የታገዱት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ አመራሮች በአዲስ ተተኩ

ዳዊት ታዬ

ሦስቱ ከፍተኛ አመራሮች ከአገር ውጭ ናቸው

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር፣ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበርና የዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ኃላፊ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ከኃላፊነታቸው ከታገዱ በኋላ፣ ያልታገደው ቀሪው ቦርድ ባንኩን የሚመሩ አዳዲስ አመራሮችን ሰየመ፡፡

በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ከኃላፊነታቸው የታገዱት የቦርድ ሊቀመንበሩ የቀድሞው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አበራ ደሬሳ፣ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ታደሰ መስቀላ፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች አቶ ቶሎሳ በየነና አቶ አበበ ጥላሁን፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ባንታየሁ ከበደ ናቸው፡፡

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ከብሔራዊ ባንክ የወጣው የዕገዳ ደብዳቤ በኋላ ዕገዳው ያልተመለከታቸው ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት በመሰብሰብ አቶ በላቸው ሁሪሳን የቦርድ ሊቀመንበር፣ አቶ ዳኛቸው ሽፈራውን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሰይሟል፡፡ በአቶ ወንድማገኘሁ ምትክ አቶ ሙሉነህ ዲሳሳን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርጓል፡፡ አቶ ሙሉነህ የባንኩ የፊንፊኔ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡ የባንኩ የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ በነበሩት በአቶ ባንታየሁ ምትክ ደግሞ የባንኩ የገቢና ወጪ ንግድ ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ ፍፁም ሐዋስ ተመድበዋል ተብሏል፡፡ አቶ ፍፁም ግን ይህ ሪፖርት እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ቢገልጹም፣ ለቦታው መታጨታቸውና ሥራውን እየሠሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

በታገዱት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ምትክ ደግሞ አቶ ፈየራ አጀታና አቶ ግዛው ኃይሉ ተመድበዋል፡፡ አቶ ፈየራ ቀደም ብሎ የሀብትና አገልግሎቶች ስትራቴጂና ለውጥ ኃላፊ ነበሩ፡፡ አቶ ግዛው ደግሞ የደንበኞች ሒሳብና የቅርንጫፎች ማስተባበሪያ የሥራ ሒደት መሪ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡

በባንኩ ውስጥ ተፈጽሟል በተባለ በውጭ ምንዛሪ ላይ በተፈጸመ የአሠራር ግድፈት በብሔራዊ ባንክ ከታገዱት አመራሮች ውስጥ ዶ/ር አበራ ዴሬሳ፣ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራና አቶ ታደሰ መስቀላ አገር ውስጥ እንደሌሉ፣ የዕገዳው ደብዳቤ የወጣባቸውም በሌሉበት እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ የኦሮሚያ ቡና አምራቾች አርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ታደሰ ከቦርዱ ኃላፊነታቸው ቀደም ብለው ወጥተው ነበር፡፡ አወጣጣቸው ከቀሪዎቹ ቦርድ አባላት ጋር ባለመስማማት ነው ተብሏል፡፡

ከኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ አካባቢ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሦስቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች የብሔራዊ ባንክ ዕገዳ ደብዳቤ ከመውጣቱ በፊት ለሥራ ወደ ውጭ ሄደዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ሊታገዱ የቻሉት ከብሔራዊ ባንክ መመርያ ውጪ ከውጭ ምንዛሪ ግብይት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ከሌሎች ባንኮች በተለየ ከፍተኛ እንደነበር የሚያስታውሱት ምንጮች፣ ከመመርያ ውጪ የሚደረግ ግብይት ተፈጽሟል ተብሎ በባንኩ ላይ ምርመራ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከመመርያና ከደንብ ውጪ የተካሄደ ግብይት ነበር የሚለውን ፍንጭ በመያዝ በባንኩ ላይ ጥልቅ ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አመራሮቹን ካገደ በኋላም ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን፣ በቀጣይ ወደ ሕጋዊ ዕርምጃዎች ሊገባ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በአሁኑ ወቅት ካሉት 16 የግል ባንኮች መካከል፣ በጥቂት ዓመታት ልዩነት በዓመታዊ የትርፍ መጠኑና ከፍተኛ የትርፍ ክፍፍል በማስገኘት በሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለ ነው፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በባንኮች የትርፍ መጠን የደረጃ ሠንጠረዥ ስምንተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ባንክ፣ በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደረጃውን ከዳሸንና ከአዋሽ ባንኮች ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ችሏል፡፡

ባንኩ በ2006 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 475 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ የ2007 በጀት ዓመት ግርድፍ የፋይናንስ ሪፖርቱ የሚያመለክተው ደግሞ ከታክስ በፊት 602 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን ነው፡፡

በ2006 በጀት ዓመት ግን ባንኩ ትርፍ ካስመዘገበባቸው የሥራ ዘርፎች ሁሉ ብልጫ የነበረው የዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ነበር፡፡ ከግል ባንኮች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከያዙ ጥቂት ባንኮች መካከል አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም ለባንኩ የሥራ ኃላፊዎች መታገድ ምክንያት ከዚህ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አመጣጥ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡ አዲስ የተሰየመው የዳይሬክተሮች ቦርድም በምክትል ፕሬዚዳንቱ ላይ የጻፈው አዲስ ደብዳቤ ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ በአቶ ጥላሁን ላይ ዕገዳ ከጣለ በኋላ በአዲሱ በቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላቸው ሁሪሳ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ላይ ባደረገው ልዩ ምርመራ ውጤት ላይ በመንተራስ፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ልዩ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ጥልቅ ምርመራ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ በዚህ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ ውጤት ላይ በመመርኮዝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወሰነው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዳሰናበታቸው፣ ከመስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ከባንኩ እንደተሰናበቱ የሚያስታውቅ ደብዳቤ ነው፡፡

ይህ ደብዳቤ የባንኩ ቦርድ ቀደም ብሎ የወሰነው መሆኑን ቢያመለክትም፣ የብሔራዊ ባንክ ዕገዳ ተፈጻሚ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ማብራሪያ ለማግኘት ቢሞክርም አልተሳካም፡፡

በታገዱት የቦርድ ሰብሳቢ ምትክ የተተኩት አቶ በላቸው ሁሪሳ ቦርዱን በአባልነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፣ ኢሌምቱ ኢንተግሬትድ የተባለውን አክሲዮን ማኅበር (ኢሌምቱ ወተት) ቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በአብዛኛው የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና ዩኒየኖችን በአክሲዮን አባልነት ያቀፈ ሲሆን፣ አገልግሎቱም ከእነዚሁ ማኅበራት ጋር የተያያዘ እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡

ባንኩን በቦርድ ዳይሬክተርነት ሲመሩ የቆዩትና በብሔራዊ ባንክ የታገዱት ዶ/ር አበራ ደሬሳ በግብርና ሙያ የሚታወቁና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.