ዳቪንቼ- ዘጎጃሜ – ነጋ አባተ                                    

( Nega Abate ,Israel)

የመጽሃፉ ቀበኛ ፤ የብዕሩ አርበኛ ሙሉጌታ ሉሌ ካለፈ ቀናት ተቆጠሩ። እኔም ካለሁበት ከእስራኤል ሃዘኑን በብቸኝነት ተያይዥዋለሁ። በቦታው ተገኝቼ ያበባ ጉንጉን ባላስቀምጥ በብዕሬ ግን ባይ ሙሌ ብየ ልሰናበተው ወደድኩ። ሙሌን ከዳቪንቼ ጋር ያመሳሰልኩበትን ፊተኛ ሃሳቤን በማራጃ ከማቅረቤ በፊት ስለ አንዲት የሃገሬ ልባም ሴት ታሪክ ትንሽ ልበል፡፡ ይህቺ ሴት  ለገበያ ፤ ለለቅሶ እና ለመሳሰሉት ማህበራዊና የግል ጉዳዮቿ ከቤቷ ስትወጣ ሴት እኩዮቿ በማጀብ የወንዴው ወገን ደግሞ አሻግሮ በመመልከት ለማድነቅ መሳለፍ በአካባቢው የተለመደና አስደማሚ ትዕይንትም ነበር ፡፡ የሲትዮዋ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የተፈጥሮ ውበቷ እና አለባበሷ ብቻ ሳይሆን ከአዕምሮዋ ልቀት የሚፈልቁት ደንደሳም ሃሳቦቿና ድብርት አባራሪ ቃሎቿም ጭምር እንጅ ! ፡፡ ይህንን በሃሳብ የበለጸገውንና በዘይቤያዊ አነጋገር የተከሸነውን ንግግሯን ለማድመጥ የሚግተለተለውን ወንዘተኛ ላስተዋለ ሲትዮዋ ላይ አንዳች እንግዳ ነገር እንዳረበበባት ይረዳል፡፡ በኋላ ላይ ግን ነገሩ ቆይቶ ሲመረመር ለዚህች ሴት በአካባቢው ደምቆ መውጣት ትልቁን ሚና የተጫወተው ለካስ የኑሮ አጋርዋ ባለቤቷ ነበር፡፡
ጊዜው ደረሶ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ የሚለው አምላካዊ ቃል ጥሪ ወደዚህ ብልህ ሰው  ሲመጣ ጥሪውን  ማጠፍ አይቻለውምና  የዘመኑን ጉዞውን ተጓዘ፡፡ ይህ ጊዜ ግን ያቺ ሃገርን ላነሆለለች  ልባም ሴት የፈተና ወቅት ሆነ ፡፡ በአንድ በኩል የኑሮ አጋርዋን በማጣትዋ ሃዘን ሲያደቅቃት በሌላ በኩል ያ በሃገሯ ልጆች ልቃ የተገኘችበት ችሎታዋም ፈተና ላይ ወደቀ፡፡ በእርሱ የተሸፈነችባቸው እነኛ ቀናት አፈተለኩ ገመናዋ ተጋለጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ጨለማው የተደቀደቀባት ይህች ሴት እንደ አስለቃሽ ሆና  አንዲት ስንኝ ቋጠረች፡፡

ማማር ባንተ ላይ ፤   መዋብ ባንተ ላይ

ዕውቀት ባንተ ላይ ፤  መድመቅ ባንተ ላይ

በኔማ ከሆነ       ፤    እንግዲህ ይታይ ፡፡

በማለት  የውስጧን ሃዘን ገለጠች ፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ስነጽሁፍ ይህን ሙሾ የምታወርድበት ጊዜ ነው ባይ ነኝ ሃይ ባይዋን ፤ ገሳጯን ብርቱውን የብዕር ሰው ሙሉጌታ ሉሌን  አጥታለችና፡፡  ለነገሩ እርግዶውን ላራግድ ብየ እንጅ አለምየ ( የወዳጆ ቅምጥል) አጀብ ባሰኘው የብዕር  ጠብታዋ የጥበቡን ሸማ አገልድማ ኪናዊ ሙሾን አወራርዳልናለች በተነካንበትም ነክታን ሃዘንተኞን ንጣናለች፡፡ አለም ጸሃይ ወዳጆ ኑሪልን!።

ጋሽ ሙሉጌታን ከስነ-ጽሁፋችን ማዕድ ማጣት በአያሌው ያጎድላል፡፡ በተለይም ደግሞ ሃገራችን አሁን ካለችበት አሳሳቢና አስጨናቂ ሁኔታ አንጻር ፤ በዘመንተኞቻችን እይታም ባህል ፤ ቋንቋ ፤ ማንነት እንደ ቁማር ጨዋታ በታየበት ሲያልፍም እጅግ በረቀቀ መሰሪነት መሰረቱ እየተናደ ባለበት በዚህ ጊዜ ሃይ የሚል እንደሙሌ ዐይነት ሁለገብ መሃንዲስ ማጣት “በዕንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ ያማል፤ ይጠዘጥዛል፡፡ እንዲህ ዐይነት ነፍሰ ብዙ ሰው  ከባድማው ሲናጠቅም ሃገር ወና ትሆናለች፡፡ በዕውቀት ማጣት ድርቅ ትመታለች ፡፡ በእንሰሳውና በነዋሪው ሰው መካከል ልዩነት ይጠፋል፡፡ ሰውን  ሰው የሚያሰኙት የማንነት ንጥረ-ነገሮችና የማህበረሰባዊ ወዞች ጠፍተዋላ!፡፡ በወፌ ቆመች ወፌ ቆመች ለመቆም እየተንገዳገደ ያለውን ጨቅላውን ስነ-ጽሑፋችንን ሲወድቅ ለማንሳት ፤ ሲሰበር ለመጠገን ፤ ሲስት ለመመለስ ጋሽ ሙሌ እውነተኛ አብነት ነበር።

ስለ ጋሽ ሙሉጌታ ከብዙ የስራ ባልደረቦቹ መልካም ምስክርነትን ሰምተናል። እኔ ግን ከዳቪንቼ ጋር ወደ አምሳሰልኩበት ቀዳሚ ሃሳቤ ልመልሳችሁ እርግጥ ነው አንዳንድ አንባቢዎቼ ምኑን ከምን አዛመድከው ትሉ ይሆናል። ለምን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ አንድና አንድ ነው ከሙሉጌታ ስራ ይልቅ የዳቪንቺ የገዘፈ ስም አዕምሮአችን ላይ ጎጆ ሰርቶ ስፍራ ይዞ በመቀመጡ ነው። የዳቪንቼ አስገራሚና አስደማሚ ስራዎቹ  ድንበር ተሻግረው በትውልድ መካከል የዘለቁ ፤ ቤተ መዘክርን ያጨናነቁ ፤ብዙ የተዜመላቸውና የንግዱን አለም ያነቃነቁ ለመሆናቸው ዋቢ መጥቀስ አያስፈልገንም። ረጋ ብለን በማስተዋል ካየን ግን በሙሉጌታ ስራዎች አንብበን የተጠቀምነውን ያክል  በዳቪንቼ ስራዎች  እንዳልተጠቀምን እሙን ነው። ከማናውቃቸው የዳቪንቼ የሩቅ ስራዎች ይልቅ የኛው ሙሉጌታ ከስጋችን ስጋን ፤ ከቀለማችን ቀለም ፤ ከባህላችን ባህልን ተካፍሎ የነፍሳችን ጩኸት እየጮኽ በብዕሩ የተሟገተልን ጀግናችን መሆኑን እንገነዘባለን። ችግሩ ግን እኛ የእኛን ማድነቅና  ማድመቅ አናውቅበትም እንጅ ያማ ቢሆን  የቅዱስ ያሬድ ድንቅ ስራዎች  ድጓው ፤ ፅመ ድጓው ምዋዕስትና ዝማሬው በቅጡ ቢመረመር ከነሞዛርት ስራዎች ያንሳልን?። የግዕዙን ቋንቋ ከነፊደሉ በወጉ ከሽነው ካስቀመጡልን ከሊቃውንት አባቶቻችን ስራ የአውሮጳ ቋንቋዎች በምን ይበልጣሉ?። ግን ምን ያደርጋል? የራስን አናንቆ የሰውን አድምቆ በመኖር የተካንን ምስኪን ህዝቦች ነን።

ዳቪንቼን ብዙዎቻቸን የምናውቀው በሂሳብ ቀመር የተነደፉትን አነጋጋሪ ስዕሎቹን ነው። ይሁን እንጅ ዳቪንቼ የእጁ አሻራ ያላረፈባቸው የሙያ መስክ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይቸግራል ። እንዲያውም  ብዙዎቹ የዳግም ልደት (ሬኒሰንስ) ሰው ብለው ይጠሩታል። ለኔ ሙሌ እንዲህ ነው በወርቃማ ዘመኑ ያላነሳቸው ጉዳዮች አልነበሩም። በአስገራሚውና በረቂቅ ምልከታው ያላየው፤ በአስደማሚ መጣጥፎቹ አንስቶ ያላፈረጣቸው ፤ ፈትቶ ያልገጠማቸው ፤ ገድሎ ያላዳናቸው አቢይ የሃገራችን ጉዳዮች አሉ ማለት ያስቸግራል። ሙሌ በተፈለገው ዐይነት እርዕስ ላይ ብቻ ይናገር አድማጭ  አለው ከህግ ባለሙያ ፤ ከህክምና ፤ ከደራሲው፤ ከጋዜጠኛው ፤ከታሪክ ተመራማሪው ወዘተ ጋር በሁሉም ጉዳዮች ላይ ያላንዳች እጥረት ዘና ብሎ ይናገራል። ያ ከጠለቀ ዕውቀቱ እንደወንዝ የሚፈሰው ትንታኔ በሁሉም ሙያተኛ ልብ ውስጥ ያላንዳች ችግር ይደርሳል። መድረስ ብቻም አይደለም ሙሌ የቅርብ ሰዋቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርገዋል አልፎም ሳያስቡትና ሳይወዱ የልብ ሰው ሆኖ ይገኝላቸዋል። ይህ ነበር ልዩ ተሰጥኦው!። ለዚሀም ነው ከህልፈቱ በኋላ በሁሉም መስክ ያሉ ሙያተኞች ህመምተኞች የሆኑት። ሙሌ ሁሉም መስክ ላይ የሚካፈለውና የሚያካፍለው ባለድርሻ ነበራ!። በሁሉም መስክ ላይ ብዙ ነገር ያለውን የኛውን ዘጎጃሜ የኔው ዳቪኒቼ ብለው ማን ይሞግተኛል?። ከሁሉ በላይ ግን ዳቪንቼ በመጨረሻ የጮኻት ጩኽት የሙሌም ጩኽት ትመስለኛለችና የጽሁፌ አንኳር ነጥብም እርሷ ትሆን ዘንድ ወደድኩ ዳቪንቺ ያለውን በአጭር ሳስቀምጠው እንዲህ ይላል “በውስጤ  ያለውን እንደሚገባው አድርጌ  ባለመግለጤ እጅግ አዝናለሁ።”   ዳቪንቼ ይህንን ነገር ሲናገር ምክኒያት ያደረገውም  እግዚአብሄርንና የሰውን ልጅ ነው። በእግዚአብሄር ላይ ያዘነው ካላጣው እድሜ ቢያበድረኝ  ምን አለበት ብሎ ይመስለኛል በሰው ላይ ደግሞ ጋሽ መስፍን (ፕሮፍ) እንዳለው አዳፍኔዎቹን ሊሆን ይችላል ብየ ጠረጠርኩ ዳቪንቺ እንዳለው በነዚህ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ምክኒያቶች ልናየው ከሚገባው በታች  እንድናየው ተገድደናል። በነኚህ ምክኒያቶችም የኛው የስነጽሁፉ ፈርጥ ሙሌ ዘጎጃሜም  ስራውን ሳይፈጽም እንዳለፈ ይሰማኛል።

በነገራችን ላይ የአዳፍኔ ነገር ሲነሳ ስለ አባ ገሪማ ታፈረ ዘጎንደር (የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ አባት) እዚህ ላይ ትንሽ ልበል እኔ በወጣትነቴ እርሳቸው ወደ ሽምግልናው እየገቡ ነው ያገኜኋቸው የአንድ ሰፈር ሰዎች ነን አባ ገሪማ በሳል ፀኃፊና የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። ጎንደሬ በጋሻው ፤ የመከራ ደወል ፤ አባ ታጠቅ ካሣ ከስራዎቻቸው  ጥቂቶቹ ናቸው እናም ጊዜ እየፈለግሁ ከአደባባይ ኢየሱስ ጀርባ ከሚገኘው ከቄስ ካህሌ ጠጅ ቤት ቁጭ ብለን እንድናወራ እጋብዛቸዋለሁ ሃዋርያው ጳውሎስ ከገማልያል ስር ህግን እንደተማረም እኔም ከርሳቸው ብዙ የሚባልን ነገር ወስጃለሁ ብየ አምናለሁ። አባ ገሪማ ብዙና የሚገርሙ ሰው ናቸው ታሪክን ሲያስተምሩ በሰው ልብ ውስጥ እንዳይጠፋ አድርገው የማስቀመጥ ልዩ ችሎታ ነበራቸው። አንድ ቀን  አንድ ጥያቄ አነሳሁባቸው “ እንዲያው ግን ስራየን ጨርሻለሁ ብለው ያምናሉ?” አልኳቸው እሳቸውም ሲመልሱ “ ተወኝ እባክህ ረመጡን አትነካካው እንዳዳፈኑት ይቀመጥ”ብለውኝ ወደ ህልማቸው  ሽምጥ ጋለቡ። የአዳፍኔዎቹ መዳፍ ጥላ እንዳጠላባቸው ገባኝ ጋሽ መስፍን ጥሩ ስም ነው ያወጣልን እግዚአብሄር ያቆይልን። በነገራችን ላይ “አዳፍኔ”ን ገዝተን እንድናነባት እጋብዛችኋለሁ ብዙ ያልፈረጡና ያሞለሞሉ የታሪክ መግሎቻችንን የምታፈርጥ ብሎም ወደ ፈውስ የምትወስድ ሊህቀኛ ምክርን ያዘለች መለኮታዊ መልዕክት ናት። ልብ ያለው ልብ ይበል። በዚህ አጋጣሚ የራሳችሁ ብቻ ያልሆናችሁ የህዝብ ሃብት የሆናችሁ ውድ አኢትዩጵያውያን ከጊዜአችሁ ከፍላችሁ ፤ ከገንዘባችሁ ቀንሳችሁ በህይዎታችሁ የተጠቀለለውን ጥቅልል መጽሃፍ ለትውልድ አስረክባችሁ እንድታልፉ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጥሪየን አስተላልፋለሁ።

ዳቪንቼ ዘጎጃሜ (ሙሌ)ም የዚሁ የአዳፍኔው መዳፍ ሰለባ ነበር። ሁለቱን አዳፍኔዎች  እንደምንምን አልፎ ሶስተኛውን ግን በቃኝ ብሎ  ገልብጦ ወጣ “ጦቢያ”!  የሙሌ ወርቃማ ዘመን!። ሙሌ በዚህች አንዳች መለኮታዊ ኃይል የተጣባት በምትመስል መጽሄት በመሶብ እንደቀረበ መልካም ማዕድ በወርቃማው እጣቱ እየፈተፈተ አጉርሶናል በልተናል። ነገ ሃገር ሲረጋ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማስተማሪያ ሊሆኑ የሚችሉ የስነ-ጽሑፍ ክህሎቶች ፤ ሞጋቸ ሃገራዊ መከራከሪያ ነጥቦች ጦቢያ ላይ ተነስተዋል። ቀልብን የገዙ አብዛኞቹ ስራዎች ደግሞ ከማይነጥፈው ከሙሌ ራስ ስር የሚፈልቁ ውድ ስጦታዎች ነበሩ።

የብዕሩ አርበኛ ሙሌ ጦቢያ ላይ ከትሞ ከቀለም ጋር ያልተዋወቀውና ከዕውቀት የተጣላው ፊደል-መለስ የወያኔ ሰራዊት በቤተ መንግስቱ ፊጥ ሲልና  በትንሽ አዕምሮ ትልቅ ሃገር ለመምራት ሲንደፋደፍ፤ ግራ ተጋብቶ ግራ ሲያጋባ ፤ ትውልድ በመሽጦዎች የሃሰት አውሎ መሃል መንገድ ላይ ቆሞ ሲናወጥና ሲደናበር ብሎም  ሁሉም ወደእያደረሰው ሽሽቱን ሲያያዘው አርበኛው ሙሌ እንደ ዊሊያም ዋላስ ብዕሩን በማንሳት “የት ትሄዳለህ? ቁም!” በማለት በትንታግ ብዕሩ ሞግቶ ነፍሱን በሳተ ትውልድ መካከል ነፍስን የዘራ የዘመናችን አርበኛ ነው።  ዊሊያም ዋላስ የስኮትላንድ ተወላጅ ነው ስኮቲሾች ከእንግሊዞች ነጻ ለመውጣት ባደረጉት ግብግብ  ድንገት ነጥሮ የወጣ ጀግና ነው። ስኮቲሾች ኑሮአቸውን ዱር ለዱር ካደረጉ ሰንባብተዋል አንድ ቀን ግን ወሳኝ የምትባል ቀን መጣችና እነርሱና እንግሊዞች ፊት ለፊት ተፋጠጡ ያኔ ስኮቲሾች በእንግሊዞች ፊት ራዱ መቆም አልቻሉም ሁሉም ነፍሴን አውጭኝ ሩጫውን ሊያያዘው ሲል ዊሊያም ብድግ ብሎ ማንም እንዳይነቃነቅ!።  ወዴት ነው ሽሽቱ? የት ነው መጨረሻው? በማለት ጋሻና ጦሩን አንስቶ ልብን በሚነካ ንግግር መስመር አስገባቸው። ተፋለሙ  ስኮቲሾች ነጻነታቸውን አገኙ ዛሬ የዊልያም ዋላስ  ምሰል ሃውልት የሌለበት የአውሮፓ ክፍል አይገኝም። ሙሌም በትውልዱ ልብ ውስጥ እንዲህ ዐይነት ታሪካዊ ስፍራ ያለው ባለውለታ አርበኛ ነው አንድ ቀንም በትውልዱ ልብ ውስጥ ያለው ወደ አደባባይ መውጣቱ አይቀሬ ነው።

ልጠቅልል ድንገት እንኳን በሙሌ ላይ አሉታዊ አመለካከት ያላችሁ ወገኖች ብትኖሩ እሱ ጥሏት በሄደችው በዚህች አለም ስንኖር በሰከን መንፈስ ስለዚህ የብዕር ሰው  እንድንመረምር እጋብዛችኋለሁ ያን ካደረግን እውነቱ ላይ እንደርሳለን እርሱ ለእውነት ኖሮ ለእውነት መስክሮ አልፎአልና። ሙሌ ለመንፈሳዊው አለም እንኳን የተለየ መነጽር የነበረው ሰው ነበርና ሁሉንም ኤፍታህ ብሎ ያለፈ ነጻ ሰው ነው። ነፍሱን ከነ አብርሃም ጋር ያድርግልን!።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.