አሜሪካ፤ የረሃብ አደጋው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን 20 ባለሙያ ልኬያለሁ አለች

አሜሪካ፤ የረሃብ አደጋው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን 20 ባለሙያ ልኬያለሁ አለች
• ከለጋሾች ገንዘብ ካልተገኘ፣ በግንቦት ወር የእርዳታ እህል ይሟጠጣል” ተመድ
• እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው የዓለም ሀገሮች፣ ኢትዮጵያ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች

usaበኢትዮጵያ ድርቅ ያስከተለው ከባድ የረሃብ አደጋ፣ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ለአገሪቱ ፀጥታ ጠንቅ እንዳይሆን የአሜሪካ መንግስት እንደሰጋ የዘገበው ሲኤንኤን፣ ሃያ የረድኤት ባለሙያዎችን ለመላክ እንደወሰነ ገለፀ፡፡ የተመድ የእርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በበኩሉ፣ ለግንቦትና ለሰኔ ወር የሚደርስ የእርዳታ እህል ለመግዛት ለጋሾች በፍጥነት ገንዘብ መስጠት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

በአለማቀፍ የፀረ ሽብር ዘመቻ ኢትዮጵያ የአሜሪካ አጋር መሆኗን ሲኤንኤን ጠቅሶ፣ ሀገሪቱ የክፍለ ዘመኑ ከባድ ድርቅ እንደገጠማትና በተለይ የአፋር አካባቢ ክፉኛ እንደተጐዳ ገልጿል – ትናንት ባሰራጨው ዘገባ፡፡ በአፋር ክልልና በሰሜን የአገሪቱ ክፍል፣ በድርቅ የተከሰተው የምግብ እጥረት አዝማሚያው አደገኛ እንደሆነ በባለሙያዎች ጥናት መረጋገጡን ሲኤንኤን ገልጿል፡፡ አደጋው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ለአገሪቱ ፀጥታ ጠንቅን እንዳይሆን የአሜሪካ መንግስት ይሰጋል፤ ይህንንም ለመከላከል እርዳታ እየሰጠ ነው ብሏል – ሲኤንኤን፡፡ የድርቁ አደጋ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን አሜሪካ ድጋፍ ተደርጋለች ብሏል፡፡

የአሜሪካ መንግስት የረድኤት ተቋም (ዩኤስኤይድ)፣ 20 የእርዳታ ባለሙያዎችን በተለይ ወደ አፋር ክልል ልኳል፡፡ ባለሙያዎቹ የድርቁን ጉዳት፣ የእርዳታውን ስርጭት የሚያሻሽል የቴክኒክ ምክር ይሰጣሉ ብሏል – ሲኤንኤን፡፡ ድርቅን መቋቋም የሚችሉና ቶሎ የሚደርሱ የእህል ዝርያዎችን ለማልማትም የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ 4 ሚ. ዶላር በጀት መድበናል ያሉት የዩኤስኤይድ ዳሬክተር፣ በዚህም ሩብ ሚሊዮን አባወራዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ባለሙያዎቹ፣ ሃይቲና ጃፓን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ባጋጠማቸው ወቅት የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውን ሲኤንኤን ጠቅሶ፣ ኢቦላን ለመከላከል በምዕራብ አፍሪካ አገራት እርዳታ ያበረከቱ አንጋፋ ባለሙያዎች ናቸው ብሏል፡፡

ሲኤንኤን የ4 ሚ. ዶላርና የ20 ባለሙያዎችን እርዳታ አጉልቶ ቢዘግብም፤ አሜሪካ በአንድ አመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ፣ ለድርቅ ተጎጂዎች ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ እርዳታ ሰጥታለች፡፡ ከጥቅምት ወር ወዲህ ባሉት ወራት ብቻ፣ 230 ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች፡፡ እንዲያም ሆኖ የተረጂዎች ቁጥር ብዙ ስለሆነ፣ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ የገለፀው የተባበሩት መንግስታት፤ ለጋሾች በፍጥነት ገንዘብ ካልሰጡ፣ ከግንቦት በኋላ የእርዳታ እህል ሊሟጠጥ ይችላል ብሏል፡፡
በሌላ በኩል፤ የበአለ ሲመታቸውን 3ኛ አመት ከትናንት በስቲያ ያከበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ፤ ለበአሉ አከባበር ተመድቦ የነበረውን ግማሽ ሚሊዮን ብር ለድርቁ ተጐጂዎች እንዲውል ወስነዋል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.