የወልቃይት ፖለቲና ተቃዉሞ በዳባት አካባቢ – ግርማ ካሳ

welkaitየኢሕአዴግ መንግስት ላይ እየቀረበ ያለው ተቃዉሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በስሜን ጎንደር ዳባት ከተማና አካባቢ ተቃዉሞ እንደተነሳም እየሰማን ነው። ተቃዉሞው ወደ ወረዳዉና የቀበሌ መንደሮች እየተዛመተ እንደሆነ ነው ዘገባዎች የሚጠቁሙት። ዳባት ከጎንደር ከተማ በስተ ሰሜን፣ ወደ ትግራይ በሚወስደው መንገድ ላይ ያለች ከተማ ናት። በደባርቅና በአምባ ጊዮርጊስ መካከል። መረጃዎች እንደሚገልጹት ከጎንደር ወደ መቀሌ የሚወስደው መንገድ በዳባትና በደባር መካከል ተዘግቶም ነበር። በዳባት ያሉ ባለስልጣናት መካከልም ከፍተኛ መከፋፈል እንደተፈጠረ ነው። የአካባቢው ብዙ ታጣቂዎች የሕዝቡን እንቅስቃሴ በሃይል ለመጨፍለቅ ፍቃደኝነት አናሳይም እያሉም ነው። በዳባት የተጀመረው ሰላማዊ የእምቢተኝነት ተቃዉሞ በቀላሉ ወደሌሎች የጎንደር አካባቢዎች ሊዛመትም እንደሚችል የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም።
በኦሮሚያ የነበረው ተቃዉሞ፣ በአዲስ አበባ የተጀመረው የታክሲዎች የሥራ ማቆም አድማ ላይ በዳባትና ደባርቅ የተጨመረው ተቃዉሞ ሲታከልበት በርግጥም የሕወሃት አገዛዝ በሁሉም አቅጣጫዎች እየተወጠረ እንደሆነ አመላካች ነው።

የዳባት ሕዝብ ጥያቄዎች በዋናነት በመሰረታዊ የመብት ጥያቄ ላይ ያነጣጠሩ ሲሆን ወልቃይት ጠገዴና ጸለምት ቀድሞ ወደነበሩበት ክልል ወይም ክፍለ ሃገር፣ በጌምድር፣ እንዲመለሱ የሚጠይቅ ነው።

10154133_10208490347406959_4824384358424213781_nየትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች የወልቃት ጠገዴ ሕዝብ “ትግሬ ነው” ብለው ይከራከራሉ። ሰልፍ ቢጤም አይተናል። ሆኖም ራስ መንገሻ ስዩም፣ የቀድሞ የሕወሃት መስራች አቶ አረጋዊ በርሄ ጨምሮ የአካባቢዉን ታሪክ የሚያውቁ ብዙዎች ከተከዜ በስተምእራብ ያለው የወልቃይት ጠገዴ ግዛት፣ ሕወሃት በኃይል ወደ ትግራይ እስከጠቀለለበት ጊዜ ድረስ፣ በትግራይ ሥር ሆኖ እንደማያወቅ ነው የሚናገሩት። የወልቃይት ጠገዴ መሬት ለትግራይ ቅርብ ስለሆነ ለአስተዳደር እንዲያመች ነው ወደ ትግራይ የተቀላቀለው የሚል መከራከሪያ ቢያቀርቡ አንድ ነገር ነው: ግን ወልቃይት ድሮም የትግራይ ነበር ብሎ መከራከር ግን የሚያስተዛዝብ ከመሆኑንን በተጨማሪ የትም አያደርስም።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የሚወክላቸውን የወልቃይት ኮሚቴ አባላት በማሰማራት፣ ጥያቄዎችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት፣ ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲታይ ማመልከቻ ያስገባ ሲሆን፣ የአቶ አባይ ወልዱ የሕወህት አመራር ግን ሕግን አክብረው በሰላም እየተንቀሳቀሱ ያሉ የኮሚቴ አባላትን እያሰሩና እያዋከቡ ነው የሚገኙት። አልፎም በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ ንቀት ያዘለ ማስጠንቀቂያና ዛቻም ሲሰነዝሩ ይሰማሉ።

በወልቃት ጠገዴ ግዛት ብዙ ትግሬዎች ይኖራሉ። ትግሬዎች በወልቃይት ጠገዴ ብቻ ሳይሆን በተቀረዉ ጎንደር ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ለዘመናት በፍቅር፣ በሰላም የኖሩ ናቸው። በወልቃይት ጠገዴ የሚኖረው ህዝብ ሲፈልግ ጎንደር ከተማ፣ ሲፈለግ ሽሬ እየሄደ የሚነግድ ነው። ሕዝቡ አማርኛም ይናገራል፤ ትግሪኛም ይናገራል። የቋንቋ ችግር የለበትም። ቋንቋ የልዩነትና የጸብ ምክንያት ሆኖ አያውቅም። እዉነት እንነጋገር ከተባለ ጎንደሬዉና ትግሬው በጣም የተዋለደ ነው። የተዛመደ ነው።

ሆኖም ሕወሃት፣ ያልነበረ መርዛማ ዘረኝነትን ረጭቶ ለዘመናት የኖረን ሕዝብ ማቃቃር ጀመረ። “እኔ አማራ ነኝ፤ እኔ ትግሬ ነኝ” ሳይባባል በኢትዮጵያዊነቱና፣ በስብዓናው ተከባብሮ ሕዝቡ እንዳልኖረ፣ አሁን “ወልቃይቶች ትግሬ ናቸው፣ ወልቃይቶች አማራ ናቸው” እየተባለ እስከ መወዛገብ ደረጃ ተደርሷል።

የ”ማንነት፡ ፖለቲካ ብዙ አይመቸኝም። ወልቃይቶች “አማራ” ነን ሲሉ አይመቸኝም። ወልቃይቶች እኔ የማያቸው እንደ ጎንደሬ እንጂ “አማራ” አይደለም። “አማራ” የሚባል ማንነት ነበረ ብዬ አላምንም። የተወሰኑ ወገኖች “አማራ” በሚል ጆንያ ዉስጥ በሕወሃት ስለታጨቁ “አማራ” መባል ተጀመረ። ያልነበረ የ”አማራ” ማንነት ማደግ ጀመረ። የአማራ ብሄረተኝነት !!!! ወልቃይት ጠገዴዎችም “ትግሬ ናችሁ” ሲባሉ ያንን ተቃወሙ። “አማራ” ነን አሉ፡ ፖለቲካው የዘር ነዉና እነርሱም የዘር ካርድ መጫወት ጀመሩ። ወያኔዎች እ እርሱ ዘረኛ ሆነው፣ ዘረኛ ፖሊሲ በማራመዳቸው ሌላውን ሳይወድ በግዱ ወደ ዘረኝነት እንዲሄድ ገፋፉት።

“አማራ” ተኮነ፣ “ትግሬ” ተኮነ ምን የሚፈይደው ነገር አለ። “አማራ ነህ”፣ “ትግሬ ነህ” የሚለው ፖለቲክ መርዛማ ቁማርን ጨዋታ እንደ ሕዝብ ወደ ኋላ ቀርንት ከመጎተትና እርስ በርስ እንድንጠራጠር፣ እንድንፈራራ፣ እንድንጠላላ ከማድረግ ዉጭ ምን የሚቀይረው ነገር አለ ? ምንን ችግር ነበረው ትግሬ ፣ አማራ ከምንባባል በቃ ወልቃይቴ ነን በሚል በወልቃይት ነዋሪነታችን፣ ዘር ሳንመለከት እንደ ቀድሞ በፍቅር ብንኖር ?

እንግዲህ ኢትዮጵያዉያን ትግሬ እንሆን ጎንደሬ መንቃት አለብን። ወልቃይት ጠገዴ ትግራይ ዉስጥ ሆነች፣ ጎንደር ዉስጥ ተጠቃለለች ቁም ነገሩ ያ አይደለም። ቁም ነገር ሕዝቡ መብቱ ተከብሮ ይኖራል ወይ የሚለው ነው። ጥያቄው የዘር ወይንም የማንነት አይደለም፤ ጥያቄው የመብት ጥያቄ ነው።

ወልቃይት “የማንነት” ጥያቄ ያነሱት ሰብአዊ መብታቸው ስለተነፈገ ነው። የትግራይ አስተዳደር መልካም፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያው አስተዳደር ቢሆን ኖሮ፣ በኃይል ትግሪኛን በመጫን የትግሪኛ ብቻ ፖሊሲ ባይኖር ኖሮ፣ አማርኛም ከትግሪኛ ጋር የክልሉ የሥራ ቋንቋ ቢሆን ኖሮ፣ አማርኛ ልጆቻችሁን ማስተማር አትችሉም ባይባሉ ኖሮ፣ ስልጣን ከመቀሌ ወደ ዞኖች ቢወርድ ኖሮ፣ የልማት እንቅስቃሴዎች በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቦታዎች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ቢከናወኑ ኖሮ፣ ወልቃይት ጠገዴዎች ወደ ጎንደር እንቀላቀል አይሉም ነበር።

እንግዲህ ያለው ትልቁ ችግር አሁን አገዛዙ ላይ ነው። የአገዝዙ ዘረኛ ፖለቲካ ላይ ነው። በዜጎች መካከል ያለውን ታሪካዊ አንድነትና ትስስር ከማጉላት ይልቅ ዜጎችን ለመከፋፈልና ለመለያየት የሚደረገው የኋላ ቀር ፖለቲክ ነው ትልቁ ችግራችን።

ሕወሃቶች በጣም ግትሮች ናቸው። እነ አባይ ወልዱ አሁንም ያኔ ጫካ ዉስጥ የነበሩ ጊዜ እንደሚያስቡት ነው እያሰቡ ያሉት። እነርሱ መቀሌ ሆነ እየፈጸሙ ባሉትም ዘረኛ ተግባራት ሰላማዊ የትግራይ ህዝብ በሌላው እንዲጠላ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። እነርሱ ዘረኛ ሆነው ሌላው ዘረኛ እንዲሆን፣ ሌላው እልህ ውስጥ እንዲገባ፣ እንደ እነርሱ ጠባብ እንዲሆን ነው ለማድረግ እየሞከሩ ያሉት። ነገር ግን እኛ በጎንደር ያለንም ሆነ በትግራይ ወደ ቀድሞ ታሪካችን መመለስ ነው ያለብን። ወደ ፍቅርና መቀባበል ነው መመለስ ያለብን።

አንርሳ. ጎንደሬው እና ትግሬው ለዘመናት አብሮ ተፋቅሮ የኖረ ነው። የተዋለደ ነው። ጥቂት ዘረኛ ሰይጣኖች ሕዝቡን እንዲያምሱት እና እንዲያቃቅሩት ሊፈቀድላቸው አይገባም። ህወሃት፣ ይሀ መሬት የትሬ፣ ያ መሬት የኦሮሞ፣ እዚያ ማዳ ያለው የጉራጌ ይሉናል።ጨለምተኛና የኋላ ቀር አመለካከት። ወልቃይት ጠገዴ የጎንደሬው አገር ነው። ወልቃይት ጠገዴ የትግሬም አገር ነው። ወልቃይት ጠገዴ የኦሮሞዉም አገር ነው። ወልቃይት ጠገዴ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን አገር ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።አራት ነጥብ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.