አረንጓዴው ጎርፍ በሴቶች 5ሺህ ተመለሰ

በቤጂንግ 15ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማጠናቀቂያ በተካሄደው የ5ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አልማዝ አያና፣ ሰበሬ ተፈሪ እንዲሁም ገንዘቤ ዲባባ የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል፡፡ ገንዘቤ በውድድሩ ለድርብ ወርቅ ብትጠበቅም፣ አልማዝ አያና በግሩም አጨራርስ ለወርቅ በቅታለች፡፡ አልማዝ አያና ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ 14:26:83 የሆነ ሰዓት ወስዶባታል፡፡ ሰንበሬ ተፈሪ ደግሞ 14:44:07 በሆነ ሰዓት ጨርሳለች፡፡ በመጨረሻው ዙር ፍጥነቷ ላይ መቀነስ ያሳየችው ገንዘቤ ዲባባ 14:44:14 በሶስተኛነት ያጠናቀቀችበት ሰዓት ነው፡፡ አልማዝ አያና ያስመዘገበችው ሰዓት የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ አልማዝ የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበርም 15 ሰክንድ ብቻ ቀርቷታል፡፡ ሰበሬ ተፈሪ  ከኬንያዎቹ ተነጥላ በመውጣት ከገንዘቤ ጋር ያሳየችው ፉክክር አስደሳች ሆኗል፡፡ በውድድሩ ገንዘቤ ዲባባ ወርቅ በማግኘት ሀገሯን ለድርብ ወርቅ እንደምታበቃ የብዙዎቹ ግምት ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ገንዘቤ ዲባባ በ1ሺህ 5 መቶ ሜትር ሴቶች ለሀገሯ ወርቅ ማስገኘቷ ይታወሳል፡፡

fana24ድሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ በ3 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሐስ ከዓለም 5ኛ ደረጃ መቀመጥ ችላለች፡፡

በጎርጎረሳውያኑ የ2003 የፓሪስ ሻምፒዮና 10ሺ ሜትር ወንዶች ቀነኒሳ በቀለ፣ ሀይሌ ገብረ ስላሴ እና ስለሺ ስህን ተከታትለው በመግባት የአርጓዴው ጎርፍ ስምን ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በ2005ቱ የሄልሲንኪ ሻምፒዮና ደግሞ በሴቶች 5ሺህ ሜትር በጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር እና እጅጋየሁ ዲባባ አማካኝነት የአርንጓዴው ጎርፍ ስም ደምቋል፡፡

አርንጓዴው ጎርፍ ስምን መልሶ ለማግኘት አምስት ሻምፒዮናዎች መጠበቅ ግድ ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን  በቤጅንጉ ሻምፒዮና በአልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪ እና ገንዘቤ ዲባባ አማካኝነት ስያሜውን አድሷል፡፡

በዚህ ውድድር የተገኙት የወርቅ ሜዳሊያዎች በሙሉ በሴት አትሌቶች የተገኙ ናቸው፡፡ የማነ ጸጋየ በማራቶን ብር እንዲሁም ሀጎስ ገ/ህይወት በ5ሺህ ሜትር ወንዶች ነሐስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል፡፡

ይህም ከ2 ዓመታት በፊት በራሺያ በተካሄደው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 10 ሜዳሊያዎች በወንዶች ከተገኙት አንድ ወርቅ ፣ ሶስት ብር እና አንድ ነሐስ ያነሰ ውጤት ሆኗል፡፡

ኬንያ በ7 ወርቅ፣ 6 ብር እና 3 ነሐስ በማግኘት ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሀገር ሆናለች፡፡ ተመሳሳይ ወርቅ ይዛ በብር ሜዳሊያ ተበልጣ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠችው ደግሞ ጃማይካ ናት፡፡  ሻምፒዮናዎችን በቁንጮነት በመጨረስ የምትታወቅው አሜሪካ ደግሞ 6 ወርቅ ይዛ 3ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዳለች፡፡ ታላቋ ብሪታኒያ በአራት ወርቅ አራተኛ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ አምስተኛ ላይ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡

በውድድሩ 32 ሀገራት ራሳቸውን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ማስገባት ችለዋል፡፡

በአዝመራው ሞሴ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.