የጀግኖች እናት አባቶቹን ተጋድሎ ከንቱ ያደረገ፣ የማንነቱ ጠላት የሆነው ትውልድ!

እንኳን ለ ፩፻፳ኛው ዓመት የአድዋ ድል አደረሳቹህ!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ትውልድ ብየ ስል ሙሉ ለሙሉ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር የሚፈረጀው አመዝኖ ባለው ገጽታው ነውና ጀምየ ስናገር እንዲያው አንድ ሰው ሳይቀር በጠቅላላ ማለቴ እንዳልሆነ ግንዛቤ ይወሰድ፡፡ እናም እንደምታዩት ትውልዱ “ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል” እንደሚባለው ሆነና ነገሩ እኳንና የእናት አባቶቹን ጥረት ተጋድሎ ምኞት ተረድቶ ዋጋ ሊሰጥ ይቅርና በዘቀጠ የቅስም (የሞራል) ፣ የግብረ ገብ፣ የሥነምግባር፣ ማጥ ውስጥ ሰምጦ ከጤነኛ ሰው ለማይጠበቅ ጉዳይ ዋጋ ሰጥቶ ብላሽ ነገርን እየተናገረ እናት አባቶቹ ያደረጉትን ጥረትና ተጋድሎ አምርሮ የሚኮንን ሆኖ ቁጭ ብሏል፡፡

አንዱ ማሳያዬ ትውልዱ ለጠላት ወረራዎች ያለው ዕይታና አስገራሚ ፍላጎት ነው፡፡ እናት አባቶቻችን እንደ ሰብእናው የተሟላና የተስተካከለ ሰው እንደመሆናቸው ልዕልና ባለው አስተሳሰባቸው ለነጻነታቸው፣ ለሉዓላዊነታቸው፣ ለብሔራዊ ክብራቸው፣ ለማንነታቸው ከፍተኛውን ዋጋ በመስጠት ለዚህ እሴታችን መጠበቅና መከበር የመጨረሻውን መሥዋዕትነት ከፍለው ይህችን ሀገር በነጻነትና በክብር አቆይተዋት ነበር፡፡

የዚህችን ሀገር የነጻነት ዘውድ ለመንጠቅ በማሰብ ተደጋጋሚ ጥረት ካደረጉ ጠላት ሀገራት አንዷ ጥሊያን ነች፡፡ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ “በእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አስተሳሰባቸው ለእንግሊዝ ባንዳነት አድረው ላገኙት ሥልጣናቸው እንጅ ለሀገር ሉዓላዊነት ክብርና ነጻነት ቅድሚያ የሚሰጡ ባለመሆናቸው፤ እሳቸው በሥልጣን የማይኖሩ ከሆነ ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ ጠላት ለማቆየት በማሰብ እዚያው አፍንጫው ስር ሆነው ጥሊያን እግሩን ካሳረፈበት አሰብ እያደር ባሕረ ምድርን (በኋላ ላይ ወራሪው ኃይል ኤርትራ ሲል የሠየማትን) የሀገራችን ክፍል ከፊሉን ለመቆጣጠር እንዲችል አድርገው ነበር፡፡ እነ ራስ አሉላ በዚህ የጥሊያን ወረራ በመበሳጨት ዶጋሊ ላይ ገጥመው ከባድ ጉዳት በማድረሳቸው ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ተቆጥተው ራስ አሉላን ቀጥነው ነበር፡፡ ጥሊያን የዐፄው ሁኔታ በመረዳት ካለበትም እየተስፋፋ ተጨማሪ መሬት ለመያዝ በቅቷል፡፡

ጥሊያን ባሕረምድርን እንዲህ ተንሰራፍቶባት እንዳለ ነው ደርቡሾች ለነጻነታቸው በሚያደርጉት ትግል ላይ እኒሁ ማየትና ማሰብ የተሳናቸው ዐፄው ከቅኝ ገዥ እንግሊዝ ጋር ሸርከውና አብረው ለነጻነታቸው የሚታገሉትን ጎረቤትና ወንድም ሕዝብን በመውጋት የነጻነት ትግላቸው እንዲኮላሽ፣ ደርቡሾቹ የግብጽንና የቱርክ ወራሪ ኃይልን በመደምሰስ ሊቀዳጁት የነበረውን ድል እንዲቀለበስ አድርገው ስለነበር ዐፄው ይሄንን ከባድ በደልና ግፍ ባደረሱባቸው በእነኝሁ ደርቡሾች የበቀል ጥቃት መተማ ላይ ሊሞቱ የቻሉት፡፡ ሀገራችንም በእሳቸው ብስለትና አርቆ ማሰብ በተሳነው ድርጊቶች የጎረቤት ጠላት ተተክሎብን እንዲቀር የሆነው፡፡ ዛሬ እነሱ ዞረው ገጥመው ወዳጆች ሆነዋል፡፡

ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ባሕረ ምድርን እንዲያ ባለ ጠባብ ራስ ወዳድና ሸፍጠኛ አስተሳሰባቸው እንዲያዝ በማድረጋቸው ነው በኋላ ላይ በዐፄ ምኒልክና በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጥሊያን ሀገራችንና በሕዝቧ ላይ ላደረሰችው ግፍ ጥቃት በደል ጥፋት ውድመት ወረራ ምቹ ሁኔታ እንዲያገኝ ያበቃው ያስቻለው፡፡

እናም ይህ የዐፄው ስሕተትና ክህደት ጥሊያን ባሕረምድር ላይ ሆና በመደራጀት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋ መጨረሻ ላይ ተሳክቶላት 1928ዓ.ም. ሀገራችንን ለመውረር አበቃት፡፡ እንግዲህ የዚህ ትውልድ ምክነት ዝቅጠት ልሽቀት የሚታየው በዚህ ታሪካዊ ኩነት ላይ ባለው አመለካከት ነው፡፡

ትውልዱ ወራሪው ፋሽስት ጣሊያን በአምስቱ ዓመታት ቆይታው ከአርበኞቻችን የሚደርስበትን ከባባድና አስቸጋሪ የማሰናከያ ጥቃቶችን ተቋቁሞ የሠራውን መንገድና ሕንፃ በመመልከት እናት አባቶቻችን ያንን የማሰናከያ ጥቃት መፈጸማቸውንና በከባድ መሥዋዕትነት ጣሊያንን ማባረራቸውን ይኮንናል ይቃወማል፡፡ ጥልያንን “ጥቂት ቆይቶልን ቢሆን ስንት ነገር ይገነባልን ሀገራችንን ያሳድግልን ነበር” በማለት ይቆጫል ይንገበገባል፡፡

በእውነቱ ለመናገር እንዲህ የሚያስበው የትውልዱ አካል የድንቁርና ልክ እዚህ ድረስ ነው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሲመስለኝ ትውልዱን ለእንዲህ ዓይነት ወራዳ አስተሳሰብ ለመጋለጥ ያበቃው ሥነ ልቡናው ሽባ ስለሆነ ነው፡፡ እንዴት ቢባል “እችላለሁ፤ እኔ ሠርቸ ሀገሬን መለወጥ እችላለሁ!” የሚል በራስ የመተማመን ሐሳብና ብቃት ጨርሶ የለውምና ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ በቅኝ ገዥም ቢሆን ለውጥ እንዲመጣለት ይመኛል፡፡

ሁለተኛው ድንቁርናው ደግሞ ቅኝ ገዥ መንገድና ሕንፃ ሲገነባ ለምንና ለማን እንደሚገነባ ጨርሶ አለማወቁ ነው፡፡ አለማወቁ አይደለም የሚያስገርመው ቢነገረውም የማይገባው የማይዋጥለት መሆኑ እንጅ፡፡ የሚገርማቹህ እንዲህ ብሎ የሚያስበው ትውልድ ምንም ማሰብ የማይችሉት መሀይም ወይም ካልተማሩ ከሆኑት እንደሆኑ ልትገምቱ ትችሉ ይሆናል ውጤቱ ግን ተቃራኒው ነው፡፡ እንዲህ የሚያስበው የትውልዳችን አካል ተማርኩ የሚለውና ብዙ ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት አለብኝ ከሚለው አካል መሆኑ ነው ጉዳዩን ትንግርት የሚያደርገው፡፡

እርግጥ ነው ፋሽስት በአጭር ቆይታው በርካታ መንገዶችን ገንብቶ ነበር፡፡ መንገዶቹ ሁሉ ግን የሚያመሩት ወደ ወደብ ነው፡፡ ፋሽስት ጣሊያን መንገዱን የሠራው ለእኛ አስቦ እኛን ለመጥቀም ፈልጎ ሳይሆን የመጣበትን ዓላማ ለማስፈጸም ማለትም የሀገራችንን አንጡራ ሀብት በመቦጥቦጥ በመዝረፍ እያጋዘ ወደ ሀገሩ ለመውሰድ መንገዱን መገንባት ግዴታው ስለነበረ ነው፡፡ ሐበሻን ለመጥቀም አልነበረም፡፡ አርበኞች እናት አባቶቻችንም ይሄንን ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር የመንገድ ሥራውን አጠናቆ ሀገሪቱን በመቦጥቦጥ ባዶ ቀፎዋን ጥሎ በመሔድ ተከታይ ትውልድና ሀገሪቱ ለከባድ ጉዳትና ችግር እንዳንዳረግ ምንም የሌለው ሆነን እንዳንቀር በማሰብና ሀገሪቱን ከመቦጥቦጥ ለማዳን ለመታደግ ነበር በመንገድ ሥራው ላይ አደጋ እየጣሉ ያሰናክሉ ያስተጓጉሉ የነበረው፡፡ ጥሊያን የሊማሊሞን መንገድ ይሠራ በነበረበት ወቅት ብቻ ከመሬቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ይልቅ አስመርሮት የነበረው አርበኞች የሚጥሉበት አደጋ ነው የነበረው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ በርካታ የተማረ የሰው ኃይልም አጥቶበታል፡፡

ከተሞች ላይ ጥቂት ሕንጻዎቹን መገንባቱም ሐሳቡ በአምስት ዓመቴ እባረራለሁ ሳይሆን የእረጅም ዘመን የቅኝ ግዛት አሥተዳደር እንደሚገነባ ነበርና ይሄንን የቅኝ አገዛዝ አሥተዳደር ለማሳለጥ የሚረዱትን አስፈላጊ የሕንፃ ግንባታዎች መገንባት አስፈላጊ ስለነበረ እንጅ ለሀገሪቱና ለሕዝቧ አገልግሎት እንዲሰጡ በማሰብ አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድም ሐበሻ ወደ ሕንፃዎቹ አይደለም ሕንጻዎቹ ወዳሉበት የከተሞቹ ክፍል እንኳን እንዲገባ አይፈቀድለትም ነበር፡፡

ትውልዱ ግን ካለበት ድንቁርናና የሞራል (የቅስም) ውድቀት ልሽቀት ስብራት የተነሣ ፋሺስት መሥዋዕትነት ከፍሎ የመጣው ሀገሪቱንና ሐበሻን ለመገንባት ለማልማት ለመጥቀም ይመስል የዚህን ያህል ግልጽ የሆነን ነገር ማየት መረዳት መገንዘብ ተስኖት “ምነው እንዲያው ትንሽ ቆይቶልን በሆነ ነበር” በማለት የደንቆሮ ምኞቱን ይመኛል፡፡

ጥሊያን ጥንሽ ቢቆይ ኖሮ ሀገሪቱን ምን አድርጎ ባዶ ቀፎዋን ትቶለት ይሔድ እንደነበር ፈጽሞ አያስብም፡፡ አሁን ድሀ ብንሆንም እድሜ ለውድ ለእናት አባቶቻችን ቢያንስ ያልተነካ ጥሬ የከርሰ ምድር ሀብት አለን፡፡ ይንደዚህኛው በራሱ ሳይሆን በሰው ጉልበት መልማት ማደግ መበልጸግ የሚፈልግ ሽባ ሥነ ልቡናና ድውይ ሰብእና እንዳለው የከሰረ የመከነ የጠፋ ጥገኛ ትውልድ ሳይሆን ራሱን ማሳደግ ሀገሩን መለወጥ የሚችለው እሱው እራሱ እንጅ ሌላ ማንም ሊሆን እንደማይችል የተረዳ ዐይኑን የገለጠ ብልህ አስተዋይና ጠንካራ ትውልድ ሲመጣ አውጥቶ ይጠቀምበታል ሀገሪቱን ያለማበታል ይለውጥበታል፡፡ አይ! እዚህ ላይ ግን አንድ ከባድ ችግር አለ፡፡ ይሄኛው ሽባው ጥገኛውና በራስ መተማመኑ የጠፋ ትውልድ ለሆዱ ሲል ለባዕዳኑ ሰጥቶ አስቦጥቡጦ ያስጨረሰው እንደሆነስ?

አርበኞቹ እናት አባቶቻችን አንድ የሚሉት አባባል አለ “ባሪያ ሆኘ ጮማ ከምቆርጥ ጨዋ (ነጻነት ያለው) ሆኘ ቆሎ ብቆረጥም ይሻለኛል!” ይላሉ፡፡ በእርግጥም በገዛ ሀገራቸው ላይ ለባዕድ ለወራሪ ባሪያ ሆነው ጮማ ከሚቆርጡ ነጻነት ያላቸው፣ ክብራቸው ያልተደፈረ፣ ሰብእናቸው ያልነተወረ ሆነው ከሕሊና ሰላማቸው ጋር ቆሎ ቆርጥመው ማደራቸው ሽህ ጊዜ እጥፍ ይመረጣል፡፡ ሌላም ተመሳሳይ አባባል አላቸው “ባሪያ ሆኘ በሕይዎት ከምኖር ጨዋ (ነጻ ሰው) ሆኘ ብሞት እመርጣለሁም!” ይላሉ፡፡ ይህችን ቃል በሁሉም እናት አባቶቻችን አርበኞች አንደበት ትሰሟታላቹህ፡፡ ይህች አባባል ለአምስት ዓመታቱ የረሀብ፣ የጥም፣ የእንግልት፣ የፈተና፣ የተጋድሎ፣ አርበኝነት ዘመን ጽናታቸውም ጉልበት ሰጭ የመንፈስ ምግባቸውም ነበረች፡፡ ይህች ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ሰው የመሆን ልዕልናን በሚገና የተገነዘበች አባባል ለአርበኞቻችን “ነጻነት ወይም ሞት!” የሚል የቆረጠ አቋም እንዲይዙ አስችላለች፡፡

እነኝህም አባባሎች ይሄኛው ትውልድ እንዴት እንደሚያያቸው ታሰበኝና ሳቄ መጣብኝ! ነገሩስ የሚያሳዝን የሚያስለቅስ እንጅ የሚያስቅስ አልነበረም፡፡ እነኝህ አባባሎች ለዚህኛው ትውልድ ሞኝነት፣ ቂልነት፣ ጅልነት፣ የዋህነት ናቸው፡፡ ለእሱ ብልህነት፣ ብልጠት፣ ጀግንነት ማለት ይዋረድም ይደፈርም ብቻ የትም ገብቶ ምንም ሆኖ ሆዱን መሙላት መቻሉ ብቻ ነው፡፡ ከሆዱ የሚበልጥበት ምንም ነገር የለም፡፡ ክብር፣ ሉዓላዊነት፣ ነጻነት፣ ማንነት፣ ኩራት የሚባሉ ነገሮች ፈጽሞ አይገቡትም፡፡

“የእሳት ልጅ አመድ” የሚባለው ነገር ነው በትክክል የደረሰብን፡፡ እንኳንና እንደ እናት አባቶቹ ለነጻነቱ መሥዋዕትነት ሊከፍል ለሉዓላዊነቱ፣ ለማንነቱ፣ ለክብሩ፣ ለኩራቱ ዋጋ ሊሰጥ ቀርቶ ለዚህ ሲሉ ተነግሮ የማያልቅ መሥዋዕትነት የከፈሉለትን እናት አባቶቹን እንዲህ በማድረጋቸው የሚንቅ፣ የሚወቅስ፣ የሚኮንን፣ የሚረግም ሆኗል፡፡ ለአንዲት ሀገር ከዚህ የከፋ የከበደ ኪሳራ ከየት ይመጣል? ምንስ ሊገኝ ይችላል? እንዲያው መሰለው እና ነው እንጅ የጌቶቻቸውን ፈስ ማሽተት እንደ ክብር ቆጥረውት ካልሆነ በስተቀር የትኛው ባሪያ ሕዝብ ነው ከጌቶቹ ጋር ጮማ የቆረጠው? የትኛውም ባሪያ የነበረ ሕዝብ ዕጣ ፋንታን ያየን እንደሆነ ምሬት መከራና ግፍ የተሞላ እንጅ እንደገዥዎቻቸው የድሎት አልነበረም ኑሯቸው፡፡

የዚህ ውለታ ቢስ ትውልድ ጉድና ውርደት ቢዘረዘር አያልቅምና እንዲያው ዝም ማለት ነው የሚሻለው፡፡ ብቻ እንደ እንስሳ ሆዱን ይሙሉለት እንጅ ማንም፣ የትም፣ እንዴትም ቢያሳድረው ቅንጣት ታክል ግድ አይሰጠውም፡፡ ለምን? እንዴት? ብሎ አይጠይቅም፡፡ ለሆዱ ሲል የማይሸጠው የማይለውጠው ነገር የለም! ሀገር ይሸጣል፣ ሃይማኖቱን ይለውጣል፣ ዜግነቱን ይጥላል፣ ማንነቱን ይከዳል፣ ታሪኩን ያጠፋል፣ ቅርሱን ይሸቃቅጣል ባጠቃላይ ለሆዱ ሲል ለጠላቱ ቅጥረኛ ሆኖ በራሱ ላይ በጠላትነት ለመዝመት በፍጹም ዓይኑን አያሽም፡፡ የወያኔንና የመሰሎቹን መንጎች አታዩዋቸውም? እንዲህ ከመሆን ይሰውረና ሌላ ምን ይባላል!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.