ሁሉም ወደ ወገንህ ሲባል ኩበት ወደ ጋጥ ገባ (ይገረም አለሙ)

አንድ ሳር ቢመዘዝ አያፈስም ጎጆው

የራሱን ክብር ነው ሞላ አስግዶም ያጣው፤

ትልቅ ቦታ ሰጥተው አክብረው ቢሾሙት

ለወንበሩ አልበቃም ጣለው ትንሽነት፤

መለከት ተነፍቶ ጥሪ ሲተላለፍ

ሁሉም አንደ ዓላማው እንደ አቅሙ እንዲሰለፍ

ጀግኖች ተጠራርተው ሲቆሙ በአንድነት

ሞላ ግን አልቻለም አላገኘም ጽናት፤

ትንሽ ነበርና ፍጥረትና ዕድገቱ

ለትልቁ ቦታ አልሆነም ጉልበቱ፤

በየዘመናቱ ታሪክ ለክብር ያጫቸው ነገር ግን መሆን ያቃታቸው በዚህም የቀድሞ መልካም   ሥራቸውን ሳይቀር እያረከሱና በተግባር እየኮሰሱ አይሆኑ ሲሆኑ አይተናል፡፡የሰሞኑ ዜና የሆነው የትህዴን ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስግዶምም ወደዚህ ጎራ ነው የተቀላቀለው፡፡

ለ10 ዓመታት የድርጅት ሊቀመንበር ከመባል የዘለለ ትውልድ በአብነት ሊጠቅሰውና ታሪክ በክብር ሊያስታውሰው የሚችል ይህ ነው የሚባል ተግባር ያልከወነው ሞላ አሁን ታላቅ ተግባር ሊፈጽም የሚችልበትን የታሪክ አጋጣሚ መሸከም አልቻለም፡፡ አራት ንቅናቄዎች የመሰረቱት ሀገር አድን ንቅናቄ ም/ል ሊቀመንበር ለመሆን የበቃው በብቃቱና በእውቀቱ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ሳይሆን በድርጅት ውክልና ቢሆንም ይህን የታሪክ ጥሪ ተቀብሎ ኃላፊነቱን ባይችለውም በሌሎቹ ድጋፍ እየተረዳ በመሪነቱ ቦታ በመቆየት የታሪኩ ተካፋይና  ባለድርሻ ለመሆን በበቃ ነበር፡ ግና ፈጣሪ ለውርደት ያለው ለክብረት ሊበቃ አይችልምና ሞላ የታሪክ ጥሪውን ወደ ጎን ብሎ ደካማ መንፈሱ ያመለከተውን  የውርደት መንገድ መረጠ፡፡

ቅዱሱ መጽኃፍ #በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፡፡እኩሌቶቹም ለክብር እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፡፡እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡$ይላል፡፡ (ጢሞቲዎስ 2፣2፣20) አዎ ሞላ ሳይታወቅ ከወርቅና ከብሮች ተርታ እንዲሰለፍ ተደረገ እሱ ግን ሸክላ ነበርና አልሆነለትም እናም ለክብር የታጨው ለውርደት በቃ፡፡

በተለያየ መንገድ እንደሰማን እንዳነበብነው አቶ ሞላ ጥምረቱን በመቃወም  ማስቀረት አልቻለም፡፡ ይህም የሀገር አድኑ ጥምረት ሊቀመንበር ፕ/ር ብርሀኑ ከንቅናቄው መመስረት በኋላ በሰጡት ቃለ ምልልስ ( ኢሳት ቪኦኤ) ካለፈው ተምረን ወደ ኋላ ሊመልሰን በማይችል መልኩ ንቅናቄውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ሞክረናል በማለት የተናገሩትን ያሳያል፡፡ ትህዴን በተጀመረው መልኩ መቀጠል አለመቀጠሉ ደግሞ ፕ/ር ብርሀኑ ያሉት ጠንካራ መሰረት ምን ያህል የጠበቀ መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥልን ይሆናል፡፡

 

የአቶ ሞላ አድራጎት ያስታወሰን ሌላው ጉዳይ የድርጅት መሪዎች የመተባበርን ጉዳይ ለድጋፍ ማግኛ ይጠቀሙበት አንደነበረ ነው፡፡ የማያምኑበት የመተባበር ጉዳይ በየመድረኩ እየተናገሩ  ለተግባራዊነቱም በጽናት እንደሚሰሩ እየደሰኮሩ የሞራልም የቁሳቁስና የገንዘብም ድጋፍ እያገኙ ለትግሉ ማጠናከሪያ ሳይሆን ለግል ህይወታቸው መቀማጠያ ያውሉት እንደነበረና አሁንም አንዲህ የሚያደርጉ አንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው ፡፡ አቶ ሞላ ራሳቸው በሚመሩት የትህዴን ራዲዮ ጭምር ስለ ተባብሮ መስራት ደጋግሞ  መናገሩን እናስታውሳለን፡፡ ለድጋፍ ማግኛ ሲል ያለ አምነቱ የተናገረው መተባበር እውነት ሆኖ ሲመጣ ግን መጀመሪያ ተቃወመ ማስቀረት ሳይችል ሲቀር  ደግሞ ኮበለለ፡፡

ሰዎች ትክክለኛ እነሱነታቸው የሚለየውና የሚታወቀው አንዲህ አይነት የሚያበጥር ወሳኝ ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡ ክረምት ካልመጣ ሁሉ ቤት አንግዳ ካልመጣ ሁሉ ሴት እንደሚባለው የተሸፋፈነው ካልተገለጠ ከሚነገረው በስተጀርባ ያለው በተግባር ካልተፈተነ ስንዴና አንክርዳዱን መለየት አይቻልም፡፡ድብቅ አላማቸው በምላስ ተሸፍኖ ትክክለኛ ማንነታቸው በማስመሳያ ጭንብል ተጋርዶ ከእነርሱ በላይ ታጋይ ከእነርሱ ወዲያ ለሀገር አሳቢ እየተባለላቸው ታጋዮን እየጎዱ በትግሉ እየነገዱ ሳይታወቁና ሳይታወቅባቸው የኖሩና የሚኖሩ እውነተኛ  ማንነታቸው ፍንትው ብሎ የሚወጣው እንዲህ የሚያጣራ ወንፊት ሲገኝ ነው፡፡ እናም ትህዴንን እግር ከወርች አስሮ አስር አመት ያለአንድ ይህ ነው የሚባል ውጤት በስም ብቻ ያኖረው ሞላ ለመጋለጥ የበቃው በሀገር አድኑ አንቅስቃሴ መመስረት በመሆኑ አንድ ድል ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል፡፡

አቶ ሞላ ለትልቅ ዓላማ የተመረጠ ነገር ግን የትህዴን ሊቀመንበር ከመባል ለዘለለ ትልቅ ዓላማ የሚበቃም የሚያበቃም ዓላማም፤ መንፈስም፤ አቅምና እውቀትም የሌለው ሆነና ያንኑ የለመደውንና የኖረበትን ትንሽነት ይዞ እንዳይቀጥልም ቀሪዎቹ የትህዴን አመራሮች ታሪክ ላቀረበላቸው ወቅታዊ ጥሪ ራሳቸውን ያዘጋጁ ሆኑና ፍላጎቱ ከሸፈ፤ ተስፋው እንደ ጉም በነነ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የዛሬው ጥምረት ነገ ወደ ውህደት እንደሚያመራ የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ ሲሆን ያኔ ሞላ ምንም ቦታ እንደማያገኝ ተረዳ፤ እናም የድርጅት ሊቀመንበር ተብሎ ተንቀባሮ የኖረው ሰው በአንዴ መጻኢ ህይወቱ ጨለማ ሲሆን ታየው፡፡

የሞላ መኮብለል ከተሰማበት ሰአት ጀምሮ የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡፡ የወያኔንም ሀተታ ሰምተናል፡፡ ትህዴንም መግለጫ አውጥቷል፡፡ ለሶስት አመታት ከእኛ ጋር ሲሰራ ነበር ተብሎ በወያኔ የተገለጸው መቼም ማንንም የሚያሳምን አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ይህን ያህል ግዜ ከእነርሱ ጋር ሲሰራ ከኖረ የሀገር አድኑ የጋራ ንቅናቄ ም/ል ሊቀመንበር ከመሆኑ አንጻር ይበልጥ ለወያኔ ሊጠቅም የሚችለው ከዚህ በኋላ ነበርና ፡፡ የትህዴን መግለጫ ዝርዝር ጉዳዮችን ባያነሳም ጥቅም የቀረባቸው ናቸው በማለት የገለጸው እውነት ነው ማለት ይቻላል፡፡

አቶ ሞላ የትህዴን ሊቀመንበር እየተባለ በዚሁ ተጠቃሚ ሆኖ ታጋዩ የሚደርስበት ሀሩርና ቁር ሳያገኘው ለአስር ዓመታት ኖሩዋል፡፡ ይህን ሊያስቀርበት የሚችለውን  ጥምረት በመቃወም እንዳይሳካ አድርጎ የኖረበትን ህይወት ለማስቀጠል ያደረገው ጥረት ሲከሽፍበት በድንገት መጪው ህይወቱ ጨለማ ሆነበት፡፡ በድርጅት ድርሻ ያገኘው የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታም ሊሸከመው የሚችለው ሆኖ አልታየውም፡፡ በቅርብ ግዜ ወደ ትግሉ ሜዳ የወረዱትና አብሮ እየተሰበሰበና እየመከረ ያያቸው ሰዎች ጋር ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ መሆኑን በተግባር ተመለከተ፡፡ ይህም የበታችነት ስሜቱን አናረው፡፡ ጥምረቱ በአጭር ግዜ ወደ ውህደት አንደሚያመራ የተደረሰውን ስምምነት ሲያስብ ደግሞ በዛን ግዜ ፈጽሞ ቦታ ሊያገኝ አንደማይችል ከወዲሁ ታየው፤እነዚህና መሰል ምክንያቶች ሲደማመሩ ሞላ የሞራል ውድቀት የመንፈስ ስብራት ደረሰበት፤የማንነት ቀውስ ገጠመው፡፡

የድርጅት ሊቀመንበር ተብሎ ተከብሮ የኖረ ሰው ቀጣይ ህይወቱ ጨለማ ሲሆን፤አዕምሮው ተጨነቀ መንፈሱ ታወከ ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ያለ ሰው ደግሞ ትናንትን አስታውሶ ዛሬን መርምሮና ስለ ነገ ግምት ወስዶ በተረጋጋ ሁኔታ መወሰን አይችልምና የተሰጠውን ኃላፊነት ምንነትና እንዴትነት አንኳን በውል ሳይረዳ በድንገት ወስኖ ኩብለላን መረጠ ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

ወያኔ በዜናው እንደተናገረውም ሆነ አንዳንድ ወጎኖች እንደሚሉት ቀደም ሲል ጀምሮ ለወያኔ ይሰራ የነበረ ከሆነ ጥምረቱን አድንቆ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚችለው ባይሆንም ተቀብሎ ምክትል ሊቀመንበርነቱ ሁሉንም ለማወቅ ያስችለዋልና ለወያኔ አሳልፎ በመስጠት የሀገር አድኑ ሰራዊት በየሄደበት ለሽንፈት እንዲበቃ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ከዚህ ከከፋም ወሳኝ የሆኑ አመራሮችን ገድሎ ማምለጥ አለያም አጥፍቶ መጥፋት ይችል ነበር፡፡ በመሆኑም  ሞላ በግዜ ያለምንም ኮሽታ ሹልክ ብሎ መኮብለሉ ወያኔ አንደሚለው ለሶስት አመት ከእነርሱ ጋር እንደነበረም አያሳይም፡፡ ድርጊቱም ትህዴንን ነጻ ያወጣ ለጋራው ትብብርም አሜኬላ ያስወገደ ነውና  እሰየው የሚያሰኝ እንጂ የሚያሳዝንም የሚያበሳጭም አይደለም፡፡ እንደውም  ሊቀጥል  እንደሚችል መጠበቅ ነው፡፡ የተሸፋፈነው እየተገለጠ፤የማስመሰያ ካባው እየተገለጠ ቢጠራ ጥሩ ነው፡፡

ሁሉም በስም ተኮፍሶ በሚኖርበት፤ ከእምነቱ ውጪ እየተናገረ አንቱታን ባተረፈበት ሁኔታ እንደነበረ ከቀጠለ ጥራት አይመጣም፡፡ ስንዴው ከአንክርዳዱ ሊለይ የሚችለው ወሳኝ የተግባር እንቅስቃሴ  ሲጀመር ነውና ወደፊትም ለትልቁ ሀገራዊ ኃላፊነት የማይበቁ በትንሽ እምነትና ማንነት ላይ ያሉ፤ከራስ በላይ ማሰብ የማይችሉ፤ ድርጅትን መታገያ ሳይሆን መጠቀመያ ሲያደርጉ የኖሩ  እየጠሩ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ የሆነውም ሆነ ወደ ፊት ሊሆን የሚችለው ጥምረቱ በመፈጠሩ የተገኘ ውጤት በመሆኑ በደስታ መቀበል ነው፡፡ ሁሉም ወደ ወገንህ ሲባል ኩበት ወደ ጋጥ ገባ እንደሚባለው ተግባራዊ እንቅስቃሴው በጥምረቱ ውስጥ የተካተቱትንም ሆነ ሌሎቹን በተቃውሞ ጎራ ያሉትን እንደ አላማና አቅማቸው እንዲሰለፉ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደ ሞላ አይነቶች ደግሞ  ይኮበልሉ፤ የሞላ መኮብለላ በእኔ እይታ ሁለተኛው የአዲስ አመት ብስራት ነው፡፡