የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በምስክርነት እንደማያቀርብ አሳወቀ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሰውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በምስክርነት እንደማያቀርበው ለልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ታህሳስ 4/2008 ዓ.ም ለልደታ ፍርድ ቤት በላከው ደብዳቤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹‹የ18 አመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት በመሆኑና ከአሁን ቀደም ምስክር ሆኖ ከማረሚያ ቤቱ ወጥቶ መስክሮ ስለማያውቅ ለመስክርነት ለማቅረብ እንቸገራለን›› ብሏል፡፡

እስክንድር ነጋ ለእነ ዘላለም ወርቃገኘው በመከላከያ ምስክርነት ከተቆጠረ በኋላ ከህዳር 13 /2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀጠሮዎች በምስክርነት ሳይቀር የቀረ ሲሆን ዛሬ ታህሳስ 6/2008 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ በላከው ደብዳቤ መሰረት ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡ ከአንድ አመት በፊት ከ6 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ተኩል ለ30 ደቂቃ ሲጠየቅ የነበረው እስክንድር ነጋ በአሁኑ ወቅት እንዳይጠየቅ ተከልክሏል፡፡ በተጨማሪም ማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ እስክንድር ነጋ የታሰረበትን ክፍል በመፈተሽ መፅሃፍ ቅዱስን ሳይቀር መነጠቁም ይታወሳል፡፡