የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት መግለጫ አወጣ – “ጣራ የለሽ እስር ቤት ከድጡ ወደ ማጡ”

ሁከት ፈጣሪ አሣሪና ገዳዩን የደርግ አገዛዝ ግንድ ፈንቅዬ የሰላም ችግኝ በምድረ ኢትዮጵያ አሰፍናለሁ፤ የሃሳብ ልዩነት ልዩነቶችን በጠመንጃ ቋንቋ ብቻ መፍታት የሆነውን የወታደር ስልት ቀልሼ በዘመኔ የክብ ጠረጴዛ ውይይት መደረክ እተካለሁ፤ እመኑኝ ቀን ይወጣላችኋል፤ ሰላም ትሰፍናለች እያለ ነብር ወያኔ ከሕዝብ የተቀላቀለው። የገባውን ቃል የግልብጥ ተርጉሞ በርግጥ ድብደባን፣ እስርን፣ ግድያና ሽብርን ማስፈኑን የዐይን እማኞች ነን። ነፍሰ ጡር፣ ወጣት የአገር ተስፋዎችን ደብድቧል፣ ሴትና አዛውንት አዋርዷል።እናት ስብእናዋንና ክብሯን ተገፋ ልጄን ልጄን እያለች በወታደር የተረሸነችበት የጭካኔ መድረክ እንጂ በክብ ጠረጴዛ በውይይት ችግር የመፍታት የሰከነ ሥልጡን ባህል በወያኔ መንግስት ሲተገበር አላስተዋልንም።
ጀግና ወላዲቷ እየተባለ የሚዘመርላት እናት ቀርቶ ውንድ ልጅ እንኳ በትግል ቆስሎ ወይም ተሸንፎ መሬት ከነካ እወደቀበት የማይመታበት ባህል ያለን ሕዝቦች ነበርን በየትም አገር ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የቢቢኤንና ኢሳትን ዜና አዳምጣችኋል በማለት ወታደሮች በሰው ቤት ጣራ ላይ እየወጡ የሳተላይት ዲሽ ሲነቅሉና ሲሰባብሩ ሰንብተዋል።

“ከድጡ ወደ ማጡ”ይሉታል አበው ከገጠር እስከ ከተማ ዱላ በጨበጡ ጠመንጃ በአነገቡ ወታደሮችና ጆሮ ጠቢዎች ሕዝቡን ማጠሩ የወያኔን ከልክ ያለፈ ፍርሃትና ከስልጣን መንጎጃው ወቅት መቃረቡን ከሚያመለክቱ ክስተቶች አንዱ ነው።

Muslim in ethiopia
የኢትዮጵያ ሙስሊም መሪዎች እነ አቡበከር፣ አህመዲን ጀበልና ሸህ መከተ ሙሄ መታሰርና በማእከላዊ መደብደብ የሕዝበ ሙስሊሙን ሞራል አጠናክሮ ወደ አንድ የትግል ጎራ እንደተሰበሰበ ሁሉ የኦሮሞ ሕዝብ መሬትን ነጥቀህ አሽከር አታደርገኝም በማለት የጀመረውን የመብት ፊልሚያ በመደገፍ  ወገናቸው ጎን የቆሙትን ጀግኖች እነ ኦቦ በቀለ ገርባ፣ አዲሱ ቦላና ደስታ ድንቃ፣ ደጀነ ጣፋ፣ ጌታቸው ሽፈራውና ዮናታን ተስፋዬ መታሰር፤ የኦሮሞ ኮንግሬስ ዋና ፀሃፊ ኦቦ በቀለ ነጋ ላይ የተፈፀመው ድብደባና ዛቻየኦሮሞን ህዝብ ብቻ ሣይሆን ድፍን የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ ለዘለቀ ትግል የሚያዘጋጅ ይሆናል። የጥቂት ታጋዮች መስዋእትነት የሺ ታጋዮች መፍለቂያ ምክንያት ነው፤ ታሪክም ይህንን ይመሰክራል።
ከወያኔ መንግስት ጋር ተሰልፋችሁ በህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን በደል በማራመድ ላይ የምትገኙ ካድሬዎች ለአንድ አፍታ ከራሳችሁ ጋር ተውያዩ፤ አስቡ፤ የዚያ ሁሉ ወጣት ደም ሲፈስ፤ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በፌደራል ፖሊስ ተከበው ሲደበደቡ ያሰሙት የነበረውን

“ወየው፣ ወየው! ”የሰቆቃ ድምፅ ከሰማችሁ በኋላ ዳግመኛ ከወያኔ መንግስት ጋር ላለመስራት ቆራጥ ውሳኔ ማስተላለፍ በተገባችሁ ነበር። እንደ ሰው መሳሳት ያለ ነው ስህተትን ተርድቶ ከአጥፋት መመለስ ግን ትልቅነትና አዋቂነት ነው። እናንተም እንደ ህዝቡ በቃ በሉ። በቃ ብለው የወታደር ዩኒፎርም አቃጥለው ወደ ህዝብ ከገቡት ጋር ሁኑ ጊዜያዊ ጥቅም ከውያኔ መንግስት ጋር ያስተሳሰራችሁ፤ ገና ለገና ንግድ ቢጤ እሞክራለሁ በሚል ተስፋ ብቻ ዳር የተቀመጣችሁ ወገኖቻችን ሃብቱም ብልፅግናውም ሕዝብ ሰላም ሲያገኝ ነው። ለሐቅና ለፍትሕ ቁሙ። አዱኛውና ቱጃርነቱ ያኔ የአብሮነት ይሆናል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በተለይም በአሁኑ ወቅት ኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ እየፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋና በደሉንም በመቃወማቸው ለእስር የተዳረጉት የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪል ድርጅቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አካላት፣ ጋዜጠኞች፣ የኦሮሞ ወጣቶች፣ ቀደም ሲል በእስር በመማቀቅ ላይ የሚገኙ የሙስሊሙ መሪዎችና ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ይጠይቃል።

በመላው የሃገሪቱ ሕዝብ ላይ የወያኔ መንግስት ያሰፈነው የሰቆቃ አገዛዝና የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ ለሱዳን ለመስጠት እያደርገ ያለውን ስምምነት በፅኑ የሚያወግዝ መሆኑን ይገልፃል።

ትግላችን እስከድል ደጃፍ ድረስ በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!

አላሁ አክበር!!!

የኢትዮጵያ  ሙስሊሞች  ሰላማዊ  ንቅናቄ  ደጋፊዎች  ሕብረት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.