር የመጀመሪያው ቀን የጀመረው ከብርሃኑ ወይም ከንጋቱ ሳይሆን ከምሽቱ ወይም ከጨለማው ስለሆነ ነው ዘፍ. 1፥ 1-5 ፡፡ ነገር ግን በዓሉን በምሽት ወይም በጨለማ ለማክበር ስለማይመች እስኪነጋ ጠብቀን ንጋቱ ላይ ነው በዓሉን የምናከብረው፡፡ ቤተክርስቲያንም አዋጁን የምታውጀው ንጋቱ ላይ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

ሳተናው
By ሳተናው September 10, 2017 01:33
Write a comment

2 Comments

  1. Wonchifu September 10, 10:36

    ውድ ወንድሜ መስከረም ፩ ንግስት ሳባ ከንጉስ ሰለሞን ልጅ ጸንሳ የተመለሰችበትን ቀን. እንች እንቁ ለጣጣሽ እያሉ ስለተቀበሏት እንጅ እርስዎ እንዳሉት እንዳልሆነ የታሪክ መዛግብት ነግረውናል::

  2. ገሞራው ተ/ብርሃን September 11, 03:08

    አይ አምሳሉ ያንተን ጽሁፍ እንኳን አላምንም፤ ስለምትዋሽ፤ ሌላ አዋቂ ሰው የጻፈው መስሎኝ ነው ያነበብኩት።

View comments

Write a comment

Your e-mail address will not be published.
Required fields are marked*

ትኩስ ዜናዎችን ቀድመው ለማግኘት ይመዝገቡ.

ሳተናው ሰበር ዜና - ማወቅ መብትዎ ነው!Archives