ጉድ እኮ ነው! – አንዱዓለም ተፈራ (የእስከመቼ አዘጋጅ)

ሐሙስ፣ ጥር ፲ ፪ ቀን፣ ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት
በዚሁ በሳተናው ገጽ፤ የተስፋዬ ገብረአብን፣ የግርማ ካሳን እና የአምሳሉ ገብረኪዳንን ጽሑፍ አነበብኩ። ያነበብኩበት ምክንያት ግልጽ ነው። አንድ ወዳጄ አንብበው ስላለኝ ነበ። በተጨማሪ ደግሞ በተደጋጋሚ በአንድ ርዕስ ላይ ልውውጥ ሲደረግ፤ እኔን ቀልቤን ሳበው። እናም አነበብኩ።

ተስፋዬ ገብረአብ፤ ምንም እንኳ ለኢትዮጵያዊያን አንድነትና ሰላም ቀና አመለካከት የለውም ብዬ አሁንም ባስብም፤ ጥቂት ቁም ነገሮችን ከመሰሪ ተንኮሉ ጋር ደርቶ አቅርቧል። እኒህ ጥቂት ያልኳቸው ቁም ነገሮቹ ሊታዩ የሚገባቸው ስለሆነ፤ እሱ ለኛ ነጋሪ ሆኖ መቅረቡ፤ ትኩረቱ ደርቶ ላቀረባቸው ነገሮቹ ነው ባይ ነኝ። ሆኖም አነበብኩት።

አቶ ግርማ ካሳ ያቀረበው የራሱን አመለካከትና ስለ ተስፋዬ ገብረአብ ጽሑፍ ነበር። የተስፋዬን ጽሑፍ በመተንተን ሂደቱን አሳይቶበታል።

የሠዓሊ አምሳሉ ግ/ኪዳንን ጽሑፍ ጓጉቼ ነበር ያነበብኩት። የግርማ ካሳን ወያኔነት ላውቅ በመቸኮል፤ ሁለቱን ቀድሜ ሳነብ በመጋለብ ነበር። ታዲያ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆኖ አገኘሁት። ምነው ሠዓሊ አምሳሉ! ሊጽፉ የተነሱበት ግርማ ካሳ ለተስፋዬ ገብረአብ የጻፉትን በሚመለከት አልነበረም? ታዲያ ምነው ረሱትና ሌላ ቦታ ገቡ? ከዚህ በፊት ግርማ ካሳ ለጻፈው መልስ መሥጠት ከፈለጉ፤ ለምን በዚያ ርዕስ አላደረጉትም ነበር?

እዚህ ላይ ሁለት አጠቃላይ ችግሮቻችንን በሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን ጽሑፍ አነበብኩ። የመጀመሪያው፤ ማንኛውንም የማንወደውን ጽሑፍ ወያኔ ብሎ መለተሙ ነው። ያሳዝናል። ግለሰቦች ሃሳባቸውን በሚገልጹበት ጊዜኅ አስቀድመን ወያኔ በማለት፤ ግለሰቡንና ያቀረበውን ጽሑፍ አላትሞ መምታት! የደካማ ሰው ግንዛቤ።

ሁለተኛው ደግሞ፤ ፍጹም ግንኙነት በሌላቸው ሁለት ጽሑፎች መካከል፤ የሚፈልጉትን እየመረጡ እንደ አንድ አድርጎ ማቅረብ ነው። ለምን? አሁንም የደካማ ሰው ግንዛቤ። ሃሳብን ከጸሐፊው ጋር የምናያይዝበት ወቅት አለ። ለምሳሌ ተስፋዬ ገብረአብን በሚመለከት፤ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ አማራንና ኦሮሞን ለማጋጨት የደረሰው መጽሐፍ      ቋሚ ነቀርሳ ነው። እናም ሰውየውን ከዚህ ጽሑፍ አውጥቶ ለይቶ ማስቀመጥ፤ በተለይ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ከባድ ነው። እናም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሚጽፈውን፤ ከዚያ አመለካከቱ አንጥሮ ማውጣት እኔን ቸግሮኛል። በተለይም ኤርትራ ነኝ ብሎ ከወገነ ወዲህ፤ ይሄን ግለሰብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በሀገራችን ጉዳይ ቀና አመለካከት ኖሮት ጽሑፍን የማነብለት፤ አፍንጫየን ይዤ ነው።

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን በግርማ ካሳ ላይ የጻፉት አሳዝኖኛል። ግርማ ካሳ ትጥቅ ትግሉን አይደግፍም። ታዲያ ይሄ ወያኔ ያደርገዋል። ከሆነማ እኔንም ሁለት በለኝ። የኢሳያስ አፈወርቂን ተግባርነ ተንኮል ፈጽሜ ከልቤ አላወጣውም። ያ ብቻ አይደለም፤ በአሁኑ የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ፤ የትጥቅ ትግል አደገኛ ነው። በዚህ አመለካከቴ ወያኔ የምትለኝ ከሆነ፤ ይቅናህ።

ወደ ቁም ነገሩ ለመመለስ ይህል፤ ግርማ ካሳ ዶክተር መሳይ ከበደ የጻፉትን በመደገፍ አቅርቧል። በደንብ አንብቦት ከሆነ፤ ዶክተር መሳይ ከበደ እንደ ተስፋዬ ገብረአብ ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያላቸው። በኢትዮጵያዊነት ጉዳዮችን ከመመልከትና ትግሉ አንድነት እንዲይዝ ከመጣር ይልቅ፤ ሌሎች የኦሮሞዎችን እንቅስቃሴ ይደግፉ ነው የሚሉት ሁለቱም። ኢትዮጵያዊያን ግን፤ ትግሉ በኢትዮጵያዊያንና በገዥው ቡድን መካከል ነው። እያንዳንዱ ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ በመሆኑ፤ በአንድነት የምንነሳበት በመሆኑ፤ ከፋፋይ የሆኑና የኦሮሞ ጥያቄ፤ የሙስሊሞች ጥያቄ የምንለውን እናቁም። እዚህ ላይ ጠላታችን ገዥው ቡድን እንጂ፤ በትግሉ ዙሪያ የተሰባሰብነው እስር በርሳችን አይደለም። የሃሳብ ልዩነት ጠላትነትን ግድ አይልም። የምንለያይበት ከምንስማማበት አንጻር ሲታይ ኢምንት ነው። አሁን ሀገር አድን ላይ ነው ያለነው። አሁን እኔ ልግዛ፣ እኔ ልግዛ፣ እያሉ በድርጅቶቻቸው ዙሪያ ብቻ ተጠምደው፤ ሀገራዊ ጉዳዩን ከሌሎቹ ጋር አብሮ በመፍታት ላይ አለማተኮራቸው ሊያሳስበን ይገባል።

እናም   “ወያኔው ግርማ ካሳ ሆይ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው” የተሳሰተና አስተማሪ ያልሆነ ጽሑፍ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.