‹‹ተከላከሉ ተብላችኋል›› የእኛ ዳኛ – ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ የፍርድቤቱን ውሎ ሲተነትን

ዛሬ በቀጠሯችን መሰረት እኔና አምሳሉ ገ/ኪዳን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ወንጅል ችሎት በጥዋት ደርሰን ነበር፡፡ ከ3፡00 ሰዓት በኋላ ዳኛው ተሰየሙ፡፡የሁለት ፋይሎችን ስም ከጠሩ በኋላ የእኛን መዝገብ የእኔን ስም በመጥራት አነሱ፡፡ ዳኛው ፊት ቀረብን፡፡ የተወከለ ዓቃቤ ሕግ መኖሩን አረጋገጡና ‹‹ተከላከሉ ተብላችኋል›› አሉን በአጭር ቃል! ‹‹ትከላከላላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘሩ፡፡ ‹‹አዎን›› አልን፤ ተገርመን በማዳመጥ፡፡ ዳኛው፣ ‹‹ተከላከሉ›› የተባልንበትን የክስ ጉዳይ አንዲትም ነገር በአንደበታቸው ሊነግሩን አልፈቀዱም ነበር፡፡ አንድ ተከሳሽ ‹‹ተከላከል›› የሚል ብይን ሲሰጠው፣ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ያየበትን የሕግ አግባብ ተንትኖ ለተከሰሹ/ ለተከሳሾቹ (ለጠበቃ)፣ ለከሳሽና ክሱን ለሚከታተል ማንኛውም ሰው ማስረዳት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹‹ተከላከሉ ተብላችኋል›› የሚለው አገላለጻቸውም አሻሚ ነው፤ ‹‹ተከላከሉ›› ያለን ችሎቱ ወይስ ሌላ አካል?! እንደዚህ አይነት የሕግ አሰራር እንዳለም አላውቅም፡፡ እኔም ብይኑን (በዝርዝር) አለማወቃችንን ለዳኛው ጥያቄ ገለጽኩላቸው፡፡ ከሬጅስትራር መውሰድ እንደምንችል ዳኛው ተናገሩ፡፡ መልሳቸው አጭር አጭር ነበር፤ አንገታቸውን ሰበር አድርገው፡፡ ከዚህ ቀደም ከሬጅስትራር መውሰድ የምንፈልገውን የውሳኔ ግልባጭ በተደጋጋሚ ጠይቀን ማግኘት እንዳልቻልን በድጋሚ አስረዳናቸው፡፡ ‹‹ጠይቃችሁ መውሰድ ትችላለችሁ›› እያሉን የቀጠሮ ቀን ለመስጠት አጀንዳቸውን ገለጡና ለታህሳስ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ከጥዋቱ 3፡00 ሰዓት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጡን፡፡
….ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ ጉራማይሌ መሆኗን ቀጥላለች፡፡ የሕግ መርህ ላይ የቆመ የፍትህ ሥርዓት በሀገራችን መገንባት እስክንችል ድረስ ጠንክሮ መታገል ወሳኙ መፍትሄ ነው ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.