አድዋ – “ያባከንነው ድላችን!” – ባዩልኝ አያሌው

Adwa Arbይህች ሀገር ብዙ የተከፈለባት ምድር ናት! ለውድቀቷ የተጉ የመኖራቸውን ያህል፣ ብዙዎች ሕይወታቸውን ከፍለው ለዛሬ ያበቋት ሀገር ናት፡፡… እኒህ ባለውለታዎቿ ሰው እንደመሆናቸው፣ የሰው ልጅ በዘመኑ የሚፈጽመውን ስህተት የፈጸሙ ቢሆን እንኳን፣ እናት ላሏት ኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ ከዋጋ በላይ ነው፡፡ ይህንን መካድ፣ አለማክበርና ማባከን አለመታደል ነው፡፡ ራስንም ለውርደት አሳልፎ መስጠት!

ስለዚች ሀገር ነጻነትና ክብር ብዙዎች በብዙ መልኩ ደክመዋል፡፡ መከፋታቸውን ችለውና ከራሳቸው ሀገራቸውን አስቀድመው ስለ እሷ ታትረዋል፡፡ በክፉ ቀንም አንገታቸውን ለሰይፍ፣ እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለአረር ሰጥተው ስለ ክብሯ ወድቀዋል፡፡ “የዛሬን አያድርገውና” ለኢትዮጵያውያን ስለ ሀገር ክብርና ስለ ሕዝቦች ነጻነት ሕይወትን መክፈል ታላቅነት ነበር፡፡ በዚህ አብዝታ የተመካችው ንግሥት ጣይቱ፤ አያውቀንም ላለችው የኢጣሊያ መንግሥት ወኪል አንቶኔሊ እንዲህ ነው ያለችው፡- “… የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡”
ይህች ሀገር ዛሬ ላይ የደረሰችው ብዙ ዋጋ ተከፍሎባት ነው፡፡ ከክፍያም በላይ የሕይወት ዋጋ ተከፍሎባት፡፡ በዚህም አባቶቻችን እኛን አልፎ የአፍሪካውያንን አንገት ከተደፋበት ቀና ያደረገ፣ ዓለምንም “አጃዒብ” ያሰኘ አኩሪ ገድል ፈጽመዋል። ይህ ማንም የማያብለው የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ ደረቅ ሀቅ!

ያም ሆኖ ታላላቅ ገድሎቻችንን ልናከብራቸውና ልንማርባቸው ሲገባ፣ ከንቱ እጅ እንደገባ ወርቅ ሁሉ አልባሌ ቦታ ተትተውና ቸል ተብለው ባክነዋል። ድሎቻችን ወደ ፊት መስፈንጠሪያችን ሊሆኑ ሲገባ ግብ የለሽ የቸከ ተረት አድርገናቸዋል። ድሎቹ የሰጡንን መነቃቃትና አቅም ከድርጊት ይልቅ በመተረት እናባክናለን፡፡ ለዘመናት እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ እውነቱን መቀበል ቢገደንም ቅሉ፣ እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው፡፡ ድሎቻችንን ለዘመናት አባክነናል፡፡ አሁንም ለመማር ዝግጁ አንመስልም። በዓለም የነጻነት ታሪክ ውስጥ እንደ ተአምር ከሚቆጠሩት ክስተቶች አንዱ የሆነው አንጸባራቂው የአድዋ ድልም እንዲሁ ከዚህ መባከን አላመለጠም።… አድዋ!
ስለ አድዋ ድል በየጊዜው የሚባለውን ሰብስበን እንበለው፡፡ የአድዋ ድል ነጮች የጥቁር ህዝቦች የበላይ ነን ብለው ለዓመታት ቀንበራቸውን ባጸኑበት፣ ጥቁሮችም ይህንኑ አምነው ለዘመናት በተገዙበት ዘመን ሀበሾች በነጮች ላይ የተቀዳጁት አንጸባራቂ የነጻነት ድል ነው፡፡… ይህ ክስተት የዓለምን አስተሳሰብ ቀይሮአል፡፡ እንኳንም በባርነት ቀንበር ተቀይደው የነበሩትን ጥቁሮች ቀርቶ የቅኝ አገዛዙ ተዋናዮቹን ሳይቀር እምነታቸውን አስፈትሾአል፡፡… የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ “የኢትዮጵያ ታሪክ- ከ1848 እስከ 1966” በሚል መጽሐፋቸው፣ የኢጣሊያ ጦር ደጋፊ የነበረ ጆርጅ በርክሌ የተባለ ጸሐፊ ስለ ክስተቱ የዘገበውን ይጠቅሳሉ፡-
“ከሰፊው የፖለቲካና የታሪክ ትንታኔ አኳያ የአድዋ ጦርነት በአፍሪቃ ምድር አዲስ ኃይል መነሣቱን የሚያበስር ይመስላል፡፡ የዚያች አህጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል ሊሆኑ እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል፡፡ እንዲያውም፣ አሁን ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም፣ ይህ ሁኔታ (ማለትም ዐድዋ) ጨለማይቱ አህጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሰራፋችው በአውሮጳ ላይ የምታደርገው አመፅ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነውም ተብሏል፡፡”

ይኸው ነው፡፡ የአድዋ ድል በዘመኑ ፋሽን የነበረውን የአውሮፓውያንን አፍሪካን የመቀራመት ዘመቻ ሲያጋፍሩ የነበሩትን ምሁራን ሳይቀር እንዲህ አሰኝቶአል፡፡… በአድዋ ድል፣ በቅኝ መግዛት ዛር የሚጋልቡት የአውሮፓ መንግሥታት የእፍረት ካባ ለብሰዋል፡፡ በመላው ዓለም በነጮች የእግር ብረት ሥር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ለዘመናት ካቀረቀሩበት ቀና ብለው ለነጻነት ትግል ተነስተዋል፡፡… በአድዋ ሀበሾች ማንነታቸውንና ምንነታቸውን ለዓለም አሳይተዋል። ማንም እንደፈለገ ሊጋልባቸው የማይችል “ጥቁር አናብስት” መሆናቸውን አውጀዋል፡፡…

ስለ ድሉ ታላቅነት ብዙዎች ብዙ ጽፈዋል፤ መስክረዋልም፡፡ የምንለውን የምናጣው ግን ታላቁ ድላችንን አድዋን ምን ያህል አክብረነዋል? ከድሉ ምን ተምረናል? ድሉ በዓለም ፊት ያስገኘልንን ሞገስና ክብርስ እንዴት መንዝረነዋል? ብለን ስንጠይቅ ነው። መልሱ (ቃሉ መልካም ባይሆንም) “አሳፋሪ” ነው፡፡ ከወቀሳ የማያድን፡፡…
በርካታ አደጉ የምንላቸው ሕዝቦች ዛሬ ላይ የደረሱት ድላቸውን የምር አክብረው፣ ከድላቸውና ከሽንፈታቸውም ተምረው ነው፡፡
በዚህም አተረፉ እንጂ አላጎደሉም፡፡ ከበሩ እንጂ አልተዋረዱም፡፡ ታሪክን በቅጡ ማክበር መክበር፤ ከታሪኩም መማር ብልህነት ነው፡፡ እኛ ግን እንደ ማህበረሰብ ለዚህ አልታደልንም፡፡ እናም የአድዋ ድልን የሚያህል አኩሪ ታሪክና የፈጠረልንን አቅም አባክነናል፡፡ ይህም ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ እያስከፈለንም ነው፡፡ ነገሩ ደረቅ ትችት እንዳይመስል ጥቂት አስረጂዎችን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

የአደዋ ድል የሰጠንን መነቃቃትና በዓለም ፊት የፈጠረልንን አቅም ማባከናችን ዋጋ ያስከፍለን የጀመረው ብዙም ሳይቆይ (ከአራት አሠርት ዓመታት በኋላ) ነው፡፡ በድሉ በዓለም ፊት ያገኘነውን ሞገስና የፈጠረልንን ታላቅ መነቃቃት ተጠቅመን እንደ ሀገር ወደ ፊት ባለመጣደፋችን በዳግም የጠላት ወረራ አንገታችንን ለመድፋት በቃን፡፡ ለዚህ ሽንፈት በታሪክ ተመራማሪዎች የሚነሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ያም ሆኖ በደማቁ የሚጠቀሰው በአድዋ ጊዜ የነበረንን መልከ ብዙ አቅም ማስቀጠል አለመቻላችንና ከድሉ አለመማራችን ነው፡፡…

ዓለም ይሆናልና ይደረጋል ባላለበት ዘመን፣ ከዘመኑ ኃያላን አንዱ የነበረውን ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ያንበረከክን ብንሆንም ድሉ የፈጠረልንን አቅም ተጠቅመን፣ ከድሉ ተምረንና ጉድለታችንን አርቀን አቅማችንን ማሳደግ ባለመቻላችን ራሳችንን ለዳግም ወረራ አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ በዚህም ጠላት እኛነታችን ላይ እንዲሰለጥን ሆኖአል፡፡ ይህ ፈተና እና ሽንፈት የአድዋ ድልን አቅም ባለማስቀጠላችን የደረሰብን ኪሳራ ነው፡፡

ድልን የማባከንና አቅምን ያለማስቀጠል አባዜአችን መልከ ብዙ፣ ኪሳራውም እንዲሁ ተቀጣጥሎ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አድዋ በዘመተው ጦርና ወደ ማይጨው በዘመተው ጦር መካከል ያለውን “የሕብረ ብሔራዊነት”ና የአንድነት ስሜት” ልዩነት እንዲሁም በሁለቱ ወቅቶች የነበሩትን መንግሥታት “ፍላጎትና ትኩረት” መለያየት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ለማይጨው ሽንፈት በምክንያትነት ካስቀመጡዋቸው ነጥቦች አንዷ ይህን ትላለች፡- “የኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ፍጹማዊ አገዛዝን ለመውለድ በምጥ ላይ ነበረች። ስለሆነም ከኃይለ ሥላሴ ይልቅ ምኒልክ የተባበረች ኢትዮጵያን ይዞ መዝመት ችሏል፡፡” ይኸው ነው፡፡ የዘመኑ ትጋት የነበረው ቀድሞ የተገነባውን፣ የተባበረች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ሳይሆን ፍጹማዊ አገዛዝን ለመውለድ ማማጥ ነበር፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው!
ሌላው የአድዋን ድል የማባከናችን መገለጫ፣ በየዘመናቱ አገዛዝ የነበረውና አሁንም ድረስ የቀጠለው የመንግሥታት “ከእኔ ወዲያ ኢትዮጵያን የበጃት (የሚበጃትም) የለም” የሚል “ፍጹም እኔ” ባይነት ነው፡፡ ይህም የቀደሙትን መስዋዕትነት አለማክበር፣ ከመንገዳቸውም  ያለመማር ብቻ ሳይሆን ሆን ብሎ ታሪካቸውን የማደብዘዝና የመሸሸግ ይልቁንም አሻራቸውን ጭምር አጥፍቶ ራስን ለማጉላት ካለ ፍላጎት የሚመነጭ ነው፡፡… የታሪክ ሽሚያ!

እንደ ማህበረሰብ ለዘመናት ተጣብተውን ከኖሩ ዕልፍ ሰንኮፎች አንዱ ይኸው ለቀደሙት እውቅና ያለመስጠት አባዜያችን ነው፡፡ ለማንሳት በምንገደድባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆን እንኳን የምናወሳው ስህተታቸውን ብቻ እየነቀስን ነው። ይህም የዓለማችን አስደናቂ ክስተት የሆነውን ታላቁን የአድዋ ድልን ጭምር ተገቢውን ክብርና ትኩረት ነፍገን እንድናባክነው ምክንያት ሆኖአል። (ለይምሰልና እንዳይቀር ያህል ካልሆነ በቀር) ድሉን በደማቁ መዘከር፣ የድሉን ተጋዳሊያን ማክበር፣ ይልቁንም ከድሉ ለመማር መሞከር ራስን ዝቅ ማድረግ ሆኖብን ድሉን ሸሽገነዋል፡፡ በዚህም ቀጣዩ ትውልድ ታሪኩን እንዳያውቅና እንዳያከብር እንቅፋት ሆነናል፡፡ እንዲህ ነን!
ቀደምት አባቶቹ ሕይወታቸውን ከፍለው ስለፈጸሙት አኩሪ ተግባር፣ በዚህም በደማቸው የጻፉትን አኩሪ ገድል የሚገባውን ክብር ሰጥተው ያላሳዩት የዛሬው ትውልድም፣ ሠርክ አፉን እያሰፋና ጥርሱን እየሳለ በሚጠራው ምዕራባዊ ባህል እየተዋጠ እኔነቱን ማጣቱን ቀጥሎአል፡፡ ይህም “የሀገሩ ጉዳይ የማይገደው፣ ብኩን ትውልድ” እያሰኘ ያስተቸዋል፡፡ እሱ ብቻ ያጠፋ ይመስል፡፡

መልካም ሰንበት!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.