አማርኛም አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ የሆነበት አዲስ ክልል አስፈላጊ ነው – ግርማ ካሳ

እስቲ እነዚህን ፎቶዎች ተመልከቱ። አንዱ የኦነግ ካርታ ነው። ሌላው ደግሞ የአማራ መንግስት ብለው ያወጡት ነው። የኦነግ ካርታ እንዳለ ቀድሞ የሸዋ ክፍለ ሃገር ተብሎ የሚጠራዉን እንዲሁም በርካታ መሬቶች ከወሎ ያጠቃልላል። የአማራ መንግስት ካርታ ደግሞ የቀድሞ የቤጌምድር፣ የጎጃም፣ የሸዋና የወሎ ክፍለ ሃገራትን፣ አሁን ወደ ትግራይ በሃይል የተጠቃለሉ ሁምራ፣ ወልቃት፣ ጠገዴን ፣ ጨለምታና አላማጣን ያጠቃልላል።

የኦነግ ካርታ ከሞላ ጎደል አሁን ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራዋን፣ በኋይል ኦነግና ሕወሃት በጦርነት አሸናፊ ስለሆኑ፣ በሕዝቡ ላይ የተጫነዉን ክልል ይመስላል።

ሁለቱም ካርታዎች አዲስ አበባን እና የሸዋ ክፍለ ሃገርን ወደ እነርሱ ቀላቅለዋል። ካርታዎቹ ተግባራዊ ይሁኑ ከተባለ፣ ሸዋን እና አዲስ አበባን የ “አማራ መንግስት” ዉስጥ ለማድረግ፣ ወይንም በኦሮሚያ ዉስጥ ለማስቀጠል ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ሊደረግ ነው ማለት ነው። የኦሮሞ ብሄረተኞች ያልሆኑት አሁን ያለችዋን ኦሮሚያ መቼም አይቀበሉም። ኦሮሞ የሚባሉት ሸዋ ወደ አማራ መንግስት መግባቱን እንደዚሁ።

አሁን ያለቸዋ ኦሮሚያ ትቀጥል ከተባለ፣ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆነውን የአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪ፣ 80 በመቶ አማርኛ ተናጋሪ የሆነው የአዳማ/ናዝሬት፣ ፣ በአጠቃላይ 44% የሚሆነው ኦሮሞኛ አንደኛ ቋንቋዉ ያልሆነው የኦሮሚያ አራቱ የሸዋ ዞኖች ነዋሪዎች እንዴት ነው የሚሆኑት ? ሸዋ ወደ “አማራ መንግስት” የሚጠቃለል ከሆነ ወደ 54% የሚሆነው ኦሮምኛ ተናገሪስ ምንድን ነው የሚሆነው ? አስቸጋሪ ሁኔታ ነው። ትርፉ፣ ንትርክ፣ ግጭት ፣ ምናልባትም የርስ በርስ ጦርነት ነው። አሁን በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዙሪያም የተነሳው ችግር ከዚሁ ጋር የተነሳ ችግር ነው።

እነዚህ ሁለቱም ካርታዎች ሕዝቡን ወደ ጦርነት የሚመሩ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ሰላም ካርታዎች ናቸው። አማራ፣ ኦሮሞ እየተባሉ ለሚጠሩት ወገኖች የሚጠቅም አይደለም። ይህ አይነቱ ካርታም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።።ለምሳሌ ሸዋ አማራ አይደለም ፣ ኦሮሞም አይደለም። ሸዋ ሸዋ ነው። ሸዋ ግማሹ አማርኛ ተናጋሪ፣ ግማሹ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ነው። የሸዋ ሕዝብ ከጥንት ተፋቅሮና ተዋልዶ የኖረ ነው። ሁለቱንም ቋንቋዎች የሚናገሩ የሸዋ ነዋሪዎች ብዙ ናቸወ፡፡

እነዚህ ካርታዎች ላይ የምናየዉን እብደት ትተን ፍቅርና መስማማት ሊያመጣ የሚችል መፍትሄ ማስቀመጥ አለብን። ለምሳሌ አማርኛም፣ አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ የሆነበት የሽዋ ክልል በማበጀት ፣ በፍቅርና በመተባበር መቀጠል ይቻላል።

በዚህ ጽሁፍ ላይ ሸዋን እንደምሳሌ ጠቀስን እንጂ ተመሳሳይ ሐሳብ በሌሎች ቦታዎችም ማንሳት ይችላል። ይሄ ዘር ላይ ያተኮረ አስተሳሰብ በሽታ ነው። ዘረኝነት በሽታ ነው። የሚያዋጣው ተከባብረን ፣ ተስማምተን ለሁላችንም የሚበጅ፣ የሁላችንም መብት የተከበረባትን አገርን መመስረት ነው።

ይሄ እንዳይሆን አሁን ያለው ዘረኛው የሕወሃት መንግስት እንቅፋት እንደሆነና አሁን እያየን ያለነው የዘር በሽታ እንዲስፋፋ ፍላጎት እንዳለው የታወቀ ነው። አማራ ፣ ኦሮሞ እያለ፣ በተናጥል ሁለቱን እየመታ፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገዉን ጥረት መቀጠሉ አይቀርም። ሆኖም መንቃት አለብን። “እኛ እና እነርሱ ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ “ ወዘተረፈ ማለታችንን አቁመን “እኛ” ማለት መጀምር አለብን። እያንዳንዳችን በዘራችን ሳይሆን በስብእናችንና በተግባራችን መመዘን አለብን። መታወቂያችን ላይ ዜግነታችን እና የትዉልድ ቦታችን ብቻ ከተጻፈ ይበቃል።

11218852_Satenaw News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.