ክፉ ቀን ይምጣ ቶሎ ይመልስ፣ ያስተዛዝባል እስካዛው ድረስ – ይገረም አለሙ

AbyssiniaPeopleይህ በርእስነት የተጠቀምኩበት የአበው አባባል መልእክቱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡የሰው ልጅ የተደበቀ ማንነት የሚጋለጠው፣ ቃልና ተግባሩ ሀራምባን ቆቦ መሆኑ የሚረጋገጠው፣ ወዳጅነቱ የአፍ ይሁን የልብ የሚለየው፣ ሀገርና ህዝብ አፍቃሪነቱ የሚታወቀው፣ ወዘተ ከተለመደው ለየት ያለ ነገር ሲያጋጥም መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡

ገና ከጅምሩ ታላላቅ ሰዎችን የነጠቀን 2008 ሩብ እድሜ ሳያስቆጥር ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮችን አሳይቶናል እያሳየንም ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የርሀብ አደጋ፣ የወልቃይት አካባቢ ነዋሪዎች በግድ ትግሬ ሁኑ ተብለናል የሚለው ተቃውሞ፤ ቅማንትና አማራ በሚል የተፈጠረው ክፍፍል፤ የጎንደር እስር ቤት መቃጠልና የዜጎች ዕልቂት፤ በኦሮምያ አካባቢ  የተቀሰቀሰውና እስካሁን ያልቆመው ተቃውሞ፤ በድንበር ማካለል ስም ለሱዳን ለም መሬት ለመስጠት እየተካሄደ ያለው የድብብቆሽ ጨዋታ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉም በየራሳቸው  ጥሩም መጥፎም ነገር እንድንታዘብ አድርገውናል፡፡ እያደረጉንም ነው፡፡  እስቲ የሁለቱን ትዝብት እንቃኝ፡፡

1-ከቀን ወደ ቀን እየከፋ ያለው ረሀብ፤ ይህ ረሀብ ወያኔ ተከታታይና ፈጣን  ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገብኩ ነው እያለ በሚፎክርበት ወቅት የተከሰተ በመሆኑ አለም የወያኔን ዋሾነት እንዲታዘብ  ያደረገ ነው፡፡ በአንጻሩም የሚባለው እድገት የፈጠራ ቁጥር አንጂ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለ አይደለም ሲሉ የነበሩ ወገኖች ተአማኒነት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ስለሚናገሩት ነገር ቅንጣት የማወቅ ሙከራ ሳያደርጉ በሉ የተባሉትን እንደወረደ እየተናገሩ ርሳቸው ባያፍሩም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ማፈሪያ እየሆኑ ያሉት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል ብለው በአደባባይ ተናግረወው ሶስት ወር ባለሞላ ግዜ ይፋ የሆነ ረሀብ በመሆኑ ወትሮም ባለሥልጣኖቹ በሚናገሩት ነገር ላይ እምነት የሌለው ህዝብ ይበልጥ አንዲታዘባቸው ይበልጥ እንዲንቃቸው አድርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሊደበቅ የማይችልን ረሀብ ለመደበቅ ያሳዩት መቀለማመድ፣ በራሳችን እንቋቋመዋለን ባሉ ማግስት ርዳታ ሲለምኑ መሰማት የአንዱ ባለሥልጣን ንግግር ከአንዱ አለመግጠም ወዘተ የመንግስት ባለሥልጣንነታቸውን አይደለም ሰው መሆናቸውን እንድንታዘብ አድርጎናል፡፡

በጥቅሉ የተከሰተው ረሀብ  በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እስካልተቻለ ድረስ ከረሀብ ተጠቂነት መላቃቅ አይቻለም የሚለውን አስተሳሰብ ትክክለኛት ያረጋገጠና በወያኔ አገዛዝ ስር ሆኖ ህዝብን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀገራዊ እድገት ማምጣት አይደለም  ከረሀብ መላቀቅ የማይቻል መሆኑን ያሳየ  ነው፡፡ በመሆኑም ለለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል አስተባብሮና አጠናክሮ ከመቀጠል ውጪ አማራጭ አንደሌለ የሚያስተምር ነው፡፡

2–በኦሮምያ አካባቢ የተከሰተውና እስካሁን ያልበረደው ተቃውሞ ፤  ጊንጪ አካባቢ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተቀስቅሶ መላ ኦሮምያን ያደረሰው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ብዙ ነገር እንድንታዘብ አስችሎናል፡፡ ከትዝብት አልፎም የሚማር ካለ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት ነው፡፡

  • የህዝቡ ብሶትና የለውጥ ፍላጎት በሀይል ታፍኖ የተዳፈነ እንጂ ጨርሶ ያልጠፋ መሆኑን ያሳየው ይህ እንቅስቃሴ የህዝብ ብሶት የመዳፈኑ መጠኑ ከቦታ ቦታ የሚለያይና ለመቀጣጠልም የሚጠይቀው ሙቀት ከአካባቢ አካባቢ የሚለያይ መሆኑን ያሳየነ ነው፡፡ይህም የአካባቢ ሁኔታዎችን ማጥናት የህዝቡን ሥነ -ልቦና መረዳትና ተስማማሚ የትግል ስልት መንደፍ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታል፡፡
  • ወያኔ ዓላማውን ከዳር ለማድረስና ፍላጎቱን ለማሳካት ማናቸውንም ርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ የማይል የሰው ህይወትና የሀገር ሀብት ደንታ የማይሰጠው መሆኑን ቀደም ብሎም የምናውቅ ቢሆንም የሰሞኑ አረመኔያዊ ድርጊቱ በሂደት ያልተማረና ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን አረጋግጦልናል፡፡ይህም አንድም ወያኔን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ከማውረድ ውጪ ሌካ አማራጭ የሌለ መሆኑንና የሚካሄደው ትግል ከድሉ መስዋእትነቱ እንዳይከብድ የሚያስችል የትግል ስትራቴጂ መቀየስን አስፈላጊነት የሳያል፡፡
  • የኦህዴዶች የወያኔ ገባርነት እስከምን ድረስ እንደሆነም ለመታዘብ አስችሎናል፡፡ በኦሮምያ የህውኃት ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሙክታር ከድር እወክለዋለሁ የሚሉትን የኦሮሞ ወጣት የገደሉ የወያኔ ነፍሰ ገዳዮችን  ሲያመሰግኑ የተመለከትነው የሰው ልጅ ህሊናውን ሸጦ አካሉን ለሎሌነት ሲያስገዛ ሊሆን የሚችለውን የመጨረሻ ደረሻ ያሳየ ነው፡፡ በጥቅሉ ወያኔዎች በኦህዴዶች ላይ ያላቸው የበላይነት ከጌታና ሎሌም ግንኙነት የላቀ መሆኑን ከሰሞኑ ድርጊት ታዝበናል፡፡ ሎሌ ነገር ሲበዛበት ጭቆናው ሲብስበት ሌላ ማድረግ ባይችል ይኮበልላል ከጌታም ጌታ አማርጦ የተሻለ ወደ መሰለው ጌታ ይጠጋል፡፡ ኦህዴዶች ግን….. ይህ ደግሞ ለወያኔ የደሩትን ሰዎች ለወያኔ ከማደራቸው በፊት ሰው መሆናቸውን እንዲያስቡና ወደ ሰውነት እንዲመለሱ የማድረግ፣ከውስጣቸው ስንዴና እንክርዳዱን የመለየት፣ ወዘተ ስራ እንደሚያፈልግ ይናገራል፡፡
  • የተቀዋሚነትን ስም ይዘው ነገር አለሙን ረስተው የተኙ ፖለቲከኞችን ይህ የህዝብ እንቅስቃሴ ከእንቅልፋቸው ቀስቅሶአቸው ኢሰብአዊውን ድርጊት በማውገዝና  የተባብሮ መስራትን አስፈላጊነትና ወቅታዊነት በመግለጽ መግለጫ ሲያወጡም ታዝበናል፡፡  ያለፈው አስቆጭቶአቸው በወያኔ መበለጣቸው አስቆጥቶአቸው በዚሁ በተናቃቃ መንፈስ ይቀጥላሉ ብለን ተስፋ አድርገንም ነበር፡፡ ነገር ግን ዜጎች በእየለቱ እየሞቱ ባሉበት በዚህ ወቅት ከእንቅልፋቸው መንቃታቸውን  በመግለጫቸው ያሳዩን ፖለቲከኞች ከመግለጫ አልፈው  ቢያንስ በመግለጫቸው ያነሱዋቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ  የሚያስችል ጅምር ርምጃ አላማሳያታቸው  መቼም የማይማሩ ከሥልጣን በላይ አሸጋግረው ማየት የማይችሉ ቃልና ተግባራቸው የማይዛመድ ወዘተ ለሚል ትዝብት የሚዳርጋቸው ሆኗል፡፡ ይህም ዋናው ነገር ቁጥር ሳይሆን ተግባር፣ ስም ሳይሆን ሆኖ መገኘት መሆኑን በማጤን ፓርቲዎችንም ሆነ መሪዎቻቸውን በዚሁ እየፈተኑ ድጋፍ መስጠትም ሆነ መንሳት እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡
  • የፖለቲካ ፓርቲ ስም ይዘው ሌላው ቢቀር ግድያውን ለማውገዝ ፈቀደኝነቱም ሆነ ድፍረቱ ያልታየባቸው ፓርቲዎችንም ታዝበናል፡፡ በርግጥ እነዚህን ስመ ፓርቲዎች ማንነትና ምንነት ህዝቡ አሰቀድሞ አውቆ አንቅሮ የተፋቸው ቢሆንም ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ በተነሳሱ ወጣቶች ለይ የተፈጸመውን ግድያ ማውገዝ አለመቻላቸው እንደ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ በህብረተሰቡ ውስጥ ምንም ቦታ ሊያገኙ አንደማይገባ የሚጠቁም ነው፡፡
  • በኦሮምያ የታየው የህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴና ተቃውሞውን ለመጨፍለቅ ወያኔ የወሰደው አረመኔያዊ ተግባር መልካም ነገር እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንም ታዝበናል፡፡ ሁሉንም በእኩል እየበደለ ያለውን የዛሬውን አገዛዝ በጋራ ትግል አስወግዶ  የነገውን መልካም መንገድ ከማሳመር በትናንት ታሪክ መወነጃጀልና መካሰስን ምርጫቸው አድርገው ለሚቃወሙት ወያኔ እድሜ መርዘም አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የነበሩ ወገኖች ቆም ብለው ፈጥነው እንዲያስቡ አብቅቶአቸዋል፡፡ በዚህም  ከመጡበት መንገድ ወጥተው ከያዙት አላስፈላጊ አስተሳሰብ ተላቀው በኢትዮጵያዊነት ተባብረን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረትን ግባችን አድርገንበአንድነት እንታገል ወደሚል ተገቢና ቅዱስ አስተሳሰብ መምጣቸውን በአድናቆት ታዝበናል፡፡ በጋራ መጮህ መቻላቸውንና እጅ ለእጅ ተያይዘው ሰልፍ መውጣታቸውንም አይተንና ሰምተንም እሰየው ብለናል፤ከእንግዲህ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ እንዳትሉ በማለትም አደራ ብለናል፡፡

ይህም በቁጥር በዝተው በተግባር የሌሉት፣በስም ተለያይተው እዛና እዚህ የቆሙት የበዛወውን ቁጥር ይቀንሱት የሰፋውንም ልዩነት ያጠቡት ዘንድ የየድርጅቶቹ አባላትም ደጋፊም ፣ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ናፋቂም ግፊት ማድረግ ተጽእኖ መፍጠር እንደሚገባው  ያሳየ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወያኔን ለማውገዝ በአንድነት ሰልፍ በሚወጡበትም ሆነ ጩኸት በሚያሰሙበት ወቅት ተቃዋሚዎችም መተባበርን ከቃል ወደ ተግባር እንዲቀይሩት ሊጠይቁ ሊወተውቱ እንደሚገባ ያመላከተ ይመስለኛል፤

  • ይሄ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለው የህዝብ እንቅስቃሴ የሀይማኖት አባቶችንም እንድንታዘብ አብቅቶናል፡፡ በሁሉም እምነት አምላክ በአምሳሉ የፈጠረውን ክቡር የሰው ልጅ መግደል ወጉዝ እንደመሆኑ በየእምነቱ መሪነት ቦታ ላይ የተቀመጡ የሀይማኖት አባቶች ገዳዮችን ሊያወግዙ ግድያውን ሊኮንኑና ግድያ ይቁም ብለው ጥሪ ሊያስተላልፉ የተቀመጡበት ቦታና እንፈጽመዋለን የሚሉት የፈጣሪ ትዕዛዝ  ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ግን ከአንዳቸውም ይህን ለመስማት አልቻልንም፡፡( ይህ ትዝብት ከሀገር ውጪ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶችን አይመለከትም)

ደፈር ብለው ተቃውሞ ለማሰማት ወደ እምነቱ መሪነት ቦታ የመጡበት ሁኔታ የማይፈቅድላቸው ከሆነ (ማለትም ለቦታው የበቁት በፖለቲከኞቹ ምርጫና ይሁንታ ከሆነ) ወይንም ከፈጣሪያቸው ይልቅ ጠመንጃ አንጋቾችን የሚፈሩና ከነፍሳቸው ይልቅ ለስጋቸው የሚሳሱ ከሆነ ደግሞ መንግስት ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ራሳቸውን አመሳስለው ከህዝቡ ግልጽ ጥያቄ ጀርባ ስውር አላማቸውን ለማሳካት የተንሳቀሱ ኃይሎች በፈጠሩት ሁከት ምክንያት ለሞቱ ንጹሀን ዜጎች እናዝናለን ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን አንዲሰጥ እንጸልያለን ማለት እንደምን ገደዳቸው፡፡ የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ካቃታቸው  ዜጎች በግፍና በገፍ ተገድለው ዝም ከማለት ከበጣም መጥፎ መጥፎውን መምረጥ ብለው ሁለተኛውን መፈጸም ይችሉ ነበር፡፡ ግና አንዱንም አላደረጉትምና ታዘብናቸው፡፡ ታዲያ ለፈጣሪ ትዕዛዛት ሳይሆን ለጠመንጃ የሚያጎበድዱና ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ኢሰብአዊ ግድያ ስሜት የማይሰጣቸው የሀይማኖት መሪዎችን እንዴት አድርገን በአባትነት መቀበል ይቻለናል፡፡

ይህም ለሀይማኖት ነጻነት መረጋገጥ የወያኔን መወገድ ግድ የሚል መሆኑን ያሳየ በተናጠል ስለ ሀይማኖት ነጻነት የሚታገሉ ወገኖች የትግላቸውን ደረጃ ከፍ አድርገው አላማቸውንም ለዴሞክራሲ ወደሚል ቀይረው ለነጻነት እንዲታገሉ ያመላከተ ይመስለኛል፡፡

 

በአጠቃላይ የሰሞኑ ክስተት ካሳየን ትዝብት ፖለቲከኞቹ ትምህርት በመውሰድ ከእንግዲህ በወያኔ መበለጥ በነገሮች ክስተትም መቀደም የለም ብለው ደጋመው በአንደበታቸው የሚናገሩትንና ሰሞኑንም አጠንክረው የጮሁበትን መተባበር በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንጻሩም ትግሉን በእምነትና በቁርጠኝነት ከምር የያዙትና አስመሳዮቹ፣ አላጋጮችንና ነጋዴዎቹ ይለዩ፡፡

ለተቃውሞ ሰለፍ በአንድነት ለመውጣት ፈቃደኝነታችውን የሳዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንኳን በጣም ብዙ ናቸውና  በስምም በፕሮግራምም በአደረጃጀትም ተመሳሳይነት ያላችው በፍጥነት ለውይይት ተቀመጠው  መቀራረብ አይደለም ውህደት በመፍጠር አንድ ይሁኑ፤ ከዛም  በዚህ መልኩ ቁጥሩ ከተቀነሰ በኋላ ሌላ ዙር ውይይት ሌላ ዙር መቀራረብ ይፈጠርና መሰረታዊ የሆነ የጎላ የኣላ ልዩነት የሌላቸው ወደ አንድ እንዲመጡ ይደረግ፤ ቀጥሎም ሁሉም በሚግባቡበት ተግባብተው በማይግባቡበት ላለመግባባት ተግባብተው  በኢትዮጵያዊነት መንፈስ  ለዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን መሆን  በጋራና በትብብር ለመታገል የሚያስችላችውን የጋራ አጀንዳ ያዘጋጁ ግባቸውን  በግልጽ ያስቀምጡ ወደ ግባችው የሚያድርሳቸው መንገድ ላይም ይስማሙ ከወያኔ በኋላ እውን ሆና ሊያዩት በሚመኙዋት ኢትዮጵያ እንዴትነት ላይም መግባባት ይፍጠሩ ከዛ በቆራጥነት  በተቀናጀ  ትግል ጉዞ  ወደ ድል፡፡

ስራው ብዙ፣ ሀላፊነቱ ከባድ ጊዜው እየመሸ ህዝብ እየቀደመ ነው፡፡ ብዙ አመታት አለአግባብ ባክነዋልና እንኳን ተዘናግቶ ሮጦና ሀያ አራት ሰአት ተሰርቶም የሚካካስ አይደለም፡፡ ስለሆነም የህዝብ እልቂት ይቁም የወያኔ አገዛዝ ያብቃ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት እውን ይሁን የምንለው በስሜት ሳይሆን በእምነት ከሆነ ይህ ወቅት የመጨረሻው መጀመሪያ መሆንአለበት፡፡ ግዜ የለም፡፡