ስንታየሁ ቸኮል ከእስር እንዲለቀቅ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላለፈ – የሚሊዮኖች ድምጽ

የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አዲስ አበባ ምክር ቤት ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቃሊቲ ምድብ ችሎት አቃቤ ሕግ የጠየቀበትን ይግባኝ በማስመልከት መዝገቡን ለመመልከት የተሰየመው ችሎት፤ ተከሳሹ ለሚገኝበት ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

‹‹ስብሰባን በማወክ ወንጀል ተከሶ›› የነበረው ስንታየሁ፣ አቃቤ ሕግ ‹‹የወንጀል አንቀፁ ፅኑ እስራት እያለ እንዴት በ6 ወር ቀላል እስራት ይቀጣል›› ብሎ ባቀረበው የይግባኝ ጥያቄ መሠረት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቃሊቲ ምድብ ወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም የቀረበ ሲሆን፤ አቃቤ ሕግ መጥሪያው ስላልደረሰኝ መዝገቡን በሚመለከት የምለው ነገር የለኝም በማለት ሲናገር ተደምጧል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ተከሳሹ ከመች ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ለተከሳሹ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ ስንታየሁ ከሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝና ቅጣቱን ነሐሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም መጨረሱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በችሎቱ ተሰይመው የነበሩት ዳኛ፣ በሌላ ወንጀል የማይፈለግ ከሆነ ተከሳሹ የእስር ጊዜውን ስላጠናቀቀ ከእስር እንዲለቀቅ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥተው፤ አቃቤ ሕግ ያነሳውን የይግባኝ ጥያቄ ለመመልከት ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሹንም በዚሁ ዕለት ፍርድ ቤት እንዲገኝ ያሳሰቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤት የማይገኝ ከሆነም መዝገቡን በሌለበት እንደሚመለከቱ ጠቁመው አልፈዋል፡፡ ‹‹የተላለፈብኝ ቅጣት በቂ ስለሆነ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሊፀና ይገባል ብለህ መከራከር ትችላለህ›› ሲሉም ለተከሳሹ አስረድተዋል፡፡

አቶ ስንታየሁ ቸኮል ‹‹ስብሰባን በማወክ ወንጀል›› ተከሶ ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንፋስ ስልክ ምድብ ችሎት የ6 ወር የእስር ቅጣት እንደበየነበት ይታወሳል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከሚገኝበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከእስር ሊለቀቅ እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.