አዲስ ዓመትና ማንነት! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

አዲሱ ዓመት መጣና ፤ ጎረቤቴን የሰፈሬን ልጅ

እንኳን አደረሽ! ብላት ፤ መልካም ምኞቴን ላውጅ

እኛን አያገባንi ብትለኝ ፤ ለምን? ብየ ጠየኳት

አታውቅም ? በእኛ ሃይማኖት ፤ ጃንዋሪ ላይ ነው አዲስ ዓመት

ብላ ብትለኝ ደንግጨ ፤ ሆኘ ቀረሁ የጨው ሀውልት፡፡

አየ አዲስ ዓመት እንቁጣጣሽ ፤ በምድሪቱ ሳይቀር ተበሳሪ

ተፈጥሮ አጅቦ የሚያመጣት ፤ በአበባ ልምላሜው ከባሪ

የእኛ አይደለሽም ተባልሽ ? እዚሁ በምድርሽ በቅሎ

ማዛሽ ማዛው ላይ እየናኘ ፤ ከአፈር አየርሽ ኮብልሎ

ምን ሳይሰማ እንዲሉ ፤ እንዲህም መቷላ ጉድ ፈጦ

መለያን ከስሩ ነቃቅሎ ፤ ልብን ከልብ ላይ ቆርጦ

አሁን ይህችን ልጅ እኅቴን ፤ ማን ናት ምን ብየስ ልጥራት?

እነሱስ ሰባኪዎቿ ፤ ሰላዮቹ የቅኝ ግዛት

ማን ብለው ይሆን ትውልዷን ፤ የሷን ዜግነት የሚያውቁት?

ኢትዮጵያዊት እንዳልላት ፤ የኔ አይደለም አለች እሴቱ

አውሮፓዊት እንዳልላት ፤ የቆዳ ቀለሟ ማሚቱ

መለስ ብየ ባጤናት ፤ ሁሉን ነገራችን ጥላለች

ከስሟ እስከ ባሕሏ ፤ ምዕራባዊ አድርጋለች

የቀረ ነገር ቢኖራት ፤ ያልተቻላት ልትለውጠው

ከልዩ የቆዳ ቀለሟ ፤ ኢትዮጵያዊነቷን ከሚያሳብቀው

እስከ ግርማዊያን ዓይኖቿ ፤ መቅረጸ ምስሉም ከሚፈራው

አካል ሰውተቷ ብቻ ነው ፤ የአምላክ ሥራ የሆነው፡፡

የሕዝቧን ማንነት ቅርስ ፤ የሀገሯን ሀብት ሁለመና

ታሪኬ ቅርሴ እሴቴ ፤ ካላለች ሰጥታ ዕውቅና

ማንነት መለያ ባሕሌ ፤ ብላ ካልጠበቀች ጀግና

እኮ በል ምን ታደርጋለች ፤ በእኛ ስም ደምና ቁመና

በእኛ ሰገነት መድረክ ላይ ፤ በአርያም ባለው ልዕልና፡፡

 

ሃይማኖት ቢቀየር ቢለወጥ ፤ ምን ይሁን የፈቃድ ነውና

ሃይማኖት ቀየርኩ ተብሎ ፤ ማንነት መለወጥ ግና

ይሄ የእብደት ነው ወገኔ ፤ ፍጹም አይደለም የጤና

ሃይማኖት ማለት ለሁሉም ፤ ሲወዱ የሚቀበሉት

ሳይወዱ ደሞ የሚተውት ፤ ነው የማንነት ጉልላት

እንደ አያት ቅምቅማቶችህ ፤ ብትጠብቀው ደግ ነበረ

የማንነት ቅርስ አሻራህ ፤ በእሱ ነውና የታሰረ

ከአንተ ወደዚያ ሄደ እንጅ ፤ በመልከጼዴቅ በዮቶር

ከዚያ እኮ ወዲህ አልመጣም ፤ ሃይማኖት ጥበብ አሥተዳደር

ባለማወቅ ወይ በሌላ ፤ ያን ሃይማኖትህን ብትቀይር

ባሕል ቅርስ መለያህን ግን ፤ እንድትጠብቅ  በፍቅር

ኢትዮጵያዊነትህ ግድ ይልሀል ፤ ዜጋ መሆንህ ለሀገር

ያያትህ አሻራ ነውና ፤ ይኖርበታል መከበር

ይሄ ነው እንግዲህ ማንነት ፤ የራስ መለያ ሀብት ስር፡፡

እንደዚህ አርገህ ካላመንክ ፤ ወጣ ባልክ ጊዜ ለሥራ

ምን ብለህ ልታወጋ ነው ? እኛ እኮ! ብለህ ስታወራ

ፉክክሩ ሲያጋጥምህ ፤ የከኔ ታንሳለህ ፉከራ

መናቅ መገዳደር ሲጋፋህ ፤ ምንም እንደሌለህ ስትጠራ?

አንገትህን ልትደፋ ነው? ምንም እንደሌለው ደሀ?

ባዶ እንደሆነ ሁሉ? አንድ እንደሌለው ዘሀ?

እንዲህ ያደረክ ጊዜ ፤ ልመሳሰል ብለህ ልጠጋ

የሞትከው ያን ጊዜ ነው ፤ ነፍስ የተለየችህ ከሥጋ

የሚንቀሳቀስ በድን ነህ ፤ ግዑዘ አካል ዲንጋ

አለሁ እንዳትል ሞተሀል ፤ በማንነት ቀውስ አደጋ

ለሆድህ ስትል ከካድካት ፤ ማንነትክን ከጣልክ ፈራርሳ

ሰብአዊ እሴት ከሌላቸው ፤ በምን ትለያለህ ከእንስሳ?

በል እራስህን ታዘበው ፤ የሰውነትህን ደረጃ

የብስለትህን ርቀት ፤ በዕውቀት ሚዛን ፍረጃ

ጽናት ጥንካሬ የሌለው ፤ ሆነሀልና ሳር ሙጃ

ሰው ነው በሉኝ እንዳትለን ፤ ምን እንደሆንክም እንጃ፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማለት ፤ በሽ የወረቀት አዋጅ

እንዲህ ሆንኩ እንዲህ ቢሉትም ፤ ለሥጋዊ ሕይዎት እንዲበጅ

የማይለወጥ ቀለም ነው ፤ ጥቁር ቀይዳማ ጠይም

በፍላት የሚንተከተክ  ፣ አካልህን የሞላው ደም

ፍቀህ የማታጠፋው ፤ ተፈስሶ የማይፈጸም

መቸም የማይለዩት ፤ የእግዚአብሔር ማኅተም፡፡

ቆዳየን ገፍፌ ልጣል ፤ ዐይኔንም ጓጉጨ ላውጣ

እንዲህ ሳያሰኛት እብደቷ ፤ ራሷን በአደጋ ሳትቀጣ

ባካቹህ ምከሩ አስተምሩ ፤ ምን ማለት እንደሆን ማንነት

በማንነት ቀውስ ስትናጥ ፤ ምንድን ነው ዝም ብሎ ማየት?

ከመንጋው ጠፍቶ የሔደ ፤ ሌላ ለመሆን የከጀለ

የትም ቢሔድ ባይተዋር ነው ፤ ለብቻው የተነጠለ

ትርፉ ማበድ ብቻ ነው ፤ ከሁለት ሳይሆን የነሆለለ

ከቶም ተለይተሽ ላትለይ ፤ ሆነሽ ላትሆኝ ሌላ

ምንም አማራጭ የለሽም ፤ ድመቂ በራስሽ ገላ

ኩሪ በማንነትሽ ፤ አያዋጣሽም ኩብለላ

ሌላው የሌላ ነው እቴ ፤ የአንችው ብቻ ነው የአንቺ

ማንነት ክብርሽን ጠብቂ ፤ ወደሽ ያዠ እንጅ አታመንቺ

የምዕራቡ የእነሱ ነው ፤ የዓረቡም ደሞ የዓረብ

እንደጆንያ ስልቻ ፤ ማንም የራሱን ትብትብ

ለምን ጠቅጥቆ ይሙላብሽ ፤ የራስሽን አስጥሎ ጥበብ

አንችም በርትተሽ ብትሠሪ ፤ እንደነሱ ሁሉ ጠንክረሽ

መለያየት መገነጣጠል ፤ እርስ በርስ መቧጨቅ ትተሽ

እንኳንና ተሳክቶልሽ ፤ ሆነሽ ሀብታም ገናና

በድህነትሽ ላይ እንኳን ፤ በሰበረሽ ባሳጣሽ ዝና

በነባር ታሪክሽ ተማርኮ ፤ ስንቱ መጥቷል እየቀና

ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ ፤ ያለ ትውልዱ በልመና፡፡

አልሰማሽውም ማንዴላን ፤ ማርክስ ጋርቤይን ማልኮልምኤክስ

ቦብ ማርሌይን ሉተር ኪነግን ፤ ማን የቀረ አለ ከሚወደስ

ኢትዮጵያዊ መልኩን ሲባል ፤ ነብር ደሞ መዥጎርጎሩን

ይለውጥ ዘንድ ይቻላል ወይ ? ብሎ ሲጠይቅ የአምላክ ቃል

እኛን ነጥሎ ሲጠራ ፤ ምንን መንገሩ መስሎሻል?

ነጩ ቢጫው ጥቁሩ ቀዩ ፤ የቆዳ ቀለሙንማ

ማንስ ቢሆን ለመለወጥ ፤ ይችላል እንዴ ስንሰማ ?

መልኩን መቀየር መለወጥ ፤ ማንም ሕዝብ ቢሆን ካልቻለ

ምን ማለቱ ነበር ታዲያ ? ኢትዮጵያዊ መልኩን ያለ ?

መልክ ያለው ማንነት ነው ፤ የራስ መለያ አሻራ

ኢትዮጵያዊ አይቻለውም ፤ ያንን ቀይሮ ሊሆን ተራ፡፡

“አንዴ በመጻኢ ስደተኛ ፤ አንዴ በሲራራ ነጋዴ

አንዴ በሰላይ ሚሲዮን ፤ ተወስዶ አለቀ ክናዴ

ጣራ መሠረቴ ተናጋ ፤ ስለወዳደቀ አዕማዴ”

ብላ ትጣራለች ኢትዮጵያ ፤ ልጆቸ ታደጉኝ ከጉዴ

ወገን ታጠቅ ለዘመቻ ፤ እንቢልታ መለከት ንፋ

ምርኮኛህን ለመመለስ ፤ አንተም ተማርከህ ሳትጠፋ

ይሄንን የሚያህል ነውር ፤ ለመነገር ደርሶ በይፋ

ምን ደርሶብሀል ወገኔ ? ከዚህ ኪሳራ የከፋ ?

ከዚህ ጦርነት የከበደ ? ጥይት ሳይጮህ ሳይሰማ

ወገንን ማርኮ ከሚያግዝ ፤ ሀገርህን ከሚያደር ባድማ ?

 

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

ምስከረም 2000 ዓ.ም.

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.