ሕወሃቶች ፎቅ ይሰራሉ ብአዴኖች ሎተሪ ይሸጣሉ – ግርማ ካሳ

Woyaneከኢትዮጵያ በቅርብ ከመጣ ከአንድ ወዳጄ ጋር አወራን። ከጥቂት ወራት በፊት ብአዴን በባህር ዳር ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ፣ የተገኘ ። በስብሰባው ከፍተኛ ጭቅጭቅ እንደነበረ ነገረኝ። ከዚህ ወዳጄ ባገኙሁት መረጃ፣ በተለይም በፓርቲው መካከለኛና ታች ባሉ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ በሕወሃት ላይ ከፍተኛ ተቃዉሞ ተሰምቷል። “በኢሕአዴግ ዉስጥ የተጠቀሙት ህወሃቶች ናቸው እንጂ ሌላው አይደለም” የሚል ከፍተኛ ምሬትና ብሶት ቀርቧል። “በሁሉም ነገር፣ ሃላፊዎቹ ፣ ወሳኞች ቀዳሚዎቹ እነርሱ ናቸው ። ለምድንን ነው ይሄ የሚሆነው ?” የሚል ጥያቄ ቀርቧል። “እነርሱ ባለፎቅ እኛ ሎተሪ ሻጭ ነው የሆንነው “ ሲሉ ነበር።

እንደሚታወቀው ኦህዴድ አምጿል። የኦህዴድ አባላትና ካድሬዎች ናቸው፣ የመንግስትን መዋቅርን በመጠቀም ፣ ህዝቡን በማደራጀት ከነጃዋር ጋር በቅንጅት በመስራት፣ ላለፉት ሁለት ወራት ተቃዎሞ እንዲታይ ምክንያት የሆኑት።

ወደ ድሃዴን(የደቡብ ሕዝቦችች ደርጅት) ከመጣን አንደኛ እርስ በርስ ፣ ሕወሃት ለርሱ እንዲመቻቸው ብሎ፣ ከፋፍሏቸዋል። ለምስሌ በወላይታና በሲዳማ የደሕዴን አባላት መካከል ችግር አለ። ሁለተኛ በድሃዴን ተራው አባላት አካባቢም ፣ ባለው ሁኔታ ደስተኛ ባይሆኑም፣ ብዙም በኦህዴድና በብአዴን እንዳለው አይነት ማጉረምረም አይሰማባቸውም። ምናልባት የኛ ሰው ነው ጠቅላይ ሚኒስተር የሆነው ከሚልም ሊሆን ይችላል።

ለጊዜው ድሃዴንን ወደ ጎን በማድረግ፣ ብአዴን እና ኦህደድ ግንባር ቢፈጥሩ የሕወሃትን የበላይነት በማስቆም የስርዓት ለዉጥ ማምጣት የሚቻልበትን ትንሽ ድፍረት ከተገኘ ቀላል መንገድ ለማሳየት ልሞክር። ፓርላማው በ ቮት ኦፍ ኮንፊደንስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማንሳት ይችላል። በፓርላማው ብአዴን እና ኦህዴድ በጋራ ከ547 መቀመጫዎች ከ313 እስከ 339 የሚሆነውንን ይቆጣጠራሉ።(ከ60% እስከ 71%) ሁለቱ ድርጅቶች የሚገናኙበትን እና አብረው ስትራቴጂያዝ ማድርግ የሚችሉበት መንገድ ቢፈለግ፣ ብዙ ሥራ መስራት የሚቻል መሰለኝ። ጥያቄው እንግዲህ እንዴት የሚለው ነው።

እነ ጃዋር ሞሀመድና አንዳንድ የኦሮሞ አክራሪዎች፣ እንዲሁም እንደ ተስፋዬ ገበረአብ ያሉ በሞጋሳ ኦሮሞ ሆነናል የሚሉ፣ ላለፉት 2 ወራትት የተጀመረው የኦሮሞ እንቅስቃሴ በኦሮሞዎች ትግል ብቻ ከድል እናደርሰዋለን የሚል እምነት ያላቸው ይመስላል። ይህ በጣም የተሳሳተና ጎጂ አመለካከት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ጋር የተሳሰረ ነው። ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ እንዳሉት ኦሮሞ ግንድ ነው። ኦሮሞን ከሌላው ነጥሎ ማየት በራሱ ጸረ-ኦሮሞነት ነው። ይሄ አንዱ ነጥብ ነው።

አንድ ሰላማዊ ትግል ብዙ ህዝብ የሚኖርባቸዉን ትላልቅ ከተሞች ሳያካትት እንዴት ነው ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለው ? አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ጂማ፣ ሻሸመኔ በመሳሰሉት ከተሞች ሕዝቡን ማቀፍና ማንቀሳቀስ ካልተቻለ እንዴት ነው አገዛዙ ትንሽ ከአቋሙ ፈቀቅ እንዲል የሚገደደው ? የነጃዋር ፖለቲካ አሮጋንትና ለበለጠ ጥፋት፣ ለትልቅ ክስረት የሚዳርግ ፖለቲካ ነው። ኦሮሞ፣ አማራ መባባሉ ቀርቶ በጋራ ለመብት፣ ለፍትህ. ለመሬት ባለቤትነት ከመታገል ዉጭ ሌላ የተሻለ መፍትሄ አይኖርም።

ለዚህም ነው፣ የኦህዴድ እና የብአዴን አባላት እርስ በርስ እየተገናኙ ራሳቸውን አጠናክረው መዉጣት ያለባቸው። ሁለቱ አብረው ቢሆኑ አንደኛ ድሃዴንን ሊቀላቀላቸዉም ይችላል። ሁለተኛ ከዚህ በፊት ከሕወሃት ጋር በመሆናቸው የተቀየማቸው ሕዝብ ይታረቃቸዋል፤ ሶስተኛ ሙሉ ለሙሉ ሕገ መንግስቱ ይፈቅድላቸዋል።

በመጨረሻ አንድ ነገር ብዬ ላቆም። በርግጠኝነት ነው የምለው። በኢሕአዴግ ዉስጥ የበላይ ብአዴን ወይም ኦህዴድ ወይ ሌላ ደርጅት ቢሆን ኖሮ፣ ህወሃቶች አሁን ብአዴኖችና ኦህዴዶች እንዲያደርጉ የምንጠይቀዉን ከማድረግ በጭራሽ ወደኋላ የሚሉ አይደለም። የሚፈልጉትን ከማግኘት፣ አላማቸውን ከማሳካት አይቆጠቡም። ይሉኝታ ብሎ ነገር እነርሱ ጋር የለም። ላመኑበት ነገር ቆራጥ ናቸው። ብአዴን እና ኦህዴዶች በድፍረትና በቅርጠኝነት አኳያ፣ ህወሃት ያለው አንድ አሥረኛ እንኳን ቢኖራቸው ነገሩ አበቃለት ነበር።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ኦህዴዶች “አምጸዋል” ።ዉስጥ ዉስጡን የተደራጁ ይመስላል። በቀላሉ ሕወሃት ገፍቶ ያስወግዳቸዋል ብዬ አላስብም። ብአዴኖች ዉስጥ ከላይ እንደጠቀስኩት ትልቅ ብሶት አለ። ብአዴኖችን reach out በማድረግ፣ ያላቸዉን አቅምና ጉልበት እንዲጠቀሙ ማነጋገር፣ ሎቢ ማድረግ፣ ማበረታትታት ያስፈለግል። በዚህ መልኩ ለዉጥ ከራሱ ከኢሕአዴግ ውስጥ ፣ ሰላማዊ፣ ሕገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ ቢመጣ በጣም የተሻለ ነው የሚሆነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.