በአርባምንጭ በርካታ ዜጎች መታሰራቸው ታወቀ

• የሰማያዊ ፓርቲ የአርባምንጭ አስተባባሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ታስረዋል
(ነገረ ኢትዮጵያ) ትናንት ጥቅምት 17/2008 ዓ.ም ከሌሊቱ 8 ሰዓት ጀምሮ በርካታ የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች በአፈሳ እየታሰሩ መሆኑን የነገረ ኢትተጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪዎችም ታስረዋል፡፡ ከአስተባባሪዎቹ መካከል አቶ ሉሉ መሰለ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸው ሌሊት 8 ሰዓት ላይ የታሰሩ ሲሆን ባለቤታቸውና ልጃቸው ከቀኑ 10 አካባቢ መፈታታቸውን ተገልፆአል፡፡ ከአቶ ሉሉ መሰለ በተጨማሪ የሰማያዊ ፓርቲ የአርባ ምንጭ አስተባባሪ እና በአሁኑ ወቅት ቂሊንጦ ታስሮ የሚገኘው የአቶ በፍቃዱ አበበ እናት ወይዘሮ አልማዝ ካሳ እንዲሁም እህቱ ወይዘሮ አየለች አበበም ቤታቸው ተበርብሮ መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአቶ በፍቃዱ አበበ ቤተሰቦች መሳሪያ ከቤታችሁ ተገኝቷል ተብለው ተከሰው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ የሚገኙ ሲሆን ወይዘሮ አየለች አበበ ቤታቸው ያልተገኘውን መረጃ ተገኝቷል ብላ እንድትፈርም መገደዷን እየታደነ የሚገኘው ወንድሟ ባንተወሰን አበበ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፆል፡፡


አርባ ምንጭ ውስጥ በአፈሳ እየታሰሩት የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ ሌሎች ሰዎችም መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ አርባ ምንጭ ከተማ 03 ቀበሌ በተለምዶ ድኩማን ሰፈር ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች አሁንም እየታሰሩ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በከተማው በርካታ ዜጎች እንደታሰሩ የተገለፀ ሲሆን ዛሬ ጥቅምት 18/2008 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 8 ወጣቶች መታሰራቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ ዛሬ ጥቅምት 18/2008 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከታሰሩት መካከል የማታ ወርቅ ጫንያለው፣ ውብሸት ጌታቸው፣ አምሳሉ ከበደ እና ሙሉነህ የተባሉ ዜጎች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፖሊስና ደህንነቶች ሌሎች ዜጎችንም በመኪና እየዞሩ እየለቀሙ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.