ልጅ የሳቁለት፣ ለውሻ የሮጡለት፣ ለፖለቲከኛ ያጨበጨቡለት -ይገረም አለሙ

Jawar
ጀዋር ኦሮምያ የኦሮሞዎች

የአበው ተረት ለልጅ የሳቁለት ለውሻ የሮጡለት ነው የሚለው፡፡ ለፖለቲከኛ ያጨበጨቡለት የሚል ቢጨመርበት  ተስማሚ ይመስለኛል፡፡ ልጅ ከሳቁለት ሁሉ ቦታ እየገባ ነገር ያበላሻል፤ ውሻ ከሮጡለት ጥሎ ካላንደባለለ ወይ ካልቦጨቀ አይመለስም ፖለቲከኛም  ካጨበጨቡለት  አበው  ልቤ አደገና ያለ ቁመቴ አላስገባ አለኝ የገዛ ቤቴ እንደሚሉት ይሆንና  ከእኔ በላይ ለአሳር በሚል መታበይ ብዙ ጥፋት ያደርሳል ኋላም ራሱን ያዋርዳል፡፡ እኛም ጥሎብን ይሁን ባህል ሆኖብን ባይታወቅም እየኮተኮቱ ማሰደግ እየገሩ ለወግ ማዕረግ ከማብቃት ይልቅ እያሞካሹ ማበላሹትን እያጨበጨቡ ወደ ገድል መግፋቱን ተክነንበታል፡፡ በዚህ መንገድ ስንት ለሀገርና ለወገን ሊጠቅሙ ይችሉ የነበሩ ሰዎችን አጥተናል፡፡

አድናቆታችንም ሆነ ነቀፌታችን ለመታበይ የሚዳርግ አንጂ ስክነትን የሚጋብዝ አይደለም፣የወደድነውን ምንም ይናገር ምንም ይስራ በማጨብጨብ በማሞካሸት እናሳብጠውና  ሳይበስል አንድፊርጥ እናበቃዋለን፡፡ አንድም በቅናት አለያም በምቀኝነት የጠላነውን ደግሞ ምንም መልካም ነገር ይናገር የቱንም ያህል በጎ ተግባር ይከውን ቃላት እየሰነጠቅን ኣቃቂር እያወጣን ማንቋሸሽ ማሳነስ  ማደናቀፍ ከተቻለም ከጨዋታ ውጪ ማድረግ ፡፡እንደ በጎ ነገር ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ልናስወግደው ያልቻልነው በሽታ፡፡

ንጉሱ የምትወደንና የምንወደህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ እያሉ በስተርጅና ሲንገታገቱ  ርስዎ ከሌሎ ጸሀይ ትጠልቃለች በሚሉ አሸርጋጆች ተከበው አረ ጃንሆይ እንደምትሉት  ህዝቡ እየወደደዎ አይደለም የሚላቸው በጎ መካሪ አጥተው  እንዳንድ ቢኖሩም ድምጻቸው ከአሞጋሽ አወዳሹ ልቆ የሚሰማ ባለመሆኑ  እንዳይሆኑ ሆኑ፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ውድ ወገኖቼ እያሉ ህዝቡ ይወደኛል በሚል ስሜት ሲናውዙ ሰልፍ ወጥቶ መፈክር የሚያሰማውን እያዩ ሲኩራሩ  አረ ጓድ መንግሥቱ ርስዎ የሚያስቡትና የህዝቡ ስሜት ሀራምባና ቆቦ ነው  ብሎ እውነቱን ከሚነግራቸው ይልቅ  ከጓድ መንግሥቱ ጋር ወደ ፊት የሚለው አሸርጋጅ በመብዛቱ  ፤ጓድ ሊቀመንበር እንዳሉት የሚለው አሽቃባጭ ዙሪያቸውን ከቦ በመያዙ  ሀገሪቱን ለውደቀት ራሳቸውን ለስደት ዳረጉ፡፡

አቶ መለስም ያለ እድሜአቸው ለሞት የበቁት ተዉ ሁሉን ነገር በልክ አድርጉት ህዝብንም አክብሩ ታሪክንም አትዳፈሩ አንደበትዎ የታረመ ስራዎ ሀገር የሚጠቅም ይሁን ብሎ የሚመክራቸው አጥተው  ያለእርስዎ  እያሉ በሚያዳንቁ አሽቃባጮች በመከበባቸው ነው፡፡

በየዘመኑ የት ይደርሳሉ የተባሉ ፖለቲከኞችም ጭብጨባ እያሰከራቸው  ፣ሙገሳ ልባቸውን እያሳባጠው ፣ምክንያታዊ ሳይሆን ስሜታዊ ድጋፍ ከእኔ በላይ እያሰኛቸው በመታበይ መንገድ ሲስቱ፣በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ   ርስ በርስ ሲተናነቁና ሲተላለቁ ፣አልፎም የራሳቸው ስራ እያዳጣቸው ሲወድቁ ሲወድቁ  አይተናል ተጽፎ አንብበናል፡፡ ከትናት መማር ብሎ ነገር አያውቀንምና  ጥሩውን ሳይሆን መጥፎውን እየወረሱ  በዛው በትናንቱ  ከእነርሱ የቀደሙት ለውድቀት በበቁበት መንገድ እየተጓዙ አለን አለን እያሉ ነገር ግን ወደ አለመኖር እየተንደረደሩ ያሉ ሰዎችን እያየን ነው፡፡

አድናቂ ነኝ ደጋፊ ነኝ የሚለው በማወቅም ባለማወቅም በጭብጨባ እያሰከረ፣በአጓጉል ሙገሳ እያሳወረ የቁልቁት መንገዳቸውን ሲያፋጥንላቸው ወደ ገደሉ አፋፍ ሲመራቸው አንጂ ቆም ብለው አንዲስያቡ ረጋ ብለው ማንነታቸውን እንዲገነዘቡ የት አንዳሉና ወዴትስ እየሄዱ አንደሆነ እንዲያስተውሉ  ምክር መለገስ ቀርቶ ፋታ ሲሰጣቸው አይታይም፡፡ አበጀህ ብቻ፤

በዚህ መንገድ እየተጎዱ ካሉና በአጭር ግዜ ውስጥ እንዳናጣቸው ከሚያሰጉ ሰዎች አንዱ ጀዋር ሙሀመድ ነው፡፡ እድሜ ለዘመኑ ጥበብ አንዳንድ የመድረክ ንግግሮቹን እንዳየነው ሲጨበጨብለት ጭብጨባውን ለማስደገም አንጂ ስለሚናገረው የሚጨነቅ አይመስልም፡፡ ወጣቱ ጀዋር ከዚህ በሽታ ተፈውሶ ለራሱም ለሀገርም የሚጠቅም ይሆን ዘንድ ምክር ሲለገሰው  አድናቂ ነን ደጋፊ ነን የሚሉ ወገኖች እሱን ጎሽ አበጀህ መካሪዎችን የት አባታቸው ስለሚሉ ጅዋር በመድረክ ጭብጨባ፣ በቅርቡ ባሉ ሰዎች አበጀህ ባይነትና በማህበራዊ ድረ ገጾች ሙገሳ በሽታው ይበልጥ ስር እንዲሰድና የማይድንብት ደረጃ እንዲደርስ  እየሆነ ነው፡፡

ሰሞኑን ከማህበራዊ ድረ ገጽ ባነበብኩት አንድ ጽሁፉ የጀዋር በሽታ ምን ያህል ስር እንደሰደደ ለመገንዘብ ችያለሁ፣ቢሆንም ግን ፈጥኖ ቢረዳና እሱም ፈቃደኛ ቢሆን ህክምናው ቢከብድም ይድናል፡፡ጀዋር የአበበ ገላውን  ጽሁፍ መነሻ አድርጎ በጻፈው ጽሁፍ ኦሮምያ የኦሮሞዎች ነች የሚለውን አጽንኦት ሰጥቶ ይህም እኛ ያልነው ሳይሆን ከሀምሳ አመት በፊት የኦሮሞ አባቶች ያሉት ነው ይላል፡፡

ዓላማቸውን  መገንጠል አድርገው ለእኔ የማትሆን ኢትዮጵያ ዘጠኝ ቦታ ትበጣጠስ ብለው ባይሳካላቸው ብረት አንስተው ታግለው የነበሩ ወገኖች  ከተሞክሮ ባገኙት ትምህረት ተለውጠው ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት ሲሉ እየሰማን ነው፡፡ ጀዋር ከሀምሳ አመት በፊት ብሎ የሚጠቅሳቸው እነማንን ነው ፡ ካሉም እነዛ ሰዎች ያኔ መፍትሄው ያ መስሎአቸው ተናረው ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ በህይወት ቢኖሩ ደግሞ ከላይ አንደገለጽናቸው ወንድሞቻችን ለውጥ ሊያርጉ ይችሉም ነበር ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ጀዋር አንደወጣት፤ጀዋር አንደተማረ ሰው ትናትን ከዛሬ እያገናዘበ ስለመጪውም አሸጋግሮ እያየ የሚናገር የሚሰራ ሊሆን በተገባው ነበር፡፡

ጀዋር ኦሮምያ የኦሮሞዎች ማለት ኬንያ የኬኒያዎች ሲዳማ የሲዳማዎች ማለት ነው  የሚለውን ሳነብ ደንግጫለሁ፡፡ ያስደነገጠኝ ብዙ ነገሮችን በማሰቤና በማስታወሴ ሲሆን አንዱ ትውስታየ አዋሳ ላይ የገጠመኝ ነው፡፡ 1994 ዓም ነው ለስራ ጉዳይ አዋሳ ተገኝቻለሁ፡፡ በወቅቱ በሲዳማዎችና በወላይታዎች መካከል ከፍተኛ የሥልጣን ሽኩቻ ነበረ፡፡አጋጣሚ እዛው እያለሁ ኢዴፓ የተባለው ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ  ይጠራል፡፡ስብሰባው የተጠራበት አዳራሽ አነስተኛ በመሆኑ ቦታ አንዳናጣ በማለት አኔ አንግዳውና ሀገሬው ጓደኛየ ቀደም ብለን ሄደን አዳራሹ መሀል አካባቢ ቦታ ያዝን፡፡ የፊት ወንበሮች በጠዋት ተይዘዋል፡፡ ገብተን አንደተቀመጥን ጓደኛየ ከፊት ለፊት የተቀመጡትን እየቃኘ ጉድ ነው አለ፡፡ የምን ጉድ አልኩት፡፡ከፊት ያሉት በሙሉ ካድሬዎችና ባለሥልጣኖች ናቸው አብዛኛዎቹ ደግሞ ሲዳማዎች ናቸው አለኝ፡፡ ታዲያ ምን ጉድ አለው አንደውም  በስማ በለው ከሚሰሙ በተቀዋሚ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ራሳቸው ማዳመጣቸውና የስብሰባው  ተካፋይ መሆናቸው መልካም ነገር ነው አልኩት፡፡

አዳራሹ ሞልቶ ሰው ዙሪያውን በመሆን የፕሮግራሙን መጀመር እየጠበቀ ነው፡፡ የመድረኩ መሪ የፓርቲው አመራሮች ከአዲስ አበባ እየመጡ መሆኑን ገልጾ ስለመዘግየታቸው ይቅርታ በመጠየቅ  በትእግስት አንድንጠብቅ ነግሮናል፡፡አመራሮቹ ደርሰው የመድረክ መሪው የፕርግራም ትውውቅ አድርጎ የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አድማሱ ገበየሁ ንግግር አንዲያደርጉ ጋበዘ፡፡ ዶ/ሩ ከመነጋገሪያው ጀርባ ቆመው እንኳን ደደህና መጣችሁ በማለት ንግግራቸውን  ሲጀምሩ ጓደኛየ ጉድ ነው በማለት የፈራው ነገር ተከሰተ፡፡ ከፊት ያሉት በሙሉ እጃቸውን አወጡ፤ በእጅ በማውጣት ብቻ አልታቀቡም ሥነ ሥርዓት አካሄድ እያሉ መጮህ ጀመሩ፡፡

በፕሮግራሙ አንደተገለጸው የውይይት ክፍለ ግዜ አለ፤ ያኔ አስተያየትም ሆነ ጥያቄ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ አሁን ግን መድረኩ የእኛ ስለሆነ መከናወን ያለበት በእኛ ፕሮግራም መሰረት ነው ሲባሉ መጀመሪያ በማን መሬት ላይ አንዳላችሁ ሳተረጋግጡ ስብሰባ መጀመር አትችሉም በማለት ረበሹ፡፡ የፖሊስ አዛዡ እዛው ከአዳራሹ ውጪ የነበረ ቢሆንም ረብሻውን ለማስቆም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በሆነው ነገር ሁሉ የተበሳጨው ተሰብሳቢ አንገት አንገታቸውን እያነቅን እናስወጣቸው አለ፡፡የፓርቲው አመራሮች እይሆንም የክልሉን ባለሥልጣናት አነጋግረን አንምጣ በትእግስት ጠብቁ ብለውን ሄዱ፡፡

ብዙ ቆይተው ሲመለሱ ፕሬዝዳንቱም ም/ል ፕ/ሬዝዳንቱም  ቤት ሄደው ሊያገኙዋቸው አንዳልቻሉ (እለቱ እሁድ  ነው) የፖሊስ አዛዡም እዛው አዳራሹ በር ላይ ሆነው እያዩ  ድብድብ ካልተፈጠረ በስተቀር ፖሊስን አይመለከተውም አንዳሉዋቸው ያ አንዲሆን ደግሞ ፓርቲያቸው አንደማይፈቅድ ገልጸው በሆነው ሁሉ እናዝናለን ነገሮች ተስተካለው በአጭር ግዜ አንደምንገናኝ ተስፋ አለን በማለት ተስብሳቢውን በትነው ወደ መጡበት ሄዱ፡፡

ልብ በሉ እነዛ የሲዳማ ካድሬዎች በማን መሬት ላይ እንዳላችሁ መጀመሪያ ሳተረጋግጡ ስብሰባ መጀመር አትችሉም ነው ያሉት፡፡ ሲዳማ የሲዳማዎች ስለሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ  ስብሰባ ጠርቶ በክልሉ ከሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ጋር ለመነጋገር የምንሰበሰበው በሲዳማዎች ምድር ላይ ነው ብሎ ማረጋገጫ ሰጥቶ ከሲዳማዎች ፈቃድ ማግኘት አለበት ነው ጥያቄው፡፡ የጁሀር ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ሲዳማ የሲዳማዎች አስተሳሰብም ይሄው ነው፡፡ ጁዋር ግን ይህ እኩይ አስተሳሰብ ተጠናውቶት አንዴ ስለ ሀገራዊ አንድነት ሌላ ግዜ ስለ ጠባብ ጎሰኝነት የሚያናግረው፤ በብሄር ኦሮሞ በሀይማኖት እስላም የሌለና መሆን የማይቻል ይመስል በእኛ አካባቢ ቀና ብሎ የሚሄድ ክርስቲያን ቢገኝ በሜጫ ነው አንገቱን የምንለው እስከማለት ያደረሰው፡፡ ይይዘው ይጨብጠውን አሳጥቶ  አንዲህ ከራሱ ጋር ጭምር የሚያጋጨው  በሽታ በዘር ተላልፎበት ይሆን ወይንስ ከለማበት የተጋባበት ሆኖ፡፡

ሌላው ጉዳይ በኦሮምያ የተካሄደው ህዝባዊ አንቅስቃሴ በኦፌኮ የተመራ አንደሆነ አድርጎ የገለጸው ነው፡፡ በወቅቱ በየቀኑ ለመገናኛ ብዙኀን መግለጫ ይሰጡ የነበሩት አቶ በቀለ ነጋ ህዝቡ በራሱ ያቀጣጠለው ተቃውሞ አንደሆነ ሲገልጡ አንጂ አንደም ግዜ ድርጅታቸው ማስተባበሩንና መምራቱን ሲናገሩ አልሰማንም፡፡ ቢሆንም አንኳን ትግሉ ከወያኔ ጋር ነውና ፣የሚኖሩት ሀገር ውስጥ ነውና አይነገርም፡፡ አንደውም ከአቶ በቀለ ስንሰማ የነበረው አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በዞንና በወረዳ ያሉ የፓርቲው አመራሮች ያለአግባብ ወንጀል እየተለጠፈባቸው መታሰራቸውን ነው፡፡ ርሳቸው ከታገቱ በኋላም ዶ/ር መረራ ከዚህ የተለየ የገለጹት  ነገር የለም፡፡ ፓርቲያቸው  የህዝባዊ አመጹ አስተባባሪና መሪ ስለመሆኑም አልተናገሩም፡፡ሊናገሩም አይችሉም፡፡

አንደኛ የፓርቲው አመራሮች ያልተናገሩትን ሁለተኛ በዚሁ ምክንያት አያሌ የፓርቲው አባላት በእስር ላይ እያሉ አቶ ጀዋር ህዝባዊ እንቅስቃሴው በኦፌኮ አንደተመራ መናገሩ ምን ይሉታል፡፡ ፓርቲውንና አመራሮቹን እየከሰሰ፤ በታሰሩትም ላይ ምስክርነት እየሰጠ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡ ጭበጨባ ያሰከረው ፣አጉል ውዳሳና ሙገሳ ያሳበጠው ፖለቲከኛ እንዲህ ነው ነገር የሚያበላሸው፡፡

ጅዋር መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ተብሎ የሚተው መሆን የለበትም፡፡ራሱን አድኖ ለሀገርም ለወገንም የሚጠቅም ዜጋ ይሆን ዘንድ ርዳታ ያስፈልገዋል፡፡ ስለሆነም አድናቂም ሆነ ደጋፊ ነን ባዮች ከጭብጨባና ሙገሳ ወጣ ብላችሁ ራሱን እንዲያይ ዙሪያ ገባውን ማስተዋል አንዲችል በሽታውንም አንዲያውቅ ልትረዱት ይገባል፡፡ ተችዎችም ወደ እልህ በማያስገባውና በሽታውን በማያባብስበት መንገድ  ስህተቱን በመጠቆም፣ችግሮቹን በማሳየት፣እውነቱን የትና እንዴት ማግኘት አንደሚችል በማመልከት ብታግዙት መልካም ይሆናል፡፡ ከዚህ ካለፈ ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.