የኢትዮጵያ አገር አድን በዴሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ ምስረታ በማስምልከት የወጣ ድርጅታዊ መግለጫ

(ማክሰኞ ጳጉሜ 3 2007 ዓ.ም)
የኢትዮጵያ ህዝብ የአገሩን ሉአላዊነት እና አንድነት አስከብሮ የኖረ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊያን ወንድሞቹና እህቶቹ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገ ጀግና ህዝብ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጀግኛ ህዝብ ከአብራኩ በወጡ ገዥዎች ነፃነቱ ተገፎ፣ መብቶቹ ተረግጠው የመከራ ኑሮ እየገፋ አያሌ ዘመናት ኖሯል፡፡ ይህ የመከራና የሰቆቃ ኑሮ ዛሬም አላበቃም፣ እንዲያውም “ከጭቆና ነፃ አወጣንህ” እያሉ የሚሳለቁበት ግፈኛ ገዥዎች የጫኑበትን የስቃይ ቀንምበር ተሸክሞ የውርደት ኑሮ እየኖረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የአገር ውስጥ ገዥ መደቦች የጫኑበትን የስቃይና የመከራ ቀንበር ሰባብሮ ለመጣል፣ ፍትህ፣ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ኑሮ ለመኖር ዓመታት የፈጀ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል አድርጓል፡፡ እስካሁን ትግሉን በአሸናፊነት ተወጥቶ የናፈቀውን ፍትህ፣ ሰላምና ብልፅግና ማግኘት አልቻለም፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ህዝባዊ ትግሉን በተባበረና በተቀናጀ መልክ መስራት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ ስር የሰደደ ያለመተባበር ችግር በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ተባብሷል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ሆን ብሎ የፈጠረው የመለያየት እና የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ለጋራ ድል አብሮ መታገልን በጭራሽ አስቸጋሪ ጉዳይ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ በጋራ አብሮ በመታገል የሚገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም የገባቸውና ካለፈው ተደጋጋሚ የታሪክ ስህተት የተማሩ፣ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት በምድር ላይ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ አራት ድርጅቶች በጥምረጥ ተሳስረው በጋራ ለመታገል ወስነዋል፡፡ እነዚህ አራቱ ድርጅቶች ለብዙ አመታት የአብሮ መታገል ፍላጎት እንቅፋት የሆነውን የገዢ መደቦች የከፋፍለህ ግዛው ሴራ በጣጥሰዋል፡፡ ይህ ዛሬ በጥምረት የተጀመረው ትብብር እያደገ ሄዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ውህደት እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ንቅናቄው ከሌሎች ለዴሞክራሲ ስርዓት መመስረት ከሚታገሉ ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ጋር ተጣምሮ ለመስራት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይገፋበታል፡፡
በዚህም መሰረት፣

1ኛ) የአፋር ድርጅቶች የጋራ ንቅናቄ
2ኛ) የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣
3ኛ) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ እና
4ኛ) አርበኞች ግንቦት 7 ለአድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ፣
የኢትዮጵያ አገር አድን በዴሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ (በአጭሩ “የአገር አድን ንቅናቄ”) የሚባል ድርጅት ዛሬ በአዲስ ዓመት መባቻ ጳጉሜ 3 ቀን 2007 ዓ.ም ፈጥረዋል፡፡ የንቅናቄውን ምክርቤት፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የተለያዩ መምሪያዎችን ከማቋቋሙም በላይ ዶክተር ብርሃኑ ነጋን ሊ/መንበር፣ ታጋይ ሞላ አስገዶምን ም/ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
የኢትዮጵያ አገር አድን በዴሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ ከአራቱ አባል ድርጅቶች የተውጣጣ አገር አድን ሰራዊት አቋቁሟል፡፡ይህ አገር አድን ሰራዊት በሚያደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች ሁሉ የአራቱ አባል ድርጅቶች ሰራዊቶች አባላት ሁሌም ከጎኑ አብረው በመሰለፍ ይታገላሉ፡፡
ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ከህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በሰላማዊ መንገድ ለመገላገል የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፣ ሁኖም ለእነዚህ ጥረቶች ከአገዛዙ የተገኘው ምላሽ እስር፣ ስደት፣ ውርደትና ሞት ብቻ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይወድ የህዝባዊ አመፅ አማራጭን እዲቀበል ተገዷል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም ለሰላም የዘረጋውን እጅ ሳያጥፍ የህወሓት/ኢህአዴግን አገዛዝ በህዝባዊ አመፅ ለማስወገድ እንቅስቃሴውን ጀምሯል፡፡

በጋራ የሚደረገው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በትግሉ ሜዳ ከሚደረገው ሕዝባዊ አመጽ በተጨማሪ የፖለቲካ፣የዲፕሎማሲና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፎችን ያካተተ ይሆናል፡፡ ይህ አዲስ ጅምር የህወሓት/ኢህአዴግን አገዛዝ ዕድሜ ለማሳጠር በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል ውስጥ የመጀመሪያውና ወሳኝ ምዕራፍ ሲሆን በዚህ አዲስ ጅምር ውስጥ አገር አድን ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉያ ውስጥ እየገባ፣ ዕዝብን እያነቃና እያደራጀ ወገኑ ከሆነው ሕዝብ ጋር የሚያደርገው የትግል እንቅስቃሴ በመጪው አዲስ ዓመት በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል፡፡
የኢትዮጵያ አገር አድን በዴሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ አገር አድን ሰራዊት መመስረቱን በዚህ መግለጫ ሲያሳውቅ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ እንዲቆም ያደርጋል፡፡እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊ መብቶቹና ነፃነቱ ተከብረው በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ሰርቶ መኖር የዜግነት መብቱ እንጂ የገዢዎች ችሮታ አለመሆኑን ማስመስከር አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያንን ለእስራት፤ለስደትና ለሞት የዳረገን የውርደት ኑሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ማብቃት አለበት፡፡
ይህንን ብሩህ ዓላማ እውን የሚያደረግ ሁለንተናዊ የአገር አድን ትግል ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ገበሬ ሆይ !
መሬት የህዝብ ነው እየተባልክ ህወሓት/ኢህአዴግ ሲያሰኘው አንተንና ቤተሰብህን ከመሬትህ እያፈናቀለና መሬቱን ለባእዳን እየሸጠ፤ አለዚያም በገዛ መሬትህ ላይ እንደ ገባር ተቆጥረህ አገሪቱ የዝናብ እጥረት ባጋጠማት ቁጥር የዕርዳታ ሰጭዎችን እጅ ተመልካች ሆነሃል፡፡
ዛሬ ልጆችህ በአገር አድን እንቅስቃሴ ዙሪያ ተሰባስበው ከዚህ የውርደት ኑሮ ነፃ ሊያወጡህ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ይህ ትግል አንተ በምትኖርበት አካባቢ፣በአንተ ድጋፍና አንተም ተሳትፈህበት የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ስለዚህ ልጆችህ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር በሚያደርጉት ትንንቅ መሸሸጊያ ጫካቸው አንተ ነህ፡፡ ውሃ ሲጠማቸው ውሃ እያጠጣህ፤ ሲርባቸው ቤት ያፈራውን እያበላህ፤ ይህንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደረግ የመብት፣ የነፃነትና የእኩልነት ትግል ከልጆችህ ጋር አብረህ እድትታገል በአገር አድን እንቅስቃሴ ዙሪያ የተሰባሰቡ ልጆችህ አገራዊ ጥሪ ያቀርቡልሃል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣት ሆይ!
“የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ ነህ” እየተባለ በተደጋጋሚ እየተነገረህ ነው፡፡ አንተ በራስህ ዓይን እደምትመለከተው የዛሬዋም ኢትዮጵያ ለአገርና ለህዝብ ደንታ በሌላቸው ሰዎች እጅ ገብታ እፈረሰች ነው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ነፃ ካልወጣች የነገዋ ኢትዮጵያ አትኖርም፡፡ የነገዋን ኢትዮጵያ የመገንባት ባአንተ በወጣቱ ጀርባ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ስራ የሚጀምረው ህወሓት/ኢህአዴግን ከስልጣን በማባረር ነው፡፡ የስደት ኑሮ አብቅቶ በገዛ አገርህ ውስጥ ባሰኘህ ቦታ ያሰኘህን ስራ እየሰራህ የክብር ኑሮ የምትኖርበትን ጊዜ አንተው ራስህ ታግለህ ማምጣት አለብህ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ራሳቸው አደራጅተው ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ከሚፋለመው የአገር አድን ሰራዊት ጋር ዛሬውኑ ተቀላቀል፤ ይህንን ማድረግ የማትችል ደግሞ በምትኖርበት ቦታ ከምታምናቸው ጓደኞችህ ጋር ሆነህ ራስህን እያደራጀህና የመረጃ ማሰባሰብ ስራዎችን እየሰራህ በየአካባቢህ የሚገኘውን የህዝባዊ እቢተኝነት ቡድን ተቀላቀል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የምትታገሉ ድርጅቶች ሆይ !
ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ ማየት የሚሹ የተለያዩ ድርጅቶች ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊትና ሥልጣን ከያዘም በኋላ በርካታ ዓመታት የፈጀ እልህ አስጨራሽ ትግል አካሂደዋል፤ዛሬም እያካሄዱ ነው፡፡ ይህ በተናጠል እየተካሄደ ያለው ትግል በመካከላችን የልዩነትና ያለመተማመን አጥር ሰርቶ ስላራራቀን ህወሓት/ኢህአዴግን ማሸነፍ ቀርቶ ጠንካራ ጡንቻ እንድናሳርፍበት እንኳን አላስቻለንም፡፡ ይልቁንም የምንታገልለት ህዝብ በየቀኑ ይታሰራል፤ ሰቆቃ ይደርስበታል፤ ይገደላል፡፡ ከዚህ ሁሉ ያመለጠው ደግሞ አገሩን ለቅቆ ይሰደዳል፡፡ በመካከላችን ያሉትን መለስተኛ ልዩነቶች ለህዝብ አቅርበን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት እስከተማመን ድረስ የአሁኑ ትግላችን ይህንኑ ለማድረግ ነውና ለዚህ እንቅፋት የሆነብንን የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት አብረን የማንታገልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ፍሬያማ ለሆነ ትብብር ራሳችንን እናዘጋጅ፤እንተጋገዝ፡፡

የኢትዮጵያ ምሁር ሆይ !
አገራችን ኢትዮጵያ ሁለት እጆቿን ዘርግታ ከምንግዜውም በላይ ያንተን የምሁር ልጆቿን የነቃ የትግል ተሳትፎ የምትፈልግበት ጊዜ አሁን ነው፡፡የኢትዮጵያ ምሁር ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብትና ነፃነት መከበር ከፍተኛ አስታውጽኦ አድርጓል፤ ግን ይህ በአብዛኛው በተናጠል አንዳዴም ድርጅታዊ መልክ ይዞ የተካሄደው ትግል የኢትዮጵያን ሕዝብ መብትና ነፃነት ማስከበር አልቻለም፡፡ በዚህ ተስፋ ቆርጠህ ከዳር ቆመህ የአገርህን ውርደት ዝም ብለህ እያየህ ከነበርክ ይህ ከዳር ሆኖ የመመልከቻ ጊዜ አሁን አብቅቷል፡፡ ስለዚህ አገር ውስጥና አገር ውጭ የምትኖረው ኢትዮጵያዊ ከወንድሞችህና እህቶችህ ጋር በመሆን ይህን የተቀጣጠለ ሕዝባዊ ትግል ተቀላቅለህ ዝንት ዓለም ስተመኝው የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት ድርሻህን እንድታበረክት አገራዊ ጥሪ ቀርቦልሃል፡፡

የህወሓት/ኢህአዴግ አባላት ሆይ!
አንዳንዶቻችሁ ከልባችሁ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምትታገሉ መስሏችሁ፤ ከፊሎቻችሁ ደግሞ በሁኔታዎች ተገድዳችሁ፤ ሌሎቻችሁ ደግሞ አማራጭ አጥታችሁ ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ከለየለት የአገር ጠላት ድርጅት ጋር ተስልፋችሁ እናት አገራችሁን ስትበደሉ ቆይታችኋል፡፡ ብዙዎቻችሁ የሕዝብ ስቃይና መከራ ተሰምቷችሁ የበደላችሁትን ሕዝብ ለመካስ አመች ጊዜ እየጠበቃችሁ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ደስ ይበላችሁ! የምትጠብቁት ጊዜ ደርሷል፡፡ መጭው እውነተኛ ዴሞክራሳዊ ስርዓት እናንተንም ነፃ የሚያወጣ ስርዓት ነውና ሁላችሁም በያላችሁበት ትግሉን ተቀላቀሉ፤መቀላቀል የማትችሉ ደግሞ መረጃ በማቀበልና ስርዓቱን ከውስጥ ሆናችሁ በማፍረስ ሕዝባዊውን ትግል ደግፉ ከህሊና እና ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳችሁን ታደጉ፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሆይ !
ያንተ ኃላፊነት የአገረህን ዳር ድንበር ከጠላት መጠበቅ ሆኖ ሳለ ህወሓት/ኢህአዴግ በአገርህ አንድነት ላይ የሚሸርባችው ሴራዎች አስፈፃሚ አድርጎህ ጭራሽ ደህንነቱን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ቃል ከገገባለት ሕዝብ ላይ መሳሪያህን እንድታነሳ እያደረገህ ነው፡፡ አንተ የወጣኸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወልዶ ባሳደገህ ወገነህ ላይ “ተኩስ” የሚል ፀረ-ሕዝብ ትዕዛዝ ሲሰጥ በፍጹም አትቀበል፣ ይልቁንም በጠላትህ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰርዓት ላይ አዙር ወይም መሳሪያህን እየያዝክ ወገኖችህን ተቀላቀል፡፡ እኛ ወገኖችህ ለነፃነት የምናደርገው ትግል በዘረፋና በሙስና ከከበሩ ዘራፊ ወታደራዊ መሪዎች ነን ባይ ሽፍቶች ጋር ነው እንጂ በፍጹም ካንተ ከወገናችን ጋር አይደለም፡፡ የእኛ ትግል አንተ የአገርህን ዳር ድንበር ለመጠበቅ የሚያስችልህን ብቃት ለመፍጠርና እውነተኛ የሕዝብ ሰራዊት እንድትሆን ለማድረግ ነው እንጂ አንተን ወገናችንን ለመበታተን የመጣን ጠላቶች ወይም አንተን በመግደል የምንደሰት አይደለንም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
አንድን ጨቋኝ አምባገነን ስርዓት ታግለህ በደመሰስክ ማግስት ከቀድሞው የባሰ የሚረግጥህና የሚጨቁንህ ስርዓት በላይህ ላይ እየተጫነ ተቆጥረው የማያልቁ የስድት፣ የሰቆቃና የውርደት ዓመታት ዓሳልፈሃል፡፡ አባቶችህ በደማቸው አስከብረው ያስረከቡህ የአገር አንድነት ላልቷል፤ አንተ ታግለህ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ያወጣሃቸው አገሮች በዕድገት ወደ ኋላ ጥለውህ ሄደዋል፤ የወለድካቸው ልጆችህ እስር ቤት ውስጥ ናቸው አልያም አንተንና አገራችውን ጥለው ተሰደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! “አምላኬ! አምላኬ! ይህ የመከራና የውርደት ዘመን መቼ ይሆን የሚያበቃው?” እያልክ ሰማይ ሰማዩን እየተመለከትክ ፈጣሪህን ጠይቀሃል፤ ለምነሃልም፡፡ ፈጣሪ አልረሳህም፡፡ የወለድካቸው ልጆችህ ተሰባስበውና ተደራጅተው የናፈቀህን የሰላምና የነፃነት ኑሮ የምታገኝበትን ቀን ለማቅረብ በአገር አድን ሰራዊትነት ተደራጅተው እየተፋለሙ ነው፡፡ የአገር አድን የጋራ ንቅናቄ ዓላማ አገራችን ኢትዮጵያ ፍትህ፣ ሰላምና እኩልነት የሰፈኑባት አገር እንድትሆን ነውና የምትችል በአካል ትግሉ ሜዳ ተገኝተህ በጉልበትህ፤ ይህን ማድረግ የማትችለው ደግሞ በገንዘብህ፣ በእውቀትህና ለዚህ ከጠላትጋር ለሚደረገው ትንንቅ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለወገን ኃይሎች በማቀበል ትግሉን ተቀላቀል፡፡
አንድነት ኃይል ነው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.