….የፈረንሳይ ልጆች

ከኮንጎ ሰፈር እድርተኞችና ከ ኑ ቡና ጠጡ ቡድኖች ያጋራኋት ጡሁፌን እናንተም እንዲህ ተጋሯት
መቼም ባልወለድበትም ግማሹን ዕድሜዬን ስለኖኩርበት የፈረንሳይ ልጅ ነኝ ልበል፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ብዙ መለያዎች ቢኖሯትም ከብዙዎቹ የሸገር የድሆች መጠለያ ወፈ ሰማይ የሚሆነውን የድሃ ቁጥር ይዛለች ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም ከዚህ ባለፈ ደግሞ እንደ ሽሮሜዳ ያለ ሰፈሮች አጎራባች ከመሆኗም ባሻገር ብዙ የሚያስተሳስሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች እንዳሉ የሁለቱ ሰፈሮች የፖለቲካና ማህበራዊ ተንታኞች በብዙ ጠጅ ቤቶች ውስጥ ጥናታዊ ወሪያቸውን ሲለግሱን ኖረዋል፡፡
ለመሆኑ የፈረንሳይ ልጅ ለመባል ብዙ መለኪዎች እንዳለ ያውቁ ኖሯል?እስኪ እኔ ከማውቀውና ከትንሹ በጥቂቱ እንዲህ ላውጋችሁ፤ቢያንስ ከነዚህ ውስጥ አንዱን አልያም ሁለቱን ሲሆን ደግሞ ሁሉንም ያልፈፀም ፈረንሳይ አድጌያለሁ ቢል ዘበት ነው፤
እናላችሁ የፈረንሳይ ልጅ ሆኖ አዘነጋሽ ሜዳ ላይ ቅሪላ ያልገፋ፣ ጨፌ ሜዳ ላይ ዋንጫ ያላነሳ፣ ጉራራ ሜዳ ላይ የኳስ ብቃቱን ያልፈተሸ፣ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ያልፈነጨ ፣እስላም መቃብር ላይ ያልተራገጠ፣ቦኖሃ ወርዶ ኳስ ያልጫወተ፣ ከሽሮ ሜዳ ልጆች ጋር ኳስ ያልገጠመ፣ እንዴት የፈረንሳይ ልጅ ነኝ ይላል?
ሌላው ቢቀር ጥንስስ ወርዶ ዋናን ያልለመደ፣ ስድስት ክንድን በ ሰቶ ያላቋረጠ፣ አባ ንጉሱ ላይ ያልተንቦራጨቀ፣ ኩባ ባህር ላይ የኋሊት ያልተንሳፈፈ የፈረንሳይ ልጅ ነኝ ሊል እንዴት ብሎ? አልያም ደግሞ ቀበናን አሳብሮ አጋምና ቀጋ ለቅሞ ያልበላ፣ ዋሻ ሚካኬል ደርሶ በመገናኛ ሜዳ ላይ ያልሮጠ፣ከሾላ ዛፍ ላይ ሾላ አውርዶ ያልበላ፣በልቶም መጥገቡን ለማሳየት ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ያልዘለለ የፈረንሳይ ልጅነትን ጣዕም እንዳላጣጣመ ይወቀው ይረዳው፡፡ በሰፈር ደረጃስ ቢሆን…? ከአቦ ሰፈር ልጆች ጋር፣ ወይም ከቦኖ ውሃ፣ አልያም ደግሞ ከ11 ቀበሌ ልጆች ጋር ግፋ ቢል ከእየሱስ ልጆች ጋር ጠብ ያልገጠመ ፣ያልተጣላ ያልተደባደበ መች ፈረንሳይ ኖረና!
እኛ ፈረንሳዮች የጉርምስና መመዘኛዎች አሉን፡፡መለኪያችንም ለየት ይላል፡፡ አንድ የፈረንሳይ ልጅ ለአቅመ ጉርምስና ሲደርስ ክብደት ይገፋል፣ ካልቻልም ኑሮውን ይገፋል፤ወይም ደግሞ ማርሻል አርት ይሞካክራል ካልሳካለት ደግሞ ዲቪ ይሞክራል፡፡
ወርቁ ጠጅ ቤት ያልተማረ አባት፣ ብሎኬት ገበያ ከእናቷ ጋር ያልሄደች ኮረዳ መቼም ፈረንሳይ አልኖረችም ማለት ነው፡፡ 
የፈረንሳይ ዳገትስ ቢሆን? እንደውም አንድ የሰፈሩ አዛውንት የአርቲስትና ጋዜጠኛ መፍለቂያ የሆነችው ፈረንሳይ አንዳንድ ግጥሞች ተነጥቃለች ይላሉ፡፡ እንደርሳቸው ምሳሌም የመሃሙድ አሕመድ ዜማ የሆነው የትዝታ ግጥም ‹‹ የትዝታን ዳገት ወጣሁት ተክዤ 
በእጄ ምናምኑን በልቤ አንቺን ይዤ ›› የምትለውን ስንኝ ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ ፈረንሳይ በነበረበት ዘመኑ የገጠማት ግጥም ስትሆን መሃሙድ ቀየር አድርጎ ተጠቀማት ብለው ይከራከራሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አባባልም ትክክለኛዋ ግጥም ‹‹የፈረንሳይን ዳገት ወጣሁት ተክዤ 
በእጄ ምናምኑን በልቤ አንቺን ይዤ›› ነበር ይላሉ፡፡ (ይህን የሰማሁት ከእንቅፋት ግሬሰሪ መረጃ ክፍል ነው) ለነገሩ ዳገቱ ዛሬ ለመንገድ ስራ እጁን ሰጥቶ የሰሚንቶ ክምር ተሸክሟል፡፡ ከእሱ ይልቅ ይህ ግጥም ለእየሱስ 41 ሊሰጠው ይገባል እላለሁ፡፡
እንደውም ፈረንሳይ ከሰፋፊ ወንዞቿና ከጥቅጥቅ ደኖቿ ባላነሰ መልኩ የቱሪስት መስዕብ የሚሆኑ የታወቁ ተዳባዳቢዎችና ደብዳቢዎች ነበሯት (የዛሬን አያርገውና)፤ እነ ድሃ ቦርጭ፣ ጌች ደረቱ፣ እነ ደበበን ማን ይረሳል? በነሱ ያልተደበደበ ወይም ከእሱ ወገን ሆኖ ያልተደባደበ የፈረንሳይ ልጅ ፤የፈረንሳይ ልጅ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ከብዙዎቹ በጥቂቱ እነዚህን አልኳችሁ እንጂ ፈረንሳይና ፈረንሳይነት እውቅና ያልተሰጠው ማንነት ይመስል ነበር፣ ዛሬ ግን ፈረንሳይ ብዙ ነገሮቿ ተለውጠዋል፡፡ ከቀደምት ነዋሪዎቿ በበለጠ መልኩ የስደተኞች መሰብሰቢያ ሆናለች፣ተከራዮች ተሰባስበውባታል፡፡ ሌላው ቢቀር የጠቅላላ ሚኒስቴራችንን ወደ ስልጣን መውጣት አጋጣሚ በመጠቀም አንቆርጫ ሰፈር ዳንዴ ቀበሌ የሚባል የወላይታ ተወላጆች ጫካ መንጥረው አዲስ መንደር መስርተዋል፡፡ ከ97ቱ ግርግር በኋላ የፈረንሳይ ነዋሪ እጅጉን በባሰ ድህነት ማቋል፡፡ ምክንያቱን መቼም አትጠይቁኝ፡፡ ቀደምት ነዋሪዎቿ ቁጥራቸው ትንሽ ነው፤አብዛኞቹ ደግሞ ለቀው ሄደዋል፡፡
ፈረንሳይና ፈረንሳይነት በዚህ ከቀጠለ ብዙ ነገሮቹ መጥፋታቸውና የልማት ቀጠና መሆኑ አይቀሬ ነው ይላሉ የልማት መስክ ተንታኝ ሽማግሌዎች፡፡ ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀሱ እንዲሉ ወግ ነው ሲለሙ መጥፋት ብለናታል፤ፈረንሳይን!

zemenic.blogspot

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.