‹‹እስካሁን ያልተዋሀድነው አንድነት ከመድረክ ጋር የነበረው ግንኙነት ይዞን ነው›› አቶ አበባው መሐሪ፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት

አቶ አበባው መሐሪ በመኢአድ ውስጥ ለ18 ዓመታት አባል ሆነው ቆይተዋል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ግን የድርጅቱ ፕሬዚዳንትነትን ከኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ተረክበው እየመሩት ይገኛሉ፡፡

› አቶ አበባው መሐሪ፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት
› አቶ አበባው መሐሪ፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት

በአሁኑ ወቅት መኢአድና አንድነት ፓርቲ ለመዋሀድ የሚያደርጉትን ሒደትና ተያያዥ የፖለቲካ ጉዳዮች በተመለከተ የማነ ናግሽ ከአቶ አበባው ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነትና መኢአድ ለመዋሀድ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሁለቱም ፓርቲዎች የቅንጅትን መፍረስ ተከትሎ በውስጣቸው መከፋፈልና መለያየት ሲስተዋልባቸው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ልዩነቶችንና ቅራኔዎችን በየራሳቸው መንገድ በውስጥ ዲሞክራሲ መፍታት ሳይችሉ ሁለቱም ወደ ውህደት ማምራታቸው ምን ያህል አዋጭ ነው?

አቶ አበባው፡– ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቅራኔው እንዴት መጣ የሚለው መቅደም አለበት፡፡ በመካከላቸው የተፈጠረው ቅራኔ በሁለት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛው ገዢው ፓርቲ፣ ፓርቲዎችን ማዳከም ስለሚፈልግ በውስጣቸው ያሉትን አባላት እስከ አመራር ድረስ ገንዘብ በመክፈል ሰላም እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይኼ በግልጽ የሚደረግ ነገር ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሕዝብ ለማገልገል ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማገልገል የሚመጡ ሰዎች ፍላጎታቸው ሳይሞላ ሲቀር ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ በዚህ የተነሳ ነው እንግዲህ በብዙ ፓርቲዎች ውስጥ በተለይ በመኢአድ መከፋፈል ጎልቶ የሚታየው፡፡ የእከሌና የእከሌ ቡድን እየተባለ በመኢአድ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም. ያንን ችግር ፈትተን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ የውስጥ ዴሞክራስ ሊባል የሚችለው እንዲህ ዓይነት ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ያውም ዴሞክራሲ ሊያሰፍን የሚቻለው በውስጡ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ ያ ደግሞ የሚሆነው ወደ ፓርቲው የሚመጡ ሰዎች ሕዝብን ለማገልገል መምጣት ሲኖርባቸው ነው፡፡ ራሳቸውን ለማገልገል የሚመጡ ከሆኑ አሁንም ፓርቲዎች ከቅራኔ የሚወጡ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚዎች በውስጣችሁ በሚፈጠር አለመግባባትና ሽኩቻ ብዙ ጊዜ ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ ወደ ኢሕአዴግ የመግፋት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይኼ ችግራችሁ በግልጽ እንዳይታያችሁ አያደርግም? ለመሆኑ ከዚህ ቀደምም በቅንጅትና በኅብረት ውስጥ እንደታየው በኢሕአዴግ ጣልቃ ገብነት በቀላሉ የሚፈራርሱ ከሆኑ፣ ምን ያህል አገር ለመምራት የሚያስችል የውስጥ ጥንካሬና አስተሳሰብ አላቸው ማለት ይቻላል?

አቶ አበባው፡- ገዢው ፓርቲ እንደዚህ ያሉ ሰዎችን አስርፆ አስገባ ሲባል መቶ በመቶ አይደለም፡፡ ነገር ግን የተወሰነ ግለሰቦችን በተደራጀ መንገድ ቁልፍ በሆነ ቦታ እንዲቀመጡ ያደርግና ፓርቲው ውስጥ ችግር ለመፍጠር በመቧደን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡

እርግጠኛ ነኝ ቅንጅትና ኅብረት እንደዚያ የሆኑት በውስጥ በነበረው ችግር ነው፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን ግን የገዢው ፓርቲ እጅ አልነበረም ብዬ አላምንም፡፡ የገዢው ፓርቲ ግፊት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ መለያየት ተፈጠረ፡፡ እነ አንድነት በራሳቸው መንገድ ሲንቀሳቀሱ ሌሎች ወደ ውጭ ወጥተው ሌላ ትግል እናካሂዳለን አሉ፡፡ ያ የሕዝቡን ሞራል የጎዳ ነበር፡፡ ገዢው ፓርቲ የወሰዳቸው ዕርምጃዎችም የፈጠሩት ችግር ነበር፡፡ አሁን አገርን ለመምራትና ሥልጣን ለመረከብ የሚችሉ ፓርቲዎች አሉ፡፡ መኢአድና አንድነት በውስጣቸው ብዙ የተማረ ኃይል አለ፡፡ ብዙ አባላት አሉዋቸው፡፡ ከሁሉም ብሔረሰብ የተውጣጣ ሰው አላቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ለመምራት አይችሉም ብዬ አላምንም፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የቆየ የእርስ በርስ ቁርሾ አላቸው ይባላል፡፡ ሌላ ሰው እንዲተካቸው የሚፈቅዱ አይመስሉም በሚልም ይተቻሉ፡፡ አዳዲስ መሪዎችን በመፍጠር መኢአድን ጨምሮ በዚህ በኩል ምን ያህል ለውጥ አለ ይላሉ?

አቶ አበባው፡- ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ አንደኛው ምሁሩ በፍርኃት ቆፈን ውስጥ ነው ያለው፡፡ ምሁሩ ሆዱን ለመሙላት እንጂ አዕምሮው ሕዝቡን ለማገልገል የተዘጋጀ አይደለም፡፡ በምንም ተዓምር፡፡ ስለዚህ ያሉንን ሰዎች ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰው ከሌለ ለማንም ሰጥተኸው አትሄድም፡፡ ስለዚህ እነዚያ ሰዎች ሥልጣን ላይ የሚቆዩት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ካለው ኅብረተሰብ እጅግ አብዛኛው በፍርኃት ቆፈን ውስጥ ነው ያለው፡፡ ወጣቱ ያንን ገልጦ ወጥቶ ለመረከብ ዝግጁ ካልሆነ፣ ምሁሩ ወጥቶ ከእነእከሌ እኔ እሻላለሁ ካላለ፣ እነዚህ ሰዎች ፓርቲው ውስጥና ቦታው ላይ ይቆያሉ፡፡ ካሉት ሰዎች በመምራት የተሻሉ ሆነው ስለሚገኙ ደጋግመው እየተመረጡ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ ግን የእኛ ፍላጎት ምንድነው? ወጣቱና ምሁሩ መጥቶ ከእነእከሌ እሻላለሁ የሚሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ሥልጣን የመቀያየርና ዲሞክራሲ በተቃዋሚዎች ይሰፍናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ይህንን ፍርኃት እግዚአብሔር ይወቀው እንዴት አድርገን እንደምንቀርፈው አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ፍርኃት ከየት የመነጨ ነው? አንዳንድ ጊዜ ሰው ራሱ በውስጡ በሚፈጥረው ሁኔታ የመነጨ ይመስልዎታል? ወይስ እውነት ከመንግሥት የሚመጣ ተጨባጭ ነገር አለ? የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆንዎ ምን የሚደርስብዎት ነገር አለ?

አቶ አበባው፡– እጅግ አስፈሪ ነገር ነው፡፡ እኔ በአውሮፓም ሠርቻለሁ፣ በአሜሪካም ሠርቻለሁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አስፈሪ ሁኔታ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ አንድ ሰው የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ወደ ተቃዋሚዎች ከመጣ ዕድገት አያገኝም፣ ከሥራ ይባረራል ገበሬ ከሆነ ግብዓት አያገኝም፣ መሬቱን ይነጠቃል፣ ከኅብረተሰቡ እንዲገለል ይደረጋል፡፡ ሰሞኑን እንኳ በጎጃም ውስጥ ማደበርያ ሲከፋፈል የእኛ አባላት ‹‹እናንተማ ፀረ ሕዝብ ናችሁ›› ተብለው ተከልክለዋል፡፡ እንደዚህ ያለ ነገር እያለ ገበሬው እንዴት እኛ ዘንድ ይመጣል? ይፈራል፡፡ እናም ይኼ ፍርኃት እየመጣ ያለው ገዢው ፓርቲ በኅብረተሰቡ ላይ ከሚያደርሰው ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ገዢው ፓርቲ በአባሎቻችሁ ላይ ያደርሳል የምትሉት አፈና ከሰላማዊ ትግል ያስወጣል? ወይስ እዚያ ውስጥ ተሁኖ የሚያሠራ ክፍተት አለ? 

አቶ አበባው፡– ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ እኛ አገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እየታገልን ስለሆነ በመሣሪያ የሚታገሉትን አንደግፍም፡፡ በአገራችን ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ መሸጋገር አለበት እንጂ በመሣሪያ መሆን አለበት ብለን አናምንም፡፡ የእኛ መርህ ይኼ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በአገራችን ውስጥ ሊሰፍን የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ሲሸጋገር ብቻ ነው፡፡ ይኼው ኢሕአዴግ በመሣርያ መጣ፣ ያለመሣርያ አልወርድም ብሎ ሥልጣን ላይ አለ፡፡

በመሣርያ ሥልጣን የያዙ አካላት ታሪካቸው ሲታይ ያለ መሣርያ አይወርዱም፡፡ በአገራችን ቅራኔና መጎሻሸምን አጥፍቶ ኅብረተሰባችንን አንድ ሆኖ የሚያገለግል ፓርቲ ያስፈልጋል፡፡ እገሌ የዚህ ዘር አባል ነው በሚል ሳይሆን ያገለግለኛል፣ ጠንካራ ሰው ነው፣ ታማኝ ነው፣ ጥሩ አመለካከት አለው፣ ዴሞክራሲ ሊገነባ ይችላል በሚል ነው ኅብረተሰቡ ሊመርጠው የሚገባው፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ በእውነቱ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቆም ብሎ ማየት ይገባዋል፡፡ ዴሞክራሲ በአገራችን ተፈጥሮ መጪው ትውልድ አገሪቱን እንዲረከብ የሚፈለግ ከሆነ፣ ገዢው ፓርቲ ብዙ እንዲሠራ ይጠበቃል፡፡ ዝም ብሎ ወጥሮ ይዞ ሰዎችን በማሳደድ ዴሞክራሲ በምንም ተዓምር አይገነባም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ከአንድነት ጋር ለመዋሀድ ስታስቡ ቀደም ብለው ተቀናጅተው ከፈረሱት የተማራችሁት ነገር አለ? ለምርጫ ብላችሁ ነው ወይስ በፕሮግራም የእውነት መመሳሰል ስላላችሁ?

አቶ አበባው፡– የመኢአድና የአንድነት ፕሮግራም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይበልጥ ተመሳሳይ ለማድረግና ወደበለጠ መስመር እንዲመራን ለማድረግ ላለፉት ሰባት ወራት እጅግ ጥልቀት ያለው ድርድር አድርገናል፡፡ ለምርጫ ቢሆን ኖሮ ላይ ላዩን አድርገን እስካሁን ተዋህደን ብዙ ሥራ በሠራን ነበር፡፡ ነገር ግን ወደፊት የሚመጣው ትውልድ የሚረከበው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ቅንጅት ምርጫው ሦስት ወይም አራት ወራት ሲቀሩት ነው የተመሠረተው፡፡ የመኢአድና የአንድነት ሒደት እንደዚህ አይደለም፡፡ እኛ ጠንክረንና አማራጭ ሆነን ገዢው ፓርቲን እንወዳደራለን፡፡ ገዢው ፓርቲ የያዛቸውን ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ፖሊሲዎችን ማስየቀር እንችላለን፡፡ ዴሞክራስያዊ የሆነ መስመር ይዘን ገዢውን ፓርቲ ተክተን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ መልካም መንገድ እንመራለን ብለን ነው የተነሳነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ከመድረክ ጋር አብሮ ለመሥራት ሞክሮ ነበር፡፡ በቅርቡ ከመድረክ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ አሁን አንድነት ከመድረክ ጋር ያለው ቅራኔ ሳይቋጭ ከእናንተ ጋር ውህደት መፍጠሩን እንዴት አያችሁት? 

አቶ አበባው፡- አንድነት ከመድረክ ጋር የነበረው ሁኔታ በግንባር አብሮ ለመሥራት ነው እንጂ በፕሮግራም ደረጃ አንድ አልነበረም፡፡ እኛ ከመድረክ ጋር አሁንም ቢሆን ቅራኔ የለንም፡፡ መድረክ በፌዴራሊዝም ላይ ያለው አቋም፣ ሥልጣን ቢረከብም በኢትዮጵያ የሚተገብረው ፕሮግራምና በመሬት ባለቤትነት ላይ ያለው አቋም ትንሽ ስለሚያስቸግር እንጂ አብረን ለመሥራትም የሚያግደን ነገር አልነበረም፡፡ ከአንድነት ጋር ብዙም የፕሮግራም ልዩነት አልነበረም፡፡ ከመድረክ ጋር ፕሮግራማቸው ፈፅሞ የተለየ ነው፡፡ ሊታረቅ አይችልም፡፡ አንድነት ከመድረክ ጋር የነበረው ግንኙነት ነው እስካሁን ይዞን የቆየው፡፡ አሁን ስምምነት ላይ የደረስነው አንድነት ከመድረክ ጋር አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ስለሌለው ነው፡፡ ውህዱ ፓርቲ አዲስ ፓርቲ ስለሚሆን ከመድረክ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ቀጥሎ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ ሁለት የሕግ ባለሙያዎች ቁጭ ብለው አይተውት መድረክ በውህዱ ፓርቲ ላይ የሚያደርሰው ችግር እንደማይኖር አረጋግጠዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለታችሁ መዋሀድ ጋር ተያይዞ አንድነት የቅንጅትን መንፈስ እንመልሳለን ብሏል፡፡ እንዴት ነው የተረዳችሁት? የሚመለሰውስ ምንድነው?

አቶ አበባው፡– የቅንጅት መንፈስ ይመለሳል ሲባል የሕዝቡን መነሳሳትና የሕዝቡን ሰላማዊ ትግል መነሳሳት ተመልሶ እንዲመለስ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል ለማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ ተቃዋሚዎች በኦሮሚያም በትግራይም ብሔርን መሠረት አድርገው ሲደራጁ ይስተዋላል፡፡ እስካሁን በአማራ ብሔር የተደራጀ ተቃዋሚ የለም? 

አቶ አበባው፡– ልዩነቱ ይኼ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ትግራዩም ቢሆን ከፖለቲከኞች በስተቀር ከኢትዮጵያዊነት ወጥቶ በዘር እንዲደራጅ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ አማራውም እንደዚያ ነው፡፡ በብሔር የመደራጀት ፍላጎት የለውም፡፡ ስለዚህ የፖለቲከኞች ፍላጎት እንጂ የትግራይ ሕዝብም ሆነ የአማራ ሕዝብ በራሱ ብሔር ብቻ የፖለቲካ ድርጅት ተደራጅቶለት እንዲጠብቀው የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ይኼንን ለማስቆም ነው ጥረት የምናደርገው፡፡ ይኼ ከአማራው ብቻ አይደለም፡፡ ትግራይም ባህሉን፣ ቋንቋውንና ታላቅነቱን ከአባቶቹ ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ሲያንፀባርቅ የኖረ ነው፡፡ አሁንም ሕዝቡ አይፈልግም፡፡

Source- Ethiopian Reporter