አቶ ታየ፥ እባክህ አሁንም እንደ ሌላው ጊዜ ተነሣ – ጌታቸው ኃይሌ

 

Taye-Reta-768x449 (1)
አቶ ታዬ ረታ

“ሞት ሁል ጊዜ እንግዳ ነው” ይባላል። ለአቶ ታየ ግን እንግዳ አልነበረም። ስልክ ስንደዋወል ጨዋታችንን የምንጀምረው “ትናንት ሞቼ ተነሣሁ” ብሎኝ ነው። እሱ ካልነገረኝም፥ “ዛሬ አልሞትክም ነበር ወይ” ብየ እጠይቀው ነበር። እንደሰማሁት፥ አሁንም ወደዘላለማዊ ዓለም የሄደው ከሞተበት ተነሥቶ አጠገቡ ለመገኘት ዕድል ያገኙትን ተሰናብቶ ነው። አቶ ታየ፤ እባክህ አሁንም እንደ ሌላው ጊዜ ተነሣ። ሌላው ቢቀር የቱን ያህል ሕዝብ ከምን ያህል ሐዘን ላይ እንደጣልከው አይተህ አንቀላፋ።

አቶ ታየ የሀገር ቅርስ ስለነበረ፥ የሱ ከዚህ ዓለም መለየት የሚያሳዝነው የቅርብ ዘመዶቹን ብቻ አይደለም። የሚፈሰው ዕንባ መሬት ያረጥባል። ዜናው አንጀት ያላውሳል፤ ልብ ያደክማል፤ የአእሞሮን በትክክል የማሰብ ችሎታ ያሳንሳል፤ እጅ እግር ይዝላሉ። የሐዘን እንጉርጉሮ ይጐርፍለታል። ድርሰት የመድረስ  ችሎታ የሌለው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቆጭ ይታያል። እንደ አቶ ታየ ያለ የታሪክ ሰው ሲሞት ስሕተቶች ቢኖሩት አብረው ይቀበሩና አስተዋፅኦዎቹ ሲያብቡ ይኖራሉ። አቶ ታየ ከሙታኑም ከሕያዋኑም ጋር አብሮ የሚኖር የታሪክ ሰው ነው።

አቶ ታየ አቻ ጓደኛየ ስለነበረ የሄደው በእኔና በሱ መካከል ያለውን የጓደኞች የውይይት ምዕራፍ ዘግቶ ነው። ከእሱ ጋር የማወራቸውን ጨዋታዎችና ቀልዶች  ከማንም ሌላ ሰው ፊት አላነሣቸውም። ጥንት “የካምፖ ሎጆ” ጓደኞች ነበርን። ደርግ ማስመሰል እንኳ ስለማያውቅ ሳይሳካልን  ቀረ እንጂ፥ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት እንደወደቀ ፓርቲ ልናቋቁም ከታየ ጋር አምስት ሆነን በሳምን አንድ ቀን አንዳችን ቤት እየተገናኘን እንወያይ ነበር።

አቶ ታየ ሁል ጊዜ የተሻለ ዘመን እንደሚመጣ ስለሚያምን፥ ምንም ነገር የማያስደነግጠው ጀግና ነበረ። አንዳንድ በሕይወቱ የደረሱበትን አስጊ ነገሮች ሲያጫውተኝ፥ “ይኸ ነገር በእኔ ላይ ደርሶ ቢሆን የምይዘውና የምጥለው ይጠፋኝ ነበር” ስለው ይሥቅ ነበር።  አቶ ታየ ያረፈው የማረፍ ፍርሀትና ሥጋት ሳይነኩት ነው።

እንዳየሁት አንዱ የአቶ ታየ የብርታት ምንጭ ከባለቤቱ፥ ከልጆቹና ከእኅቶቹ የሚደርሰው ወሰን አልባ ፍቅር ነው። አጠገቡ ላሉ ኢትዮጵያውያን ክቡር አቶ ታየ እና ጋሸ ታየ ሲሆን፥ ለእኅቶቹ ጋሽዬ ነበር።ከአቶ ታየ ጋር ጥቂት ጊዜ አብሮ የሚቆይ ሰው ታሪክ ተምሮ የሕይወት ምሥጢር ተገልጾለት ይሄዳል።   አሁን እንግዴህ ያለ ታየ መኖርን ልንማር ነው። ትምህርቱ እንዲስማማን አምላካችንን እንለምነዋለን።

አቶ ታየ ንጹሕ ሕይወት ስለ ኖረ፤  ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፥ “አምላክ ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቦና ያልታሰበውን ቅዱስ ስሙን ለሚወዱ ያዘገጀውን” ያውርስልን። ከአባቶቻችን ከአብርሃም፥ ከተክለ ሃይማኖት፥ ከኢየሱስ ሞአ፥ ከኤዎስጣቴዎስ ጋራ ለዘላለም ያኑርልን።

ሐዘንተኞች ሁሉ፥ በተለይም ቤተ ሰቦቹ፥ ባለቤቱ፥ ልጆቹና እኅቶቹ እግዚአብሔር ያጽናችሁ።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.