ኢራን በአንድ መንደር የሚኖሩ አዋቂ ወንዶችን በሙሉ በስቅላት ቀጣች

excution (ሳተናው)  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸረ አደንዛዥ ዕጽ ኤጀንሲ ኢራን እጹን የሚያዘዋውሩትንና የሚያመርቱትን ለመዋጋት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ዜጎቿን በሞት መቅጣቷን እስክታቆም ድረስ ድጋፍ ማድረጉን እንዲያቆም ተጠይቋል
የኢራን የሴቶችና የቤተሰብ ጉዳዩች ተቋም ምክትል ፕሬዘዳንት ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በምትገኝ አንዲት መንደር የነበሩ አዋቂ ወንዶች በሙሉ በእጽ ዝውውር እጃቸው እንደሚገኝበት በመነገሩ የአገሪቱ መንግስት በሞት ቀጥቷቸዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣን መህር ከተባለ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግስታቸው በዕጽ አዘዋዋሪዎች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን ተከትሎ ምክትል ፕሬዘዳንቷ ሻሂንዶህት ሞላቨርዲ ኢራን ዕጽ አዘዋዋሪዎች የምትላቸውን በጅምላ በመወንጀል ብዙዎችን በሞት እየቀጣች እንደምትገኝ ለማሳየት ሲሉ በመንደሪቱ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
‹‹በሲስታንና ባሉቼስታን ወረዳዎች በሚገኙ መንደሮች የነበሩ ወንዶች በሙሉ በስቅላት ተቀጥተዋል፡፡በእነዚህ መንደሮች የሚገኙ ህጻናትም ወደፊት የወላጆቻቸውን በሞት መቀጣት ለመበቀል ሲሉ ወይም ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ሲሉ እጽ አዘዋዋሪዎች ይሆናሉ፡፡ለእነዚህ ሰዎች የሚሆን ምንም አይነት ድጋፍ የለም››ማለታቸው ተወስቷል፡፡ወይዘሮዋ ግድያው ተፈጸመባቸውን መንደሮችና ስቅላቶቹ በተመሳሳይ ቀን ወይም በተለያዩ ጊዜያት ስለመፈጸማቸው የሰጡት መረጃ የለም፡፡
እንደ ሞላቬርዲ አስተያየት ከሆነም የፕሬዘዳንት ሃሳን ሩሃኒ አስተዳደር በልማት እቅዶቹ መለጠጥ የተነሳ ለኢራናዊያን ወላጆች ያደርገው የነበረን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ አቋርጧል፡፡‹‹እነዚህን ሰዎች መደገፍ ካልቻልን ወንጀል ይስፋፋል፡፡በሞት ለተቀጡት ሰዎች ቤተሰቦች ህይወት ማህበረሰቡ ኃላፊነት አለበት የምንለውም ለዚሁ ነው››ብለዋል፡፡
አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርትም ኢራንን ከቻይና በመለጠቅ የአለማችን ሁለተኛዋ ዜጎቿን በስቅላት የምትቀጣ አገር ብሏታል፡፡በ2014 በትንሹ 753 ሰዎች ተሰቅለዋል ያለው አምንስቲ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከእጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ የተፈረደባቸው ነበሩ ብሏል፡፡በ2015 ግማሽ ዓመት ብቻ 700 ሰዎች በስቅላት መቀጣታቸውንም ‹‹አስደንጋጭ ቁጥር››በማለት ገልጾታል፡፡
የሞት ቅጣትን ለማስቀረት ንቅናቄ በማድረግ ላይ የሚገኘው ሪፕራይቭ ኢንተርናሽናል የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አባል መያ ፎ ‹‹በአንድ መንደር ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን በሙሉ በመስቅላት መቅጣት የሚያሳየው በኢራን የሚፈጸመው የሞት ቅጣት ምን ያህል አስፈሪና ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡እነዚህ የሞት ቅጣቶች የሚከናወኑትም በሟቾቹ ላይ በሚፈጸሙ ግርፋቶች፣ማሰቃየቶችና መደበኛ ባልሆኑ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እየታገዙ ነው፡፡የተባበሩት መንግስታት ዜጎቻቸውን በስቅላት በመቅጣት ላይ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር በመስራት ላይ መገኘቱም ያሳፍራል››ማለታቸውን ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
በኢራን የተባበሩት መንግስታት ልዩ ሰራተኛ ሆኑት አህመድ ሻሂድ በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝና ስቅላት ተፈጸመባቸው የተባሉትን መንደሮች አስመልክተው በሰነዘሩት አስተያየት‹‹ ሲስታንና ባሉቼስታን በኢራን ከሚገኙ ወረዳዎች ልማት ያልጎበኛቸው፣ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ድሆች የሚገኙባቸው፣የህጻናት ሞት ከፍተኛ ቁጥር ተመዘገበባቸውና ያልተማሩ ሰዎች የሚገኙባቸው ናቸው፡፡በወረዳዎቹ በአብዛኛው ከእጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በስቅላት ሲቀጡ ቆይተዋል፡፡እነዚህ ሰዎች የሚገደሉት ከአምላክ ህግ ተጻራሪ የሆነ ወንጀል ፈጽመዋል እተባሉ እንጂ መደበኛ ፍርድ ቤት ቀርበው አይደለም››ብለዋል፡፡
የአፍጋኒስታን ጎረቤት የሆነችው ኢራን ለአለማችን አደንዛዥ እጾችን ከሚያመርቱና ከሚያዘዋውሩ አገራት ዝርዝር ውስጥ በዋነኞቹ ጎራ ትገኛለች፡፡ወጣቶቿም በርካሽ ዋጋ በየትኛውም ስፍራ ሊገኙ የሚችሉ እጾችን በመጠቀም ፈተና እየጋረጡባት ይገኛሉ፡፡የአገሪቱ መንግስት በበኩሉ ሰዎችን በስቅላት በመቅጣት የእጽ ዝውውሩን ለመግታት ከሞመከር ውጪ ሌላ አማራጭ አለመፈለጉን ብዙዎች ይተቻሉ፡፡