አበባ አረጋዊ ቀጣይዋ የዶፒንግ ሰለባ ትሆን?

abeba-aregawi-tests-positive-2013-world-champion

ለስዊዲን በመሮጥ ላይ የምትገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አበባ አረጋዊ በተደረገላት የመጀመሪያ ዙር የሽንት ምርመራ አበረታች ነገር መውሰዷን የሚያሳይ ውጤት በመገኘቱ በጊዜያዊነት ከውድድር መታገዷን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የስዊዲን አትሌቲክስ ፌደሬሽን ባወጣው መግለጫም ‹‹ ይህንን መግለጫ የምናወጣው ጥልቅ በሆነ ሀዘንና ድንጋጤ ውስጥ ሆነን ነው፡፡የትኛውንም አይነት ህገ ወጥ መንገዶችንና የማታለያ ዘዴዎችን አስወግደናል፣ ይህንን የምናስተናግድበት ምንም አይነት ፍላጎት የሌለን በመሆኑ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም››ብሏል፡፡
አለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በበኩሉ ‹‹እኛና የስዊዲን አትሌቲክስ ፌደሬሽን በአትሌት አበባ አረጋዊ ላይ በላብራቶሪ ከተደረገ የሽንት ምርመራ ስለተገኘው የተከለከለ አበረታች ነገር የሚያሳይ ውጤትን መቀበላችንን እናረጋግጣለን››ማለቱ ከድረ ገጹ ተገኝቷል፡፡
የላብራቶሪውን ግኝት የሚያሳይ ማረጋገጫ ከተገኘ በኋላም አትሌቷ በፈቃደኝነት ከየትኛውም ውድድር የመጨረሻው የምርመራ ውጤት እስኪገለጽ ድረስ ማግለሏን አስታውቃለች፡፡አበባ ሁለተኛው የምርመራ ናሙና የሚኖረው ውጤት በፍጥነት ተሰርቶ ውጤቱ እንዲነገራት መጠየቋም ተሰምቷል፡፡አለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽንና የስዊዲን ፌደሬሽን ዋነኛው የምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስም በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
አበባ በ2013 በ1500 ሜትር አሜሪካዊቷን ጄኒ ሲምፕሰንን ከኋላዋ በማስከተል በ4፡02፡67 ሰዓት በማጠናቀቅ ወርቅ ማጥለቋ አይዘነጋም፡፡የአበባ ድልም አሜሪካዊቷ አትሌት በአለም ሻምፒዮን ሺፕ ለሁለተኛ ጊዜ ለማግኘት የነበራትን ህልም አጨናግፎባታል፡፡
በኢትዮጵያ የተወለደችው አበባ በ2012 የታህሳስ ወር ዜግነቷን ወደ ስዊዲን መቀየሯ ይታወቃል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.