ተመስገን ደሳለኝ በህይወቱ የኢህአዴግን ህገ ወጥነት እያጋለጠ ነው – ዳዊት ሰሎሞን

Temesgen
ተመስገን ደሳለኝ

የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በህይወታቸው እንደ ተመስገን ደሳለኝ አይነት ደፋር ጋዜጠኛ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ መስክረዋል፡፡ ሁላችንም አቶ ቡልቻ ልክ ስለመሆናቸው ለመመስከር የተመስገንን አንድ አርቲክል ከፍትህ፣ አዲስ ታይምስ፣ ልዕልና ወይም ከፋክት ብቻ ማንበብ ይበቃን ይሆናል፡፡ተመስገን ያለ ገደብ የመናገር፣የመተቸት፣የፈለገውን ሀሳብ የመደገፍ መብቱን ገዢዎቹ ካሰመሩለት መስመር በላይ ተጉዞ የተጠቀመ ጋዜጠኛ ነው፡፡በእጁ አንዳች ገዳይ መሳሪያ ሳይኖር እንደ አንድ ቅን ዜጋ በብዕሩ ተጋድሏል፡፡
ተመስገን ወህኒ ከተቆለፈበት በኋላም እጁን ከወረቀት በማገናኘት የስርዓቱን የወህኒ ቤት ምስጢሮች ዘክዝኳል፡፡አሁን ተመስገን ጠያቂ እንዳያገኘው ጭምር ተከልክሎ ቤተሰቦቹ ተርበውታል፡፡ግን ጋዜጠኛው ሰው እንዳያየው ቢደረግም የስርዓቱን ህገ ወጥነትእንደ ቀድሞው በወረቀት ላይ ባይሆንም በህይወቱ እያጋለጠ ነው፡፡
የአገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ 21 ታሳሪዎች ስለሚያገኟቸው መብቶች ቢዘረዝርም ለተመስገን አንዳቸውም እየተፈጸሙለት አይደለም፡፡የተመስገን ህገ ወጥ አያያዝ ህገ መንግስቱን የደፈጠጠ መሆኑን ከህመሙ፣ከርሃቡ፣ቤተሰቦቹን ከማጣቱ የተነሳ ከሚደርስበት ጭንቀት በመነሳት እያነበብን እንገኛለን፡፡
የተመስገን አሳሪዎች የህትመት ውጤቶቹን በመዝጋት አንድ የመጽሔት ገጽ የነፈጉት ቢመስላቸውም ህይወቱን ወረቀት በማድረግ ህገ ወጥነታቸውን በወፍራም ቀለም እየጻፉበት ይገኛሉ፡፡እኛም በተመስገን የተጻፉትን ጭካኔዎች እያነበብን የስርዓቱን ህገ ወጥነት እየተመለከትን ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.