አነጋጋሪው መፅሐፍ – “የኢየሱስ ሕይወት” – ደሳለኝ ሥዩም

Dan-Brown-DaVinciከዚህ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አንድ ገጸ ባህርይ በመውሰድ፣ “ኢየሱስ የሰው ልጅ ስህተቶችን ሁሉ ተሳስቷል-በተቃራኒ ጾታ ፍቅር እስከመውደቅ በመድረስ” በሚል መነሻ የተጻፈው “የዳ ቪንቺ ኮድ” የተሰኘ መጽሐፍ የዓለምን ክርስቲያኖች አስቆጥቶ ነበር፡፡ የዓለም ታላላቅ ቤተክርስቲያኖች እንደ ሮማ ካቶሊክ ያሉቱ በውግዘቱ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ደግሞ መጽሐፉን ደጀ ሰላም ላይ ከማቃጠል ባሻገር ካህናቱ የመልስ ምት የሚሆን መጽሐፍ እስከ ማሰናዳት ደርሰዋል፡፡

እንዲያውም በዚህ ደረጃ አፋጣኝ የተቃውሞ ምላሽ በመስጠት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን የመጀመሪያዋ ሳትሆን አትቀርም፡፡ “የዳ ቪንቺ ኮድ” ወደ አማርኛ ተመልሶ ሲታተም በቤተሰብም ውስጥ ሳይቀር ከፍ ያለ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለምሳሌ መጽሀፉን ያነበበ ልጅ ሳይጠመቅ እቤታቸው ድርሽ እንዳይል የከለከሉ አንድ አባወራ አውቃለሁ፡፡

በዛሬ ዳሰሳዬ ለመቃኘት የፈለግሁት መጽሀፍ ከ153 ዓመታት በፊት በ1863 በፈረንሳይኛ ቋንቋ የታተመ ሲሆን የእንግሊዝኛ ትርጉሙ “The Life of Jesus” በሚል በመላው ዓለም ተሰራጭቷል፡፡ ይሄ እጅግ አወዛጋቢና ተነባቢ የሆነ መጽሐፍ በሚል በሚሊዮኖች ቅጅ ይቸብቸብ እንጂ ለኛ ሀገር አንባቢያን አዲስ ይመስላል፡፡ በእንግሊዝኛም ይሁን በፈረንሳይኛ መጻሕፍትን ማንበብ በተለመደበት በ1960ዎቹ እንኳ እኛ ሀገር ገብቶ ስለመነበቡ መረጃ አላገኘሁም፡፡ ይሁንና በቅርቡ በአንጋፋው ደራሲና ተርጓሚ ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም “የኢየሱስ ህይወት” በሚል በአማርኛ ተተርጉሞ መውጣቱን አውቃለሁ፡፡
ቅኝቴ የሚያተኩረው በዚሁ የሳህለሥላሴ ትርጉም ላይ ሲሆን በተለይ በመጽሐፉ ጭብጥ ላይ ያተኩራል፡፡ ከዚያ በፊት ግን አስገራሚም አወዛጋቢም የነበረውን የደራሲውን ኧርነስት ረና (Ernest Renan) አጭር ታሪክ እንመልከት፡፡

ሰውየው  ለ69 ዓመታት በዚህች ዓለም የቆየው ኧርነስት ረና፤ ከ19ኛው ክፍለዘመን ፈላስፎች ተርታ ይደመራል፡፡ በፈረንጆቹ ጥር ወር ሃያ ስምንተኛ ቀን ላይ በ1823 የተወለደውን ጆሴፍ ኧርነስት ረና፤ በዘመኑ የፈረንሳይ ምርጥ ከነበሩ ምሁራን ጐራ የሚመድቡት ወገኖች አሉ፡፡
በወቅቱ ብሪታኒያ በሚባለው ሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ ግዛት የተወለደው ረና፤ ዋነኛ የትምህርት ዝግጅቱ ጥንታዊ የመካከለኛው ምሥራቅ ቋንቋና ሥልጣኔ ጥናት (ፊሎሎጂ) ይሁን እንጂ ፈላስፋ፣ የታሪክ አዋቂ ብሎም የፖለቲካ ሳይንሱም ውስጥ ሱታፌ የነበረው ሰው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዝነኛ የሆነባቸውን የቀደምት ክርስቲያን ጥናትን ለመስራትና ብሔራዊነትና ብሔራዊ ማንነት የሚል ንድፈ ሐሳብን ለመንደፍ አስችሎታል፡፡
በአሳ አጥማጅ ቤተሰብ ውስጥ የተወለደውና ረና፤ እስከ አምስተኛ ዓመት ዕድሜው ድረስ የእናትና አባቱን የፖለቲካ ሐሳብ ልዩነት ውዝግብ ሲጋት ቢቆይም ወዲያው አባቱን በሞት ተነጥቋል፡፡ እንደትውልድ ቀዬው ማቲዎች፤ እሱም ትምህርቱን የጀመረው በሰፈር የቄስ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ረና ዝምተኛ፣ ታታሪ፣ ታጋሽ፣ ጠንካራና ጠንቃቃ ተማሪ እንደነበር ይነገርለታል፡፡

እ.ኤ.አ በ1840 በጊዜው ዝነኛ የስነመለኮትና ፍልስፍና ውህድ እሳቤ የሆነውን ስኮላስቲዝምን ለማጥናት የፍልስፍና ትምህርት ቤትን ተቀላቅሎ ነበር፡፡ የፍልስፍና ዲግሪውን እንደተቀበለም የእብራይስጥ ቋንቋ መማር ጀመረ፡፡
ይሄኔ ነበር ግማሹ ክፍል ትንቢተ ኢሳያስ፣ ከሁለተኛው (ከሚቀጥለው) ክፍል ትንቢተ ኢሳያስ በአጻጻፍና በጊዜ (ወቅትም) ልዩነት እንዳለው ማመን የጀመረው፡፡ ይሄ ጥርጣሬው ለረዥም ጊዜ አብሮት ቆይቷል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ራሱን እንደ ብጹዕ የካቶሊክ ቄስ ይቆጥር የነበረው ረና፤ “General History of Semitic Language” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1947 ዓ.ም የጀመረው የጥናት ጽሑፉ ረቂቅ በማስተርስ ደረጃ የዩንቨርሲቲ መምህር እንዲሆን አስችሎታል፡፡
በኋላ ደግሞ ዝናም መከራም የጨመረለትን “የኢየሱስ ህይወት” የተሰኘ መጽሐፍ ሊያሳትም በቅቷል፡፡ “ኢየሱስ ራሱን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ የሚፈልግ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም” በሚል መነሻ የተጻፈው ይሄ መጽሐፍ፤ መጀመሪያ የተተረጐመው ወደ እንግሊዝኛ ነበር፡፡

መጽሐፉ ይበልጥ መሰረቱን ያደረገው በዮሐንስ ወንጌል ላይ ነው፡፡ ረና እንደሚለው፤ “ኢየሱስ በምድር ሲመላለስ በነበረ ጊዜ ከያዕቆብ፣ ከዮሐንስና ከጴጥሮስ ጋር በመሆን የመሰረተው ልዩ ቡድን ወይም አንጃ ነበር፡፡ ይሄንንም ወንጌላዊው ዮሐንስ እየደጋገመ ‹ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀመዝሙር› እያለ ራሱን በመጥራቱ፣ ከኢየሱስ ጋር ይበልጥ ምስጢረኛ እንደነበር ይገልጻል”፡፡

መጽሐፉ በሳይንሳዊ የታሪክ አጻጻፍ እንከን የለሽ እንደሆነ የሚመሰክሩለት ወገኖችም አልጠፉም፡፡ እንደነዚህ ወገኖች አረዳድ፤ ይሄ ሥራ ምሁራዊ ነው፡፡ እናም ክርስቶስን እንደ አንድ በታሪክ ውስጥ ያለፈ ግለሰብ በተለይ ደግሞ ክብር ፈላጊ እንደነበረ ታዋቂ ሰው፣ በዚህ ዓይነት የታሪክ አጻጻፍ ቢታወስ ክፋት የለውም ባይ ናቸው፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ ከክርስቲያን አማኞች ጋር ቁርሾ ውስጥ የከተተው፡፡ ይሄም ቁርሾ የረናን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከማስገፈፍ አልፎ ወደ ጀርመን ተሰዶ በጥገኝነት እንዲኖር አስገድዶታል፡፡

ረናን የሚያሞግሱት የመኖራቸውን ያህል እ.ኤ.አ በ1887 የታተመውን “የእስራኤል ታሪክ” የተሰኘ መጽሐፉን እየጠቀሱ፣ ሰውየው ለእምነታዊ አስተሳሰብ ያለውን ጥላቻ ከማንፀባረቅ በቀር ከታሪክ እውነታ ጋር ዝምድናም ሆነ የታሪክ እውቀት የለውም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
ይሄ አወዛጋቢ ሰው በጥቂት ቀናት ህመም እ.ኤ.አ ጥቅምት 2 ቀን 1982 ዓ.ም አርፏል፡፡ እሱ ቢሞትም ግን “የኢየሱስ ህይወት” የሚል መፅሐፉ አሁንም ማወዛገቡን ቀጥሏል፡፡

መጽሐፉ “The Life of Jesus” ከተሰኘው የእንግሊዝኛ ቅጅ የተመለሰው የደራሲ ሳህለሥላሴ የአማርኛ ትርጉም፣ ለኛ ሀገር አንባቢያን እርባና የላቸውም የተባሉ ገጾች ተዘለው የቀረበ ሥራ ነው፡፡ የተርጓሚውን ማስታወሻና አንዳንድ አባሪዎችን ሳይጨምር መጽሐፉ 295 ገጾች አሉት፡፡
ይሄ መጽሐፍ እንደሌላው ዓለም ሁሉ በኢትዮጵያ ክርስቲያኖችም ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል መገመቱ ቀላል ነው፡፡ ለ “የዳ ቬንቺ ኮድ” ምላሽ የጻፉ ካህናት፤ ይሄን በዝምታ ያልፉታል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ተርጓሚው እንደሚሉት፤ በመጽሐፉ ውስጥ ስሜታዊነትንና ቁጣን የሚያፋፍሙ ገለጻዎች በመኖራቸው፣ ነጻ ትርጉምን መርጠው አለዝበው አቅርበውታል፡፡ በእርግጥ የተርጓሚውን ጥንቃቄ በመጽሐፉ ውስጥ በትክክል ማስተዋል ይቻላል፡፡
በነገራችን ላይ ምዕራባዊያኑ እንደተስማሙበት፤ የእኛም ሀገር የታሪክ፣ የእምነትና የፍልስፍና ሰዎች፣ በተለይ ወጣቶቹ መጽሐፉን ትልቅ የውይይት መነሻ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ክርስቲያኖች በኧረነስት ረና መጽሐፍ ላይ የተቃውሞ ሐሳብ ሰነዘሩ እንጂ ሁለት ሺህ ዓመት እድሜ ያለው የክርስትና ሃይማኖታቸው ተናወጠ የሚል ነገር አለማንበቤን ልመሰክር እፈልጋለሁ፡፡ ለማንኛውም ከመጽሐፉ ማጠንጠኛዎች ጥቂቶቹን አለፍፈለፍ እያልን ለማየት ብንሞክር ክፋት የለውም፡፡

“የአዲሱ ነብይ አስተምህሮት በዚህ ጊዜ ወሳኝ ነበር፡፡ ሁላቸውም መለያቸው ታዳጊያዊ ግልጽነትና ቀላል ንጽህና የተላበሰ ተመሳሳይ መንፈስ የነበረው የወንዶችና የሴቶች ስብስብ በእሱ ዙሪያ ተኮልኩሎ መሲሁ አንተ ነህ አለው፡፡ መሲሁ የዳዊት ልጅ መሆን ስለነበረበት እነሱ እንደሚጠበቀው ይሄንን መጠሪያ ሰጡት፤ ከዚያኛው ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ፡፡ በትውልድ ማን እንደሆነ ስለሚታወቅ ትንሽ ሀፍረት ሊያስከትልበት የሚችልበት ቢሆንም፡፡ …”
ይህ የረና ትረካ ክርስቶስ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ “ክርስቶስ በጊዜው መንፈሳዊነትን አጥብቆ የሚፈልግ ፣ በአስተሳሰቡም የመጠቀ፣ በልጅነቱም በትምህርትና በንባብ ያደገ በመሆኑ፣ የእስራኤል ህዝብ ምን እንደሚፈልግ፣ ምን እንደሚጠብቅም በትክክል ተገንዝቦ ስለነበር ታማኞቹን በእሱ ዙሪያ አሰማርቶ፣ የመሲህነትን ስያሜ አገኘ” ይላል ደራሲው፡፡

“ኢየሱስ በወንጌል እንደሚያስተምረው የክርስቲያን ሀገሩ በሰማይ መሆኑ ከስንፍና የሚመነጭ ነው፡፡” የሚለው ፀሐፊው፤ “ሀብታም መንግስተ ሰማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀለዋል” የሚለውን ጥቅስ በመውሰድም መሬት ላይ በሀብታቸው የሚደሰቱቱ በሰማይ የሚኮነኑት ተራቸው ስለሆነ ነው ሲል ይተረጉመዋል፡፡

ድሆች በመሬት ሲኖሩ ስለተራቡና ስለተሰቃዩ በሰማይ ምቾት ማግኘታቸው ኢ-ፍትሀዊ መሆኑን የሚገልፀው የረና መጽሐፍ፤ ሀብታም – ሀብታም ስለሆነ ብቻ መንግስተ ሰማይን ይከለከላል በማለት ያልተፃፈ ይተርካል፡፡ ለዛሬ በዚሁ ይብቃኝ፡፡ ያሰንብተን!