የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት በህወሓት አገዛዝ የጦር ኃይል ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከፍተኛ ድልን ተቀዳጀ!!

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)

የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት ተደጋጋሚ የሽምቅ ውጊያዎችን በማድረግ የህወሓትን መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጦር አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የህዝብ አለኝታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
ባለፈው ሳምንት ህዳር 21/2008 ዓ.ም ጀግናው ሰራዊታችን በዋልድባ በጠላት ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዋልድባ ወደ አዲ-አርቃይ በመወርወር ማክሰኞ ህዳር 28/2008 ዓ.ም አዲ-አርቃይ ላይ ከወያኔ መከላከያ ሰራዊትና የሚሊሻ ታጣቂ ኃይል ጋር ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1፡00 ለሶስት ተከታታይ ሰዓታት የዘለቀ ከባድ ውጊያ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የጠላት ጦር በመግደልና በማቁሰል ድልን ተጎናፅፏል፡፡
ሰራዊታችን በጦር ሜዳ ውሎው፣ ከጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት በተቀዳ ወኔ፣ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን የህወሓትን መከላከያ ሰራዊትና የሚሊሻ ታጣቂ ኃይል በጦር ሜዳው ላይ በጥይት ቆልቶና አሳሮ አስቀርቶታል፡፡
ፍልሚየው በማግስቱ ረቡዕ ህዳር 29/2008 ዓ.ም ከጥዋቱ 1፡00 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ሰዓታት ማለትም እስከ ረፋዱ አራት ሰአት በዚያው አዲ-አርቃይ ላይ የቀጠለ ሲሆን ፣ ወያኔ ከሌላ ቦታ አጓጉዞ ለጦርነት ያሰለፈውን ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ጀግኞቹ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የነፃነት ፋኖዎች የጠላትን ጦር ድባቅ መትተውታል፡፡

ለነፃነት የሚደረገው ጦርነት አሁንም ቀጥሏል፡፡የወያኔ ባለስልጣናት የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው በተለይ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የሚገኘውን ድንበር የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ሰራዊት ለመዝጋት ቢሯሯጡም ድንበር ላይ የተመደበው ወታደር ከወያኔ እየከዳ የነፃነት ትግሉን ከነትጥቁ እየተቀላቀለ ይገኛል፡፡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሰራዊት በተቀዳጀው ድል የአካባቢው ህዝብ ጮቤ እየረገጠ እደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ጀግናው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሰራዊት ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ፣ በህዝብ ድጋፍ ታጅቦ ወደ መሃል አገር እየገሰገሰ ነው፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.