የዘር እልቂቱ ምክንያቱ የዘር ፖለቲካው ነው #ግርማ_ካሳ

ሳተናው
By ሳተናው September 13, 2017 22:47

ቤልጄሞች ለመግዛት እንዲያመቻቸው በሁቱዎችና በቱትሲዎች መካከል የዘር ግጭትና መቃቃር እንዲኖር አደረጉ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ የጋራ ማንነታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ሩዋንዳዎች ዘራቸውና ጎሳቸው ላይ አተኮሩ። መታወቂያቸውም ላይ ከየት ዘር እንደሆኑ ይጻፍ ነበር።፡ ልክ አሁን በአገራችን ኢትዮጵያ እንዳለው።  ሩዋንዳ በጦርነት በምትታመስበት ጉዜ መታወቂያ እየታየ፣ የይትኛው ዘር እንደሆነ እየተለየ ነበር የሰው ልጅ ይገደል የነበረው።

በአገራችን ኢትዮጵያም ህወሃት ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው፣ ኢትዮጵያዉያን ታሪካዊ ዝምድናቸውና ትስስራቸው ላይ እንዳያተኩሩ በማድረግ  በዘር ከፋፈላቸው። አገሪቷን በዘር ሸንሽኖ ይሄ ቦታ የኦሮሞ፣ ያ ቦታ የሶማሌ፣ እዚያ ማዶ የትግሬ እያለ ሁሉም አጥሩን አበጅቶ፣ እንዳይግባባ፣ እንዳይተማመን አደረገ።

ከዚህ ፖሊሲ የተነሳ በርካታ ኢትዮጵያዉያን አማራ ናችሁ ተብለው ከሌሎች የኢትዮጵያ ግዛት በግፍና በጭካኔ ተፈናቅለዋል። አንዴ፣ ወይም ሁለቴ አይደለም። ላለፉት 25 አመታት እየተደጋገመ። ወደ ኋላ ከሄድን እንደ በደኖና አርባ ጉጉ ያሉትን ቦታዎች መጥቀስ እንችላለን። ወደ ቅርብ ጊዜ ደግሞ ከመጣን ከጉሩፈርዳ፣ በበኔሻንጉል፣ እንደ ምእራብ ሸዋ፣ ጊምቢ ባሉ ቦታዎች ዜጎች “አማራ ናችሁ” ተብለው ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።ከቃያቸውም በግፍ ተፈናቅለዋል።

ኢሰመጉ በቂ መረጃዎችን በማሰባሰብ አቅርቦት የነበረዉን ሪፖርት ብቻ መመልከት ይበቃል፡

“በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ የአማራ ተወላጆች የተለያየ ዓይነት ሰብሎችን በመዝራት ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ክልሉን በአጠቃላይ ለአገሪቱ ገበያ የሚቀርብ ምርት በማምረት የሚታወቁ ውጤታማ አርሶ አደሮች ነበሩ። ይሁንና በአካባቢው የሚገኙ ባለሥልጣናትና የጸጥታ ኃፊዎች እነዚህን አርሶ አደሮች “እናንተ የዚህ አካባቢ ተወላጅ ሳትሆኑ ሀበት እያፈራችሁ የአካባቢው ተወላጅ ግን ከእናንተ ያነሰ ገቢ ያላቸው ናቸው፤ ይህን ገቢ ያገኛችሁት በእኛ መሬት ላይ ነው፤ ስለዚህ የክልሉ ተወላጆች ባለመሆናችሁ ክልሉን ለቃችሁ ውጡ” በማለት ንብረታቸውን በተለያየ ጊዜ በመንጠቅ እነዚህን አርሶ አደሮች በተለያየ ጊዜ ለእስራት ዳገዋቸዋል። የአካባቢውን ሕዝብም “በእናንተ መሬት ነው ሀብት ያፈሩት” እያሉ ጥላቻና ግጭትን ሲሰብኩ እንደቆዩ በሰመጉ በ136ኛ መግለጫና ምስክርነታቸውን በሰጡ አርሶ አደሮች ተነግሯል”  ሲል ነበር ኢሰመጉ በኖኖ የነበረዉን ሁኔታ የተነተነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ኦሮሞዎች ልክ እንደ ሩዋንዳ፣ መታወቂያቸው እየታየ ፣ ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ከቅያቸው በግፍ ሲፈናቀሉ እያየን ነው።

የኦሮሚያ ሕግ መንስት አንቀጽ ስምንት ኦሮሚያ የኦሮሞዎች እንደሆነች ነው በግልጽ የሚያስቀምጠው። በኦሮሚያ የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነው ሌላው ኢትዮጵያ በኦሮሞዎች ፍቃድ የሚኖር “እንግዳ” ወይም መጤ እንደሆነ ነው ሕጋዊው የኦሮሚያ ክልል ሕግ መንግስት የሚገልጸው። የሶማሌ ክልልም ተመሳሳይ አንቀጽ ነው ያለው። በክልሉ ሕግ መንግስት መሰረት የሶማሌ ክልል የማንም አይደለችም፣ የሶማሌዎች እንጅ። ስለዚህ ኦሮሞው ይሁን ሌላው በሶማሌ ክልል በሶማሌዎች ፍቃድ የሚኖር እንግዳ ነው። ወደ ቤኔሻንጉል ክልል ስንሄድ ደግሞ ኦሮሞና አማራ ነን የሚሉ ሲደመሩ ከ55% በመቶ በላይ ቢሆኑም፣ የክልሉ ባለቤት የጉሙዝ፣ ሸናሽ፣ በርታ፣ ማኦ ብሄረሰቦች ናቸው። ኦሮሞዉን አማራው በቤኔሻንጉል ክልል እንግዳ ነው። መሬቱ አይደለም።

ስለዚህ አማራዎች ከኦሮሚያና ከቤኔሻንጉል ክልል ፣ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል መሬታችሁ አይደለም ተብለው መፈናቀላቸው፣ ኢሰብአዊ የሆነ፣ በአለም አቀፍ ሕግ መሰረት የዘር ማጽዳት ወነጀል ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ሆኖም ግን አንድ ነእግር በትልቁ ሊሰመርበት የሚገባ ነገር አለ። ህወሃት/ኢሕአዴግ በዘረጋው የፌዴራልና የክልል ሕገ መንግስታት መሰረት ኦሮሞዎች የሶማሌና የቤነሻንጉል ክልሎች፣  አማራዎች የኦሮሞያ፣ የሶማሌና የብኔሻንጉል ክልሎች መሬታቸው አይደለም።

ይሄም የሚያሳየን ዘር እየለዩ ፣ መታወቂያ እያዩ ዜጎችን የማጥቃትና የማፈናቀል እኩይ ተግባራት ምንጫቸውና ምክንያታቸው፣  በአገሪቷ በዘር ላይ የተመሰረተው ፌዴራላ አወቃቀርና ሕጎች መሆኑን መረዳት ያስፈላጋል። የችግሩ root cause (ዋና ምክንያቱ) በዘር ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ ነው።

ሩዋንዳዎች አሁን የዘር ነገር ትልቅ ዋጋ ስላስከፈላቸው የዘር ነገርን በጣም የሚጠየፉትና የሚሸሹት ጉዳይ ነው። የዘር ነገር  እጅግ በጣም መጠፎ ነገር ነውና።አገራችን ኢትዮጵያ ፣ዜጎች በአገሪቷ ሁሉ በፈለጉት ቦታ መሬታችን ነው ብለው በነጻነት መኖር የሚችሉባት፣ በዘራቸው ሳይሆን በስራቸው፣በሞያቸው ፣ በብቃታቸው የሚመዘኑባት አገር ካለሆነች እንደ አገር መቀጠል አትችልም።

ሳተናው
By ሳተናው September 13, 2017 22:47
Write a comment

1 Comment

  1. Bill September 14, 13:01

    እውነት ነው ከሩዋንዳዊያን መማር ይገባናል ሰብአዊነት የሚሰማው መሪ እግዚአብሔር ይሰጠን ዘንድ ወደ ፈጣሪ እንፀልይ።

View comments

Write a comment

Your e-mail address will not be published.
Required fields are marked*

ትኩስ ዜናዎችን ቀድመው ለማግኘት ይመዝገቡ.

ሳተናው ሰበር ዜና - ማወቅ መብትዎ ነው!Archives