በሰንበት ት/ቤት ስለኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እየተማርኩ ነው ያደግሁት፤ግብጻውያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና ታሪኳን እንዲያውቁ እመክራለሁ: አቡነ ታዎድሮስ ካልዕ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ጥንታውያን እኅት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። የኹለቱ ግንኙነት ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ነው። ሃይማኖታዊ ትስስሩ ከኹለት ሺሕ ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረ ነው። በተፈጥሮ ያለው ግንኙነት ደግሞ የዓባይ ወንዝ መፍሰስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ነው።

ይኸው የሁለቱ እኅት አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መጥቶ ዛሬ ላይ ደርሷል። በኢትዮጵያ በኩል ቤተ ክርስቲያኗን የሚያስተዳድሯት ፓትርያርኮች ግብጽን በተለያዩ ጊዜያት ጎብኝተዋል፤ ለግንኙነቱ መጠናከርም ይበጃል ያሉትን ተግባራት ከውነዋል። ለአብነት ያኽልም በጥር ወር 2007 ዓ.ም በአኹኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ የኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለስድስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል።

በተመሳሳይም በግብጽ የእስክንድርያው ጳጳስ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ የኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ ኹለተኛ ሰሞኑን ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ፓትርያርኩ በጉብኝታቸው የመጨረሻ ዕለት አመሻሽ ላይ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ነበራቸው። በቆይታቸው ከሰጧቸው ዋና ዋና ምላሾች፡-

ስለ ኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፡-

ከዐሥርት ዓመታት በፊት ገና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ እያለኹ ስለ ኢትዮጵያ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ በርካታ ታሪኮችን እየተማርኩ ነው ያደግኹት። ያ ትምህርት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትልቅ ተስፋ እና ሕልም አሳድሮብኛል። ያ ትምህርት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትልቅ ተስፋ እና ሕልም አሳድሮብኛል። አጠንክሬ ልናገር የምወደው፣ የእኔ ጉብኝት መንፈሳዊ እና ከኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት የእርስ በርስ ግንኙነት ጋር የተያያዘ እንጂ ከግድቡ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ነው፡፡

እ.አ.አ የ1994 የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ፕሮቶኮል፡-

በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳት ሲኖዶሶች አማካይነት እ.አ.አ በ1994 የተፈረመውን የጋራ ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ በየሦስት ዓመቱ ለመገናኘት በኹለቱም ወገኖች ተወስኗል። እግዚአብሔር ቢፈቅድ በ2018 በካይሮ ለመገናኘትና ለመመካከር አስበናል። በየሦስት ዓመቱም በፓትርያርክ እና በጳጳስ ደረጃ ጉብኝት ይኖረናል። በእኛ በኩል ይህን ተግባር የሚከታተል አንድ ጳጳስ አለን።

የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር፡-

እንዲኽ ዐይነት ትልቅ ሃይማኖታዊ በዓል ተመልክቼ አላውቅም። የበዓሉ አከባበር ዘመናትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያውያን ባህላዊ መንገድ የተቃኘ ነው። ይህ ለእኔ አዲስ ነው። በሕዝቡ እና በካህናቱ አለባበስ ሳይቀር በጣም ተማርኬያለኹ። የአልባሳቱ ቀለማት፣ ዝማሬው እና እንቅስቃሴዎች ሁሉ አስደሳች ነበር።

ስለ ዴር ሡልጣን የታሪክ እና የቅድስና ይዞታ፡-

ያረጀ ችግር ነው። እዚህ የመጣነው ስለ አረጀ ችግር ለመወያየት አይደለም። እኛ እየጣርን ያለነው ኹለቱ አገሮች አዲስ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ነው። እንደ አጠቃላይ ለመናገር ግን፣ በኢየሩሳሌም ባሉ የግብጽ እና የኢትዮጵያ መነኰሳት መካከል መልካም የኾነ ግንኙነት አለ።

ስለ ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊነት እና ገዳማዊ ሕይወት፡-

ከሕዝቡ ጋር በተገናኘሁባቸው አጋጣሚዎች ኹሉ የተረዳሁት ነገር፣ ሕዝቡ ምን ያህል ቅንና የዋህ እንደኾነ ነው። ስለ አገራቸው ማደግ ያላቸው ፍላጎት ታላቅ ነው። ለሃይማኖታቸው ያላቸው ጥልቅ ፍቅርና ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸው ጥብቅ ቁርኝት ታላቅ ነው። በገዳም ውስጥ በነበረኝ ቆይታም ፍጹም ገዳማዊ የኾኑ መነኰሳትን ተመልክቻለኹ። በኢትዮጵያ ያለው ገዳማዊ ሕይወት በግብጽ ካለው የበለጠ ከባድ ነው።

ስለ ጉብኝታቸው ለግብጽ ሕዝብ የሚናገሩት፡-

ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ብቻ ሳትኾን በሕዝቦቿም ጭምር በጣም ውብ አገር መኾኗን ነው። ግብጻውያን ቀሳውስትም ኾኑ ሌሎች ግብጻውያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አበረታታለኹ። ግብጻውያን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እንዲያነቡና እንዲያውቁ እመክራለኹ። በአጠቃላይ የአምስት ቀናቱ ጉብኝት እስከ ዘላለም አብሮኝ የሚኖር ትዝታን ጥሎብኝ አልፏል።


(አዲስ ዘመን፤ አርአያ ጌታቸው፤ 75ኛ ዓመት ቁጥር 022፤ ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም)

ብፁዕነትዎ ለሰጡን ጊዜ እያመሰገንን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ዋና ዓላማ ምን እንደነበር ሊነግሩን ይችላሉ?

በቅድሚያ ይህችን ውብ አገር በመጎብኘቴ የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለኹ። ከዐሥርት ዓመታት በፊት ገና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ እያለኹ ስለ ኢትዮጵያ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ በርካታ ታሪኮችን እየተማርኩ ነው ያደግኹት። ያ ትምህርት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትልቅ ተስፋ እና ሕልም አሳድሮብኛል። እግዚአብሔር ያን ሕልሜን እውን አድርጎልኝ እነኾ ለአምስት ቀናት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ችያለኹ።

የጉብኝቴ የመጀመሪያው ዓላማ፣ በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውንና ለክፍለ ዘመናት የዘለቀውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ነው። ከዚኽም ባሻገር የኢትዮጵያን ሕዝብ በማኅበራዊ አገልግሎቶች ማገልገል የምንችልበትን ዕድል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር በመነጋገር ኹኔታዎችን ለማመቻቸት ነው።

በኹለተኛ ደረጃ፣ በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳት ሲኖዶሶች አማካይነት እ.አ.አ በ1994 የተፈረመውን የጋራ ሰነድ ወደ ሥራ ለማስገባትም ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት። ይህ ስምምነት እ.አ.አ በ2008 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ኢትዮጵያን ጎብኝተው በነበረበት ወቅትም ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት መደረጉ የሚታወቅ ነው።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ሌሎች ጳጳሳት እንዲኹም እኔና ከእኔ ጋር የመጡ የቤተ ክርስቲያናችን ልኡካን ይህን ሰነድ ወደ ሥራ ለማስገባት መግባባት ላይ ደርሰናል፤ ሰነዱን ተግባራዊ ለማድረግም በየሦስት ዓመቱ ለመገናኘት በኹለታችንም ወገኖች ተወስኗል። በዚኽ መሠረት እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት እ.አ.አ በ2018 በካይሮ ለመገናኘት እና ለመመካከር አስበናል። በተጨማሪም በየሦስት ዓመቱ በፓትርያርክ እና በጳጳስ ደረጃ ጉብኝት ይኖረናል። በእኛ በኩል ይህን ተግባር የሚከታተል አንድ ጳጳስ አለን።

በጉብኝትዎ ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መገናኘትዎ ይታወቃል። ከባለሥልጣናቱ ጋር በነበርዎ ቆይታ በምን ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ ሊነግሩን ይችላሉ?

እንደተባለው ጉብኝቴ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም መገናኘትን ይጨምር ነበረና ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ ከአፈ ጉባኤው አቶ አባዱላ ገመዳ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ጋር ቆይታ ነበረኝ።

ከባለሥልጣናቱ ጋር በነበረኝ ቆይታ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተወያይተናል። በዚኽም ግድቡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የሚውል መኾኑን አረጋግጠውልኛል። ከዚህ ውጭ ለመስኖም ኾነ ለምንም ዐይነት የእርሻ ተግባር እንደማይውል ተገልጾልኛል። በአጠቃላይ ግድቡ በግብፃውያን ላይ ተጽዕኖ እንደሌለው ነው የተረዳኹት። ይህን በመስማታችን እጅግ ተደስተናል።

ይህን ርግጠኛ የኾነ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል ከመስኩ ባለሞያዎችም እንደምንሰማው ተስፋ እናደርጋለን። የባለሞያዎቹ መልስ እና ማረጋገጫ ለኹላችንም የተሟላ መልስ ይኾናል፤ ለግብጻውያንም መልካም ዜና ይኾናል። ከዚኽ ባሻገር ከባለሥልጣናቱ ጋር በነበረኝ ቆይታ፣ በኹለቱ አገሮች መካከል ስላለው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነትም ተወያይተናል። በውይይታችን ያረጋገጥነውም በአገራቱ መካከል የሚኖረው ጠንካራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ውጤታማ በኾነ መጠን የኢትዮጵያንና የግብጽን ሕዝቦች ተጠቃሚ ያደርጋል።

የግድቡ ግንባታ ስለሚኖረው ተጽዕኖ ከመስኩ ባለሞያዎች የሚሰጠውን ምላሽ ለመስማት እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል። ይኼ ማለት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተሰጠዎት ማረጋገጫና ማብራሪያ አልተደሰቱም ወይም አልረኩም ማለት ነው?

በጭራሽ አልተረዳኸኝም ማለት ነው። ጉብኝቴ መንፈሳዊ ጉብኝት እንደመኾኑ መጠን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በነበረኝ ቆይታ ስለ ግድቡ ዝርዝር ውይይት አላደረግንም። ያም ኾኖ ግን ግድቡ በግብጽ ላይ ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ተነግሮኛል። ይኼ በባለሥልጣናቱ የተነገረኝ ሐቅ እንዳለ ኾኖ ከዘርፉ ባለሞያዎች የሚሰጠው አስተያየት ግን የተሻለና አስተማማኝ ይኾናል።

ቀደም ብሎ ከሦስቱ አገራት የተውጣጣና ዓለም አቀፍ ባለሞያዎች የተካተቱበት ቡድንኮ ግድቡ በግብጽም ኾነ በሱዳን ላይ ምንም ዐይነት ጉዳት እንደማያስከትል በሪፖርቱ ገልጿል።

በእዚህ ዙሪያ የምነገርኽ በግብፅ ከሚታተሙ ጋዜጦች አንብቤ ያገኘኹትን መረጃ ነው። በወቅቱ ቡድኑ ያወጣው መረጃ ጊዜያዊ መኾኑን ዐውቃለኹ። ዝርዝር መረጃው ያለው በባለሞያዎቹ እና በአገሮቹ መንግሥታት ባለሥልጣናት እጅ ነው። ስለዚኽ ከእነዚኽ አካላት መረጃውን ማግኘት ምንጊዜም ለሕዝቡ የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። አኹንም አጠንክሬ ልናገር የምወደው፣ የእኔ ጉብኝት መንፈሳዊ እና ከኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት የእርስ በርስ ግንኙነት ጋር የተያያዘ እንጂ ከግድቡ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ነው።

በግድቡ ዙሪያ የቤተ ክርስቲያንዋም ኾነ የእርስዎ የግል ስሜት ወይም አቋም ምንድን ነው?

ማንም አገር ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመልማትና በአገሩ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የማልማት መብት አለው፤ ነገር ግን ከዚሁ ጎን ለጎን መታወቅ ያለበት ልማቱ የጎረቤት አገሮች እና ሕዝቦች ላይ ጉዳት ማስከተል እንደሌለበት ነው። የእኛ ትልቁ ሐሳብም ይኸው ነው።

እንደማስበው ግብጽ እና ኢትዮጵያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላቸው ታላላቅ አገሮች ናቸው። ስለኾነም በተለያዩ መስኮች የዚህ ዐይነት ታላቅ ፕሮጀክት ያስፈልጋቸዋል። ሕዝቦቻቸውም ይህን ዐይነት ግዙፍ የኃይል፣ የኢንዱስትሪ፣ የሕክምና፣ የትምህርት እና መሰል የማኅበራዊ ግልጋሎት መስጫ ፕሮጀክቶችን ይፈልጋሉ። ስለኾነም ፕሮጀክቱን ማልማት የኢትዮጵያ መብት ነው፤ ነገር ግን በግብጽ ላይ ጉዳት ማስከተል የለበትም።

መስቀል ዐደባባይ በተከበረው የደመራ በዓል ላይ መታደምዎ ይታወሳል። በወቅቱም በስፍራው ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር አድርገዋል። ብዙ ወገኖች ከንግግርዎ መስማት ይፈልግ የነበረው፣ «ስለ ግድቡ ምን ይላሉ?» የሚለውን ነበር። እርስዎ ግን ምንም ያሉት ነገር የለም። ለምን ይኾን?

በዓሉ መንፈሳዊ በዓል ነበራ። ዕለቱ የመስቀል በዓል የሚከበርበት እንጂ ስለ ግድቡ ወይም ስለ ውኃ የሚወራበት በዓል አልነበረም። ይኸው ነው ምክንያቱ።

ጥሩ። የመስቀል በዓል አከባበርንስ እንዴት አገኙት?

በጣም የሚያስደስት በዓል ነበር። ከዚህ በፊት እንዲህ ዐይነት ትልቅ ሃይማኖታዊ በዓል ተመልክቼ አላውቅም። የበዓሉ አከባበር ዘመናትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያውያን ባህላዊ መንገድ የተቃኘ ነው። ይህ ለእኔ አዲስ ነው። በሕዝቡ እና በካህናቱ አለባበስ ሳይቀር በጣም ተማርኬያለኹ። የአልባሳቱ ቀለማት፣ ዝማሬው እና እንቅስቃሴዎች ሁሉ አስደሳች ነበር።

በናይል ወንዝ የተነሣ የምሥራቅ አፍሪካ አብዛኞቹ አገሮች እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። ከዚኽ አንጻር አገሮቹ ወንዙን እንዴት በጋራ መጠቀም እንደሚገባቸው ያለዎት አባታዊ ምክር ምንድን ነው?

ሦስት ዐይነት ባህሎች አሉ። የመጀመሪያው፣ የውይይት ባህል ነው። ኹለተኛው፣ የጠብ ወይም የጦርነት፤ ሦስተኛው ደግሞ የመለያየት። ከሦስቱ ባህሎች የመጀመሪያው በጣም አዎንታዊና ተመራጩ ነው። ስለኾነም የወንዙ ተጋሪ አገሮች ሊከተሉት የሚገባው ይህን ዐይነቱን መንገድ ነው። ኹላችንም በሰላም፣ በእኩልነት፣ በመቻቻል፣ በፍቅር መኖር እንፈልጋለን። ሕዝባችንና አገራችንን ማገልገልም እንፈልጋለን። የአፍሪካ አገሮች በተፈጥሮ ሀብት ባለጸጋ ናቸው። ይህን ሀብት በመተጋገዝና በመተባበር ካለማነው ታላቅ አህጉር እንኾናለን።

በኹለቱ አገሮች መካከል ካለው ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ አንጻር በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያለው ትስስር ያን ያህል ጠንካራ ነው ማለት አይቻልም። ከዚኽ አንጻር አገሮቹ በቀጣይ ምን መሥራት አለባቸው ይላሉ?

በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በታዋቂ ዲፕሎማቶች እና መሰል አካላት መካከል የሚካሔድ ጉብኝት እና ውይይት ኹሉን አቀፍ ግንኙነት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማምጣት ይችላል ብዬ አስባለኹ። የዚኽ ዐይነቱ አካሔድ በአገሮቹ መንግሥታት እና በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል መተማመንን ይፈጥራል። መጪውንም ጊዜ በጋራ አብረን የምንገነባው ይኾናል።

ቅዱስነትዎ ወደ ሌላ ነጥብ ልውሰድዎና፤ ኢየሩሳሌም አገር በሚገኘው የዴር ሱልጣን ይዞታ ዙሪያ በኢትዮጵያ እና በግብጽ አባቶች መካከል አለመግባበት እንዳለ ይታወቃል። በዚህ ዙሪያ ከኢትዮጵያው ፓትርያርክ ጋር ተወያይተዋል? በጉዳዩ ዙሪያስ ምን አስተያየት አለዎት?

ይኼ ያረጀ ችግር ነው። እዚህ የመጣነው ስለ አረጀ ችግር ለመወያየት አይደለም። እኛ እየጣርን ያለነው ኹለቱ አገሮች አዲስ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ነው። እንደ አጠቃላይ ለመናገር ግን፣ በኢየሩሳሌም ባሉ የግብጽ እና የኢትዮጵያ መነኰሳት መካከል መልካም የኾነ ግንኙነት አለ።

ቀደም ሲል ስለ ኢትዮጵያ የነበረዎት ዕውቀት ምን ይመስል ነበር? እዚኽ ከመጡ በኋላስ ምን አዲስ ነገር ተመለከቱ?

ኹሉም ነገር ተለውጧል። ከሕዝቡ ጋር በተገናኘኹባቸው አጋጣሚዎች ኹሉ የተረዳኹት ነገር ሕዝቡ ምን ያኽል ቅንና የዋህ መኾኑን ነው። ኹሉም ማለት እችላለኹ። ስለ አገራቸው ማደግ ያላቸው ፍላጎት ታላቅ ነው። ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸው ጥብቅ ቁርኝት ታላቅ ነው። ይኼ ደግሞ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። በገዳም ውስጥ በነበረኝ ቆይታም ፍጹም ገዳማዊ የኾኑ መነኰሳትን ተመልክቻለኹ። በኢትዮጵያ ያለው ገዳማዊ ሕይወት በግብጽ ካለው የበለጠ ከባድ ነው።

ወደ ግብጽ ሲመለሱ ለአገርዎ ሕዝብ ምን ይናገራሉ?

ለግብጻውያን የምናገረው፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ብቻ ሳትኾን በሕዝቦቿም ጭምር በጣም ውብ አገር መኾኗን ነው። ግብጻውያን ቀሳውስትም ኾኑ ሌሎች ግብጻውያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አበረታታለኹ። ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እመክራለኹ። በተጨማሪም ግብጻውያን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እንዲያነቡና እንዲያውቁ እመክራለኹ። በአጠቃላይ የአምስት ቀናቱ ጉብኝት እስከ ዘላለም አብሮኝ የሚኖር ትዝታን ጥሎብኝ አልፏል።

አዲስ ዘመን፦ ለሰጡኝ ጊዜ እና ምላሽ በጣም አመሰግናለኹ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ፦ እኔም አመሰግናለኹ።

Source:: haratewahido

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.