አለነ ማህጸንቱ በፍርድ ቤት የተናገረው ንግግር

አለነ ማጸንቱ ከአንጋፋ የተማሩ የአንድነት አመራሮች መካከል አንዱ ነው። ባላጠፋው ጥፋት ፣ ክስ ተመስርቶበት በወህኒ እየማቀቀ ይገኛል። ዛሬ በዋለው ችሎት የሚከተለውን ልብ መሳጭ ንግግር ተናግሮ ነበር።

‹‹ስሜ አለነ ማህፀንቱ ይባላል፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነኝ፡፡ በትምህርቴ የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት ነኝ፡፡ በሙያዬ የተለያዩ ቦታዎች ሰርቼያለሁ፤ በተለያዩ ኮሌጆች ላይ ዲን ሆኜ ሰርቼያለሁ፡፡ በትምህርት ቤቶችም በርዕሰ መምህርነት አገልግያለሁ፡፡ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖሊሲና ፕሮግራም ኃላፊ ሆኜ ሰርቼያለሁ፡፡ ሀገሬን ወክዬ በተለያዩ ሀገራት በመጓዝ ተከራክሬያለሁ፡፡ የሀገሬን ጥቅምም አስከብሬያለሁ፡፡ በፖለቲካ ዘርፍ የ11 ዓመት ልምድ አለኝ፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመቅረብ አንስቶ፤ በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ብሔራዊ የስራ አስፈፃሚ አባል፣ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ ሆኜ እስከተያዝኩበት ቀን ድረስ አገልግያለሁ፡፡

የታሰርኩበትና የተያዝኩበት ምክንያትም በፖለቲካ አመለካከቴ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራ አባል በመሆኔና እኔም ስታገል የነበርኩት በሀገሬ ላይ ዲሞክራሲን ለማስፈን፤ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኛና ነፃ ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ፤ ዜጎች ያለምንም ምክንያት የማይታሰሩባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ፣ ትክክለኛ ፍትህ በሀገሪቱ እንዲሰፍን፣ ትክክለኛ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን ነው፡፡ እንደ ተማሩ ወጣቶች ሁሉ ለሀገሬ ሰርቼያለሁ፡፡ በዚህ ስብእናዬ፣ በአካዳሚክ ባክግራውንዴ፣ ባለኝ ማህበራዊ ኃላፊነት አሁን የተከሰስኩበትን ክስ ማለትም አቃቤ ሕግ ያቀረበውን ‹‹አይኤስን ምክንያት በማድረግ መንግስትን በሀይል ለመናድ….›› ወዘት የሚሉ ነገሮች፤ የቀረቡብኝ ባለኝ የፖለቲካ አመለካከት ነው፡፡ በክሱ ላይ የተዘረዘሩት ነገሮች ሁሉ ባለኝ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ኃላፊነቴ ልፈፅማቸው የማልችላቸው መሆኔን አረጋግጬ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ከቤቴ በማይታወቁ ሰዎች ታፍኜ ተወስጄያለሁ፤ ከምኖርበት አካባቢ በአራት ደህንነቶች ታፍኜ ተወስጄ ክስ ተመስርቶብኝ፤ በሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግርም ሆነ የሌሎችን ንግግር ለመግታት፣ ‹‹ጉባኤ አውከሃል›› በሚል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 490/3 በመናገሻ ፍርድ ቤት ቀርቤ፤ የአቃቤ ሕግ ምስክር በፖለቲካ ሴራና በተንኮል የተደራጀ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ስላረጋገጠ በነፃ አሰናብቶኛል፡፡

ይህንንም የተከበረው ፍርድ ቤት አምጥቶ ያረጋገጠ ይመስለኛል፡፡ የመናገሻ ፍርድ ቤት በነፃ ካሰናበተኝ በኋላ፤ የኢህአዴግ መንግስት እኔን ማሰር አላማው አድርጎ ስለተንቀሳቀሰ ብቻ በሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ከሶኝ የነበረውን ክስ ሰርዞ፤ ‹‹በሚያዚያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ለቅሶ ቦታ ላይ ተገኝተህ አመፅ ለማነሳሳት ሞክረሃል›› በማለት ክስ አቅርቦብኛል፡፡ ይህ ክስ እኔንም ሆነ ፍርድ ቤቱን የማይመጥን ክስ ነው፡፡
‹‹ወጣቶችን አደራጅትህ በሪቼ አድርገህ፣ ወደ መስቀል አደባባይ ወስደሃል›› የሚል ክስ ነው የቀረበብኝ፡፡ የሀሰት ምስክሮች ማለትም፡- የቀበሌ አመራሮች፣ የፎረም አባሎች፣ ሰብስቦ በማምጣት በሀሰት ተመስክሮብኝ እንዲህ አይነት ክስ ሊመሰረትብኝ ተችሏል፡፡ በዚህች ሀገር ላይ የመኖር ዋስትናዬ አልተከበረልኝም፤ እየተከበረልኝም አይደለም፡፡ ስለዚህም የተከበረው ፍርድ ቤት ጭብጥ ማስያዝ የምፈልገው በወቅቱ እኔ ከ2፡30 እስከ 3፡00 ባለው ግምታዊ ሰአት ከጓደኞቼ ጋር ማለትም ከአቶ ግርማ ሰይፉ ቢሮ መገኘቴን ነው፡፡ ‹‹ሙሾ እያወረደ ሲያሳምፅ ነበር›› የሚለው የፈጠራ ክስ በጭራሽ የማይገናኝ ነው፡፡ ከእነዚህው ጓደኞቼ ጋር እስከ ምሳ ሰዓት አብሬ ነበርኩ፡፡›› በማለት የተከሳሽነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.