የግብጽ እና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶሶች በዝግ ይመክራሉ

የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶች፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ ተገለጸ፡፡
በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ከሚመራው ልኡክ ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የሚካሔደው ምክክር፤ የኹለቱን አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል ወደ ከፍተኛ መተማመን እንዲያመራ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡
በክርስትናው አስተምህሮ ባላቸው የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት፣ “እኅትማማች” የሚባሉት ኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጋራ ተልእኮዎቻቸውን በአንድነት በመፈጸም ጥንታዊውንና ታሪካዊውን ግንኙነታቸውን ለማዳበር የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት ጥር ባደረጉት የግብጽ ይፋዊ ጉብኝታቸው ወቅት ጠይቀዋል፡፡
የግብጹ አቻቸው ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም ጥያቄውን በመቀበል፤ በሃይማኖታዊ፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አብሮ የሚሠራና በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ኮሚቴ ለመሰየም ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀው እንደነበር ተወስቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈለገ ግዮን ተብሎ የሚታወቀውና ኹለቱ አገሮች በጋራ የሚጠቀሙበት ተፈጥሯዊው የዓባይ ውኃ የማኅበራዊ ትስስሩ መሠረት ሲኾን በዝግ በሚካሔደው የኹለቱ ቅዱሳት ሲኖዶሳት ምክክርም ዐቢይ ትኩረት እንደሚያገኝ ተጠቁሟል፡፡
የዓባይ ውኃን በመተማመን ከተጠቀሙበት ከኹለቱ አገሮች አልፎ ለመላው አፍሪካ የሚበቃ የአምላክ በረከት እንደኾነ ለግብጽ ባለሥልጣናት የተናገሩት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚኾኑት የእግዚአብሔር ጸጋ በኾነው በዓባይ ነው፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ደግሞ ሰው ሊለያየው አይችልም፤” ያሉ ሲኾን ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም፤ “እኛ የግብጽ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ አንድ ብርጭቆ ውኃ በጠጣን ቁጥር ኢትዮጵያን እናስታውሳታለን፤” ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በወቅቱ ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በ2008 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ እንዲገኙ ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው ግብዣ፣ ትላንት ሌሊቱን ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሃይማኖት አባቶች ልኡክ በማስከተል ዐዲስ አበባ የገቡ ሲኾን ከዛሬ ጀምሮ የአምስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡  ለጉብኝቱ የወጣው መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው ፓትርያርኩ፣ ትላንትና መስከረም 14 ቀን ሌሊት 9፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የፕሮቶኮል ባለድርሻ አካላት አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመንበረ ፓትርያርኩና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ የእንኳን ደኅና መጡ ፕሮግራም ይደረግላቸዋል፤ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም ይወያያሉ ተብሏል፡፡
ጠዋት በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተገኝተው ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራት፣ ሥርዐተ ቅዳሴውን የሚያከናውኑ ሲኾን ከቀትር በኋላም በመስቀል ዐደባባይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር የመስቀል ደመራ በዓልን ያከብራሉ፡፡
ከመስከረም 17 – 19 ቀን የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያምን፣ የጎንደርን፣ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ታሪካዊ ስፍራዎችን፣ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን እንዲኹም በአዲስ አበባ የሰበታ ጌቴሰማኔ ቤተ ደናግል ወጠባባት ገዳምንና የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመጎብኘት ጸሎት እንደሚያደርጉና እንደሚባርኩ ታውቋል፡፡ በግብፅና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ትብብር እንደ ድልድይ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ በ1951 ዓ.ም እስከሾመችበት ጊዜ ድረስ ለ1600 ዓመታት ከግብጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሾሙ ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች፡፡ በሀገራቱ መንግሥታት ምክክር ጭምር የመንበሩ ነጻነት ከተገኘም በኋላ የሚካሄዱ ፕትርክናዊ ጉብኝቶች ለውጭ ግንኙነታቸው መጠናከር አስተዋፀኦ እንዳለው ይታመናል፡፡

Source- addisadmas

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.