መለስና ኢሳያስ ማንዴላን ቢሰሙ ኖሮ …….

ፕ/ር ማሞ ሙጬ ስለ ኢትዮጵያዊነትና ፣ ስለ ዘር ፖለቲካ በአንድ ወቅት የተናገሩት

የዘር ፖለቲካ አይጠቅምም የሚለው አቋሜ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ አፍሪካዊነት ብቻ ይበቃል፡፡ ወደ ታች ወርዶ በቋንቋ ምናምን መከፋፈሉ አያዋጣም፡፡ ዋናው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶቹ መጠበቃቸው ነው። ቋንቋ የሰውን ልጅ ሊከፋፍል አይገባውም፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ 11 ያህል ቋንቋዎች ለማስተማሪያነት ይውላሉ፡፡ በእነሱ ዘንድ ቋንቋዎቹ ከመግባቢያነት ያለፈ ትርጉም የላቸውም፡፡ እኔ አሁን ኦሮሚኛ፣ ትግሪኛ፣ አማርኛ… የሌሎች ቋንቋዎችን ሙዚቃዎችም ስሰማ ደስ ይለኛል፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አማራ ብዬ ራሴን የምነጥለው፡፡ በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን ማለት ምን ማለት ነው? እኔ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ መብቶች በሙሉ በህግ ጥበቃ ከተደረገላቸው በቂ ነው፡፡

እኔ አሁን ማሞ ሙጬ ነው ስሜ፡፡ አላውቅም አባቴ ኦሮሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎች ጎንደርን ለረጅም አመታት አስተዳድረዋል፡፡ ጎንደር ቤተ መንግስት ውስጥ ኦሮሚኛ ቋንቋ ይነገር ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍፁም የተደባለቀና የተቀላቀለ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያዊነትም ባለፈ አፍሪካዊነት ላይ አስቀድመን ብንንቀሳቀስ ለእኛም ሆነ ለአፍሪካውያን ትልቅ ድል ነው፡፡ ህዝቡ የፓን አፍሪካኒዝምን ፅንሰ ሃሳብ ቢረዳ፣ ሌሎች አፍሪካውያን በፊት ከሚሰጡን ፍቅር የላቀ ፍቅር ይሰጡን ነበር፡፡ አሁን ያሉት ፖለቲከኞች በዚህ መንፈስ እንዲራመዱ እግዚአብሔር ይርዳቸው።

እኛ ሁሉም ነገር አለን፡፡ ቋንቋው፣ የስነ ህንፃ ጥበቡ፣ ስነፅሁፉ… ሁሉም አለን፡፡ ግን የራሳችንን ትተን ሌላውን ወደ መኮረጁ ገባን፣ ኩረጃ ጥሩ አይደለም፡፡ አወዛግቦናል። ሁሉንም ሚስጥራችንን የጥንት ኢትዮጵያውያን ተንትነው አስቀምጠውልናል፡፡ የእግዚአብሔር ማንነት ሚስጥር፣ የቀንና ሌሊት ሚስጥር የመሳሰሉት፡፡ በአቡሻከር እስከ 15 እና 22 ፕላኔቶ አሉ የሚል ተፅፏል፡፡ እኛ 9 ፕላኔቶች አሉ ተብለን ነው የተማርነው፡፡ አሁን ፈረንጆቹ 13 አድርሰዋቸዋል፡፡ እንግዲህ እኛ በመደበኛ ትምህርት ባንማረውም የቀደሙት ግን 22 ፕላኔቶች አሉ ብለው በአቡሻከር አስቀምጠዋል፡፡ አሁን እኔ ፕሮፌሰር ተብዬ በድጋሚ 13 ፕላኔቶች አሉ እየተባልኩ ልማር ነው ማለት ነው፡፡

ማንዴላ ከእስር ቤት ሲወጣ ነው ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው፡፡ ማንዴላ በወቅቱ ምን አለ አሉ? ለአቶ መለስ እና ለአቶ ኢሳያስ ስልክ ደውሎ “እንዴት አንድ ህዝብ ትከፋፍላላችሁ እኛ ከአውሮፓ የመጡ አፍሪካኖችንና ከአፍሪካ የተፈጠሩ አፍሪካኖችን አንድ እያደረግን፣ ለእናንተ አንድ የሆነውን ህዝብ እንዴት ትለያያላችሁ”? ብሏል ይባላል፡፡

በወቅቱም አቶ መለስ እና አቶ ኢሳያስ አንደኛቸው ፕሬዚዳንት አንደኛቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ምክር ለግሷል፡፡ አገሪቱ ሳትገነጠል ማለት ነው፡፡ ግን አልተቀበሉትም፤ መከፋፈሉ መጣ፡፡
እኔ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስሄድ፣ አንድ ደስ ያለኝ ነገር ምርጫ ሲያደርጉ ማንም ይመረጥ ዋናው የምርጫው ሂደት ውጤታማ መሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ወገን ተጠቃሁ አይልም፡፡ ለምሳሌ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መሪ ብዙዎቹ አይወዱትም ግን ምርጫው ከወገናዊነት የፀዳ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ሂደት አምስት ጊዜ ሰላማዊ ምርጫ አድርገዋል፡፡ እኔ በዚህ በጣም እኮራባቸዋለሁ፡፡

ነጮች ጥቁርን ሰይጣን ነው እንጂ ሰው አይደለም ይሉ ነበር፡፡ እነ ማንዴላ ያንን ችግር በግጭት ሳይሆን በእርቅና በሰላማዊ መንገድ ነው የፈቱት፡፡ አሁን ከአፍሪካ ሃገራት መካከል እነ ቻድ፣ ማሊ፣ ሊቢያ ሌሎችም በግጭት ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህ ሃገሮች የደቡብ አፍሪካን ፈለግ ተከትለው ችግራቸውን ቢፈቱ ህዝባቸው ምንኛ በታደለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ለግጭቶች መላ ሲፈለግ በመገዳደል ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ በመናናቅ፣ በመዘላለፍ፣ ባለመተማመንና በውይይት ቢሆን ሃገርን በማስበለጥ፣ በመረዳዳት፣ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና በመወያየት መሆን አለበት፡፡ እኛ የፈለግነው ወገን ሥልጣን ካልያዘ ሞተን እንገኛለን የሚለው አስተሳሰብ መለወጥ ይኖርበታል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.