በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ በተከሰተው የጉርብርብ (LSD) የበሽታ ፍንዳታ ከብቶች እያለቁ መሆኑ ተገለፀ

በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ በተከሰተው የጉርብርብ (LSD) Lumpy Skin Disease የበሽታ ፍንዳታ ከብቶች እያለቁ መሆኑ ተገለፀ። ” አርሷደሮች ለበሽታው መስፋፋት የወረዳውን የግብርና ሀላፊዎች ተጠያቂ ናቸው” ብለዋል።

ዘሪሁን ገሠሠ

በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ በተቀሰቀሰው የጉርብርብ (LSD) ፍንዳታ ሳቢያ የቀንድ ከብቶች እያለቁ መሆናቸውን ከስፍራው ያነጋገርናቸው አርሷደሮች ገልፀዋል። ይህ አደገኛና ከብቶችን የሚያጠቃው በሽታ በወረዳው በተለይም 05፣012፣013፣015 ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ መስፋፋት እያካሄደ እንስሳቱን ለሞት እየዳረገ የሚገኝ ሲሆን በወረዳው በኩል እየተደረገ ያለው እገዛና በሽታውን ለመቆጣጠር የሚከናወነው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ በመሆኑ በሽታው በአጎራባች ወረዳዎችም በመስፋፋት ከፍተኛ እልቂት ሊያደርስ እንደሚችል አርሷደሮችና የጤና ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የወረዳው የእንስሳት ጤና ባለሙያ እንደተናገሩት “በሽታውን ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ ለመቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ ነበር። ይህም ከብቶቹ በበሽታው ሳይያዙ የሚሰጥ ክትባት ነው። ነገርግን በሽታው ከተከሰተ በኃላ ይህን ክትባት እንዲከተቡ ማድረግ ይብስ በሽታውን ማባባስ መሆኑን እንደባለሙያ ብንገልፅም ሀላፊዎች የኛን ሙያዊ ምክር ተረድተው ተግባራዊ ከማድረግና ሌላ የተሻለ ዘዴ ከመፈለግ ይልቅ በሽታው ከተከሰተና ከፍተኛ እልቂት እያስለተለ ባለበት ሁኔታ መከተብ የሌለበትን ክትባት እንድንሰጥ በሀላፊዎች ጫና በመደረጉ ክትባቱ በመሰጠት ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ እንደባለሙያ በእሳት ላይ ጭድ እንደመጨመር ቢሆንም ክትባቱን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆን ባለሙያዎች ላይ የአመለካከት ችግር ያለባችሁ፣የሀላፊን ትእዛዝ የማትፈፅሙ፣… …ናችሁ በማለት በዲሲፕሊን እስከመከሰስና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከመሰጠት ደርሰናል። ነገርግን እኔ በግሌ ከሙያዬ ውጭ የካድሬዎችን ትእዛዝ ለመፈፀም ሙያዊ ስነ ምግባሬን አልጥስም፣የመጣውን እቀበለዋለሁ።” ሲል ተናግሯል።

በወረዳው ያነጋገናቸው በርካታ አርሷደሮች በወረዳው የእንስሳት ሀብት የስራ ሂደት አስተባባሪ በሆኑት አቶ ተገኘ ፈንታው ላይ ቅሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን ወረዳው እስካሁን በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉ ሁኔታውን ከዚህ የከፋ እንደሚያደርገው ስጋታቸውን ገልፀዋል። የሚመለከታቸው አካላትም ለዚህ አስከፎ በሽታ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.