ሰበር ዜና – የአገር አድን ንቅናቄው ም/ሊቀመንበሩን አጣ፣ ከዚህ በኋላስ ?

(ሳተናው) አራት በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ድርጅቶች፣ የአፋር ድርጅቶች ንቅናቄ፣ የአማራ ሕዝብ ንቅናቄ፣ የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደሚት) እና የግንቦት ሰባት አርበኞች ንቅናቄ ፣ በዚህ ሳምንት ዉስጥ አገር አድን ንቅናቄ በሚል ስያሜ መቀናጀታቸው በስፋት መዘገቡ ይታወሳል። ዶር ብርሃኑ ነጋ የቅንጁት ሊቀመንበር፣ አቶ ሞላ አስግዶም ደግሞ ም/ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።

የአራቱ ድርጅቶች መቀናጀት ይፋ በሆነ በጥቂት ቀናት ዉስጥ ጳጙሜን 5 ቀን፣ አቶ ሞላ አስግዶም፣ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ ኢሳት በሰበር ዜና ለአድማጮቹ ዘግቧል። የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደሚት ሊቀመንበር ከንቅናቄው ከድተው ወደ ኢትዮጵያ ማምለጣቸውን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። አቶ ሞላ አስግዶም ንቅናቄው ተለይተው ከጥቂት ጓዶችቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ ያመለጡበት ምክንያት ያልታወቀ ቢሆንም በቅርቡ ከተፈጠረው ጥምረት ጋር የተያይዘ ሳይሆን እንደማይቀር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ የጥምረቱን መመስረት በአብላጫ ድምጽ ሲወስን አቶ ሞላ አስግዶም ልዩነት እንደነበራቸው እነዚሁ የኢሳት ምንጮች አስረድተዋል።የሚል ነበር የኢሳት ዜና።

አቶ ሞላ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ነገር ግን አቶ ሞላ አስግዶም፣ ኢሳት እንደዘገበው ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ሱዳን እንደሄዱ የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ደሚት ጥምረቱን ከመሰረቱት ድርጅቶች መካከል ጠንካራው ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል። ወደ ሰላሳ ሺህ ሰራዊት እንዳለው የሚገመት ሲሆን፣ በአንጻሩ ግንቦት ሰባት አርበኞችን ጨምሮ ሌሎች የጥምረቱ ድርጅቶች ከአንድ ሺህ የሚበልጥ ሰራዊት እንደሌላቸው ይነገራል። የኃይል ሚዛኑ ደሚት ጋር እንደመሆኑ፣ አቶ ሞላ አስግዶም ቅንጁትን መምራት ያለበት በደሚት አመራር መሆን አለበትየሚል አቋም እንደያዙ የገለጹት ምንጮቻችን ፣ ዶር ብርሃኑ ሊቀመንበር እንዲሆኑ የተደረገው በደሚቶች ስምምነት ሳይሆን በሻእቢያ ትእዛዝ እንደሆነ ይናገራሉ።

ወደዚህ የመጣነው ሕወሃትን ለመወጋት ነው። ለምንድን ነው ኤርትራ ዉስጥ ፣ ታስረን፣ እንድንቀመጥ የምታደረጉን ? ለምንድን ነው መረብንና ተከዜን ተሻግረን እንድንዋጋ የምታከላክሉን ? “ በሚል ከሻእቢያ ጋር ቀደም ሲል፣ የደሚት አመራሮች ቅሬታ እንደነበራቸው የገለጹት ምንጮቻችን፣ የአገር አድን ንቅናቄ በሚመሰረትበት ወቅት ቀጥተኛ ተጽኖ በደሚት ላይ ሻእቢያ ማድረጉ እንዳስከፋቸው ከምንጮቻችን የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

ሰላሳ ከሚሆኑ አመራር አባላት፣ ከሃያ በላይ የሚሆኑት ከሊቀመንበራቸው አቶ ሞላ አስግዶም ጋር ወደ ሱዳን እንደገቡ የገለጹት ምንጮቻችን አብዛኛው የደሚት ሰራዊት ግን አሁንም በኤርትራ እንደሆኑ ይናገራሉ።

አቶ ሞላ አስገዶም፣ ኢትዮጵያ ገቡ፣ ወያኔ ነበሩ ..” የሚለዉን ወሬ ሆን ብሎ ሻእቢያ እያስወራ እንደሆነ የገለጹት ምንጮቻችን ፣ እነ ሞላ አስግዶም ወያኔ ቢሆኑ ኖሮ እዚያው ሆነው ለወያኔ ይሰልሉ ነበር እንጂ ጥለው አይሄዱም ነበር ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡን የመለስ ትሩፋት መጽሀፍ ደራሲ አቶ ኤርሚያ ለገሰም፣ አቶ ሞላ አስገዶም፣ ከወያኔ ጋር የሚሰራ ነው የሚለውን አባባል እንደማይጋሩት ይገልጻሉ። በትግራይ ከፍተኛ በደልና ግፍ እየተፈጸመ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ኤርሚያስ፣ አቶ ሞላ አስገዶምም ሆነ በሺሆች የሚቆጠሩ የደሚት ሰራዊት አባላት፣ በረሃ የወረዱት ክፉኛ የሕወሃት ተቃዋሚ ስለሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ። አቶ ሞላ ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ሱዳን እንደሚሄዱ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ሱዳን እና ወያኔዎች ስምምነት ስላላቸው ፣ የመን አቶ አንዳርጋቸውን አሳልፋ እንደሰጠች፣ ሱዳኖች የሕወሃት ደመኛ ተቃዋሚ የሆነውን አቶ ሞላ አስግዶምን አሳልፈው ሊሰጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ያስረዳሉ።

አቶ ሞላ የተንቤን ሰው ሲሆኑ በባድመ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያን ወታደር እየመሩ ባሬንቱ የገቡ ወታደር ነበሩ። የራስ አሉላ አባ ነጋ አገር ፣ ተንቤን ፣ ሕወሃትን ከሚቃወሙ የትግራይ ቦታዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ጥቂት የአድዋ ሰዎች የሚቆጣጠሩት ሕወሃት፣ በተለይም ከባድመ ጦርነት በኋላ በተንቤኖች ላይ ከፍተኛ በደልና ግፍ እየፈጸመ እንደሆነም ለአካባቢው ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ።

በተያያዘ ዜና እውቁ ብሎገር ሚኒሊክ ሳልሳዊ አስመራ ያሉ ምንጮቹን በመግለጽ ፣ አቶ ሞላ አስግዶም ወደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ሱዳን መሄዳቸውን ዘግቧል። አቶ ሞላ አስገዶም ላለፉት ረዥም አመታት ምንም ሳይሰራ ውጤት ስላላመጣን አሁን የመሰረትነው የአገር አድን ንቅናቄ በተግባራዊ ስራ ላይ በመሰማራት በቂ የሆነ ዝግጅት እና የሰው ሃይል ስላለን ወያኔን በአፋጣኝ መውረር አለብን የሚል አቋም በመያዝ በንቅናቄው መስራች ስብሰባ ላይ መናገራቸው የሻእቢያን ሰዎች እንዳላስደሰተ የአስመራ ምንጮች ገልጸዋልሲል የጦመረው ሚሊኪክ ሳልሳዊ፣ አቶ ሞላ በቂ ዝግጅት ስላለን ጦርነት እንክፈት የሚል አቋም መያዛቸው ሻእቢያን ስላላስደሰተው እንጂ ፣ አቶ ሞላ ከወያኔ ጋር ስለሚሰሩ እንዳለሆነ ይገልጻል።

በዚህ ጉዳይ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት የዉጭ አመራር ሆነ ከአዲሱ የአገር አድን ንቅናቄ አመራር አባላት የተሰጠ ምንም አይነት መግለጫና ማብራሪያ እስከአሁን የለም።

አዲስ የተቋቋመው የአገር አድን ንቅናቄው እድል ፈንታ ምል ሊሆን እንደሚችል የጠየቅናቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ተመርጠው ይሁን ሻእቢያ ሾሟቸው፣ ዶር ብርሃኑ ነጋ ፣ እነ አቶ ሞላ አስግዶም ወደ ሱዳን ቢገቡም፣ አብዛኛው የደሚት ጦር አሁን በርሳቸው ስር እንደመሆኑ፣ ደሚቶችን ከሌሎች ጋር ሰራዊቱን አስተባብረው የመቀጠል አቅምና ብቃት እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ሰራዊቱ ወደ ኢትዪጵያ ምድር ሄዶ መዋጋት ይፈልጋልያሉት እኝሁ ተንታኝ፣ በዶር ብርሃኑ የሚመራው የአገር አድን ንቅናቄ፣ በቃል አቀባዩ በኩል፣ ወልቃይት ጠገዴ ፣ አርማጭሆ ..ዉጊያ አድርገን ይሄን ያህል ወያኔን ደመሰስን ..” የሚል ሊረጋገጥ የማይችል ዜና ማሰማት ሳይሆን፣ በተጨባጭ የትጥቅ ትግል መክፈት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ወያኔዎች ጥቂት ሽፍታ ሆነው ነው ከአስመራ አዲስ አበባ ያለውን መንገድ ዘግተው የነበረው። የአገር አድን ንቅናቄ በሺሆች የሚቁጠሩ ሰራዊት ያለው እንደመሆኑ፣ ቢያንስ ድንበር ላይ ያሉትን የሁመራና የመተማ ከተሞችን በመዝጋት ትልቅ መልእክት ለአገዛዙ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብና ከአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ማሰማት ይችላሉያሉት እኝሁ ተንታኝ፣ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ያንን ማድረግ ካልተቻለ ግን፣ የአገር አድን ንቅናቄ የወደፊት አቅጣጫ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት በጣም የሚያስቸግር እንደሚሆን ያስረዳሉ።

ኤርትራን ለቀው ወደ ሱዳን የገቡት የደሚት ሰራዊት አባላት

10455662_1636650653272798_5289973650861035070_n
ፎቶው የሱዳን ወታደሮች በትራክተር ዓቀባበል ሲያደርጉላቸው ያሳያል

12011218_1636650693272794_6821264144640664383_n 11836768_1636650636606133_7627711421588856507_n

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.