ምኒክልና አድዋ በ“አንዳርጋቸውን በምናቤ” ሰበብ ዛሬም ሲወቀሱ – ዳንኤል አበራ

 

የኤርትራው ወንድማችን አቶ ተስፋዬ ገብረ አብ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ ካስመራ ወደ አሜሪካ በተመለሰ ሰሞንና የአድዋ ድል በሚዘከርበት ወር (February 3, 2016) አንድ መጣጥፍ በድረ ገጾች (http://www.zehabesha.com/amharic/archives/50599 ፣  http://www.ethiofreedom.com/andargachew-in-my-mind-tesfaye-gebreab/) ድረ ገጾቹ ደግሞ በፌስ ቡክ በኩልም አድርሰውናል። ተስፋዬ ገብረ አብ “አንዳርጋቸው (ፅጌ)ን በምናቤ” ይለናል። ተስፋዬ ገብረ አብ ምናባዊ ናቸው ቢልም ሁለት ነገረ-ሃሳቦቹ አልተመቹኝም። አንዱና ዋነኛው (የምኒልክና አድዋ ወቀሳ) መልስ ያሻዋል ወቀሳው እውነት ስላልሆነ። ሁለተኛው (የአንዳርጋቸው በእስር መንደላቀቅ) እውን የተስፋዬ ምናብ ነው በሚል አንስቼዋለሁ።

Adwa33ሁለቱ ነገረ-ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው በአድዋው ጦርነት ወቅት አማራው ትግራይ ላይ ላደረሰው ጉዳት፣ የዛፍ መቆረጥና የዶሮ መፈጀት፣ ይቅርታም አላላችሁ፣ ካሳም አልከፈላቸሁ የሚለው ክስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአንዳርጋቸው ፅጌን የኢትዮጵያ እስር ቤት ቆይታ አልጋ በአልጋነት፣ መንደላቀቅ በምናቤ ታየኝ ነው። ከአለሙም ከአሰቡም እንዲህ ደግ ደጉን ነው።

ወጋችንን “ምናብ” በተሰኘው ቃል ፍቺውን በማየት ብንጀምርስ? በሚያስገርም መልኩ ባዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ማዕከል ያሳተመው የኣማርኛ መዝገበ ቃላት ሆነ የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ምናብ የተሰኘ ቃል ድርሳናቸው ውስጥ አልተገኘም። ቢሆንም የ1994ቱ የባህሩ ዘርጋው “ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት” እና የ1995ቱ የይላቅ ሀይለማርያም “ሐበሻ የአማርኛ መዝገበ ቃላት” በድርሳናቸው ገፅ 84 እና ገፅ 175 “ምናብን” “በቅርብ በስሜት ህዋሳት እማይደረስባቸውን ነገሮች በአይነ ህሊና እንዲደረስባቸው የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ሀይል” እና “ከእውነታ ከተገኙ ስሜቶች በመነሳት እውን ያልሆነ አዲስ ስሜታዊ ወይም ሀሳባዊ ምስል በህሊና ውስጥ መፈጠር ምናብ ይባላል” ይሉናል።

እነዚህን የምናብ ብይኖች ሰንቀን ተስፋዬ ገብረ አብ የአንዳርጋቸው ፅጌን የኢትዮጵያ እስር ኑሮ በምናቡ እንዲህ ነው ያየው “አንዳርጋቸውንም አየሁት። …ጠረጴዛው ላይ ቁጭ ብሎ ኮምፕዩተር ከፈተ። ምንም አልፃፈም። ዘጋውና ተነሳ። ወደ ደጅ ወጣና በረንዳው ላይ ቁጭ አለ። ሰማዩ ላይ መልሶ አፈጠጠ። ከጥቂት ደቂቃዎች ማፍጠጥ በሁዋላ አይኖቹን ጨፈናቸው። በዚያ መልኩ ብዙ ቆየ። …”

ይቺ የተስፋዬ ገብረ አብ ምናብ በምኞት ደረጃ ለአንዳርጋቸው ፅጌ እንዲሁም ለሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች የእስራቸውን አያያዝ ያድርግላቸው ቢያሰኝም መሬት ላይ የኢትዮጵያ የእስር ቤት ሁኔታ እና እስረኞች አያያዝ ያየና የሰማ ግን የተስፋዬን ምናብ መሳለቅ ነው ቢል አያስወቅስም።

ምናብ በስሜት እማይደረስባቸው ነገሮች በአይነ ህሊና ወይንም ቀለል ባለው የምናብ ፍቺ ከእውነታ ከተገኙ ስሜቶች በመነሳት እውን ያልሆነ ምስል በህሊና ውስጥ መፈጠር ሲሆን በሁለቱም ብይን ቢሆን የተስፋዬ ምናብ አያስኬድም። ሲጀመር ታስታውሱ እንደሆን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ስለ አንዳርጋቸው እስር ሲጠየቁ ልማታችንን እናስጎበኘዋለን፣ ኮምፒውተርም ሰጥተነው አንዳርጋቸው መጽሀፍ እየጻፈ ነው። ብለውን አልነበር፤ ታዲያ የተስፋዬ ምናብ እጠቅሳለሁ “..ጠረጴዛው ላይ ቁጭ ብሎ ኮምፕዩተር ከፈተ። ምንም አልፃፈም። ዘጋውና ተነሳ።” ምኑን ምናብ ሆነ የዶ/ር አድሃኖም ኮፒ ፔስት ነው እንጂ!!! ይቺ ኮፒ ፔስት ተስፋዬ ጽሁፎች ውስጥ ድሯን አደራች።

የኢትዮጵያ እስር ቤቶችን ጓዳ ካንድ ሁለት ጊዜ በላይ አይቼ አላውቅም። ግን በዚሁ እድሜዬ የታሰሩ ወገኖቼን፣ ቤተሰቦቼን ጥየቃ በተለያየ ጊዜ የእስር ቤቶቹን ደጃፍ አይቻለሁ። የታሰሩ ወገኖቼን እንግልትም በሚገባ አውቃለሁ። ታስረው የተፈቱ ወገኖቼን የመንፈስ ስብራት አዳምጫለሁ፣ ታዝቤያለሁ። በድርጊቱ ፀያፍነት እንዲሁም ድርጊቱ የተፈፀመባቸውን ወገኖች ጉስቁልና የተነሳ ባደባባይ መናገር የማንቸለውን ትተን፤ አሁን በቅርቡ እንኳን የዞን ዘጠኝ ብሎገር እህታችን እንኳን ለአድራጊው ለሰሚው የሚያሳዝን እርቃነ ገላዋን፣ መለመላዋን ወንዶች መርማሪ ፊት ቁማ ስትመረመር አልነበር? የተነገረው ይህን ያህል ከከበደ ያልተነገረ ስንቱ አለ? ስንቱ የአካል ቁስል ተረፈው፤ ስንቱ የመንፈስ ስብራት ደረሰበት፤ ስንቱ በሞት ተሰናበተ። ተስፋዬ ይህንን የኢትዮጵያ እስር ቤት የምድር ገሃነም እኮ ነው በምናብህ ገነት ያስመሰልከው። በእውነት ሲጀመር የዶ/ር አድሃኖምን መግለጫ ምናቤ ነው አልከን፤ ሲቀጥልም አንዳርጋቸው የኢትዮጵያ መንግስት እስረኛ ሲፈልግ የሚወጣ፣ ሲፈልግ የሚገባ፤ የኢትዮጵያ እስረኛ ከአሳሪዎቹ ጋር መሳፈጡን ነገርከን። ይህ ያንተ ምናብ ጡርነቱ ቢቀር ፍትሐዊ አይደለም።

ይቺኛዋን ነገረ ወጌን ልቋጭ፣ ተስፋዬ አንዳርጋቸውን ካነሳህ አይቀር በስም ጠቅሰህ ለስብሃት ነጋ አንዳርጋቸውን ፍቱትና ለንደን ይግባ ያልከውን መልዕክት ወድጄልሃለሁ። ለሚሰማ ጥሩ መልዕክት ይመስለኛል። ግን ማን መልካም ነገር ይጠላል?

ወደ ተስፋዬ ገብረ አብ ነገረ አድዋ፤ ነገረ ምኒልክ ጥላት ቅቢያ

ያራዳ ልጆች እንደሚሉት ወደ ገደለው ስንገባ እኔም እንደታዘብኩት የፌስ ቡኩ ዮሀንስ ሞላም በትክክል እንደገለጸህ ሀሳብህን ለመግለጽ የሌለ ግለሰብ/ ገፀ-ባህሪ ትፈጥራለህ። በዚህኛው ፅሁፍህም ይህንን የአድዋ ሰበዝ የምኒልክ ሰበዝ ለማምጣት ተድላ የሚባል ባንተ አባባል “ቀዌ” “መንዜ” ፈጠርክ። በዚህ በድረ-ገፅ በተሰራጨው መጣጥፍህ ከተድላ፣ ከብርሃኑ ጠባቂ ኤርትራዊው ወታደርና ከአንተ እንግዳ በስተቀር በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቁ ግለሰቦች ናቸው። የማይታወቀው፣ ብለሀል ወይ ተብሎ የማይጠየቀው የአንተ አፈ-ተስፋዬ፣ “ተድላ” ነው። ተድላ “መንዜ” ነው ፦ ስንተረጉመው ያው ነፍጠኛ ነው። አማራ ነው ማለት ይሆናል።

የማትናገር ወፍ እርሟን ብትናገር እለቁ እለቁ አለች እንደሚባለው ነፍጠኛው ተድላ፣ አማራው ተድላ፣ “መንዜው” ተድላ፣ “ቀዌው” ተድላ አፈ-ተስፋዬ ሶስት ነገር ተናገረ ለአፍቃሬ-ኢህአዴጉ ለሪፖርተሩ አዘጋጅ ለአማረ አረጋዊ። ነገሮቹን እጠቅስና የሚመሰለኝን እውነት አስከትላለሁ። አውዱን ላለማዛባት እንዳለ እጠቅስና መልስ የሚያሻውን አሰምርበታለሁ።

ነገረ-ተስፋዬ ወአድዋ ወምኒልክ አንድ

ጥቅስ (1) “የኢትዮጵያ ስልጣኔና ስልጣን የትግሬ እና የአማራ መሆኑን አምናለሁ። እንግዲህ አሁን ለመግዛት ተራችሁ ሆኖአል። … አንድ ነገር ግን በጥብቅ ማወቅ አለባችሁ። የምትወድቁበት ዘመን ሲደርስ ስልጣኑን መልሳችሁ ለኛ መተው ነው። OLF በመካከሉ ከገባ እናንተም እኛም የምንሊክን ቤተመንግስት ለዘለአለሙ አናገኘውም።…”

ሲጀመር የኢትዮጵያ ስልጣኔና ስልጣን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው። በማስረጃ መነጋገር ይቻላል። ሁለተኛ “OLF” የሚለው ቃል እዚህ ተመርጦ የገባው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በመጣው የኦሮሞ ብሔረሰብ ንቅናቄ ምክንያት ከሆነ ያሳዝናል – ከሞጋሳው ተስፋዬ ብዕር ይሄ መውጣቱ። ለወግ ያህል “OLF” ማለት ኦሮሞ ማለት አይደለም። “OLF”  የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያቋቋሙት አንድ ፓርቲ ነው። የኦሮሞ ህዝብ እንደፍላጎቱ በተለያዩ ፓርቲዎች ተወክሎ አይተናል። ይወከላልም። “OLF” እንደ ፓርቲ በዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ምርጫ ስልጣን ቢይዝ ከዚህ በፊት እዚያች ምድር ላይ ያልተፈጠረ ምን ሊፈጠር ይችላል? ምንም። ስለዚህ ይህ ማስፈራሪያ “OLF በመካከሉ ከገባ እናንተም እኛም የምንሊክን ቤተመንግስት ለዘለአለሙ አናገኘውም።” አይሰራም።

ከዚሁ ነገረ-ጉዳይ ሳልርቅ ተስፋዬ “… የምንሊክን ቤተመንግስት ለዘለአለሙ አናገኘውም።” ይላል። መንበሩ፣ ቤተ መንግስቱ የኢትዮጵያ እንጂ የምኒልክ የግል ሀብት ወይም ንብረት አይደለም። ስንት ነገስታት ከምኒልክ በፊት ስንት ነገስታት ከምኒልክ በሁዋላ ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል። አፄ ምኒልክ እዚህ ለምን በብቸኝነት ይነሳሉ? እንዳልኩት መንበሩም ላይ እኮ ሌሎችም ነበሩበት።

ነገረ-ተስፋዬ ወአድዋ ወምኒልክ ሁለት

ነፍጠኛው አፈ-ተስፋዬ ለአፍቃሬ-ኢህአዴጉ አማረ አረጋዊ እንዲህ ይለዋል።

ጥቅስ (2) “…የትግሬ ህዝብ ወንድማችን ነው። እየተፈራረቅን ገዝተናል፤ …። ‘ምኒልክ ዮሃንስን ሸውዶ ነው ዙፋን የያዘው’ ምናምን ብላችሁ እየተቆጣችሁ ስለመጣችሁ…”

የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አካል ነው። እሱ ምንም አያጠያይቅም። “ምኒልክ ዮሃንስን ሸውዶ ነው ዙፋን የያዘው” ይቺኛዋ ነች ችግሯ። ሲጀመር ስልጣን ቅብብሎሽ ነበር፤ ነውም። ሽወዳ የሚባል ነገር የለም። በየዘመኑ ሁሉም ሁለን ነገር አድርጎ ነው ስልጣን የነጠቀው። እኔ ኢትዮጵያን የገዙ፣ ያስተዳደሩ እና ሕይወታቸውን የሰው መሪዎችን አንስቼ ጥላት አልቀባም። ቢያንስ ቢያንስ ግን ተስፋዬ አፄ ዮሀንስ እኮ ቀዳሚውን አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ገሎ እኮ ነው ንጉሰ ነገስት የሆነው። ይቺ የምኒልክ በክፉ መነሳት ሰሞኑን የአድዋ ድል መዘከሪያ ወር ስለሆነ ያንን የኢትዮጵያ ህዘብ የድል፣ የነጻነት ምሳሌ ጥላት ለመቀባትና ለማስቀባት ካልሆነ በስተቀር ምን የተለየ ፋይዳ አለው። ፈሊጥም ከሆነ ነቀርሳ ፈሊጥ ስለሆነ ቢቀርስ? ወዳጄ ተስፋዬ ለመነበብ ከሆነ ብዙ አቅም አለህ። እሱኑ ተጠቀም ታሪክ ውስጥ እየገባህ አትዳክር ማጡን አትወጣውም።

ነገረ-ተስፋዬ ወአድዋ ወምኒልክ ሶስት

ተስፋዬ በገጸ ባህሪው-አፍ እንዲህ ይላል። ለውይይት እንዲመች ከዚህ በታች የጠቀስኩትን የተስፋዬ ገብረ አብን ሀሳብ በቁጥር አስቀምጨዋለሁ።

ጥቅስ (3) “…የትግሬ ህዝብ ወንድማችን ነው። እየተፈራረቅን ገዝተናል፤ አይደለም እንዴ? ‘የሞትንም እኛ – የነገስንም እኛ’ እንዲሉ። የናንተ ችግር መቶ አመታት በተራራ መሃል ተቀብራችሁ መኖራችሁ ነው። አሁን ባነናችሁ። ‘ምኒልክ ዮሃንስን ሸውዶ ነው ዙፋን የያዘው’ ምናምን ብላችሁ እየተቆጣችሁ ስለመጣችሁ እንግዲህ ቤተመንግስቱንም ባንኩንም ትተንላችሁዋል። (1)ርግጥ ነው፤ በአድዋ ጦርነት ከምኒልክ ጋር የመጣን ጊዜ አንዳንድ ጉዳት አድርሰናል። (2)ብዙ ዛፎች ቆርጠናል(3)ብዙ ዶሮዎች ፈጅተናል። መቸም ይሄ በክፋት የተደረገ አይደለም። (4)ካሳ ባለመደረጉ ብትቀየሙ እንገነዘባለን።”

ተስፋዬ የምር ይሄ በእውነት አሳፋሪ ስራ ነው። እንዲያው ሰምተኸዋል ተብሎ ቢታሰብ እንኳ መልሶ ለመናገር ከተናጋሪው የባሰ ደካማነት ነው። መፃፍም አልነበረበትም። ከተፃፈ ደግሞ ሀላፊነቱ ያንተ ነው። ለሪከርድ ያህል ግን መታረም ይኖርበታል። እውነታው ከላይ ከ1-4 የተዘረዘረው ስላልሆነ።

እሺ ይህ ሁሉ ጉዳት ደረሰ እንበል። ሲጀመር በአድዋ ጦርነት ወቅት የጦሩ አዛዦች የጦርነቱ ጀግኖች የመሀል አገር ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የትግራይም የኤርትራም ሰዎች ናቸው። እነ ራስ መንገሻ እነ ራስ አሉላ ዋና ዋናዎቹ የጦር አበጋዞች ነበሩ እና በምን ተለይቶ ነው ነፍጠኛው ትግራይ አካባቢ እና ዶሮዎች ላይ ጉዳት አደረሰ የሚባለው?

ካሳ የሚባለውም ቢሆንስ ((4ኛዋ) “ካሳ ባለመደረጉ ብትቀየሙ እንገነዘባለን።”) ካሳ እኮ ለጎረቤት ለባእድ እንጂ ለራስህ አካል እንዴት ይታሰባል? አኻ እዚህ ጋ ለካ ልምድ አለ። አደይ ኤርትራ በተገነጠለች እና የጎረቤት መንግስት በመሰረተች ማግስት አዲሲቷን ሀገር የብአዴን አባላት ነፍጠኛውን ወክለው አስመራ ሄደው ይቅርታ ጠይቀዋል ለካ። ተስፋዬ እንግዴህ ሰሞኑን እንደሚናፈሰው ከሆነ ደግሞም ውስጥ አዋቂም አይደለህ “የህወሀት የትግራይ ሪፐብሊክ” ሀገርና መንግስት ሊመሰረት ነውና እንደተለመደው ለይቅርታና ለካሳ ክፍያ ተዘጋጁ ከሆነ ባለ-ልምዱ ብአዴንና አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርጉትን ያድርጉ። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ይህ ጉዳይ አይመለከታቸውም። አጥፊዎቹም እነሱ አይደሉም ታገሰኝንና ማስረጃውን እዘረዝራለሁ።

ጣሊያን ከአስመራ ተንደርድሮ ትግራይን ያለከልካይ ሲፈነጭባት ኢትዮጵያውያን የወንድሞቻቸው መናቅ መደፈር ግብግብ አድርጓቸው ከመስከረም ወር ጀምሮ አምስት ወር ተጉዘው ነው ትግራይ የገቡት። የሄዱትም እኮ ትግራይን ለማቅናት አልነበረም። ትግራይና ኤርትራን የወረረውን የጣሊያንን ጦር ለማስወጣት እንጂ። እድላቸው አመድ አፋሾች ሆኖ ላከሰላችሁት እንጨት ለበላችሁት ዶሮ የልጅ ልጆቻቸው ይቅርታ ጠይቁ ካሳ ክፈሉ ተባሉ ይርጋ የሌለበት ክስ። ከሆነ አይቀር እንዲህ ነው። ኢትዮጵያውያን “ዛፍ ቆረጡ” “ዶሮ ፈጁ” ነው የምትለው ተስፋዬ? ኢትዮጵያውያን እነሱስ የከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት? ሕይወት መቸም ከዛፍና ከዶሮ አንሶ ዛፍና ዶሮ ቆረጡ ፈጁ ተብሎ ይወራል?

መጣጥፍህን በዚህ ሳምንት ያሰራጨኸው ተናግሮ ለማናገርም ከሆነ ጉዳይህ ተሳክቶልህ ነበር ግን ከሸፍክ። አንተ ባልጠበቅከው አጋጣሚ የበእውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” የሰውን አእምሮ ሰንጎ ያዘልህ። ባይሆን ለመልስ-መልስ ከመጣህ ያኔ ትንታጎቹን ጠብቅ። በፊትም አቅማቸውን አሳይተውኻል። ሲያሻቸው ሁለት አመት ታግሰው ሲያሻቸው በሳምሰንግ ሰካነር “አሁንስ ፈራሁ” አሰኝተውኻል። ማንን ፈርተው ዝም ይላሉ ብለህ ነው?

adwaኢትዮጵያውያን የከፈሉትን የሕይወት መስዋዕትነት ተስፋዬ መቸም አላነበብክ አልሰማህ ከሆነ አባትና ልጅ የጦር አበጋዞች ያለፉበት የ19 እና የ20 አመት ሙሽሮች ከጫጉላ ቤት ወጥተው የተማገዱበት ስንቱ አባወራ ያለፈበት ስንቱ ትዳር አልባ ስንቱ የሙት ልጅ የሆነበትን የአድዋ ጦርነት ነው እኮ ዛፍ ዶሮ እያልክ የምትሳለቀው። ኢትዮጵያውያን አባትና ልጅ የጦር አበጋዞች፣ ሙሽሮች፣ አባ-ወራዎች እማ-ወራዎች ጉብሎች ኮበሌዎች ካንድ ቤት የወጡ ወንድማማቾች እህትማማቾች ሕይወታቸውን እኮ ላገራቸው የለገሱት ስጦታ ነው። እድለኞች ሆነው ምኒልክን የመሰለ መሪ ያገኙ ነበሩ። ቢያንስ የነሱ የልጅ ልጆች አይታዘቡንም ዛፍ ቆረጡ ዶሮ ፈጁ ስንል። ሐውልት ባናቆምላቸው ቢያንስ ሲዘለፉ ሲወቀሱ ዝም አንልም። ክብር ለአድዋ ጀግኖች- ክብር ለአድዋ ሰማዕታት ከመቶ ሀያ አመት በሁዋላም ቢሆን መስዋዕትነታቸውን አንዘነጋም።

የኔ ነገር ሐውልት ባናቆምላቸው ስል ምን ትዝ አለኝ አይቁጠርብን እንጂ ካንድም ሁለቴ ለወጉን ለጣሊያኖች በዚሁ በዚሁ በኛው ምድር በወጉት ሀገር ለወታደሮቻቸው ሀውልት ቆሞላቸዋል በኤርትራ ዶግአሊ https://en.wikipedia.org/wiki/Battle_of_Dogali#/media/File:Dogali_Monument.jpg

እንዲሁም በትግራይ አድዋ https://www.flickr.com/photos/nichelin/4998221948/። እኛ ዛፍ ቆረጡ ዶሮ በሉ እያልን ማፈሪያ ስራ እንሰራለን።

መስዋዕትነት እያልኩ ትንሽ መረር አልኩ መሰለኝ። እሱን ላቆይና “ጉዳት አድርሰናል- ዛፍ ቆርጠናል-ዶሮ ፈጅተናል” የሚለውን ነገረ-ሀሳብ እስኪ ይሁን ብለን እናሰላስለው። እውነታው ግን ትግራይ የጦር አውድማ ስለነበረ ምንም ምርምር አያሻውም በሰው ሕይወትና በአካባቢ ላይ ጉዳት ደርሷል። ጥያቄው ግን ይህንን ጉዳት ያደረሰው ሕይወቱን የገበረለት የኢትዮጵያ ጦር ነወይ? ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክን ያጠናና የጻፈ ወዳጅም ጠላትም አፉን ሞልቶ ጉዳት አድራሹ የኢትዮጵያ ጦር ነው አላለም። ተስፋዬ ከየት አመጣኸው? ተስፋ አደርጋለሁ የነገር ቅሪት የነገር እርሾ እየያዝክ እንዳልሆነ።

 

ሆነም ቀረም እውነታው ይህ ነው።

1)በጦርነቱ ዋዜማ ጣሊያኖች በበሽታ የተለከፉ ከብቶች አምጥተው ምፅዋ አራግፈው የኢትዮጵያ ከብት ሁሉ በበሽታ እንዲያልቅ ምክንያት ሆኗል ትግራይንም ጨምሮ። ጉዳት አንድ

2)አፄ ዮሀንስ ካለፉ በሁዋላ የትግራይ ባላባቶች ስልጣን ለኔ ይገባል ለኔ ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ጦርነቶችን አካሂደዋል። በዚሁ ሳቢያ እርሻ ተስተጓጉሏል። የአካባቢ ውድመት ደርሷል።(በነገረ-ወጋችን ስመ-ገናናው የአድዋው የተድአሊው (የዶጋሊው) ጀግና ራስ አሉላም ወንድማቸውም ይህን በመሰለ የጎጥ ውጊያ ነው ሕይወታቸውን ያጡት)። ጉዳት ሁለት

3)እኔም እንዳቅሚቲ በወዳጆቼ ጥረት የታሪክ መጻሕፍት የማንበብ እድል ገጥሞኛል። ጣሊያኖችም እንደፃፉት ኢትዮጵያን እንደጠላት ይፈርጃት የነበረው ዋይልድም እንደፃፈው ጣሊያኖች አምባአላጌ ድረስ ሲመጡ ማገዶና ዶሮ ከሮም አይደለም ያስመጡት። እዚያው ትግራይ ውስጥ ያለውን ጨፍጭፈው ነው የተጠቀሙት፤ ጉዳት ሶስት። በምን ሂሳብ ነው የኢትዮጵያ ጀግኖች የራሳቸውን ዛፍ ቆረጡ የራሳቸውን ዶሮ ፈጁ ተብለው ስማቸው የሚነሳው? እየተስተዋለ?

4)ቢያንስ ቢያንስ እትጌ ጣይቱ ያስደረመሱትን የመቀሌን ምሽግ ጣሊያን የገነባው እኮ የትግራይን ደን መንጥሮ ነው። ማጆር ጋሊያኖ የመቀሌው ምሽግ በኢትዮጵያ ጦር እንዳይሰበርበት በአካባቢው ያለውን ደን ምሽግ የሰራበት አልበቃ ብሎት የኢትዮጵያን ጦር ይሸሽጋል ብሎ ጨፍጭፎታል አስጨፍጭፎታል። ደኑ አልበቃ ብሎት በአስካሪዎቹ በመርስነሪ ቅጥረኞቹ የአካባቢውን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ደፍሯል አስደፍሯል። አቦይ ተስፋዬ አስካሪዎቹ ደግሞ ማን እንደሆኑ ልቦናህ ያውቀዋል።

  • የአዲግራት ምሽግ ይሰበርብኛል ብሎ የተንበቀበቀው ጣሊያን ከአድዋ ጦርነት በፊት ካዲግራት መቀሌ በሚወስደው አቅጣጫ እኮ ደኑ የኢትዮጵያን ጦር ይደብቃል እንጨቱም ማገዶ ይሆናል ፍራቻ ከ 20 ኪሎሜትር በላይ የተንሰራፋውን ደን አስጨፍጭፏል። ተስፋዬ በአዲግራት የነቀኛዝማች ታፈሰን እጅ የቀመሰው ጣሊያን እኮ ከአድዋም ጦርነት በሁዋላ ከዛሬ ነገ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን እርዴን ይሰብሩብኛል ፍራቻ አዲግራት ዙሪያ ያለውን ደን ያስጨፈጨፈው በየት አውራጃ ሰዎች እንደሆነ ይቺን ጉድ ልብህ እያወቀ ምነው በኢትዮጵያውያን ላይ ታላክካለህ?

እርግጥ ነው ምኒልክን አድዋ ላይ ነጩም ሌላውም የሚረባረበው ይቺ ኢትዮጵያ ለምንላት አገር ተምሳሌት ስለሆኑ ነው። የመንፈስ ጥንካሬና የነፃነት ልዕልና ስላጎናፀፉ ነው። ምን ይደረግ እንግዲህ? ተስፋዬ ገብረ አብና መሰሎቹ እናንተም ጻፉ እኛም እናበራየዋለን። ምኒልክና አድዋም ይኸው በመቶ ሀያኛ አመታቸውም እየተዘከሩ ነው። በድጋሚ ሐውልት ባናቆምላቸው የት እንደወደቁ ባናውቅ ቢያንስ ሲዘለፉ ሲወቀሱ ዝም አንልም። ክብር ለአድዋ ጀግኖች- ክብር ለአድዋ ሰማዕታት ከመቶ ሀያ አመት በሁዋላም ቢሆን መስዋዕትነታቸውን አንዘነጋም።

ከዚህ የበለጠ ዝርዝር ማወቅ ለምትፈልጉ አንባቢያንም ተስፋዬ ገብረ አብም ወዳጅ ጠላትም የአድዋ ድል መቶኛ አመትን ኢትዮጵያ ባከበረችበት ወቅት ብዙ ጥናቶች ለአንባቢያን በቅተዋል። እነሱን ገልበጥ ገልበጥ ማድረግ ነው። የታሪክ ምሁሩ የአስናቀ አሊ The environmental impact of the (Adwa) campaign ለአካባቢው ውድመት ጥሩ መነሻ ጥናት ነው። እሱን ማንበብ ነው። የአስናቀ አሊ ወራሾች እንዲሁም የአሳታሚው የአ.አ.ዩ. ፈቃድ ስለሌለኝ ጥናቱን ፖስት ማድረግ አልችልም።

ቸር ያቆየን

(February 10, 2016)

ለጸሀፊው አስተያየት መለገስ ለምትፈልጉ (danlinet@yahoo.com) ኢጦማር ብትሰዱ ይደርሰኛል።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.