የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ማን ነው፤ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ወይንስ የጠ/ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ?

ሰንደቅ  ጋዜጣው ሪፖርተር

News146

ኢትዮጵያ መንግሥት የቃል አቀባይነት ሥራን እንዲያከናውን በሕግ የተቋቋመው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ተግባርና ኃላፊነት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሥር የተዋቀረው የፐብሊሲቲ እና የኢንፎርሜሽን ክፍል በመውሰዱ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት መቋጫ አለማግኘቱን ምንጮቻችን ገለፁ።

ምንጮቻችን እንደገለፁት፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ጠ/ሚኒስትርነት ከመጡ በኋላ አቶ ጌታቸው ረዳ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፐብሊሲቲና ኢንፎርሜሽን ኃላፊ በማድረግ የሾሟቸው ሲሆን፤ ይህ ክፍል በአዋጅ የተቋቋመውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሥራ በመተካት የመንግሥት ቃል አቀባይ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል። ይህ የኃላፊነት መደራረብ በተለይ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ከፍተኛ አመራሮች ቅሬታ በመፍጠሩ፤ ጉዳዩ ተከታታይ ውይይት ተደርጎበት በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ የተቋቋመው ክፍል ከአደረጃጀት ውጪ መሆኑ የጋራ ግንዛቤ ተወስዶ እንዲቀር መደረጉን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

በተደረሰው የጋራ መግባባት የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የፐብሊሲቲና ኢንፎርሜሽን ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው የጠ/ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ተብለው በአዲስ መልክ የተመደቡ ሲሆን፤ የመንግሥት ቃል አቀባይነቱ ሥራ በአቶ ሬድዋን ሁሴን ሚኒስትርነት የሚመራው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት እንዲመለስለት መደረጉ ታውቋል።

ይህ ማስተካከያ ከአራት ወር በፊት ቢደረግም አቶ ጌታቸው ረዳ የመንግሥት ቃል አቀባይነት ሥራ ደርበው መሥራታቸው በመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ አሁንም ቅሬታቸው እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል።

    በተለይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የመንግሥት ቃል አቀባይነት ሥራ የሚከናወነው በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትሩ በኩል እንደነበረ ምንጮቹ አስታውሰው፤ መ/ቤቱ በአዋጅ ሳይፈርስ ኃላፊነቱን መሸራረፍ ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.