የአቶ ግርማ ካሳ  #ቅዠት$  – ስንታየሁ በሱፈቃድ 

የተወሰኑ ድረ ገጾችን አለፍ አልፍ እያልኩ ባነብም  ልምድ ማጣቱ ይሁን የግዜ እጥረቱ ለእኔም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት መጻፉ አይሆንልኝም፡፡ አንዳንድ ጽሁፎች እየገፋፉኝ ለመጻፍ ብሞክርም ተሳክቶልኝ ለንባብ ማብቃት አልቻልኩም፡፡

ዛሬ ግን  ግርማ ካሳ የሚባሉ አይደለም ስራቸው ህይወታቸው ራሱ በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ መጻፍ ብቻ የሚመስል ሰው በየቀኑ የሚጽፉዋቸውን  ርስ በርሳቸው የሚቃረኑ የቅዠት ጽሁፎች እያነበብኩ በዝምታ መቀጠል አልተቻለኝምና ግድቡን ጥሼ ይህችን  አስተያየት ለመጻፍ በቃሁ፡፡  ለዚህም ምስጋና ሳይገባቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ብዬ ነበር እመክራለሁ የሚሉ ከአቶ ግርማ ጽሁፍ ውስጥ የማይጠፉ ቃላት  የአቶ ግርማ ካሳን ሁሉንም አውቃለሁ ከእኔ በላይ ባይነት ያጋልጣሉ፡፡ ነገር ግን በቅዠት አለም ውስጥ ሆነው በስሜት አልያም በይፋ ባልተገለጸ ፍላጎት እየተነዱ  በቀን በቀን ከመጻፍ ውጪ ቢያንስ ባለፉት ሀያ አመታት በኢትዮጵያ ፖለተካ ውስጥ ይሄነው ተብሎ የሚጠቅሱት ለአውቃለሁ ባይነት የሚያበቃ የተግባር ተሳትፎ አልነበራቸውም፣ የላቸውም፡፡

የአቶ ግርማን የቀን ተቀን የቅዠት ጽሁፍ አስመልክቶ ብዙ ሰዎች ለአቶ ግርማ  ምክር ለግሰዋል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የሚሰድቡቸውም ወያኔ ብለው የሚፈርጁዋቸውም አሉ፡፡እነዚህ ጸያፍ ተግባራት የማይደገፉ ብቻ ሳይሆን የሚወገዙም ናቸው፡፡ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት ድብቅ ዓላማና ፍላጎት አለ ከተባለም በማስረጃ ማጋለጥ እንጂ ስድብ ዘለፋና ፍረጃ አይገባም ፣ የጨዋ ተግባርም አይደለም፡፡ አቶ ግርማ ግን  ለራሳቸው የሰጡት ቦታ በፈጠረባቸው መታበይ  ሁሉን ጆሮ ዳባ ብለው አንዳሉ አሉ፡፡

ፕ/ር ብርሀኑ ከኤርትራ ወደ አሜሪካ አቅንተው በአንድ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር አድናቆታቸውን የገለጹት አቶ ግርማ በማግስቱ ቅዠታቸው አገርሽቶ ከሁለት ኣመት በፊት  የመክርኳችሁን ተግባራዊ አላደረጋችሁም ብለው  መሬት ጠብ የማይለው  ምክራቸው ተግባራዊ ባለመሆኑ ወቅሰው  ጽፈዋል፡፡ ለዚህች ሀገር የሚበጀው ትክክለኛው መንገድ ርሳቸው የሚሉት ብቻ አንደሆነ  የሚነግሩን  አቶ ግርማ   ትክክል የሚሉትን  በበቂ ጥናት ላይ ተመስርተውና  በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፈው  የማያቀርቡ በመሆናቸው እንኳን አንባቢው ሊቀበለው ቀርቶ ራሳቸውም የሚሉትን የሚያውቁት አይመስልም፡፡  ይህም በመሆኑ በአንድ ጽሁፋቸው ሳይቀር  ሀሳባቸው ርስ በርሱ ይጋጫል፡፡ ይህንንም ክቅርቡ ጽሁፋቸው ከአንዱ መመልከት ይቻላል፡፡

በሰላማዊው ትግል ትልቅ ንቅናቄ የመፍጠር አቅም የነበራቸው መሪ፣ ከአረመኔው ኢሳያስ ጋር በመቆራኘት ከብዙ ደጋፊዎቻቸው ጋር ተጋጩ። ራሳቸውን አሳነሱ።ሆኖም ዶር ብርሃኑ ካለፉት ስህተቶቻቸው ተምረው፣ በጥበብ ከተንቀሳቀሱ የቅንጅቱ ዶር ብርሃኑ ነጋ የማይመለሱበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ከዚህ የአቶ ግርማ የቅዠት ጽሁፍ  ብዙ ማለት ቢቻልም የነገር ብዛቱ ሳይሆን እውነትነቱ ነውና ጥቂት ብቻ  ልበል፡፡

ዶ/ር ብርሀኑ ሀገር ውስጥ ገብተው ከመሰል የሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበርን በመመስረት ያከናወኑትን ተግባር የሚያውቅ፤ በምርጫ 97 የነበራቸውን ሚና የማይዘነጋ፣ በእስር ቤት ሆነው የጻፉትን መጽሀፍ ያነበበ በጥቅሉ አንደጋሪ ፈረስ የፊት የፊቱን ብቻ ሳይሆን መለስ ብሎ ማያት የሚያስችል አንገት ያለው ሰው  ዶ.ር ብርሀኑን የህዝብ ንቃናቄ በመፍጠር ለሀገር በመስራት ብሎም በሰላማዊ ትግል ሊወቅሳቸው አይችልም፡፡ደፋሩ አቶ ግርማ ግን እያደረጉት ነው፡፡

አቶ ግርማ ዶ/ር ብርሀኑን ከብዙ ደጋፊዎቻቸው ጋር ተጋጩ  ራሳቸውን አሳነሱ ሲሉ ምንም ማስረጃ አላቀረቡምና በቅዠት በጥላቻና በቅናት  የሚጽፉ መሆናቸውን ከማሳየት ባለፈ ተአማኒነት አይገኙም፡፡  ለነገሩ አቶ ግርማ ለራሳቸው የሰጡት ግምት አበው ልቤ አደገና አለ ቁመቴ አላስገባ አለኝ የገዛ ቤቴ ይሉት አይነት በመሆኑ ርሳቸው የጠሉትን ሰው  ሌላው ሰው ሁሉ የሚጠላው  አድርገው ነው የሚያዩት፡፡ የሚገርመው ግን ይህ አይደለም፣ እዛው ጽሁፋቸው ላይ ብዙዎች ሕይወታቸዉን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ኤርትራ ሄደዋል ይላሉ፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ደጋፊ ከሌላቸው  ርሳቸው የሚመሩት ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ብዙዎች አንዴት ይሄዳሉ; አቶ ግርማ እነርሱንም አላዊቂ ብለው ይፈርጁዋቸው በጥፋኝነትም ይከሱዋቸው ይሆን ;  ካለፉ ስህተቶቻቸው ተምረው የሚለው አገላለጽም ከእኔ በቀር አዋቂ እኔ ከምለው ውጪ ትክክል የሚባል ነገር የለም የሚል አንባገነናዊ አስተሳሰብ ነው፡፡እንዲያም ሲል ትምክህተኝነት፡፡

በፕሮፖጋንዳ ከሚነገረው ዉጭ በተጨባጭ በትጥቅ ትግሉ ዘርፍ የታየ ውጤት የለም። አንድ ነጻ የወጣ ቀበሌ ወይንም ወረዳ እንዳለ አልሰማንም። ብዙዎች ሕይወታቸዉን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ኤርትራ ሄደዋል። ዉትድርና እየሰለጠኑ እንደሆነ፣ ተመረቁ ሲባልም እንሰማለን። የተለያዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎችንም እናያለን። ግን በተግባርና በተጨባጭ ግን የታየ ነገር የለም።

የሁሉ ነገር አዋቂ ነኝ የሚሉት ነገር ግን ምንም እንደማያውቁ በብእራቸው የሚጋለጡት አቶ ግርማ የትጥቅ ትግል ካፌ ተቀምጦ ማኪያቶ አንደመጨለጥ ይመስላቸዋል፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአንድ ወገን የትጥቅ ትግልን እቃወማለሁ እያሉ በሌላ በኩል ለምን በቶሎ ጦርነቱን አትጀምሩትም  በማለት በሌሎች መስዋዕትነት ርሳቸው የሚያልሙትን ለማግኘት ሲጎመዡ ይታያሉ፡፡

ምልመላና ሥልጠና ስራ ሆኖ ያልታያቸውና አንድ ቀበሌ ተያዘ የሚል ዜና ባለመስማታቸው ትግሉንና ታጋዮችን የሚያናንቁት አቶ ግርማ በዛው ጽሁፋቸው “ሸንጎ፣ የብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ  በማለት  ሲያደንቁ ይታያሉ፡፡ አቶ ግርማ እውነት ማለት የርሳቸው ቅዠት ሆናባቸው በመቸገራቸው እንጂ  እዚህ ሀገር ቤት ፕ/ር ብርሀኑም ሆኑ ድርጅታቸው በደንብ ይታወቃሉ፡፡ አረ በመላው ዓለም ማለት ይቻላላ፡፡ ወያኔም ባደናቀፈው ቁጥር የሚጠራው እነርሱን ነው፡፡ የጠቀሱዋቸው ድርጅቶች ምን ያህል እንደሚታወቁ እኔ አላውቅም፣አቶ ግርማ ይናገሩ፡፡ እነ ፕ/ር ብርሀኑ በርስዎ ምስክርነት ምልመላ ስልጠና እያካሄዱ ነው  ይህም ማለት እየሰሩ ነው እየተዘጋጁ ነው ማለት ነው፡፡ እነርሱን ለማናናቅ ሲሉ አድናቆትዎን የቸሩዋቸው  ድርጅቶች  ለመደነቅ የሚያበቃ ምን ሰሩ ምንስ እየሰሩ ነው; ወይንስ ቅዠት የወለደው አድናቆት ነው፡፡

ሀሳባቸው ሀራምባና ቆቦ የሚረግጠው አቶ ግርማ   በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ህዝቡ ነፍጥ አንስቶ የተነሳበት ሁኔታ አለ። በወልቃይት ጠገዴ፣ በአርማጭሆ፣ ጭላጋ በመሳሰሉት ቦታዎች በቴፒ ፣ በጋምቤላ ..ግፍና ጭቆና የመረረው ወገናችን የትጥቅ ትግል የጀመረበት ሁኔታ አለ። ይሉና ብዙም ሳይቆዩ በአሁኑ ወቅት ብቸኛው አማራጭ እኛው እራሳችን የምናደርገዉ የተባበረ ሰላማዊ ትግል ነዉ ይላሉ፡፡ ይህ አገላለጽ ርስ በርሱ የሚጋጭ  ብቻ ሳይሆን ራሳቸው  ጭቆና የመረረው ወገናችን  ጀመረው ያሉትን ትግል የሚያጣጥል ነው፡፡ይህ ነው እንግዲህ የቅዠት ሀሳብ ማለት፡፡

አቶ ግርማ እኛ ሲሉ ራሳቸውን አንደዋንኛ ሰላማዊ ታጋይ እየቆጠሩ ነው፡፡ ከምር ሰላማዊ ታጋይ ከሆኑ ወያኔ በምንም ሁኔታ በክፉ የሚፈልግዎት አይደሉምና ደግሞስ ምን አድርገውት ( ይህ ውሸት ከሆነ በምን ምክንያት ክፉ አንደሚያስብብዎት ይናገሩና እኔ ይቅርታ እጠይቅዎታለሁ)  ለምን ሀገር ቤት መጥተው ፓርቲ መስርተው በተግባር አናይዎትም፡፡ በሰላማዊ ታጋዮች ተስፋ ብንቆርጥም ርስዎን በአዲስ መንፈስ አንቀበልዎት ይሆናል፡፡ ያኔ ቅዠቱና እውነታው ፍንትው ብሎ ይታይዎት ነበር፡፡

ግንቦት ሰባት፣ ከሻእቢያ ጋር ያለዉን ግንኙነት በአስቸኳይ በጥሶ በማለትም  ሁሉን አዋቂው ግርማ ምክር ይለግሳሉ፡፡  አቶ ግርማ ራሳቸውን ብቻ አዋቂ በማድረግ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተው  አስተያየት የማይቀበሉና ምክር የማይሰሙ በመሆናቸው አንጂ  በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ተብሏል፡፡ ትግሉ እንዴት ይካሄድ ከየት ይነሳ ወዘተ ብሎ ለመነጋገር በቅድሚያ በትግሉ ምንነት ላይ መስማማት ያስፈልጋል፡፡ በማይስማሙበት የትግል አይነት ላይ አንዲህ ይሁን ከዚህ ይነሳ ወዘተ ማለት አግባብ  አይደለም፡፡ ከልቡ ለመታገል የወሰነ ሰው ከሱ የሚጠበቀው  የሌላውን መኮነን ሳይሆን ይበጃል የሚለውን የትግል አይነትና መንገድ በተግባር ማሳየት ነው ፡፡ ስለሆነም ርስዎ አቶ ግርማ ልምከራችሁ የሚሉዋቸው ሰዎች የእውቀትም የልምድም የተሞክሮም ድሆች አይደሉምና  እኔ ከማንም በላይ አውቃለሁ እያሉ በየቀኑ ቅዠትዎን እየጻፉ አይረብሹ ፡፡ ይልቁንስ የእውነት ለውጥ ፈላጊ ከሆኑ ከምር ራስዎን ለሰላማዊ ትግል የሰጡ ከሆኑ የሌላውን የትግል ስልትና መንገድ ከመቃወም  ይበጃል የሚሉትን መንገድ በወሬ ሳይሆን በተግባር  ያሳዩ፡፡

 

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ስለ አቶ ግርማ ያደረብኝ ጥርጣሬ፤

አቶ ግርማ ስራየ ብለው  በየቀኑ  ነባራዊውን እውነታ ያገናዘቡ ሳይሆን በቀዠት የተወለዱ የሚመስሉ ጽሁፎችን መጻፋቸው፣ እኔ ከምለው ውጪ እውነት እኔ ከምደግፈው መንገድ ሌላ ትክክለኛ መንገድ የለም ማለታቸው ስለ እርሳቸው አንድ ነገር አንዳስብ አደረገኝ፡፡በተለይ ደግሞ ለደካማ ፓርቲዎች ጥብቅና ቆመው ሲከራከሩ እንጂ ከጠንካሮች ጎን ሲቆሙ አለመታየታቸው የሚደግፉዋቸው ፓርቲዎች የውስጥ ችግራቸውን ፈትተው አንዲጠናከሩ ሳይሆን በርስ በርስ ንትርክ እየታመሱ እንዲዳከሙ ማገዛቸው ሞቅ ባለበት ሁሉ አለሁ ማለታቸው ወዘተ አቶ ግርማ ሰላማዊ ትግልን የሚፈልጉት የሀገር ቤት ፓርቲዎች እያሉም የሚጮኹት ለውጥ ፈልገው ሳይሆን  የዚህ ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ እየተባሉ በመኖር የሚያገኙት ነገር ቢኖር  ነው ብየ አሰብሁ፡፡

 

ይህን አሳቤን ከጥርጣሬ በላይ  ያደረገልኝ ደግሞ ሰሞኑን የሰማሁት ነው፡፡ ይህችን አስተያየት ለመጻፍ እያሰብኩ ባለሁበት ወቅት  ከአንድ ጓደኛየ ጋር ስናወራ እኔ የማላውቀው የጓደኛየ ጓደኛ ድንገት ተቀላቀለን፡፡ ጥቂት ካዳመጠን በኋላ አይ እናንተ ግርማ ካሳን ስለማታውቁት ነው እንዲህ ተጨንቃችሁ ስለርሱ የምታወሩት ሲለን፡ በተለይ እኔ ለማወቅ በመጓጓት  በጥያቄ አዋከብኩት፡፡

እኔ የአንድነት አባል ነበርኩ  በማለት የጀመረው የጓደኛየ ጓደኛ መርህ ይከበር ብለን ከእነ ኢ/ር ግዛቸው ጋር ስንታገል አቶ ግርማ  ከእነ እገሌ ጋር በመሆን ( ስማቸውን የገለጸ ቢሆንም  አሁን ድምጻቸው የማይሰማን ሰዎች በአቶ ግርማ ጦስ የእነርሱን ስም ማንሳት ተገቢ መስሎ ስላተሰማኝ ነው) እኛን ወያኔዎች፣ ፓርቲ አፍራሾች፣ ሰርጎ ገቦች በማለት እነ ግዛቸው ከፓርቲው አንዲያባርሩን እየመከሩ  በጎን ደግሞ እኛ ጋር በመደወል እነዚህን ሽማግሌዎች ለምን አትተዋቸውምና የራሳችሁን ቢሮ አትከፍቱም እኛ እንረዳችኋለን ይሉን ነበር፣ሰማያዊ ላይም ጣታቸውን የቀሰሩት በእነርሱ ምሪት ባለመሄዱ ነው  በማለት የማውቀው ያለውን ብዙ ነገር አወራን፡፡ሰላማዊ ትግል ፣የሀገር ውስ ፓርቲዎች፣  ህብረት አንድነት እያሉ በነጋ በመሸ የሚያደነቁሩን አቶ ግርማ እንግዲህ እኝህ ናቸው፡፡

 

ለመካሪው ግርማ ትንሽ ምክር ፤

ከእኔ በላይ የሚሉት አቶ ግርማ ምክር የማይቀበሉ መሆኑ በተደጋጋሚ የታየ  ቢሆንም  ትንሽ ምክር ልለግሳቸው ወደድሁ፡፡ፕ/ር ብርሀኑ ሀገራቸው ገብተው በሙያቸው ሰርተው አሳይተዋል፤ በመድረክ ሀሳብን በሀሳብ ሞግቶ ማሸነፍ አንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል፡፡ስለምርጫ ምንነትና እንዴትነት ራሳቸው ተወዳዳሪ ሆነው ተመርጠው አሸንፈው አሳይተዋል፣ ሰላማዊ ትግልን እስከ እድሜ ልክ እስራት ፍርድ ሄደውበታል ፡፡ ወያኔን ማሸንፍ የሚቻለው በሁሉን አቀፍ ትግል ነው ብለው ሲያምኑም ዓላማቸውን ግልጽ አድርገው ድርጅት መስርተው የተንደላቀቀ ኑሮአቸውን ጥለው ትግሉና ታጋዩ ካሉበት መስክ ተገኝተዋል፡፡

አቶ ግርማ ግን ለአመታት የሆነ ያልሆነውን ከመጻፍ ውጪ የትኛው ቦታ አልታዩም፡፡ ስለሆነም የሚነግሩን የሚያምኑበትን ከሆነ ፡ወያኔ ርስዎን የሚፈልግበት ምክንያት ይኖረዋል ተብሎ ስለማይገመት (ካለ ይንገሩን) ቀጣዩ ምርጫ ከመድረሱ በፊት በቶሎ ወደ ሀገር ቤት ይምጡና ቢፈልጉ አሉ ከሚሉዋቸው  ፓርቲዎች ከአንዱ ተቀላቅለው ካልፈለጉም አዲስ ፓርቲ መስርተው  መስኩ ላይ በተግባር እንይዎት፡፡ይሄ  በሞቀበት ሁሉ ለመጣድ መፈለግና ጭር ሲል አልወድም አይነት ተግባርዎ ግን ከእንግዲህ ይብቃዎት፡፡ አይጠቅምዎትም፡፡

Comment