በኦሮሚያ ባገረሸው ግጭት የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል – አለማየሁ አንበሴ

5ca

በአርሲና በምዕራብ ሃረርጌ ሰሞኑን በተነሳው ግጭት በርካታ ሰዎች እንደሞቱና እንደቆሰሉ የተገለፁ ሲሆን፤ የእርሻ ማዕከላትና የተለያዩ ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
በአምቦ ከተማም ከትናንት በስቲያ በተቃውሞ ት/ቤቶች ተዘግተው መዋላቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ በከተማዋ በሚገኘው እስር ቤት ትናንት ቃጠሎ ተነስቶ እስረኞች እንደወጡ ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል፤ ወደ ጎዳና የወጡ ተቃዋሚዎች፣ “ኦሮሚያ የኛ ናት” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደነበር ተገልጿል፡፡ የፀጥታ አካላትም ተቃውሞውን ለማስቆም አስለቃሽ ጭስ መጠቀማቸው ተነግሯል፡፡

ካለፈው አርብ ጀምሮ በምዕራብ አርሲ ሲራሮ አካባቢ የተፈጠረውን ድንገተኛ ግጭት ተከትሎ፤ በተለያዩ ከተሞች ዙሪያ ተቃውሞና ግጭት ሲከሰት ሰንብቷል፡፡ በሻሸመኔ፤ በዋቢ፣ ኤዶ፣ አሣሣ፣ ዶዶላ፣ ሻላ፣ ኮፈሌ፣ ነገሌ እና ሌሎች የአርሲ ከተሞች፣ የመግቢያ መውጪያ መንገዶችን እየዘጉ የነበሩ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡ መንግስት በግጭቶቹ ዙሪያ አሁንም ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡ 7 ፖሊሶችን ጨምሮ በግጭቱ በርካታ ሰዎች መሞታቸው፣ መጐዳታቸውና ንብረት መውደሙን ገልፆ፤ አካባቢውን እያረጋጋሁ ነው ብሏል፡፡

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ለፋና በሰጠው መግለጫ ደግሞ፤ በከተማዋ ዳርቻ ሁከትና ዝርፊያ ቢፈፀምም በቁጥጥር ስር አውለነዋል ብሏል፡፡ ከሰሞኑ ባገረሸው ግጭት ምን ያህል ጥፋት እንደደረሰ የሚገልፅ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ በአርሲና በምስራቅ ሀረርጌ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡ ቪኦኤም 12 የፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉን ጠቅሷል፡፡ ተቃውሞና ግጭቱ በተለይ ረቡዕ ዕለት ተባብሶ እንደነበር ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን፣ በኮፈሌ አቅራቢያ “ኦፈር” እና “ሴሮፍታ” የተሰኙ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ማውደማቸውን ከሰራተኞች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሻሸመኔ ከ60 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ የሚገኙት ሁለቱ የእርሻ ማዕከላት በጁቡቲ ኢንቨስትመንት የተቋቋሙ መሆናቸውን፤ የጠቆሙት ምንጮች፣ ረቡዕ ከቀኑ 8 ሰዓት የእነዚህ ማዕከላት ቢሮዎች፣ የሰራተኞች መኖሪያ ቤቶች፣ መጋዘኖች፣ ተሽከርካሪዎችና ጋራዥ ሙሉ ለሙሉ መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ግጭቱ ወደተፈጠረባቸው አካባቢዎች ዜጎቻቸው ጉዞ ከማድረግ እንዲታቀቡ አሊያም እንዲጠነቀቁ የአሜሪካ፣ የኖርዌይና የእንግሊዝ መንግሥታት አሳስበዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ሊባባስ እንደሚችል ስጋቱን የገለፀው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታና ደህንነት ዲፓርትመንት፣ ወደ አካባቢው የሚጓዙ የውጭ ዜጐች መጠንቀቅ አለባቸው ብሏል፡፡ ቀደም ሲልም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተቃውሞዎች ወደ ግጭት ማምራታቸው ያሳስበኛል ያለ ሲሆን፤ ጉዳቶችም በገለልተኛ አካላት መጣራት አለባቸው ብሏል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ ሁኔታው ያሳስበናል፤ መንግሥት ማስተር ፕላኑን መሰረዙ ጠቃሚ እርምጃ ነው” ካሉ በኋላ፤ ተቃውሞዎቹ በከተሞች ማስፋፊያ እቅድ ላይ የታጠሩ አለመሆናቸው እንገነዘባለን” ብለዋል፡፡ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ በዚህ ዓመት በተፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ በሰው ነፍስ ንብረት ዙሪያ ጉዳት መድረሱን ገልፆ፤ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመናድና ልማቱን ለማደናቀፍ የተደረገ ጥረት ነው ብሏል፡፡ ሁከቱ በህዝቡ ተሳትፎ ከሽፎ፣ መረጋጋት ተፈጥሮ ህዝቡ ወደ ልማት ስራው ተመልሷል ያለው መግለጫው፤ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ጠቁሞ ህብረተሰቡ አብሮ የመኖር ባህሉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡ ከእነዚህ ጥቅል መግለጫዎች ውጭ፤ መንግስት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ከመቆጠቡ ከመቀጠሉም በተጨማሪ፤ የመንግስት የሚዲያ ተቋማት ዝርዝር ዘገባ አላቀረቡም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.