የሀገር አድን ጥሪ ለወጣቱ!(ከአርበኞች ግንቦት7 ወጣቶች መምርያ)

እኛ የዘመኑ ወጣቶች በሃገራችን ላይ የተጫነብን የወያኔ የመርገምት አገዛዝ ያጎሳቆለን፤ በኑሮ የተበደልንና በሰላም ለመኖር ያልታደልን ፍጡሮች ብንሆንም ህዝባችን ነጻነቱን ሲቀማ፣ መብቱ ሲደፈር፣ ክብሩ ሲዋረድ ከዳር ቁመን የምንመለከትበት አንዳች ምክንያት ሊኖረን አይገባም። ወቅቱ ለነፃነታችንና ለመብታችን ባላንጣ የሆነውን አምባገነን የወያኔን ስርዓት ፊት ለፊት ተጋፍጠን፣ በትግላችን ደቁስን ማንነታችንን የምናስመስክርበት ወቅት እንጂ በፍርሃትና በዝምታ ተውጠን ወደኋላ የምንልበት ስዓት አይደለም። ደግሞም እኛ ወጣቶች ለመብት እና ነፃነታችን ተፈጥሮ የለገሰችንን እምቅ ኃይልና ጉልበት ተጠቅመን በቁርጠኝነት ተነስተን ካልታገልን የሥርዓቱን አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ በፍርሃትና በዝምታ እንደተቀበልን ተደርጎ መወስዱ የማይቀር ነው።


ከምንግዜውም በላይ እኛ ወጣቶችን ዛሬ ሁለት አበይት ጉዳዮች በጉልህ ያሳስቡናል፤ ሊያሳስቡንም ይገባል። እነዚህም ሃገራችን ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታና የኛ የተተኪው ትውልድ የወደፊት ተስፋ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉት ናችው። በቀደመው ጊዜ በሃገራችን የተፈራረቁት አምባገነን ገዥዎች ለወጣቱ ተስፋና የተሻለ ነገር ከመስጠት ይልቅ በጠላትነት ፈርጀው በሽብር እየገደሉና ጥቃት እየፈጸሙበት ሲያሳድዱት ኖረዋል። የወጣቱ ሰቆቃ አሁን በወያኔ ዘመን ደግሞ እጅግ በጣም በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል።


የወያኔ መሪዎች ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ማዕከላዊን፡ ቃሊቲን፤ ሽዋሮቢትን፣ ዝዋይን እና የመሳስሉ የሰቆቃ እስር ቤቶችን ሲያሰፉ እንጂ የሥልጠናና የምርምር ተቋም ሲያድሱና ሲገነቡ ለማየት አልታደልንም። የሚገነቡ የትምህርት ተቋማትም ለሥርዓቱ የእድሜ ማራዘሚያ እንጂ የእውቀት ማስጨበጫ ተቋም እንዳልሆኑ ተግባራቸውንና ውጤታቸውን መመልከት ይቻላል። በአደባባይ ያለፍትህ የሚገደለው ወጣት ባንክ ሲዘርፍ ተገኘ፣ ወንጀል ሲሰራ ተያዘ የሚሉ የሀሰት ምክንያቶች እየተለጠፉበት ያለኃጢአቱ የሀሰት ስም በመቀባት ዳግም ይገሉታል።


የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከሚፈራበት የትምህርት ተቋም ድረስ በመግባት የአማራ ህንጻ፣ የኦሮሞ ህንጻ፣ የትግሬ ህንጻ…ወዘተ እያሉ የትምህርት ሥርዓቱን ከጠባቡ የፓለቲካ ግባቸው ጋር በማያያዝ በነገ ተስፋችን ላይ ዘምተው የልዩነት ግድግዳ ባሳፋሪ መልክ እየገነቡ ቀጥለዋል። አላማው ደግሞ በጎስኝነት በሽታ ተውጠን ከእህቶቻችንና ከወንድሞቻችን ጋር እየተባላንና እየተገዳደልን የምንኖርበት ሲኦል ለመፍጠር መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህም ሳቢያ ብሔራዊ ሰሜታችን እየደበዘዘ ሄዷል። ብሔራዊ ሰሜት ከሌለን ደግሞ አገር አለን ማለት ጨርሶ የሚታስብ እንደማይሆን ግልጽ ነው።


በነገራችን ላይ ዛሬም ድረስ ወያኔዎች ለእድገትና ለልማት መዘጋጀታችውን እየደሰኮሩ ህዝብን በማታለል የስልጣን ዘመናቸውን ለማርዘም መውተርተራቸውን አላቆሙም። በየጊዜው ኢትዮጵያ ተመነደገች፤ ልማቱ ተፋጥኗል እያሉ በሃሰት ህዝብን ለማወናበድ ይሞክራሉ።እውነታው ግን በእጅጉ ተቃራኒ መሆኑን የህዝቡን የኑሮ ሁኔታን በመመልከት መረዳት ይቻላል። ዛሬ የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ በፈጠረው የተወሳሰበ ችግር በሀገሪቱ የወጣት ሥራ ፈትና ተጧሪ ሞልቶና ተትረፍርፎ በሚታይበት፤ ሥራ የማግኘት እድል በፓለቲካ ታማኝነት ብቻ በሆነባት ሃገርና ወያኔ የፓለቲካ ሥልጣኑንና ወታደራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ የሀገሪቷን ሀብት እያጋበስ በሚዘርፍበት ሁኔታ ላይ ቆመን ልማትና እድገት ማለት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ተራ ማጭበርበሪያና ዲስኩር ካልሆኑ በስተቀር ፈጽሞ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም።
ለነገሩ ወያኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያዘጋጀልን ቃሊቲ፤ ማዕከላዊ፤ ሁርሶን፤ ሽዋሮቢትንና የመሳሰሉትን የማሰቃያ ማጎሪያዎች መሆኑን የተረዳን ስለሆነ በዚህ የምንደናገር አይደለም። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት እኛ ወጣቶች ተሰባስበንና ተደራጅተን ከመታገል ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም ብለን በድፍረት የምንናገረው።
አምባገነንነት ስርዓት ካልተገታ የአገር ሰላም ሆነ የህዝብ ህልውና እና አንድነት ዋስትና አያገኝም። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሥልጣን የጨበጡት ወንበዴ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብን ሀብት እየተቀራመቱ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ፣ ህዝቡን የሚገሉ፤ የሚረግጡና የሚበድሉ በተለይ ደግሞ ለባእድ ጥቅም የተገዙ ናቸው። እነዚህ ግለስቦች ብሔራዊ ስሜታችውን አሽቀንጥረው የጣሉ፤ የራሳችውን ባህል፤ ወግ፤ ታሪክና ሕዝብ አምርረው የሚጠሉ ከራሳቸውና ሥልጣን ላይ ካስቀመጧቸው መንግሥታት ጥቅም ውጪ ሌላ ምንም የማይታያቸው ናችው።


ታዲያ የሃገራችን ህልውና ከመቼውም በላይ ለከፋ አደጋ ተጋልጦ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለይ የእኛ የወጣቶች ግዴታና ድርሻ ምን መሆን አለበት ብለን ራሳችንን መጠየቅና ብሎም መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ሀገራዊ ግዴታንና ኃላፊነትን ለመወጣት የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ይኖርበታል።


ጭቆናንና በደልን በመታገል ረገድ ደግሞ የቀደምት የታላላቅ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አኩሪ ገድል ለዛሬው ትግላችን ትልቅ የትምህርት ማእከል ሆኖ ያገለግለናል። ሀገራችን ከኋላቀር ሥርዓትና ከብልሹ አገዛዝ ተላቅቃ፤ ድህነትን አሸንቀጥራ ጥላ በልማት ጎዳና እንድትራመድ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን፤ ማህበራዊ ፍትህ እንዲስፍን ባጠቃላይም ተጨባጭና ዘላቂ ለውጥ በሃገራችን እንዲመጣ ጽኑ እምነት ሰንቀው ለሕዝባዊ ትግሉ ሕይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ሲታገሉ የነበሩ ጀግና ወጣቶች እንዳሉ ታሪክ ያስገነዝበናል።


ዛሬም ጭምር ግንባራችውን ሳያጥፉ መስዋእትነትን በመክፈል እያስመስከሩ ያሉ መኖራቸውን ስንመለከት ጀግና የሚያፈራው ጀግናን ነውና እኛም ወጣቶች አንገታችንን ቀና አድርገን ዛሬም እንደ ትናንቱ ለሃገራችንና ለህዝባችን ነፃነት መታገል ብሔራዊ ግዳጃችን ብቻም ሳይሆን ታላቅ ክብርም ጭምር መሆኑን ተገንዝበን ለሞት ሽረቱ ትግል በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርብናል። ከፊታችን ለሚጠብቀንና ሃገራችን እያሰማች ላለው የሀገር አድን ጥሪ መልስ ለመስጠት እኛ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሃገር ቤት እስከ ውጪው አለም ድረስ የተቀናጀና የተቀነባበረ ንቅናቄ በመፍጠር ምላሽ ልንሰጥ ይገባል።


በኅብረትና በጽናት ከታገልን ደግሞ የወያኔን የሰቆቃ አገዛዝ አሰወግደን የሕዝባችንን ሮሮ የማናስቆምበት እና ተጨባጭ ለውጥ በሀገራችን ለማምጣት የማያስችለን አንዳች ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ዛሬ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዳለ ብልጭ ብልጭ እንደሚል ኮኮብ ብንመስልም በርግጠኝነት ነገ ከፀሐይ ደምቀን ከአሽዋ በርከትን የምንታይበት ጊዜ ይመጣል፤ እየመጣም ነው።


በመጨረሻም የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ወጣቱን ትውልድ መብቱንና የዜግነት ክብሩን ለመጎናጸፍ እንዲችል ብሎም የሀገር እና የወገን ነፃነትን ለማምጣት ወያኔን ታግሎ ማሸነፍና ከስልጣኑ ማውረድ ግድ ነው ብሎ በጽኑ ያምናል። በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ተበታትኖ የሚገኘውን ወጣት በአገሩ ተከብሮ እንዲኖር የተለየና የተቀደሰ አማራጭ አለው። ይኸውም እየተደራጁ መታገል፣ እየታገሉ መደራጀት ነው ብሎ ንቅናቄያችን ያምናል።


የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የነደፈውን ጊዜ የማይሽረውን ሁለገብ የመታገያ ስልትና አላማን ከግብ ለማድረስ ትግልን በጽናት መቀጠል የሚለው መርሁ ሲሆን ተደራጅቶ በጽናት መታገልን በተግባር ለማዋል ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ንቅናቄውን እንዲቀላቀል ጥሪ ያደርጋል። ተደራጅቶ ሊያጠፋን የተነሳን ጠላት በተደራጀ ሃይል ማንበርከክና ከስር መሰረቱ ማስወገድ ይቻላልና። ስለዚህ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በአረመኔው የወያኔ አገዛዝ ላይ የሚካሄደውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል በአገር ውስጥ ወጣቱን በህቡዕ ከማደራጀት ጀምሮ በውጭው ዓለም በየአህጉሩ በተዋቀሩ የንቅናቄው መዋቅሮች አማካኝነት ወጣቱን አደራጅቶ በማንቀሳቀስ አስፈሪ የሆነ የነፃነት ማዕበል ፈጥሯል። አሁንም የንቅናቄውን ዓላማ የሚደግፉና በነፃነት ትግሉ ለመሳተፍ የቆረጡ ወጣቶች እንዲቀላቀሉ የአርበኞች ግንቦት7 ወጣቶች መምርያ በድጋሚ ሃገራዊ ጥሪ ያቀርባል!

 

ፈሪዎችንና ባንዳዎችን ወደ ጎን በመተው እውነተኛ ታጋዮችን ይዘን ትግላችንን እንቀጥላለን!!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!