የቡዳ ፖለቲካና የአቶ ግርማ ሰይፉ እይታ – ሽመልስ ወርቅነህ

አቶ ግርማ ሰይፉ ለዶ/ር መራራ “የቡዳ ፖለቲካ እና መቀበል ያቃተው መራራ እውነት” በሚል ርዕስ  የተፃፈውን አነበብኩ፡፡ የዶ/ር መራራን “የኢትዮጲያ ታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ህልሞች” የሚለውን መጽሐፍ ባላነብም ዶ/ር መራራ እንደጸበል መድሀኒት የሚያዙትን የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን   ወደመሀል የመምጣት ፖለቲካውን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስለምከታተለው አዲሱ መፅሐፉቸውም የፀበሉ አካል እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ ከሀገር ቤታችን በተለያዩ ምክንያቶች ወጥተን   ፈቅደንም ሆነ ሳንፈቅድ የኢትዮጲያ ፖለቲካ አካል ለሆንን ወገኖች ግርምት የሚፈጥሩ በርካታ ሁኔታዎችን እየተመለከትን ነው፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ ከማክብራቸው አንድነት ፖርቲ አመራር አባል አንዱ ነበሩ፡፡ ዶ/ር መራራ ለረዥም አመታት ( ኦብኮ) መሪነታቸው በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ባላቸው ተሳተፎ አውቃቸዋለሁ፡፡ በሁለቱ መካከል የዕድሜ ልዩነት ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ ጋር የሚፈጠር የአስተሳሰብ ሁለንተናዊ አመለካከት ልዩነት ቢኖርም በፖለቲካው ግን አንድ ያደርጋቸዋል ብዬ የማስበው ሁለቱም በኢትዮጲያዊነታቸውና በኢትዮጲያ ፍትህ እኩልነት ሰላም እንዲሰፍን ያላቸው አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በሐሜት ደረጃ አዳንዶች ዶ/ር መራራ በብሔረሰብ ድርጅት ስለታቀፉ ወይም ስላቋቋሙ ከኢትዮጲያዊነታቸው ላይ ትንሽ ሸረፍ ለማድረግ ሲሞክሩ ቢታዩም የአቶ ግርማንም በሥርዓቱ ላይ ጠንካራ አቋም የሌላቸው አድርገው የሚሥሉ የፖለቲካ ሰዓሊዎች ባይጠፉም ሁለቱም       ለትግሉ ያበረከቱት አስተዋፅኦ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ዛሬ ሀጊሪቱ ካላት ፖለቲከኞች ውስጥ በአንጋፋነት የመሚደቡ ናቸው፡፡ ይህን በመጠኑ ካልኩ በኋላ ሰሙኑን አቶ ግርማ የዶ/ር መራራ የቡዳ ፖለቲካ በመተቸት የጻፉትና እግረ መንገዳቸውንም በአነድነትና በመድረክ የተፈጠረውን ውዝግብ ሂደት ለማሳየት የሞከሩበትን የዘገየም ቢሆን ብዙ ኢትዮጲያውያንን ተስፋ ያስቆረጠ ፍችን ከድርጅታዊ ስሜት ውጭ ላለነው ወገኖች የተሰጠው አስተያየት በመጠኑም ቢሆን ሳያስገርመን አልቀረም::

በመጀመሪያ ወንድሜ አቶ ግርማ ዶ/ር መራራ ዛሬም የመኤሶን አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው በ  ማለት ኮንነዋቸዋል ::  ለፕሮፈሰር መራራ ለመናገር ሳይሆን  ለኩነኔ ው ግን ማረጋገጫ አልሰጡም በፖለቲካ አሳማኘ የሆኑ ነጥቦችን በማንሳት አቶ ግርማን የማውቃቸው ቢሆንም   እንደ እኔ ግምት ትላንት ግለሰቦች የነበሩበትን የፖለቲካ ድርጅት ስም በመጥራት ኢህአፓ መኤሶን ደርግ ኢሰፓ  ትመስላለህ በማለት ትላንት የተከፈለውን መስዋዕትነት በማሸማቀቂያ ፖለቲካ ለማቅረብ መሞከር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር ብዙ ኢትዮጲያውያን ተስፋ ጥለንበት የነበው አንድነትና  ቀረው መድረክ እንዴት  ሊለያይ  ቻለ የሚለው ጥያቄ በውጭ የምንገኘው ኢትዮጲያውያን የመድረክ ደጋፊዎችም የምናውቀውን ያህል ማለት ተገቢ ይመስለናል፡፡  በመጀመሪያ በግሌ መድረክን ለመደገፍ ያነሳሳኝ የመድረክ ማኒፌስቶ    ሁሉን አሳታፊና በተለያዩ የሀገራችን ፖለቲካ እምብርት  የሆነውን

ጥያቄዎች  ማለትም

የብሄረሰብ ችግሮችን አፈታት

የሉአላዊነት ጥያቄና

የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ላይ  ያላቸው የጋራ አመለካከትና ይህንኑም ለመፍታት

ከጠረጴዛ ዙሪያ ውጪ ምንም መፍተሔ የሌለው በውይይትና በሂደት ሰጥቶ በመቀበል ፖለቲካ ሁሉም አንድነት ፖርቲን እንዲመስሉ ሳይሆን በልዩነት አንድነትን ሊያመጡ የሚችሉ ስብስቦች ናቸው ከሚል ቅን እምነት ነው::  ከዚህም ባሻገር አምባገነኑን ስርዓት ለመጣል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አካል የሆነውን ብሔራዊ መግባባትን እንደ አንድ የመፍትሄ ሃሳብ  አጀንዳው አድርጎ መነሳቱ ነው፡፡ በእርግጥም በተለያዩ ጉዳች ላይ የወሰዷቸው የጋራ አቋሞች ወደዚያ ሂደት የመሩ እንደነበር  ግልጽ ነው::

በዲያስፖራ የምንገኝ በርካታ ኢትዮጲያውያን ይሄን ጅምር ለማበረታታት ያለምንም አደራጅነት ነፃ በሆነ መድረክን ለመደገፍ በራሳችን መሰባሰብ ነበረብን፡፡ በርግጥ በወቅቱ በዲያስፖራው የአንድነት ደጋፊዎች ቁጥር በርካታ ሲሆኑ ቀጥሎ አረና ትግራይ የተሻለ ደጋፊ ያሰው ኃይል የነበረው ነው፡፡ ኦብኮም በየአካባቢው ትንሽ ደጋፎዎች ያሉት ሲሆን በዶ/ር በየነ የሚመራው ድርጅት በቁጥር አነስተኛ ደጋፊ እንዳለው የድርጅቶቹን  ጩኸት በመጮህ የፖለቲካ ስራ በመስራት ሊመዘን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ከሚዲያዎች የሚዲያ ባለቤቶቹ የመድረክ አባል ድርጅቶች አባል ወይም ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች ከፖለቲከኞችም እንደዚሁ ለመድረክ የጋራ ጩኸትን በማሰማት ትልቅ ድጋፍ እንደነበረው ግልጽ ነው፡፡  ወደ ውህደት እንዲሸጋገሩ በዲያስፖራው በኩልም ትልቅ  ግፊት ነበር፡፡ እንዲያውም ለአባል ድርጅቶቹ በግልም ሆነ በጋራ በዲያስፖራው አንድ ወጥ የሆነ የመድረክ ድጋፍ ኮሚቴ እንዲቋቋም ይህም ጊዜን ጉልበትን እውቀትን ለማስተባበር እንደሚረዳ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ በተለይም ዲያስፖራው ትልቅ ድጋፍ በፋይናስ ስለሆነ ለየድርጅቶቹ የተበጣጠሰ ድጋፍ ከማድረግ እንደሚያድን የታመነ ስለነበር ነው ::በመድረክ አብል ድርጅቶችና በአንድነት መካከል የነበረው ሽኩቻ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ ዶ/ር መራራና አቶ ግርማ ሰይፉ ወደውጭ በወጡበት ወቅት ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ :: ደጋፊዎችን በጋራ ከማወያየትና ስብሰባ ከማድረግ ይልቅ እነ መራራ አላሰሩንም ከነሱ ጋር መጎተት አንችልም የሚሉ የአንድነት ደጋፊዎች ጩኸትና አንድነቶች ገንዘብ ስላላቸው ሊጫኑን ይፈልጋሉ የሚለው የሌሎቹ መድረክ አባል ድርጅቶችችበየፊስቡኩና በየዌብ ሳይቱ መታየት ጀመረ እጅግ የሚገርመው ብዙዎቻችን የማንም ድርጅት አባል ሳንሆን መድረክ ይጠናከራል በሚልና የአንዱ ወደኋላ መቅረት ሌላውንም እንዳያዳክም ለአንድነት ለኦብኮም  ለአረናም   የሚውል የገንዘብ ድጋፍ

በተጠየቅን ጊዜ እናደርግ እንደነበረ ነው፡፡ በኋላ ላይ የአንድነት ደጋፊዎች ነን ከሚሉት ውስጥ አንድነትን ከመድረክ በማስወጣት  በወቀቱ  የፓለቲካ ጫጉላውን ያከብር በነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ጋር እንዲዋሃድ ጩኸታቸውን ማሰማት ጀመሩ::

መድረክም ረዥም ጉዞ ተጉዞ ወደተሸለ ደረጃ መምጣት ሲገባውም ጠንካራ ሀይሉ የሆነውን አንድነትን አግጄዋለሁ የሚል መግለጫ አወጣ፡፡ ምንም እንኳን አንድነት ከመድረክ የተለየበት መሠረታዊ የልዩነት ነጥቦች የሉም ባይባልም ትልቁ ምክንያት ግን የአንድት   ደጋፊዎች    አንድነትን ለመምጣት ሁሉም የአንድነት ፓርቲን እንዲመስል   የፈለጉበት ጊዜውን ያልጠበቀና በብሔረሰብ የተደራጁትም የአቅም ማነስ ጉዳይ ወደብሔረሰብ ጉያ እንዲሸጎጡ መሆኑ ነው፡፡  ከድርጅቱ ፕሮግራም ይልቅ አንድነት የሚለው ቃል የሚያሰባሰባቸው በርካታ ኢትዮጲያዊያኖች አሉ፡፡ ችግሩ ለአንዳንድ ወገኖቻችን አንድነትን የጠየቀ ሁሉ በአማራ ፖለቲካ ስብስብ ውስጥ እንዲነከሩ መፈለጉ ነው፡፡ በብሔረሰብ የተደራጁትን በኢትዮጲያዊነታቸው ላይ ጎሰኞች በሚል እንደምናቀርበው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ዶ/ር መራራም ከዚህ ፖለቲካ መጓተት ውጭ ሊሆኑ ያልቻሉትና የአማራና ኦሮሞ ኢሊት ወደመሃል መምጣት የሚለውን ፖለቲካ ለመጫወት የፈለጉት። ዛሬ በርግጥ ትልቁ ገመድ ጉተታ ያለው በአማራው በኦሮሞውና በትግሬው ሊሂቃን መካከል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያለምክንያት ሳይሆን ያለፉት ስርዓቶችን የአሁኑንም ጨምሮ እነዚህ ብሔረሰቦች በፖለቲካው በኢኮኖሚውና በትምህርተ ዘርፍ ጭምር ከሰጣቸው ቦታ የሚመነጭ ነው፡፡ የአማራው የኦሮሞና ወይም የትግሬ ሊሂቃን በኢትዮጲያ ውስጥ የሚኖራቸው የፖለቲካ ተሳትፎና  እንደፈለገ ሕብረተሰቡን ማሽከርከር የሚያቆመው ከአማራነት ከኦሮሞነት  ከትግሬነት ወዘተ   በአጠቃላይም በብሔረሰብ ማሰብ አቁመን  እድገት ብልጽግና ፍትህ ሰላም እኩልነትን ለሰው ልጅ ይገባዋል ከሚል እምነት ስንነሳ ነው፡፡  ማለፍ የማንችለውን የታሪክ ሀቅ ጋር መታገል ሳይሆን በፖለቲካ ጥበብ  ነባራዊ ሁኔታውን ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንዲጉዋዝ መግፋት ነው።ዛሬ  በርካታ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር በጋራ መስራትን መተባበርን አስፈላጊነት ጠዋትና ማታ የማይሰብኩበት ጊዜ የለም። የሚያሳዝነው ግን ለርዥም ጊዜ ታላቅ መስዋእትነት ተከፍሎበት የተሰራውን ህብረት በጥቂት ቀናት ውስጥ እያፈረስን ሌላ መገንባት ባህል እየሆነ መምጣቱ ነው። የፖለቲካ ምሁሮቻችንም የሃይል አሰላለፍ አቅዋም በየሳምንቱ እየተቀያየረ መሰረታዊ መርሆዋችን ጭምር በፖለቲካ ታክቲክ እየደፈጠጥን አንዱንም ሳንሆን እየዋዥቅን እንገኛለን ። በብሄረሰብ ወይም በጎሳ ተደራጅቶ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት እንደማይቻል ካለፉት ልምዶቻችን በሚገባ የተማርን ቢሆንም ከህብረተሰባችን እድገት ማለትም ዛሬም የብሄረሰብ ፖለቲካን የሚሸክም ህብረተሰብ ቁጥር ቀላል አለመሆኑን መረዳቱና ተመጣጣኝ የፖለቲካ ስትራተጂና ታክቲክ መንደፉ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። የብሄረሰብ ፖለቲካ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን የፖለቲካ መስመርና ጥያቄ እየደገፍንና አብርናችሁ እንሞታለን እያለን እየፎከርን በሌላ በኩል ለምን በብሄረሰብ ተደራጁ እያልን የተሰበሰበውን መበተን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። መድረክ በዚህ ረገድ የጀመረው ጉዞ ባይቀጭ ኑሮ ዛረ አምባገነኑን ስራት በጋራ ቆመን በታገልነው ነበር።   መድረክን የደገፍንበት ትልቁ አላማም በሂደት በመነጋገር መመወያየት በመተማመን አብሮ መስዋእትነት በመክፈል የተፈለገውን ሃገራዊ አጀንዳ ወደአለው የፖለቲካ ድርጅት ይቀየራል በሚል እምነት ነበር:: ዛረም በዚህ ሂደት ላይ ያሉና በጋራ ለመስራት የተዘጋጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊያልፉት የማይችሉት የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ነው። በተለይም በሃገር ቤት ያሉና በሰላማዊ መንገድ ትግሉን የተያያዙት ድርጅቶች እየወደቁም እየተነሱም መሪዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸውንም ሂይወት በመስዋእትነት እየገበሩም ህዝቡን ከጊዜ ወደጊዜ ለአምባገነኖች ምቹ ፍራሽ እንዳልሆነላቸው እይተመለከትን ነው። ይህ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን ህዝብን ከማንቃት ከማደራጀት በጋራ ከማታገል የሚመነጭ የታሪክ እውነት ሂደት ነው። ህዝቡ የጎደለው አንድ ነገር ነው በአንድነት ስም ወይም በብሄረሰብ ስም የመደራጀትና ያለመደራጀት ሳይሆን የጠራ የፖለቲካ ግብ ያለውና የሃገሪቱን አንድነት የህዝቦችን እኩልነት የዲሞክራሲና የፍትህ ስራትን ለመመስረት የሚችል በራሱ ድርጅታዊ ህይዎት አርአያ የሆነ የፖለቲካ ሃይል ነው። ከሁሉም በላይ የሃገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ሆደ ሰፊና ከሽፍጥ የጸዳ የፖለቲካ አሰላለፍ ነው። ሲሞቅ ብሄርተኛ ሲቀዘቅዝ ጎሰኛ በቲዮሪ አንድነትን ሰባኪ በተግባር አንድነትን ሸርሻሪ የሰላማዊ ትግሉ  ሲያይል ሰላማዊ   የጦርነት አታሞ ሲመታ አካኪ ዘራፍ ባይ በሞላበት የፖለቲካ ጉዞ አትራፊው በስልጣን ላይ ያለውና ሃገሪቱን በአጥንትዋ እያስቀረ ያለው የጥቂት ፋሽስታዊ መንገድ አራማጆችና ጸረ ኢትዮጵያ አቅዋም ያላቸው ጠላቶቻችን ናቸው። ባለፈው የፖለቲካ ድርጅቶች የእርስ በርስ መናቆርና አልያም ጠብቀኝ ነጻ ላወጣህ ነው ከሚል ደረቅ ፕሮፓጋንዳ ተላቀን አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድን ይጠይቃል ::

ወንድሜ አቶ ግርማ ሰዪፉ ከአንድነት መፍረስ በሁዋላ  ህዝቡ የዚህ አይነት የፖለቲካ ድርጅት እንደሚያስፈልገው የጠቆሙበት ጊዘ እንዳለ አስታውሳለሁ። በየትም ይምጣ በየትም በታሪክ አጋጣሚና በሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተፈጠሩትን የብሄረሰብ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያገል ወይም የአንድነት የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያቀጭጭ የፖለቲካ ስብስብ አሁን ተነስተን በአንዴ ልንገነባው የምንችልበት ሁኔታ ግን ያለ አይመስለኘም። መፍትሄው የመድረክን ሰጥቶ የመቀበልና ብሄራዊ መግባባትን ያማከለ አስተሳሰብ በሂደትም የማይፈለገውን አስተሳሰብ የሚያስወግድ እስትራተጂ ሊቀየስ ይገባል።

 

gishag70@yahoo.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.