በአባይ ግድብ ውሃ መሙላት ዙሪያ ግብጻዊያን የተለያየ አቋም እያንጸባረቁ ነው

sisi(ሳተናው) ግብጻዊያን በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአባይ ግድብ ውሃ ስለሚሞላበት ሁኔታና ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ለመሙላት በያዘችው የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ስጋት ገብቷቸው ቆይተዋል፡፡የአገሪቱ ሚዲያዎችም ግድቡ ውሃ መሙላት ጀምሯል ወይም ግድቡን ውሃ የመሙላት ሂደት በቅርቡ ይጀምራል የሚሉ ዘገባዎችን ሲያስራጩ መቆየታቸውም ውዝግቡ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡
አሁን በቅርቡ ከሳታላይት የተገኘ የፎቶግራፍ ማስረጃ ኢትዮጵያ በተለይም ሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት እንዲጀምሩ ለማድረግ በማሰብ ግድቡን ውሃ ለመሙላት መዘጋጀቷን ያሳያል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ለመሙላት መዘጋጀቷን የሚገልጹ ፎቶግራፎችን በተመለከተም ከተባበሩት መንግስታት ጋር በጋራ በሚሰራው የዞኑ የህዋ ጥናት ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት አላ ኤል ናሃሪ ማብራሪያ መስጠታቸውን ካይሮ ኒውስ አትቷል፡፡
የአላ ኤል ናሃሪን ማብራሪያ በማስተባበል አስተያየታቸውን የሰጡት የግብጽ የውሃ ሃብት ሚኒስትር ሆሳም ሞጋዚ በግድቡ ላይ የሚደረገው የቴክኒክ ጥናት ተጠናቅቆ እስኪቀርብና ይሁንታ እስኪያገኝ ድረስ ሶስቱ አገራት ሱዳን፣ኢትዮጵያና ግብጽ ግድቡ ውሃ መሙላት እንደማይጀምር ስምምነት ላይ በጥር ወር ደርሰዋል ይላሉ፡፡
የሞጋዚ ማስተባበያ በበኩሉ በግብጽ የውሃ ባለሞያዎችና በቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት ተአማኒነት አላገኘም፡፡በካይሮ ዩኒቨርስቲ የውሃና የአፈር ጥበቃ ባለሞያ የሆኑት ናዳር ኑረዲን ለአል ሞኒተር በሰጡት አስተያየት አዲስ አበባ በጥቅምት ወር ኤሌክትሪክ ማምረት ትጀምራለች ይህ ደግሞ ሚኒስትሩ ከሰጡት አስተያየት ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ይሆናል ብለዋል፡፡
ሱዳን ግብጽንና ኢትዮጵያን የሚያካትተው የሶስቱ አገራት ኮሚቴ የተመሰረተው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር፡፡በቅርቡ በግድቡ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተጽእኖ ዙሪያ ሁለት ድርጅቶች ጥናት በማድረግ የደረሱበትን ድምዳሜ ከስምንት እስከ 15 ወራት ውስጥ አጠናቅቀው እንዲያቀርቡ ስምምነት መፈራረማቸው አይዘነጋም፡፡
ሃታም አዋድ የአሌክስንዴሪያ ዩኒቨርስቲ የሀይድሮሊክ ምሁር ናቸው፡፡ለአል ሞኒተር ከሳታላይት ተገኙ ተባሉ ፎቶግራፎችን በመንተራስ በሰጡት አስተያየት ‹‹ኢትዮጵያ ከጥር ወር መጨረሻ በፊት ግድቡን ውሃ መሙላት አልጀመረችም ነገር ግን አሁን የሙከራ ስራ ለመጀመር በመዘጋጀቷ በቅርቡ በውሃ ግድቡን መሙላት ትጀምራለች››ብለውታል፡፡ሃታም ውሃ መሙላት የሚጀመረው ግን ዋነኛውን ግድብ ሳይሆን ከብሉ ናይል አጠገብ የሚገኘውንና በቅርቡ በተርባይኖች አማካኝነት ኤሌክትሪክ ማምረት ይጀምራል የተባለለትን ነው ማለታቸውን ጋዜጣው አስፍሯል፡፡
በባለስልጣናቱና በምሁራኑ መካከል የተለያየ አስተያየት እየተሰጠበት ስለሚገኘው የሳታላይት የፎቶግራፍ መረጃ አልሞኒተር ጋዜጣ ማብራሪያ እንዲሰጡት በግድቦችና በአባይ ወንዝ የግብጽን መንግስት በማማከር ላይ የሚገኙትን አላ ያስን አናግሮ ነበር፡፡አማካሪው ‹‹እመኑን ለአሁኑ በግድቡ ውስጥ ምንም የተጠራቀመ ውሃ የለም››ብለዋል፡፡
ያስ ማብራሪያቸውን በመቀጠልም ‹‹ሶስቱ አገራት የተስማሙበት ጥናት እስኪቀርብ ድረስ ግድቡን ኢትዮጵያ ውሃ እንደማትሞላ ተስማምተዋል››ማለታቸውን ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የግብጽ የውሃ ሚንስትር ሙሐመድ ናስር ‹‹ይህ ምክንያታዊ አስተያየት አይደለም ››ብለዋል፡፡
ምንጭ አል ሞኒተር