የቀድሞ ዴምሕት አባላት በወያኔ ፎቶገጭ ቤት – ነፃነት ዘለቀ

እንደምን ሰነበታችሁ፡፡ እንኳን ለአዲሱ ዓመት የ2008 ዓ.ም ሁለተኛ ወር “ለጥቅምት አንድ አጥንት” በሰላም አደረሳቹ፡፡ ጥቅምት ብርዳምና ንፋሳም ነው፡፡ ዘንድሮም እንደዛው ነው፡፡ የአዲስ አበባ የሰሞኑ ብርድ ሚስት ያሳቅፋል፡፡ ግን ስንገናኝ ሰላምታ የማንለዋወጠው ለምንድነው? ብዙ መጣጥጥፍ ጸሐፊዎች ይህን ወግ ልማድ ረስተው በቀጥታ ሊያስተላልፉት ወደሚፈልገጉት ቁም ነገር ይገባሉ – ያበሳጩኛል፡፡ “እንዴት ሰነበታችሁ” ማለት ማንን ገደለ? ኧረ ሳልረሳው – በመግቢያየ “አደረሳቹ” የሚል ቃል ሆን ብዬ ጽፌያለሁ፡፡  አማርኛ ቋንቋ በጣም ቅጥ አምባሩ እየጠፋ መምጣቱን ለመጠቆም ፈልጌ ነው እንዲያ ያልኩት፡፡ ትልልቅ የመሥሪያ ቤት ደብዳቤዎችን ብታዩ – አማርኛ አፍቃሪው ሕወሓት እንዳይቆጣኝ እንጂ – አማርኛው እንዴት እንደተመሰቃቀለ ልገልጽላችሁ አልችልም፤ በስማም! ውጥንቅጡ ወጥቶላቹሃል – እምልክ ገባክ? እንዲክም ስልክ በአንድ ወይ በሁለት አካባቢውች ብቻ እንዳይመስልክ –  በሁሉም ቦቶችና ሥፍሮች ነው አማርንኛ እየተቀጠቀጠ ያለልክ፡፡ ምን እንደነካን አይታወቅም – ደግሞም “ዋናው መግባባት ነው” የሚል ፈሊጥ ተስፋፍቶልካል – ደካማ ጎንንና ስንፍናን መሸፈኛ ፈሊጥ ነው፡፡ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ …”  ‹ጨው ነጋዴ መልሶ ገዛው› እንዲሉ ነው ነጎሩ፡፡ ምን ይሻላል? “ እዚህም እሳት…እዚያም  እሳት … እሳት.. እሳት” አለ ያ ታሪካዊ የኪነ ጥበብ ሰው ቴዲ አፍሮ በ17 መርፌ ዘፈኑ (“ጃን ያስተሰርያል” ለማለት ፈልጌ ርዕሱ ለጊዜው ተሰውጦብኝ ነው)፡፡

ዋናው ሥራ አሥኪያጅ ወይም ሚኒስትር “…አስታውቃለሁ” መባል የሚገባውን “ …አስታውቃለው፡፡” የሚል ማሣረጊያ ቃል ያለው ደብዳቤ ላይ ፊርማውን አስቀምጦ በተላላኪው ሲሰድ ታያላችሁ – ዘመነ ድንቁርና ነው የገጠመን፤ ዘመነ ግዴለሽነትም ጭምር፡፡ እንዲያውም ይህ ዓይነቱ ስህተትማ ቀላልና ሊታገሱት የሚቻል ስህተት ነው፡፡ ይህን መሰል ከየቢሮው የሚወጣ ደብዳቤና በየቦታው የተለጠፉና የተሰቀሉ የማስታወቂያ ጽሑፎችን ብናይ አማርኛና እንግሊዝኛ በእግራቸው እየሄዱ እንደሆነ ማረጋገጥ እንችላለን፤ የጉራማይሌው ድረታ – የሆሄያት አጻጻፍ ችግር (የእስፔሊንግ ስህተት) … ግዘፍ ነስቶ “የቋንቋ መምህር ያለህ!” እያለ ነው – የቋንቋ መምህራኑ ራሳቸው ለምሳሌ “How is yours childs?” ወይም “ከአርዕስቶቹ ጋር የማይሄዱ ከባባድ ቃላቶችን ካለመጠቀም ተቆጠቡ” የሚሉ በሰዋስው ስህተት የታጨቁ ዐረፍተ ነገሮችን ሲናገሩ ልትሰማ ትችላለሀ – ጊዜው ነው፤ ጊዜውም ስህተትንና ነውረኝነትን እንደመልካም ዕሤት የሚቀበልና ሰዎችን ሳይወዱ በግድ የሚያባልግ ነው፡፡ ዕውር ለዕውር እየተማራ ሀገር ገደል ገባች! ወይ ወያኔ፤ በምን ዓይነት የሥኬት ጉዞ እየተምበሸበሹ እንደሆነ በጣም ጥቂቶች ብቻ ነን የምናውቀው፤ ዶግሞ’ኮ ይህ አደገኛ ሁኔታ የሚያሳስበውም ሆነ የሚያስጨንቀው አካል የለም፡፡ ተዓምር ነው፡፡ እንዲያው ለመግቢያ ያህል እንዲህ አልኩ እንጂ አነሳሴ ሌላ መሆኑን ርዕሴ በግልጽ ይናገራል፡፡ በዚህ በጠቀስኩት የቋንቋ አጠቃቀም ስህተት ልጻፍ ብልማ ወረቀት አይበቃኝም፤ የነገ ሰው ይበለኝ ግን፡፡ እንደሞትን ካልቀረን መገናኘታችን “ግድ ይላል”፡፡ ወይ አማርኛ! ኤርምያስ ለገሠ “ባለቤት አልባ ከተማ” ብሎ መጽሐፍ መጻፉን አትርሱ፡፡ “ባለቤት የሌለው እየጠፋ ያለ ቋንቋ” በሚል ‹አርዕስት› – ማለትም ርዕስ – ደግሞ አንዱ ይጻፍ፡፡

ዛሬ የወያኔን ቴሌቪዥን ድንገት አየሁ፡፡ ቤተሰቦቼ የቲቪ ጣቢያ (ቻናል) ሲቀያይሩ ድንገት EBC 1 የሚባለው የወያኔ ቱሪናፋ መስመር ላይ ይደርሳሉ(የስም መለዋወጥ የተፈጥሮ ጠባይን የሚለውጥና ውሸታምነትን በሕዝብ ዘንድ የሚያስረሳ ይመስል በኩረጃ የሚስተካከለው የሌለው ጦጣው ወያኔ ቲቪውን EBC አለና ወደ BBC, CBC, CNN,… ለማጠጋጋት ሞከረ – ማፈሪያዎች! ለመሆኑ “ኮርፖሬሽን” ምን ማለት ነው? አንድ የወያኔ ካድሬ እንደፈለገው ለሚያሽከረክረው ጥሩምባ መሥሪያ ቤት ይህ ስም ይከብደዋል፤ ነገሩ “ሲወልዱ አይታ ..” እንደሚባለው ነው፡፡ አሃ፣ ለስምማ “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አይተ ማነው ብፃይ ኃይለማርያም ደሳለኝ” ይባልስ የለም? ቂቂቂቂ…. እኔን ጠ/ሚኒስትር ያድርገ..ኝ!) ዝኮነ ኮይኑ የወያኔን ቲቪ እንደማላይ የምታውቀው ባለቤቴ ፊቴን አየት አድርጋ ልትቀይረው ስትል ተይው አልኳት – አለወትሮየ ተይው በማለቴ እየገረማት ተወችው፡፡ ቀርቦ የነበረው ዝግጅት የሞላ አስገዶም ልጆች በወያኔ ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ እየተደረገላቸው የሚያሳይ ዶኩመንተሪ የሚመስል ፊልም ነበረ፡፡ እንደምንም ጨክኜ ለመከታተልና ምን እንደሚሉ ለመስማት የትግስት ፈረሴን ቼ አልኩና ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡

“የቀድሞ የዴምሕት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የ… ግንባር መሪ” የሚል የማዕረግ ቅጥያ በምስላቸው ግርጌ የተለጠፈላቸው ፍጹማን ባላገሮች ናቸው የሚጠየቁት፤ ባላገር ስል ያልተማሩና ሥልጣኔ ያልዳሰሳቸው ደናቁርት ማይማን ለማለት ፈልጌ እንጂ በሌላ መልክ እንዳትተረጉሙብኝ አደራችሁን – ፀጉር ስንጠቃ አልወድም፡፡ አነጋገራቸው፣ (የተሰጣቸው ሊሆን ቢችልም) አለባበሳቸው፣ የሰውነት መላ አኳኋናቸው፣ የቋንቋና የሃሳብ ግንኙነታቸው፣  እንኳንስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሊመስሉ የዕድር ቤት ዘበኛም ሊሆኑ የማይችሉ ፋርጤዎች ናቸው – (ውይ ጉዴ – “ፋርጤ” ለካንስ “ፋርጣ” ከሚል የቦታ ስም የወጣ የወገን ቅጽል ነው፡፡ ግን ግዴለም “ባላገር” ለማለትም በፈሊጣዊ አገባብ ስለምንጠቀምበት እንደዚያ ተረዱልኝ – በቦታ አመልካችነቱ ከሆነ ብዙ ፋርጤ ጓደኞች አሉኝና በቃሉ ፈሊጣዊ አገባብ ቅር እንደማይሰኙብኝ አምናለሁ፡፡) እናም እነዚህን የመሰሉ ሰዎች በርግጥም ነፃ ሊያወጡን በረሃ ወርደው ከሆነ ከበፊቱ ስህተት ነበር ብቻ ሣይሆን እነሱን ፊደል ለማስቆጠርና ቀለም ለማስለየት እንዲሁም መጠነኛ የፖለቲካ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እኛ ነበርን እነሱ ወደሚኖሩባቸው አካባቢዎች መውረድ የነበረብን፡፡ ሀገርንና ሕዝብን ነፃ ማውጣት ለካንስ እንዲህ ቀላል ኖሯል እንዴ? ቼጉቬራና ሆቺሚን እንደነዚህኞቹ ማይም ባላገሮች ነበሩ ይሆን? እኔማ ሣቄን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ደግሞም ሁሉ ነገር ተወነባበደብኝና ግራ ገባኝ፡፡ ነፃ አውጪ መጀመሪያ ራሱ ነፃ የወጣ መሆን አለበት፡- ከተራው ዜጋ በበለጠ ወይም በተሻለ የነቃ፣ የተማረና የተመራመረ፣ ለማንኛውም ዓይነት ግልብና ህንፍሽፍሽ አስተሳሰብ በቀላሉ የማይንበረከክ፣ የጠንካራ አቋም ባለቤት፣ የጠንካራ ዲስፕሊን ጌታ … መሆን ይገባዋል እንጂ እንደነዚህ ዓይነት ልፋጭ ዜጋ ነፃ አውጪ ቢባል የነፃነትን ዋጋ ከዜሮ በታች ማውረድ ነው፤ እውነቴን ነው የምለው – ደግሞም አሁን እነዚህን የመሰሉ ማፈሪያዎች ስላየሁ አይደለም – ነፃ አውጪ እንደዚህ ከሆነ ባፍንጫዬ ይውጣ፡፡ ስለነፃነት ምንነትና አስፈላጊነት ምን አውቀውና ምን ገብቷቸውስ ነው ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ “ነፃ ሊያወጡ” በረሃ የወረዱት? ሞላ ራሱን ባለፈው ሰሞን ሳየው የተሰማኝ ስሜትም ይሄው ነበር፤ ከኔ የማይሻል ሰው ምን መሆኔንና እንዴት እንደምኖር ሣይረዳ ነው ነፃ ሊያወጣኝ የሚነሣ? ይህማ ልክ እንደወያኔ የወታደር አመላመል ማለት ነው፡፡ ወያኔና ወታደር ምልመላው ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ ነው – ቢታወቅለት፡፡ አንድ አንቀጽ ጣልቃ ላስገባና እመለስበታለሁ፡፡

ይቺ “የሻቢያን ሜካናይዝድ ጦር፣ እግረኛ ጦር፣ .ቲሪሪም ቲሪሪም ‹እየጠራረግን› ከስምንት ሞቶ በላይ ሠራዊት ይዘን ከኤርትራ ምድር ወጣን” የሚሏት የነአስገዶም ንግግር በጣም ትገርመኛለች፡፡ እንዴት ነገሩ – ያን ጠረጋና የሰገሌን ጦርነትና ገና ወደፊት እንደሚደረግ የሚጠበቀውን ›ስፔስወር› የሚያስንቅ ድንቅ ጦርነት አንዳቸው እንኳን በሞባይላቸው ቀርጸው ያላሳዩን ለምን ይሆን? እንደዚህ ዓይነት ታላቅ ወታደራዊ ‹ኦፐሬሽን› ሲታቀድና ሲፈጸም ኮብላዩ የቀድሞ የዴምሕት ሠራዊት ይህን ታላቅ ጀብድ ቀርፆ እንዴት ለታሪክ አያስቀምጥም ወይንስ ገና በወያኔ ስቱዲዮ እየተቀናበረ ይሆን? ከማንም ወገን ሆኜ ሣይሆን እንደ አንድ ነፃ ታዛቢ ይህን “እየጠራረግን ወጣን” የሚሉትን ቀልድ ስሰማ ከማሣቅ አልፎ በጣም ያስገርመኛል – በውነትም ጠራርገው ከሆነ ከካርን የተሠሩ ወታደሮች በየበረሃው አርቲፊሻል ጠበንጃና የካርቶን ተዋጊ ጀቶችን ይዘው ቀሞው ነበር ማት ነው – እነዚህ ጀለንፎዎች ናቸው አንድን የሠለጠነና የታጠቀ ጦር ጠራርገው የሚወጡት፤ መሪዎቹ እነዚህ ከሆኑ ተመሪዎቹ ምን ዓይት ይሆኑ? ለምን በአግባቡ አይቀለድም? የቀልድም እኮ ጡር አለው፡፡ ደግሞም “ጄኔራል” ሞላ አስገዶም እጁን እያወናጨፈ እንዴት እንደጠራረጓቸው በሰውነት እንቅስቃሴ ተደራቢ “ቋንቋ” ሲገልጽ አንድም የሻቢያ ጦር የቀራቸው አይመስልም፡፡ እነሞላ በጣም ጀግኖች ናቸው ማለት ነው፡፡ ግን ግን ማስረጃ ስላላቀረቡ የሚሉት ሁሉ ከወታደር ቁጥር አንስቶ እስከ ግዳይ መጣሉ ድረስ ውሸት እንደሆነ መረዳት አይቸግረኝም – በበኩለይ፡፡ የወታደር ቁጥርን ካነሳሁ ዘንዳ ደግሞ ይህ ከዴምሕት አፈነገጠ የተባለ ጦር ከ70 እስከ 900 መሆኑ የሒሣብ ችሎታየን በእጅጉ ተፈታትኖብኛል(ለነገሩ ሀገራችን በዚህ የስታትስቲክስ አኀዛዊ መረጃ ጉዳይ አትታማም፡፡ ፈገግ በሉ፡- መንጌ የተጋነነ ቁጥር ይወድ ነበር አሉ፡፡ እናላችሁ በዘመቻ ፕላን ቀጠና ጽ/ቤት – ስድስት ኪሎ አ.አ.ዩ. ዋና በር ፊት ለፊት የሚገኘው – በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ለእርሻ ምቹ የሆነ(arable land) የቦታ ስፋት በካሬ ኪሎ ሜትር ተመንዝሮ በግብርና ሚኒስትሩ ሲነገር ከተሰብሳቢዎቹ ብዙዎቹ በሣቅ ፈነዱ አሉ – ነገሩ የገባቸው፡፡ ለካንስ ሞኙ ሚኒስትር ጓድ መንጌን ማስደሰቱን እንጂ የተናገረው አኀዝ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት መብለጡን ልብ አላለውም ኖሯል! እኛ እንዲህ ነን እንግዲህ!) በውቀቱ ሥዩም በአንዲት ዚቀኛ ጭውውቱ “የቁጥር ችሎታየ እንኳን እስከዚህም ነው ግን በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት ሰዎች ብዛት ከ7 እስከ 700 ይሆናል፡፡” ብሎ ነበር፡፡ እንግዲህ ይታያችሁ የነሞላ አስገዶም ቁጥር እንደወያኔና እንደነሞላ ከ800 በላይ ማለትም 900 ገደማ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ መረጃ ደግሞ ከ70 የማይበልጡ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እውነቱ የትኛው ነው? እውነት ከማን ጋር ናት? ሌሎች እንዲህ ሰኞ ማክሰኞ የእንክሻ ጨዋታ የሚጫወቱባት ከሆነ ለምን እውነት ራሷ እውነቱን አትነግረንም? ሁለቱን ደምረን አማካዩን እንውሰድ ወይንስ ቀን እንጠብቅ? … ውሸት ከዚህች ምድር የምትጠፋበትን ወቅት በጉጉት ከሚጠብቁ የዓለም ምሥኪን ዜጎች መካከል አንዱ መሆኔን ብገልጽ ጉረኛ ትዕቢተኛ ትምክህተኛ … ምናምነኛ እባል ይሆን? ልባል፡፡ ምን ቸገረኝ፡፡ እናም ሀሰት በእውነት የምትሸነፍበትንና ሁሉም ለኅሊናው ተገዢ የሚሆንበትን ቀን በከፍተኛ ጉጉት እጠብቃለሁ፡፡

ወያኔ ወታደር የሚመለምልበት የተለዬ መሥፈርት አለው፡፡ “ካጠናቀርኩት መረጃ” ውስጥ ከቃል ፈተናው አንደኛውን ጥያቄ ልንገራችሁ፡- “ዕንቁላል የጓሮ አትክልት ነው፤ እውነት ወይንስ ሀሰት?” ለዚህ ጥያቄ “እውነት” ብሎ የሚመልስ ተመልምሎ የሚቀጠርና እንደነገሩ ሠልጥኖ ወያኔ ለፈለገው ግዳጅ የሚሠማራ ሲሆን “ሀሰት” ብሎ የሚመልስ ግን አንጎሉ ስለሚሠራ የወያኔን የውትድርና መሥፈርት አያሟላምና አይቀጠርም፡፡ በተረፈ የወያኔ ወታደር ከመጠነኛ የመግባቢያ ደረጃ ባለፈ አማርኛ ቋንቋ እንዲያውቅ አይጠበቅበትም – ብዘውን ጊዜም ከአማራው አካባቢ ወታደር አይቀጠርም ከደቡብና ከጋምቤላ ነው ይበልጡን የሚመለመለው፤ የትምህርት ደረጃም ምናልባት ከማንበብና መጻፍ ባለፈ አይፈቀድለትም፤ ከዜጎች ጋር ተግባብቶ መኖር ምሕረት የለሽ ቅጣት ያስቀጣዋል፤ በአንድ ቦታ ግፋ ቢል ከሦስት ወር በላይ እንዲቆይ አይደረግም (ከሕዝብ ጋር እንዳይግባባና የርህራሄ መንፈስ እንዳይኖረው)፣ ከወታደሮችም ጋር ሆነ ከሲቪሎች ጋር እንዲገናኝና ብሶቱንም ሆነ ሌላ ነገር እንዲያወራ አይፈቀድለትም – በቡድን ሆኖ መቆምና መቀመጥም ሆነ ማውራት በወያኔ የጦር ሠፈር ነውር ነው(የነሱው ምርጥ ሰው ማለትም ዘውጋዊ ቁርኝት ያለህ የውድቡ አባል  ከሆንክ ይህ ህግ አይመለከትህም)፣ አንድ የወያኔ ወታደር ግደል ሲሉት እነማንንና ስንት ብሎ ካልሆነ በስተቀር ለምን ብሎ መጠየቅ አይችልም – ቢጠይቅ ከጭፍን እንስሳዊ ታዛዥነት ወደሰውነት ደረጃ እንደተለወጠ ተቆጥሮ መፈጠርን የሚያስረግም እርምጃ ይወሰድበታል ወይም ዕድል ከቀናው ይባረራል – ለዚህም ነው ፌዴራል ሲባል ተግባሩ ሁሉ በአረመኔነት የተሞላው – ደግሞም ተከታታይና ታዛቢ ስለሚመደብበት ቢራራ ራሱን ችግር ውስጥ ይከታልና ሳይወድ በግዱ ይጨክናል – ጥሎ ካልጠፋ በስተቀር ሕይወቱ እንደዚህ ባለ መርገምት ውስጥ የታጠረ ነውና ብዙም አንፍረድበት – ይህም ሥራ ሆኖ ሥራውን ቢለቅ ሌላ መኖሪያ የለውም፤ ድህነት ያጨክናል፤ ድህነት የለዬለት ጭራቅ ያደርጋል፤ የመኖር ጉጉት ከሰውነት ተራ ያወጣል፡፡ ስለዚህም በየከተማው የምናያቸው መለዮ ለባሾች ሰው ሣይሆኑ በሰው አምሳል የሚንቀሳቀሱና ማኅበረሰቡን ወያኔ እንደሚፈልገው አንቀጥቅጠው ለመያዝ የተመደቡ ሥጋ-በል ዐውሬዎች ናቸው፡፡ ወታደር ስናይ የኛ ስለማይመስሉን እንሸሻቸዋለን፤ ፖሊስ እንደሚሻለን በእግረ መንገድ መጠቆሙ ግን አግባብ ነው፡፡ የወፓንና የፌዴራል ተብዬውን ወታደር ግን ተውት፤ እነሱን ስታስብ ጥሩ እንቅልፍ ላይዝህ ይችላል – ያቃዥሃል፡፡ አንተ ቀንቶህ ባትገረፍና ባትደበደብም ሌላው ወንድምና እህትህ ስለሚሰቃይ ቁስላቸው አንተንም ይጠዘጥዝሃል – ሰው ከሆንከ፡፡ ግን ስንታችን እንሆን ሰው? ይህም አጠያያቂ ነው፡፡

ፋርጤዎቹ የሞላ ልጆች አሳዘኑኝ፡፡ ደግሞም ወያኔ በተለመደ ቅጥፈቱ “የብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን” ተዋፅዖ ለማሟላት ከሚል ከንቱ ልፋት አንዱን ከደቡብ አንዱን ከሰሜን አንዱን ከምሥራቅ አንዱን ከምዕራብ እያደረገ ነው ቃለ መጠይቅ ያካሄደው፡፡ ሌላውና ለዚህ አጭር መጣጥፍ መጻፍ የወዲያው ምክንያት የሆነኝ እነዚህ የቀድሞ የዴምሕት “ከፍተኛ ባለሥልጣናት” (አላውቅም- ሊሆኑም ይችሉ ይሆናል፤ ማረጋገጫ እስካገኝ ግን ማላገጤም ይቀጥላል) ቃለ ምልልሱን ያካሄዱት ልክ እንደፎቶ ገጭ የመታወቂያ ፎቶ ማንሻ ወንበር አንድ ወንበር ላይና አንድ ግድግዳ አጠገብ ነው፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡ ለባለቤቴ እያሳየሁ ሳቅንባቸው፡፡ ከ25 ዓመት የሥልጣን ዘመን በኋላም ፋራነቱን ሊቀርፍ ያልቻለ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘ የወንበዴ ቡድን በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ማየት የሚደንቅ ነገር ነው፡፡ አንድ ሰው እንኳን እንዴት አይነቃምና ይህን ቀላል ችግር ማስተካከል አልተቻለም? አምስት ይሁኑ ስድስት ተጠያቂዎች ሁሉም የተቀመጡበት ወንበር አንድ ነው፡፡ ቦታውም አንድ ነው፡፡ በራስጌያቸው መስኮት አለ፤ በግራ ጎናቸው በር አለ፤ በቀኛቸው መረብ የለበሰ በር ይሁን ጣሪያ አለ፡፡ እንዳልዋሽ ያህል ሰውዬው ሲቀመጥ ወዲያና ወዲህ ስለሚገፋውም ሊሆን ይችላል ወንበሩ ከመስኮቱ ወዲህ ወይም ወዲያ  እየሆነ በጣም መጠነኛ ለውጥ በአንዳንዶቹ ተጠያቂዎች ላይ ይስተዋላል እንጂ አቀማመጣቸው የሁሉም አንድ ዓይነት ነው – የኛ የቀድሞ ነፃ አውጪዎች፣ የአሁን የወያኔ ባሮች፡፡ ወያኔ ማለት “አታምሪ ወይ አታፍሪ” የሚባል ዓይነት የክፍለ ዘመኑ ጉድ ነው – “ወላድ አይይህ” የሚባል ጉድ፡፡ ግን ግን ይህን ያህል የአገዛዝ ዘመን ለዚህ የወያኔ ግሪሣ የሰጠው ማን ይሆን? እኛ? ሰይጣን? ድግምትና መተት? ምዕራባውያን? የገዛ ኃጢኣታችን? እግዚአብሔር? ብልጣብልጥነታቸው? የአስተዳደር ዕውቀትና ጥበባቸው? ጭካኔያቸው? ጉልበታቸው? የኛ ሞልፋጣ ባሕርይ? ወይንስ ማን? በአርምሞ አስቡት፡፡ በጥቂት ሽፍቶች አገር ሲታመስ ማየት፣ ብዙ ዜጋ በእግር አውጪኝ አገር ጥሎ እየተሰደደ ራሱንና ቤተሰቡን ብቻ ከሽፍቶቹ የእሳት ጨንገር ነፃ ለማውጣት ሲሯሯጥ መታዘብ የማያመልጡት የክፍለ ዘመናችን እርግማን ሆነ፡፡ ማን ለሐዝብ ያስብ? ማን ለሀገር ይቆርቆር? ማን ለትውልድና ለታሪክ ይጨነቅ? ይህን በስብሶ ሊወድቅ የደረሰ የወያኔ ቤተ መንግሥት ማን ይግፋው? መቼስ በራሱ አይወድቅ፡፡ ትንሽም ቢሆን ገፊ ኃይም ያስፈልጋል፡፡ ራስ ወዳድነት በነገሠበት ዘመን ያ ከየት ይምጣ? እኔም አንተም አንቺም … የምንጨነቀው ስለራሳችን ሆነ፡፡ ነገን ትተን ዛሬ ላይ ብቻ አተኮርን፡፡ የጋራ ህልምና ራዕይ አጣን፡፡ ምን ይዋጠን?

ታስታውሳላችሁ መቼም – አንዳርጋቸውን በቲቪ ሲያቀርቡ ከበስተጀርባው የነበረው “ሳውንድ ትራክ” የታይታኒክን ፊልም ያጀበው የሴሌንዲዎን  ዘፈን ወይም የቦብ ማርሊ “stand up for your right” ሣይሆን የሚገረፍ ሰው የሚያሰማው የስቃይ ድምፅ ነበር፡፡ አቡበከርን አንድ  “ ምሁር ፈላስፋ”ና “ግሩም አንባቢ” የወያኔ ካድሬ ከካሜራ ተደብቆ በግዳጅ ቃሉን ሲቀበል በዓለም የእሥረኞች ምርመራ ታሪክ (በቲቪ ለሕዝብ በሚቀርብ ማለቴ ነው) ምናልባት የመጀመሪያው ሊሆን በሚችል መልኩ እጆቹን በካቴና አሥረው ነበር – የግፍ ግፍ፤ ወያኔዎች ምንም ዓይነት ሥነ ምግባር (ethics) እንደሌላቸው በዚያች ልይት ኹነት ብቻ ለዓለም አስመስክረዋል፡፡ በቅርቡም  የ“ዓለምን መሪ” በኢትዮጵያ ሲቀበሉ ያደረጉት መስተንግዶና መሪውን ለማየት ሲተራመሱ ያሳዩት የፋርጤ ድርጊት ሲታይ የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ አለማወቅ ብቻ ሣይሆን ሀገሪቱን ለማዋረድ ሆን ብለው ታጥቀው የተነሱ ይመስላሉ – እርግጥ ነው ከእረኞች ከዚህ የበለጠ መጠበቅ የዋህነት ነው፤ አብዛኞቹ ሞፈር ቀምበር ሰቅለው የመጡ ገበሬዎች ወይም ከፍየል ጥበቃ በቀጥታ ወደ መንግሥት ሥልጣን ያመሩ እረኞች ናቸው፤ በዚያ ላይ ነባር አሠራርን – ዓለም አቀፋዊም ቢሆን – የመጠየፍና ያለመቀበል ጠባያቸው የጎላ ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ግና እነዚህን የዮዲት ጉዲት ውላጆች ሊያጠፋ የሚችል  በሀገራችን እንዴት አንድ ወንድ ይጥፋ? እነሱስ ምን ዓይነት “ዕድለኞች” ይሆኑ? ለነገሩ ከ1.2 ሚሊዮን ሕዝብ 11 ጀግና ልጆች ተገኝተው ትሪንዳድና ቶቤጎን አንድ ወቅት ለዓለም ዋንጫ ሲያበቁ ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 11 ሰው ጠፍቶ ለአፍሪካ ዋንጫ እንኳን አለመብቃታችን … ግን ይህን ለምን እዚህ አመጣሁት በል? አስፖርትና ፖለቲካስ ምን አገናኛቸው … ስለዚህ ወሬ አለቀብኝ ማለት ነውና ሌላ ነገር ሳልዘባርቅ በጊዜ ልሰናበት ምዕመናን፡፡

ለማንኛውም አስተያየት nzeleke35@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.