ኦነግና ኦነጋዊያን ወያኔና ሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ተፈጥሯዊ የተጠያቂነት ፖለቲካዊ ቁመና አላቸውን? – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

b23ae_Amsalu
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ባለፈው ጥር 4, 2008ዓ.ም. “ለኦነግና ኦነጋዊያን! የወያኔን ዓላማ አንግቦ ወያኔን ለመውጋት የእንተባበር ጥሪ አይሠራም!” በሚል ርእስ ለጻፍኩት ጽሑፍ ኢልማ ኦሮሞ (የኦሮሞ ልጅ) በሚል የብእር ስም “የተጠቀሙ አንድ ሰው ትግሉን በአሸናፊነት ለመጨረስ መወሰድ የሚገባቸው ዋናዋና ነገሮች! ለሠዓሊ አምሳሉ ላወጡት ጽሑፍ መልስ” በሚል ርእስ  “ይህንን ሐሳብህን የሚጋሩ እጅግ ብዙ ሰዎች ስላሉ ነው እንደ ሌላው የወያኔ ሐሳብ  ነው ብዬ መግፋት ያልፈለኩትና ለዚህ ጽሑፍህ መልስ መስጠት የፈለኩት” በማለት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰው የሆኑ ባስመሰለ አቀራረብ መልስ ያሉትን ሐሳብ በጽሑፍ አቅርበው ለተለያዩ ድረ ገጾች አሰራጭተው አስነብበዋል፡፡ እኔ ግን እኒህ ሰው እሳቸው በጽሑፋቸው ስለማንነታቸው እንድናስባቸው የፈለጉትን ዓይነት ሰው እንዳልሆኑ ከዚያው ከጽሑፋቸው ተረድቻለሁ፡፡ ለማኝኛውም የአመራር ቦታ ያላቸው ይሁኑ ተራ ደጋፊ ያንጸባረቋቸው ሐሳቦችን በርካቶቹ የሳቸው ቢጤዎች ስለሚጋሯቸውና ለፈጸሙብኝ ስም ማጥፋቶች ምላሽ መስጠት ስላለብኝ ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡

ሰውየው ማንንም ይወክሉ ማን መልስ ከሰጡ አይቀር ነጥብ በነጥብ ለመመለስና ለመተቸት ቢሞክሩ ተወያይቶ ችግርን የመፍታት ልምድንና ባሕልን ከማዳበርና ከአርአያነት አኳያ ምን ያህል በጠቀመ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ለራሳቸው የተመቸ መስሎ የታያቸውን ነጥቦች ብቻ መዘው መረጃንና እውነታን በማጣረስ ነው መልስ ለመስጠት የሞከሩት፡፡

ሲጀመር እኔ እራሴን እንጅ የማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲን (የእምነተ አሥተዳደር ቡድንን) አልወክልም፡፡ ስለሆነም እሳቸው የሚመስላቸው የሆነ አካል አመራር እንደሆንኩ በመቁጠር “ላቀረብነው ጥያቄ ቀና ምላሽ ብትሰጡን ኖሮ፣ እንዲህ ብታደርጉ ኖሮ፣ ለእንደዚህ ብትዘጋጁ ኖሮ” እያሉ ሊመልሱ አይገባም ነበር፡፡ በእርግጥ ከጽሑፎቸ መረዳት እንደሚቻለው ለዚህች ሀገር ይጠቅማሉ የምላቸውን ሐሳቦች በተሻለ ሁኔታ ከመያዙና በሀገራችን ያለውን ነባራዊ ሐቅ በሚገባ ተረድቶ ማለትም የሰላማዊ ትግል አማራጭ ዝግ መሆኑን ተረድቶ ጊዜ ሳንፈጅና ብዙ ሳንከስር ብቸኛውንና ቀሪውን የትጥቅ ትግል አማራጭ መጠቀም እንዳለብን ተገንዝቦ ወደ ትግል የገባው የአርበኞች ግንቦት 7 ደጋፊ ነኝ፡፡ ይሁንና ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን በማንሣት ለእኔ በሚሰጥ ምላሽ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት መናገር አይቻልም፡፡ ተገቢም አይደለም ደጋፊ እንጅ አመራር አይደለሁምና፡፡

ከጊዜ አንጻር ፍሬ ፈርስኪውን ትቸ አንኳር አንኳር ወደ ሆኑት የጸሐፊው ሐሳቦች ሳልፍ “ተቃውሞውን ከአካባቢያዊ እይታ ሊያወጣው የሚችል ንቅናቄውን የጀመረው አካል ሳይሆን የንቅናቄውን አድማስማስፋት ያለበት ንቅናቄውን የሚቀላቅል ሌላኛው የኅብረተሰብ ክፍል ነው ለምሳሌ ኦሮሞ በማስተር ፕላኑ ላይ የጀመረውን አማራው አካባቢያዊ ጥያቄውን ለምሳሌ ለሱዳን የተሰጠውን መሬት በመቃወም ጋምቤላው  መሬቱን ደቡቡ ለምሳሌ ሲዳሞው የራሱን አካባቢያዊ ጥያቄ ቢያነሣ ንቅናቄው ሀገራዊ ወደ መሆን ያድጋል። ዋናው ነገር ኦነግ ያላሰበውን ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው ካልክ ሌላው ጥያቄ እንኩዋን ባይኖርብህ የኦሮሞ  ተማሮዎች ጥያቄ የእኔም ጥያቄ ነው ብሎ ቢወጣ ኢትዮጵያዊነትን መስበክ ለእኔ ይህ ነው የጋምቤላው ህመም ህመሜ ሳይሆን የጎንደር እስረኞች ችግር ችግሬ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ መሆን የምንችል አይመስለኝም ይህንን የምልህ ለፖለቲካል ኮሬክትነስ አይደለም” ብለዋል፡፡

ይህ ያሉት ነገር ግን ምን ማለት እንደሆነ ራሳቸው ጸሐውም የሚያውቁት አልመሰለኝ፡፡ ምክንያቱም ሁለት ተጻራሪ ሐሳቦችን ነው አንድ ላይ ያጨቋቸው፡፡ ይህ ሐሳባቸው ጽሑፌን በቅጡ እንዳልተረዱት እንዳልገባቸው የሚያሳይም ነው፡፡ እኔ እኮ ያልኩት ይህ የተቃውሞ ጥያቄ ዘርንና ጎጥን መሠረት ያደረገ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን በኢትዮጵያዊነታቸው በተጠቀሰው መሬት ላይ ያላቸውን መብት መቀበል ያልፈቀደ ያገለለ ጠባብና አጥፊ አስተሳሰብ በመሆኑ ነው የተቀረው ኢትዮጵያዊም ጥያቄያቹህን ጥያቄው አድርጎ ሊነሣ ያልቻለው እያልኩ እያለሁ እሳቸው ጭራሽ ይሄንን ስሕተት ሌላው ኢትዮጵያዊም እንዲደግመው “አማራው ጋምቤላው ሲዳሞው የየራሱን ጥያቄ ቢያነሣ ንቅናቄው ሀገራዊ ወደ መሆን ያድጋል”  ብለው አረፉት፡፡ አየ ብስለት አሁን እነኝህ ናቸው…

አቶ ጸሐፊው “ሀገራዊ” ማለት ምን ማለት ነው የሚመስልዎት? ይህ ንቅናቄ ሀገራዊ የሚሆነው እርስዎ እንደተረዱት በሁሉም ብሔረሰቦች ዘንድ እናንተ ያነሣቹህት ጥያቄ መነሣቱ ሳይሆን ጥያቄው እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሁሉ ለአንድ የጋራ ጥቅም ቢነሣ ነው ሀገራዊ የሚሆነው እንጅ ሁሉም ሌላ ሌላውን ሕዝብ እያገለለና እንደማይመለከተው እያሰበ የኔ መሬት ለእኔ ብቻ እያለ ተመሳሳይ ጥያቄ ለየራስ በማንሣት አይደለም ሀገራዊ የሚሆነው፡፡ ይሄ ጎጣዊ ነው እንጅ ሀገራዊ አይደለም እሽ አቶ ጸሐፊው?

ንቅናቄውን ሀገራዊ የሚያደርገው ጥያቄው የጋራ መሆን ሲችል ነው እንጅ የየራሳቸውን ጥያቄ ሁሉም ለየራሳቸው ስላነሡ አይደለም፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው የተቀረው ኢትዮጵያዊ ሊቀላቀለው ያልፈለገው፡፡ ከዚህ ምላሽ እንኳን አይረዱም እንዴ? ወያኔ ለሱዳን በሰጠው መሬት ጉዳይ ላይስ እሽ ያንሡ ማንሣትን አለባቸው እሱም ቢሆን ግን ድንበር ላይ ስላሉ ጉዳዩ የእነሱ ብቻ ሆኖ መታየቱ አሁንም እጅግ ስሕተት ነው፡፡

ቀጠሉና አቶ ጸሐፊው ኦነግና ኦነጋዊያኑ የእንተባበር ጥሪን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከማቅረባቸው በፊት መሥራት ያለባቸውን የቤት ሥራ መሥራት ነበረባቸው ይሄንን ያድርጉ ብየ ላነሣሁት ነጥብ ሲመልሱ ““መሥራት ያለባቸውን የቤት ሥራማ ጠንቅቀው ሠርተው ነበር ነገር ግን ቅን ማኅበረሰብ ስላልነበረ እንዲህ ሆንን፡፡ ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት መግባባትና የምንፈልገውን ነገር በግልጽ መረዳት ባለመፈለግ የመጣ ችግር ነው የማየው፡፡ ኦሮሞ በቅርበት እንደምከታተለው ከሆነ ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ የሆነ ራዕይ አላቸው ኦነግን ጨምሮሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ “በማንም ቀዬ ላይ የማንንም አለቃነት አንቀበልም እራስ በራስ ማስተዳደር ይህ ካልተቻለ ግን የራስን መንግሥት መመሥረት” ነው የሚሉት ይህ ደግሞ ሌላ አጀንዳ ከሌለህ በስተቀር ተገቢና ሌጂትመንት የሆነ ጥያቄ ነው።  የብሔርን ስምይዞ መደራጀት የብሔሩን መብት ለማስጠበቅ ነው ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ውስጥ ተገቢና ትክክለኛ አደረጃጀት ነው”” ነበር ያሉት፡፡

አዎ ይሄንን ችግር የተሞላበት አስተሳሰብ የፈጠረው አለመብሰልና የአመለካከት ድህነት እንደሆነ ስለምረዳም እኮ ነው በተቻለኝ መጠን እንድትበስሉ እንድታስተውሉ የተሻለውን የሠለጠነውን አስተሳሰብ ለማጋራጥ ጥረት የማደርገው፡፡

ሲጀመር አቶ ጸሐፊው “መሥራት ያለባቸውን የቤት ሥራማ ጠንቅቀው ሠርተው ነበር” ሲሉ የገለጹትን እኔ “ኦነግ አስቀድሞ መሥራት ያለበት የቤት ሥራ” ብየ የገለጽኩትን ማለትም “ተገንጣይነቱን ጣል እርግፍ አድርጎ ትቶ የአንድነት ኃይሉን ይቀላቀል” ስል የገለጽኩትን እርምጃ ለመውሰድ ፈልጎ ተንቀሳቅሶ እንደነበርና ጸሐፊው እንዳሉት ቅን ማኅበረሰብ ስላልነበረ እንዲህ ልንሆን እንደቻልን ገና ዛሬ ከሳቸው መስማቴ ነው፡፡ ስለ እውነት ለመናገር ኦነግ ተገንጣይነቱን ትቶ የአንድነት ኃይሉን ለመቀላቀል ሲሞክር የአንድነት ኃይሉ ቅን ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቶ እንዲህ ሆነን ከሆነ ይህ ጉዳይ በግልጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገልጾ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዳጅ ጠላቱን እንዲለይ እንዲያውቅ ቢደረግ እጅግ መልካምና መሆን ያለበትም ጉዳይ ነው፡፡

እስከማውቀው ድረስ ግን ኦነግ ይሄንን ነገር እንኳን ሞክሮት አስቦትም እንደማያውቅ ነው፡፡ ጸሐፊው መረጃ ካላቸው ቢጠቅሱልን መልካም ነው ለጊዜው ግን እንዲህ ማለታቸውን የምረዳው እሳቸው “ይህንን የምልህ ለፖለቲካል ኮሬክትነስ አይደለም” ይበሉ እንጅ ለሱ እንዳሉት ነው የምረዳው፡፡ ይሄ አኪያሔድ ደግሞ አብሶ የመረጃ ዝውውርና ልውውጥ እንደሚያዩት ፈጣንና ተደራሽ በሆነበት ዘመን ራስን ለትዝብት ከመዳረግ በስተቀር ለማንም የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡

አቶ ጸሐፊው “የኦነግም ሆነ የሌሎች የሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማና አቋማቸው ግልጽ ነው እሱም በማንም ቀዬ ላይ የማንንም አለቃነት አንቀበልም እራስን በራስ ማስተዳደር ይህ ካልተቻለ ግን የራስን መንግሥት መመሥረት! ነው የሚሉት፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ አጀንዳ ከሌለህ በስተቀር ተገቢና ሌጂትመንት የሆነ ጥያቄ ነው”

ያሉትን አስተሳሰብ እርስዎም ሆኑ ቢጤዎችዎ ማሰብ መረዳትና ማስተዋል የሚችል ጭንቅላት ካለዎት፣ ለሞራል (ለቅስም) ሕግጋትና ድንጋጌዎች ዋጋ የሚሰጥ ሰብእና ካለዎት፣ ለፍትሕ ክብርና ልዕልና ታማኝና ዋጋ የሚሰጥ እንዲከበሩ እንዲተገበሩ የሚሻ ማንነት ካለዎት ይህ ያሉት ጥያቄ ብላሽና የድንቁርና የውንብድና የግፈኛ የቀማኛ አስተሳሰብ መሆኑን አረጋግጥልዎታለሁና እባክዎኝ እርስዎም ሆኑ መሰሎችዎ በጥሞና እንድትከታተሉኝ እማጸናለሁ፡፡

የመገንጠል ፍላጎትና ዓላማ ላላቹህ ኦነግና ኦነጋዊያን አንድ ጥያቄ ብቻ በማንሣት ከላይ የጠቀስኳቸው የሰብእና እሴቶች ቅንጣቱ እንኳን እንደሌላቹህ ለራሳቹህ ማረጋገጥ ትችላላቹህ፡፡ እሱ ምንድን ነው “ዛሬ እንገነጥለዋለን የምትሉት የሀገራችን ክፍል ኦሮምኛ ተናጋሪ መቸ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ተቆጣጥሮ የሰፈረበት?” ኦሮሞ መቸና ነባሩን ሕዝብ ምን አድርጎ ተስፋፍቶ እንደሠፈረበት በሚገባ ታውቁታላቹህና እዚህ ላይ እሱን ስዘረዝር አልውልም፡፡

በእንዲህ ዓይነት ኢፍትሐዊ አኪያሔድና ውንብድና አረመኔያዊ ዘመቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም የተያዘን መሬት ልክ የራስ እንደሆነ ሁሉ “እንገነጥላለን!” ስትሉ የፍትሐዊነት የሞራል (የቅስም) ጥያቄዎች እንደሚነሡባቹህና ከእነዚህ ጥያቄዎች አንጻር ይሄ ጥያቄያቹህ ፍጹም አግባብነት የሌለው መሆኑን፤ እናንተንም ፍትሕን ጨርሶ የማታውቁ፣ ለፍትሕ ታማኝ ያልሆናቹህ፣ የሞራል (የቅስም) ስሜት የሚባል ነገር የሌላቹህ ቀማኞች ወንበዴዎች እንደሚያደርጋቹህ ታውቃላቹህ ወይ? ዝርፊያንና ውንብድናን በሕጋዊና ፍትሐዊ ጥያቄ ተቀባይነት ኖሮት ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ወይ?

እንዲህ ዓይነት ክፉ ሰዎች ነን ይሄንን ውንብድና ማድረግ አለብን እያላቹህ እንደሆነ ልብ ብላቹሀል ወይ? ስም እየለወጣቹህ ቢዛምና ዳሞት የነበረውን ወለጋ፣ ፈጠርጋ የነበረውን አሩሲ፣ ለኮመልዛ የነበረውን ወሎ፣ እናርያ የነበረውን ኢልባቡር፣ ቤተ ጊዮርጊስ የነበረውን ወረኢሉ፣ ሒርማታ የነበረውን ጅማ፣ ግራርያ የነበረውን ሰላሌ ወዘተረፈ የነበራቸውን ስም እያጠፋቹህ የራሳቹህን ሥያሜ ስለሰጣቹህ የሚሆን ይመስላቹሀል? እንዴት ዓይነት የዋሀን ናቹህ ጃል? እንዲህ ዓይነት ግለሰቦችና ቡድኖች ሆናቹህ እናንተ እንዴት ነው የፍትሕን ጥያቄ የማንሣት የሞራል (የቅስም) ብቃቱ ሊኖራቹህ የሚችለው??? እኛን ተውን ግን እንዲያው “እርዱን ደግፉን” የምትሏቸውን የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እንኳን እፈሩ እስኪ እባካቹህ? አመለካከት አስተሳሰብ ዓላማቹህ በፍጹም አሳፋሪና ነውረኛ ነውና፡፡

እሽ አሁንስ ማን እንደሆናቹህ አወቃቹህ? ሐፍረትስ ሊሰማቹህ አይገባም? ካልተሰማቹህ የተሟላ ሰብእና አልባ ጉድ ፍጥረቶች መሆናቹህን አሁን አረጋግጡ፡፡ የዋሁና ቅኑ አማራ ግን እንኳንና የሀገር ሥያሜ ሊቀይር ይቅርና በታሪክ አጋጣሚ የኦሮሞ ተወላጆች የሠፈሩበትን የጎንደር ወረዳዎች እንኳን “የኦሮሞው ሀገር” (ሥያሜው በዘመንኛ መጠሪያ ተለውጦ ነው) እያለ ነው የሚጠራው፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ እነዚያ ወረዳዎች “የኦሮሞው ሀገር” ከመባል በስተቀር በእነዚያ የጎንደር ወረዳዎች ያኔ ሰፍረው የነበሩት ኦሮሞዎች ከአማራው ጋር ተዋሕደው ዛሬ ላይ በነዚያ ወረዳዎች ያሉ ዜጎች ቅምቅማታቸው ኦሮሞዎች እንደነበሩ እንኳን ብዙም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ኦሮሞዎቹን እዚያ እንዲሠፍሩ ያደረጓቸው ዐፄ ሱስኒዮስ ከጦራቸው አብዛኛውን ቁጥር በያዙት ከወለጋ ባመጧቸው ተዋጊዎች ዐፄ ያዕቆብን ወግተው ድል በማድረግ ዐፄ ከሆኑ በኋላ ከወለጋ ላመጧቸው የኦሮሞ ተዋጊዎች የአብያተክርስቲያናቱን ርስት በመውረስ እያከፋፈሉ እዚያ እንዲሰፍሩ አድርገዋቸው ስለነበር ነው፡፡

ስለዚህ ጥያቄያቹህ ሊሆን የሚገባው ፍትሕ እኩልነት ነጻነትና ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት ሀገር ትኑረን የሚለው ብቻና ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በአሐዳዊ የአሥተዳደር ሥርዓትም መስተናገድ እንደሚችል ልታውቁ ይገባል፡፡ ቁልፉ ነገር ሕዝቡ በመረጣቸው የሕዝብ ተመራጮች (ባለሥልጣናት) ሊተዳደር የሚችልበት ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት መመሥረት መቻሉ ላይ ነው፡፡ ይሄ እየተቻለ ቋንቋንና የብሔር አሰፋፈርን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ (ራስ ገዛዊ) አሥተዳደር ነው መኖር ያለበት ብሎ ክችች ማለት ከመገንጠል ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ጥያቄውም ሸፍጥ ያዘለ ለሀገርም ለሕዝቧም የማይበጅ ኢፍትሐዊ የጥፋት አስተሳሰብና ጥያቄ ነው፡፡

ሌላው አብሮ የተነሣው ነጥብ “የብሔረሰብን መብት ለማስጠበቅ የብሔርን ስም ይዞ መደራጀት የብሔሩን መብት ለማስጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ውስጥ ተገቢና ትክክለኛ አደረጃጀት ነው” የተባለው ይሄንን ማድረግ መብት መሆኑን ባምንም አስተሳሰቡ ግን አሁንም የደነቆረ ኋላ ቀር አጥፊ ለኢፍትሐዊነትና ለውንብድና የሚያጋልጥ ከንቱ አስተሳሰብ መሆኑን ላረጋግጥላቹህ እችላለሁ፡፡ ይሄንን ለመረዳትም ወያኔንና ሥራውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ዛሬ እናንተ ወያኔን ትግሬን ብቻ ተጠቃሚ ማድረጉን፣ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች ማድረጉን ታወግዛላቹህ፣ ትኮንናላቹህ፣ ትቃወማላቹህ፣ እንታገለዋለንም ትላላቹህ፡፡ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኘ የምነግራቹህ ግን ነገ እናንተ ሥልጣን ብትይዙ ወያኔ ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሆነውን ያህል ቅንጣት ታክል ሳትለወጡ ምናልባትም ከዚያም የከፋ የምትሆኑ መሆናቹህን ነው፡፡

ምክንያቱም ወያኔን እንዲህ እንዲሆን ያደረገው ጎጠኛ ዘረኛ አስተሳሰቡና ዓላማው ነውና፡፡ እናንተም አስተሳሰብ ዓላማቹህ ጎጠኛ ነውና ይህ ጎጠኛና ዘረኛ አስተሳሰባቹህ እናንተንም እንደዚህ ከማድረግ የሚቀር አይሆንም፡፡ ወያኔ ትግሬንና ትግራይን በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እየጣረ ያለው የታገልኩት የደማሁት መሥዋዕትነት የከፈልኩት ለሕዝቤ ለትግሬና ለትግራይ ነው የሚል በመሆኑ ነው፡፡ እናንተም ነገ ሥልጣን ብትይዙ ልክ ወያኔ ብሎ እንዳደረገው ሁሉ እናንተም የታገልንለት፣ የሞትንለት፣ የደማንለት፣ መሥዋዕትነትን የከፈልንለት ለሕዝባችን ለኦሮሞ ሕዝብ ነውና በማለት በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ደም ስታስለቅሱ ነው የምትገኙት፡፡

ይሄንን የማታደርጉ ከሆነና አሁን እያላቹህት እንዳላቹህት “ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ ነጻነትን፣ ሰብአዊ መብትን በሀገሪቱ እንዲከበር ለማድርግ” ከሆነ የኦሮሞ የምንትስ ማለቱ ምንም አስፈላጊነት የለውም፡፡ የኦሮሞ ካላቹህ በቃ የኦሮሞ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊሆን አይችልም፡፡ የትግሬ ያለ በቃ የትግሬ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም አልሆነምም፡፡ ይህ ምንም ብታደርጉት ሊቀረፍ የማይችል ተፈጥሯዊ የጎጠኛና ዘረኛ አስተሳሰብ ችግር ነው፡፡ ዓላማቹህ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት በፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) አሥተዳደር የሚስተናገድባት ሀገር ለመፍጠር ከሆነ የኦሮሞ የትግሬ የምንትስ ብላቹህ ልትታገሉ የምትችሉበት አንድም አሳማኝና ትክክለኛ ምክንያት የለም፡፡

በተደጋጋሚ እንደተናገርኩት ይህ ብሔር ተኮር ዘውጋዊ አስተሳሰብ ኋላ ቀር፣ ኢፍትሐዊ፣ አንባገነናዊ፣ ኢሰብአዊ በመሆኑ ነው በሠለጠነው የዓለማችን ክፍል የማይሠራበት እንጅ የተለያዩ ብሔረሰቦች እዚያ ስለሌሉ አይደለም፡፡ የአሜሪካው ርዑሰ ሥልጣናት (ፕሬዘዳንት) አቶ ኦባማ ኬንያ ሔደው ለዘመዶቻቸው የመከሩትን ምክር ያሳሰቡትን ጥብቅ ማሳሰቢያ አልሰማቹህም? “ከብሔር ተኮር ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ራቁ ሀገር ይበትናል ያጠፋል!” ይሄ ነው በሀገራችንም እየሆነ ያለው፡፡ ይሄንን ነው ለማድረግ እየጣራቹህ ያላቹህት፡፡

አስተሳሰባቹህ ሰፊና ትክክል፣ ፍትሐዊ፣ ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) የሚሆነውና የመሆን ዕድል የሚያገኘው ጠባቹህ በጎጥና በዘር ስትደራጁ ሳይሆን ፖለቲካቹህ (እምነተ አሥተዳደራቹህ) ልክ እንደምዕራቡ የዓላም ክፍል የሰው ልጆችን መብቶችና እነኝህን መብቶች ለሁሉም ዜጋ በእኩልነት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችሉ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) የአስተሳሰብ ልዩነቶች ላይ የተመሠረተ ሲሆንና ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ይሄኔ አፋቹህን ሞልታቹህ ማሰብ መገንዘብ የምንችል፣ ኃላፊነት የሚሰማን፣ ለፍትሕና ለእኩልነት ተቆርቋሪ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጠበቆች የሆንን ታጋዮች ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራዊያን) ነን ማለት የምትችሉት፡፡ ምዕራባዊያኑ እንዲህ ብለው ሲያበቁ በተሟላ መልኩ የቆዳ ቀለም ልዩነት ሳይገድባቸው ተፈጻሚ ያደርጉታል ወይ? ከተባለ ይሄ ሌላ ጥያቄ ነውና ይታለፍ፡፡

ደሞ እኮ የሚገርመው እየተነሣቹህ የትግሬ የኦሮሞ የምንትስ እያላቹህ መከራ የምታበሉብን ነገር የሌለ ሆኖ እያለ መሆኑ ነው፡፡ በዚህች ሀገር ኦሮምኛ ተናጋሪ፣ ትግርኛ ተናጋሪ፣ ጉራጌኛ ተናጋሪ ወዘተረፈ. እንጅ ኦሮሞ የለም ትግሬም የለም ጉራጌም የለም ወዘተረፈም የለም፡፡ ያለው የተዋሐደ አንድ ሕዝብ፣ የየብሔረሰቡ ቋንቋና ባሕል ብቻ ነው፡፡ ቋንቋና ባሕሉም ቢሆን ያንደኛው ከሌላኛው ጋር ተዋውሶ ተቀላቅሎ ተዋሕዶ ተወራርሶ እንጅ ወጥ የሆነ ያልተቀላቀለ ያልተወራረሰ ያልተዋሐደ የለም፡፡ እንዴትስ ሊኖር ይችላል ተብሎ ይታሰባል? አለማወቅ ነዋ! ሌላ ምንም አይደለም፡፡

ሕዝባችን በረጅሙ የሀገራችን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) መስተጋብር በደንብ ተደርጎ የተቀየጠ የተዋሐደ የተዋለደ ሕዝብ ነው ያለው፡፡ ይሄንን እውነታ የየራሳቹህን የዘር ኃረግ በመፈተሽ ልታረጋግጡት ትችላላቹህ፡፡ ከአባቱ በላይ መጥራት የማይችል ስለዘር ሀረጉ በቂ መረጃ የሌለው ሰው ካልሆነ በስተቀር በደሙ ውስጥ በእናት ወይ ባባት ወይም በሁለቱም ከሁለትና ከሦስት ብሔረሰብ በላይ ያልተዋለደ ዜጋ የለም ሊኖር የሚችልበትም ዕድል አልነበረም የለምም፡፡ በእውነት ይኖራል ብሎ ማሰብ ጠልቆ የመረዳት ብቃት የማጣትና የመረጃ እጥረት ችግርን ያሳያል፡፡ ይሄንን ጉዳይ “ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት የሚታደገው ብቸኛው መንገድ!” በሚለውን ጽሑፌ ላይ በስፋትና በጥልቀት ከመረጃዎች ጋር ዳስሸዋለሁና ጎግል አድርጋቹህ እሱን በመመልከት ያለውን እውነታ መረዳት ትችላላቹህ፡፡

እንግዲህ እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ እየተነሣቹህ ሩቅ ሳይሆን በእናቱ ሌላ በአባቱ ሌላ የሆናቹህት ሁሉ እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ ትግሬ ነኝ፣ እኔ ምንትስ ነኝ ብትሉ ኢፍትሐዊነታቹህን፣ ጥቃታቹህንና ክህደታቹህን የጀመራቹህት ከራሳቹህ መሆኑን መረዳት ይኖርባቹሀል፡፡ ግማሹ ደም ሌላ ሽማሹ ደም ሌላ በሆነበት ሁኔታ አንዱን ብቻ ይዞ እኔ ምንትስ ነኝ የሚል ሰው እንዴትስ ነው ትክክለኛ ፍትሐዊ ተአማኒ ሰብአዊ ወዘተረፈ. ሊሆን የሚችለው? እንዲህ ባለ በተሳከረ፣ እውነታን መቀበል ለእውነታ መገዛት ባልፈለገ የማንነት ቀውስ ውስጥ ነው ሰምጣቹህ ለማስመጥ እየጣራቹህ ያላቹህት፡፡ በእንዲህ ዓይነት የማንነት ቀውስ የምትዋዥቁ የምትጓጉጡ ሰዎች ከዚህ የሥነልቡና ሕመማቹህ ካልተፈወሳቹህ በስተቀር እመኑኝ ለምንም የምትሆኑ አይደላቹህም፡፡

ሌላው አቶ ጸሐፊው “አየህ የኦሮሞ ሕዝብ አንተ እንዳከው ደንቆሮ ሕዝብ አይደለም!” ብለው ፈጥረው ከሰውኛል፡፡ ከየት እንዳመጡት መጠየቅ እፈልጋለሁ “እራሳቸውን የኦሮሞ ልኂቃን አድርገው የሚቆጥሩ ጽንፈኛ ግለሰቦች አለመግባባትን እንዴት እንፍታ? በሚል ጉዳይ ላይ ከአንድ ደንቆሮ ደጋፊያቸው የተለየ ወይም የተሻለ ሐሳብ ማመንጨት የማይችሉ…” የሚል ቃል ተጠቅሜያለሁ፡፡ ይሄ እንዴት ሆኖ ነው የኦሮሞ ሕዝብ ተብሎ ሊተረጎም የሚችለው አቶ ጸሐፊው? ነው ወይስ እርስዎ የገዛ ሕዝብዎን መስደብ ፈልገው ነው? በጣም ነውረኛና ባለጌ ነዎት፡፡

እንኳን አንድ ግለሰብ አናንተ እንኳን የኦሮሞን ሕዝብ አትወክሉም፡፡ እርግጥ ነው ቀላል የማይባል ደጋፊ አላቹህ የኦሮሞ ተወላጅ ነኝ ከሚሉት ጽንፈኛ አመለካከት ካላቸው ሁሉም የናንተ ደጋፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ቁጥር ከኦሮሞ ሕዝብ ከፊሉ እንኳን ቢሆን እራሳቹህንና እኩይ ሰብእናን ብቻ እንጅ በጭራሽ የኦሮሞን ሕዝብ አትወክሉም፡፡ ከኦሮሞ ሕዝብ እንደናንተ ያለ የጥፋት ኃይል እንዳለ ሁሉ በርካታ ደግሞ አስተዋይና ለውድ ሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑ ደግሞ ነበሩ አሉንም፡፡ እናንተ የኦሮሞን ሕዝብ ትወክላላቹህ ብሎ ማለት የኦሮሞ ሕዝብ እነኝህ ዓይነት ብርቅና ድንቅ ልጆች አልነበሩትም የሉትምም ብሎ ማለት ነው የሚሆነው፡፡ ይህ እንዳልሆነ ደግሞ እናንተው እራሳቹህም የምታውቁት ሀቅ ነው፡፡

ሌላው እናንተን ከወያኔ የሚለያቹህ ምንድን ነው? ብየ ለጠየኩት ጥያቄ ማንነታቸው ያልታወቀው “መልስ ልንሰጥህ ፈልገን ሰጠንህ” ባይ አቶ ጸሐፊው መልስ ሲሰጡ ምን አሉ፡-

““አየህ ወዳጄ ከወያኔ ጋር የሚለየን ብዙ ነገር አለ እስቲ ጥቂት ልዘርዝርልህ
. ኦሮሞ እንደ ማኅበረሰብ በምሥራቅ አፍሪካ  እጅግ ብዙ ሕዝብ የሆነ፣ በኢትዮጵያ   ከግማሽ በላይ የሆነ፣ ምንም ዓይነት ኮምፕሌክስ የለለው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዲሞክራሲን ለማስፈን ብቃቱ ያለው፣ የሀገሪቷ የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነ፣ እርሻ ቢሆን ቡናው ቢሆን ወርቁ ቢሆን በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ከ80% በላይ ኮትሪቢዩት የሚያደርግ እስከ ዛሬ በነበሩት መንግሥታት የበይ ተመልካች የሆነ ይቅር ባይ ቻይ ግሩም የሆነ ሕዝብ ነው፡፡ ወያኔ ግን በተቃራኒው አናሳ  የሆነ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ኮንትሪቢዩት የማያደርግ በበታችነት ኮምፕሌክስ የሚሰቃይ ተራ ወንበዴ ነው፡፡ እንደትስ አድርገህ ነው የምታወዳድረን እኛን እንደ ጥፋት ኃይል ማየት የቤት ምሶሶን ነቅለህ ግርግዳውን እንደ ማሰማመር ነው የምናየው  ይህ ግን ሊገባህ ስለማይችል አንብበው የሚረዱ አይጠፉም ብዬ ነው በዝርዝር አየሔድኩበት ያለሁትኝ”” በማለት አንብቦ የመረዳት ደካማ ችሎታቸውን ቁልጭ አድርገው አሳዩን፡፡ እኔ የጠየኩት የኦነግንና የወያኔን ልዩነት እንጅ ወያኔ ኦሮሚያ ክልልና ትግራይ ክልል እያለ የሚጠራቸውን የሀገራችን ክፍሎች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት ልዩነት አይደለም የጠየኩት፡፡

ሲጀመር የጠቀሱት የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር የተሳሳተ ነው፡፡ እናንተ የኦሮሞ ሕዝብ ነው ብላቹህ ከምትጠቅሱት ቁጥር ከ7 እስከ 10 ሚሊዮን (አእላፋት) የሚሆነው በሽግግሩ ወቅት በፈጸማቹህት ዘግናኝና አስደንጋጭ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ከዚያም በኋላ አማራ በመሆናቸው ብቻ በምትፈጽሙባቸው ኢሰብአዊና አሥተዳደራዊ በደሎች እራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ማንነታቸውን ከአማራነት ወደ ኦሮሞነት ለመቀየር ተገደው እራሳቸውን ኦሮሞ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይሄንን አሳምራቹህ ታውቁታላቹህ፡፡ የእናንተ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከዚህ ይጀምራል አስገድጋቹህ ማንነትን ከማስቀየር፡፡

እናንተና ወያኔ አንድም ልዩነት እንደሌላቹህ ማረጋገጥ ይቻላል:-

 1. ወያኔ የታገለውና የሚሠራው ጎሳየ ለሚለው ለትግሬና ቦታየ ነው ለሚለው ግን በከፊል ላልሆነው የሀገራችን ክፍል ነው፡፡ ኦነግም የሚታገለው ብሔረሰቤ ለሚለው ለኦሮሞና ቦታየ ለሚለው ግን ላልሆነው የሀገራችን ክፍል ነው፡፡
 2. ወያኔ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ የአማራን መሬት ወስዷል ተጨማሪም በመውሰድ ለመገንጠል ይፈልጋል፡፡ ኦነግም ምንም እንኳን ዛሬ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተዋልዶ የተዋሐደ ቢሆንም መጀመሪያ የገቡት ግን ይሄንን መሬት የያዙት በወረራ፣ ኦሮሞ ያልነበሩትን አናሳ ጎሳዎች ኦሮሞ በማድረግና የዘርማጥፋት ወንጀሎችን ፈጽመው በመሆኑና በእንዲህ ዓይነት ግፍና ኢፍትሐዊ አሠራር የተያዘን መሬት አብረው ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በማጥፋትና በማስወጣት የራስ ለማድረግ ለመገንጠል ይሠራል፡፡
 3. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለዚህች ሀገር ሥልጣኔ ነጻነት ህልውና ላያበረክቱ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት የሌለና ያበረከቱ ቢሆንም፤ ያለ መላ ሕዝቧ ተሳትፎ ይህች ሀገር ሀገር ትሆን እንዳልነበረ ቢታወቅም ወያኔም ሆነ ኦነግ ግን እራሳቸውን ለዚህች ሀገር ባዕድ ያደርጋሉ፣ እንደጠላት ሀገር ይቆጥሯታል፣ የዚህች ሀገር ታሪክ ባሕል መለያ መገለጫ ማንነት እሴቶች ሁሉ የእነሱም እንደሆነ አያስቡም፣ አያምኑም፣ ላላቸው የጥፋት ተልእኮ ስለማያሠራቸውም በሽዎች ዓመታት የሚቆጠረውን የሀገሪቱን ታሪክ በመቶ ዓመታት ብቻ ይገድባሉ፡፡
 4. ወያኔ ሀገሪቱን ለትግሬ ብቻ አድርጎ የተቀረውን ሕዝብ እንደ ባሪያ አደረገው፡፡ ኦነግና ኦነጋዊያንም ከቻሉ መፈክሮችን ሁሉ በግልጽ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች እያሰሙን እንዳሉት ኢትዮጵያን ለኦሮሞ ለማድረግ እንደሚታገሉ ይሄንን ካልቻሉ ግን እንደሚገነጥሉ አስታውቀውናል፡፡
 5. ሁለቱም ለአማራ ሕዝብ ከባድ ጥላቻ አለባቸው፡፡
 6. ሁለቱም ስንት የተደከመባት ሀገር፤ ለህልውናዋ ለነጻነቷ ስንትና ስንት መሥዋዕትነት ያስከፈለች ሀገር በሚፈጽሙት የጠላት ተግባራቸው የመፈራረሷ ጉዳይ ቅንጣት ታክል አያሳስባቸውም፡፡ አስተሳሰባቸው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነው፡፡
 7. ሁለቱም የሞራል (የቅስም) እና የተያቂነት ጉዳይ አያስጨንቃቸውም አያሳስባቸውም፡፡
 8. ሁለቱም ሐሰትን፣ ክህደትን፣ ውሸትን፣ ፈጠራን ለጥፋት ዓላማቸው ማሳኪያነት ትልቅ አቅማቸው አድርገው ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌም ፋሽስት ጣሊያን “አማሮች ለአገዛዜ እንቅፋቶች ናቸው” ብሎ በማሰቡ አማራን ጠላት አድርጎ በማቅረብ በሌሎቹ ብሔረሰቦች ለማስጠቃት በእውነተኛ ታሪካዊ ኩነት ላይ ተመሥርቶ ፈጠራ ጨምሮ በማውራት በወቅቱም ይህ ሰይጣናዊ ሴራው ሠርቶለት በአማራ ተወላጆች ላይ ወያኔ አሁን ኦሮሚያ ብሎ ከሚጠራው 20,000 (ሃያ ሽህ) አማሮች እንዲሰለቡ ሌሎች እንዲፈናቀሉ እንዲገደሉ ማድረግ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያም 900,000 (ዘጠኝ መቶ ሽህ) አማሮች እንዲፈናቀሉ ከባድ ጥፋት እንዲደርስባቸው ማድረግ መቻሉ ይታወቃል፡፡ ዛሬም ኦነጎች በሽግግሩ ወቅት የፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሸፋፈንና ምክንያታዊ ለማስመሰል ጣሊያን ለጥፋት ዓላማው ፈጥሮ ያወራውንና ምንም ዓይነት መረጃ የሌለውን፤ የጦሩ አዝማች ኦሮሞ (ራስ ጎበና ዳጬ) በሆኑበት ሁኔታ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ጥናትና ምርምር ከዚያ ሠራዊት 99 በመቶው ኦሮሞ በሆነበት ሁኔታ ጣሊያን ፈጥሮ ያወራው ሐሰተኛ ወሬ ይሆናል ይፈጸማል ብሎ ለማሰብም ፈጽሞ በማይቻልበት ሁኔታ ሐሰት መሆኑን እያወቁ የጣሊያንን የጥፋት ፈጣራ ወሬ አንሥተው ለተመሳሳይ የጥፋት ዓላማ ተጠቅመዋል፡፡
 9. ሁለቱም ሩቅ ማለምና መመልከት አይችሉም፡፡
 10. በሚገርምና ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ሁለቱም የሚያስቡትና የሚሠሩት የቱንም ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ቢነገራቸውም የሚገባቸው አይደሉም፡፡ ድንቁርናቸውን አምላኪዎች ናቸው፡፡
 11. ሁለቱም 21ኛው መቶ ክ/ዘንን የሚመጥኑ አይደሉም፡፡ አስተሳሰብ አመለካከታቸው የሰው ልጅ የደረሰበት የሠለጠነ አስተሳሰብ እጅግ ወደ ኋላ የሚመልስ ነው፡፡
 12. የሁለቱም ተፈጥሯዊ ማንነት ለፍትሕ ለዲሞክራሲ (ለመስፍነ ሕዝብ) ለሰብአዊ መብቶች በከበር ዕድል የሚሰጥ የሚፈቅድ የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ ወዘተረፈ.

እናም ወገኖቻችን እባካቹህ አሁንም ደግሜ የማሳስባቹህ ጉዳይ እባካቹህ እልሁን ነውትና ማንንም የማይጠቅመውን የቀደመ አቋም ዓላማቹህን ትታቹህ ጥላቹህ የሠለጠነውንና ሁላችንንም የሚጠቅመውን አቋም ዓላማ አንግባቹህ በዘርና በጎጥ ሳትታጠሩ እንደሰው ልጅና እንደዜጋ በማሰብ የአንድነቱን ኃይል ተቀላቀሉና የወያኔ ቁማር የመጫዎቻ ካርድ ከመሆን እራሳቹህን አውጡ ለዩ፡፡

ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ እንደነገርኳቹህ ሕዝባችን ይሄንን ያህል የወያኔን የማይቻል የግፍ ቀንበር ተሸክሞ በዝምታ እንዲኖር ያደረገው ወያኔ እናንተንና ሌሎች መሰሎቻቹህን መጠቀሚያ በማድረግ የእርስ በእስር የዘር ፍጅት አደጋን በመጋረጥ ይሄ እንዲሆን ፈጽሞ ባለመፈለጉ ነውና የአንድነቱን ኃይል ስተቀላቀሉ ይሄ ሕዝባችንን ከባድ ሥጋት ላይ የጣለው የእርስ በእርስ የዘር ፍጅት ሥጋት ስለሚገፈፍ ስለሚወገድና ሕዝባችን በመተማመን አንድ ስለሚሆን ያለውን አቅም ተጠቅሞ በቀላሉ ወያኔን ለማስወገድ እንዲችል ያደርገዋል፡፡ ወያኔን ማስወገድ እኮ ለሕዝባችን በጣም ቀላል ሥራ ነበር፡፡ እናንተ መሰናክል ሆናቹህበት ነው እንጅ፡፡

ይሄንን ማድረግ ሳትችሉ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርስ በእርስ ፍጅት ሥጋት እያለበት የዐመፅ አማራጭን ተጠቅሞ ወያኔን ለማስወገድ ሊሞክረው አይደለም ሊያስበው አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ቀሪው ሕዝብም በወያኔ የተሰቃየ ቢሆንም ዐመፁ የኦሮሞ ብቻ ሆኖ የቀረው፡፡ እንዲህ ሆኖ እንዲኖር ያደረገው የእናንተና መሰሎቻቹህ ለወያኔ ቁማር መጠቀሚያ መሆናቹህ ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለተያዘበት የወያኔ ወጥመድና በተያዘበት ወጥመድም ሳቢያ ዐምፆ ወያኔን ከማስወገድ ታቅቦ ለተቀበለው ግፍ ሁሉ ተጠያቂዎች ሆናቹህ እንዳትቀሩ ፈጥናቹህ የአንድነቱን ኃይል ተቀላቀሉ፡፡ እባካቹህ! እባካቹህ! እባካቹህ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.