የዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ አጭር የህይወት ታሪክ (በየነ ተስፉ)

ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ
ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ

ከአባቱ አቶ ዳባሳይ ካሕሳይና ከናቱ ወይዘሮ መሕረታ ዓዶዑማር በ 1933 ዓ.ም. በኢሮብ ወረዳ ዋና ከተማ በዓሊተና ተወለደ። ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ እዛው ዓሊተና ከነበረው የካቶሊክ ቤተክርስትያን በውቅቱ ለልጆች ይሰጥ የነበረውን ትምህርተ ክርስቶስና ፊደል መቁጠርና ማንበብ ተማረ። ዓሊትና የነበረው የቆየው ታሪካዊው የካቶሊክ ትምህርት ቤት፣ ከጣልያን ሁለተኛ ጊዜ ወረራ በኋላ ተዘግቶ ስለነበረ፣ የመማር ከፈተኛ ፍላጎት የነበርው ተስፋይ ትምህርት መቀጠል አልቻለም። ምክንያቱም በውቅቱ መደበኛ ትምህርት የሚሰጥ የነበረው ዓዲግራት በነበረው የካቶሊክ ትምህርት ቤትና በመንግስት ደረጃ ደግሞ አግ ኣዚ መልስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ብቻ ስለነበ፣ ዓዲግራትም ከዓሊተና ሩቅ ስለነበረ፣ ወላጆቹ ገንዘብ ከፍለው እንዳያስተምሩት ደግሞ ድሆች ስለነበሩ ነበር።

ከፍተኛ የመማር ፍላጎት የነበረው የተስፋይ ምኞት ግን መና ሆኖ አልቀረም። አስመራ ሲኖሩ የነበሩ የአያቱ (የናቱ እናት እህት፣ እናቴ ጋቢሩ ዓሊ) የሚባሉ ሞኖክሴ ከአስመራ ቤተሰብ ለመጠየቅ መጥተው የተስፋይ ለትምህርት የነበረ ጉግት ከእህታቸው ሰሙና ወደ አስመራ ከመመለሳቸ በፊት ይዘዉት ወደ ዓዲግራት በመሄድ አስፈላጊውን ልብስ ገዝተው፣ የዓመት ክፍያውን ከፍለው አዲግራት የነበረው የካቶሊክ አዳሪ ትምህርትቤ አስገቡትና ህልሙ እውን ሆነ፣ እስከ 8ኛ ክፍልም ትምህርቱን በአዳሪነት እዛው ዓዲግራት ካቶሊክ ትምህርት ቤት ቀጠለ። 9ኛ ክፍል መቐለ በሚገኘው አጼ ዮሃንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረ። 10ኛ ክፍል እንደገና ወደ ዓዲግራት የካቶሊክ ትምህርትቤ ተምልሶ ተማረ።

10ኛ ክፍል እንደ ጨረሰ ለክፈተኛ የፊሎዞፊና ቲዮሎጂ ትምህርት ወደ ጣሊያን (ቫቲካን) ተለከ። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ መመራመር የሚወድ የነበረ ተስፋይ የፍልስፍና ትምህርቱን በUrbaniana Universy መማር ጀመረ። ከአርስቶትል እስከ ዘመናዊ ፈላስፋዎች ፍልስፍና በሚገባ ተከታትሎ በመጨረሳ በፍልስፍና ታሪክ የዶክተረይት መዓርጉን በከፍተኛ ወጤት አገኘ። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተስፋይን ወደ ቫቲካን ስትልከው ዓላማው ተስፋይ የተማረ የካቶሊክ ካህን እንዲሆን ነበረ። ተስፋይ ግን ከዚህ የተለየ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝቦች ከመስፍናዊ አገዛዝ ነጻ የመውጣት ዓላማ በውስጡ ይዞ ስለነበረ ክህነትን ወይድ ብሎ ሁኔታዎችን በሀገር ቤት ሆኖ ለመከታተለ የዶክተረይት ድግሪውን እንዳገኘ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በህዝቡ መካከል እየኖረ ሁኔታውን ይበልጥ ለማጥናትና ለመስራት ወሰነ።

ወደ ሀገር ቤት እንደተመለሰ በስራ ፍለጋ የሚረዳው ቤተሰብ ሆነ ጓደኛ ባይኖረውም ዶክተር ተስፋይ ከፍተኛ ዕውቀትና ችሎታ ስለነበርው ስራ ለማግኘት ብዙ አልተቸገረም። በወቅቱ በተለያዩ ሚንስቴር መስራቤቶች ኤክስፐርቶች ይፈለጉ ስለነበረ የተለያዩ መስራቤቶች ለስራ ፈላጊዎች የሚያውጡዋቸው ማስታወቂያዎች በጋዘጦች፣ በረዲዮና በተልቪዥን ይተላለፉ ስለነበረ፣ ዶክተር ተስፋይ የሚፈልገውን ስራ በማስታወቂያዎቹ አማካይነት ይከተተል ጀመረ። አገር ቤት እንደተመለሰ ብዙ ሳይቆይ በማስታወቂያ ሚንስተር በስነጽሁፍ ክፍል፣ በተመራማሪነትና ፕላንግ የሚሰራ ሰራተኛ እንደሚፈለግ የሚገልጽ ማስታወቂያ ተመለከተና በቀጥታ ለስራው ማመልከቻ አስገባ። በማመልከቻው መሰረት ለቅጥር ምርመራ ሲደረግ መርማሪዎቹ የዶክተር ተስፋይን ብቃት በቀላሉ ለማየት ስለቻሉ በቀጥታ ቀጠሩትና በማስታወቂያ ሚንስተር፣ በስነጽሁፍ ክፍል በተማራማሪነት ስራ ጀመረ። በዚህ ስራው እያለ ከተለያዩ ሚንስተር መስራቤቶች ሰራተኞች፣ የተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ በተለይ በውቅቱ የተማሪው እንቅስቃሴ ሲመሩ ከነበሩ ታዋቂ ተማሪዎች ጋራ ለመተዋውቅና የረጅም ጊዜ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥሩ ዕድል አገኘ። የስርዓቱም ቢሮክራሲ በሚገባ ለማጥናት ቻለ። ከዚህ በተጨማሪም ማታ ማታ በአባዲና ኮለጅ መኮነኖችን ፍልስፍና ያስተምር ስለነበረ ከተለያዩ ወታደራዊ መኮነኖችም ለመተዋወቅና በኋላ በደርግ የተመታው ክፍል በራሱ በደርግ ውስጥ እንዲፈጠር የተለያዩ ወታደራዊ መኮነኖች ከሰራዊቱ ለወድፊቱ ትግል ለመመልመል ጥሩ ዕድል አገኘ። በዚህ የስራ ወቅቱ ከሌሎች ተራማጅ ምሁራንና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋራ በመሆን ዶክተር ተስፋይ ከፍተኛ ቱክረት ሰጥቶት ይሰራ የነበረው ከተማሪው እንቅስቃሴ ከተለዱት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሲመሰረት የኢትዮጵያ ህዝቦች የአርነት ድርጅት (ኢህአድ) በኋላ ከ1967 ነሓሴ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ለመመስረት የሚደረግ የነበረውን ዝግጅት ጀመረ።

በ1964 ዓ.ም. መጀመሪያ በሀገር ቤት በነበረው የተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ስለ ፖለቲካ ድርጅት ኢህአድ መመስረት ስምምነት ከተደረስ በኋላ ለሚመሰረተው የፖለቲካ ድርጅት ከፍተኛ አስተዋጽ ኦ ሊያደጉ የሚችሉ በውጭ በተለይ በአውሮጳና በአመሪካ የነበሩትን የተማሪዎች ማህበራት በዚህ ድርጅት ዙሪያ ለመሰባሰብ ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ ትምህርትን አሳቦ ወደ አውሮጳ ሱዊዘርላንድ ተመለሰ። ለሁለተኛ ድግሪው የሚማረው ትምህርት እንዳለ ሆኖ ዋናው ተልእኮው ግን በኢውሮጳና አመሪካ በተለያዩ ሀገራትና እስተይትስ የነበሩ የተማሪዎች ማህበራት በፈደረሽን ማደራጀትና ማገናኘት ቀጥሎም ከነዚህ ማህበራት ለሚመሰረተው የፖለቲካ ድርጅት አባላት መመልመል ስራን ከሌሎች ጓዶቹ ጋራ ለመስራት ነበር። በውጭ በተለያዩ ሀገራት የነበሩ የተማሪዎች ማህበራት ወደ አውሮጳ የተማሪዎች ማህበርና ወደ ሞላው አመሪካ የተማሪዎች ማህበር እንዲያድጉ በተደረገው ትግል የዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ አስተዋጽኦ ከፈተኛ ነበር። እንዲሁም ከነዚህ ማህበራት የኢህአድ አባላትና ደጋፊዎች በመመልመል ስራ ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ ከፈተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከተማሪው እንቅስቃሴ በ1964 በጀርመን (በርሊን) የተወለደው ኢህአድ መስራች ጉባኤ በማዘጋጀትና በመምራት ከፈተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱትና በጉባኤው የድርጅቱ አመራር ሆነው ከተመረጡት 9ኙ አመራሮች አንዱ ሆኖም ተመረጠ።
ኢህአድ ከተመሰረተ በኋላ ለሁለተኛ ድግሪው እየሰራ እያለ የ1966ቱ ህዝባዊ ኢብዮት ተቀጣጥሎ የአፄ ኃይለስለኣሴ ስርዓት መንገዳገድ በጀመረበት ወቅት ህዝባዊ አቢዮቱን ሀገር ቤት ሆኖ መምራት የግድ ይል ስለነበረ ዶክተር ተስፋይ የሁለተኛ ድግሪው ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ሀገርቤት ተመለሰ። በስዊዘርላንድ ትምህርቱን እየተክታተለ እያለ በስዊስ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ልጅ ሚካኤል እምሩ ዶክተር ተስፋይ ጋር ጥሩ ትውውቅና ቅርበት ስለነበራቸው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ልጅ እንዳልካቸው መኮነን በንጉሱ ትዕዛዝ ጠቅላይ ሚንስተር የነበሩትን አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ እንዲተኩ በተደረገበት ወቅት የልጅ እንዳልካቸው ቦታ ተክተው ይሰሩ ስለነበርና የዶክተር ተስፋይ ወደ ሀገር ቤት መግባት ያውቁ ስለነበረ ዶክተር ተስፋይን አስጠርተው የመሬ ይዞታ ሚንስተር ሆኖ እንዲሰራ ጠየቁት። ዶክተር ተስፋይ የራሱ የተለየ ዕቅድ ስለነበረው ለተከበሩ ልጅ ሚካኤል የሚንስተሩን ቦታ እንደማይቀበለውና በትግራይ በመሬት ይዞታ ሃላፊነት ለመስራት ግን ዝግጁ መሆኑ ነገራቸው። ልጅ ሚካኤልም ጥያቄውን ተቀብለዉት በትግራይ ጠቅላይ ግዛት የመሬት ይዞታ ሃላፊ ሆኖ እንዲሰራ መደቡት። ግልጽ ስራው የመሬት ይዞታ ሃላፊ ሆኖ መስራት ሆኖ ተጨማሪ የህቡእ የኢህአድ ስራውን በግልጽ ስራው ሽፋን ማቀላጠፍ ሆነ። ከትግራይ በመነሳት ሞላው ሀገሪቷ ውስጥ በተለያየ ሰበብ እየተንቀሳቀሰ ከሌሎች ጓዶቹ ጋራ እየተገናኘ የኢህ አድ መዋቅር በሀገሪቷ ሁሉ እንዲዋቀር ከፈተኛ አስተዋጽ ኦ አበረከተ። በተለይ ደግሞ በበርሊኑ የጉባኤ ወሳኔ መሰረት በውጭ በሶሪያ በPLO ሰልጥኖ ትጥቅ ትግል ለመጀመር ትግራይ (ዓሲምባ) እንዲገባ ተወስኖ ለነበረው ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ቦታ በዓዲ ኢሮብ ሲያዘጋጁ ለነበሩ ጓዶቹ በቅርበት መመሪያ በመስጠትም ሰራ። በ1967 መጋቢት 23 ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ወደ ዓሲምባ ከገባ በኋላም ከቡድኑ ጋራ በመገናኘት፣ ትጥቅ ትግሉና የከተማው የህቡእ ትግል በማገናኘት ሰራ።

በዚህ ሁኔታና ስራው ደርግ ስልጣን ከያዘ በኋላም በልጅ ሚካኤል እምሩ በተመደበበት የመሬት ይዞታ መስሪያቤት የመግስት ደሞዝ እየውሰደ፣ የመንግስት ነበረት ሁሉ እንደልቡ እየተጠቀመ በመሬት ይዞታ ስራ ሽፋን በዋናነት የኢህ አድን ስራ እየሰራ እስከ 1967 መጨረሻ አከባቢ ቆየ። በ1967 ክረምት ላይ ከትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን 8 የሚሆኑት አንድ ላይ ከድተ ወደ ደርግ ከገቡ በኋላ፣ እነዛ ከድተው የገቡት ዶክተር ተስፋይ ደበሳይን በተለያየ ጊዜ ዓሲምባ ድረስ እየሄደ ከብርሃነ መስቀል ረዳ (የትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን መሪና የኢህ አድ አመራር አባል የነበረ) ጋራ በየጊዜው ሲያደርገው የነበረ ግኑኝነት ያቁ ስለነበረ የመሬት ይዞታ ስራው ሽፋን ተጋለጠ፣ ከዛች ዕለት ጀምሮም የመሬት ይዞታ ስራውን አቁሞ ህቡእ ኣንዲገባ ተገደደ።

ከ1967 መጨረሻ እስከ ተሰዋበት መጋቢት 15 ቀን 1969 ዓ.ም. በህቡእ ኢህ አፓን የመምራት ስራውን አዲስ አበባን ማእከሉ አድርጎ ከጓዶቹ ጋራ በመሆን ሲሰራ ቆየ። ህቡእ ከገባባት ዕለት ጀምሮ ፋሽስታዊ ደርግ ብዙ ክትትል ቢያደርግበትም ዱካዉን ለማግኘት አልቻለም ነበር። በ1968 መጨረሻዎቹ አከባቢ በኢህ አፓ ላይ በደርግ የተጀመረው የማጥፋት ዘመቻና በራሱ በድርጅቱ አመራር ወስጥ የተጀመረው የሃሳብ ልዩነት የዶክተር ተስፋይና መሰሎቹ የኢህ አፓ አመራር የህቡእ ኑሮና ስራ እጅጉን ኣያወሳሰቡት ጀመረ። በ1969 ደርግ ቀይ ሽብር በሚል በኢህ አፓ ላይ ግልጽ የማጥፋት ዘመቻ ካወጀ በኋላ ውስብስብ የነበረው ሁኔታ ኢህ አፓ ሊቆጣጠረው ከምችለው በላይ ሆነ። እጅግ ብዙ የኢህ አፓ አባልት፣ የወጣት ክንፉ የኢህ አወሊ አባልት፣ ከኢ አፓ ጋር ግኑኝነት ያልነበራቸው ንጹሃን ኢትዮጵያዊያን ባጭር ቀናት ውሽት በዚህ ቀይ ሽብር ዘመቻ በፋሽስቱ ደርግ ታጨዱ። ከኢህ አፓ አመራርም በርካቶቹ በዚህ ቀይ ሽብር ተሰዉ። በዚህ የቀይ ሽብር ዘመቻ በተጧጧፈት ወቅት ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ አዲስ አበባ ሆኖ ይህን እልቂት ይመለከት ነበር። ራሱን ማዳን ቢፈልግ ደግሞ ራሱን ለማዳን ዕድል ነበረው። ግን ይህን አልመረጠም፣ በተቻለው አቅም ለራሱ ህይወት ሳይሳሳ ማዳን የምችለውን ያህል ጓዶቹን ከእልቂቱ ለመታደግ መሯሯጠን መረጠ። በዛ ዘመቻው እጂግ ከባድ በነበረበት ዕለታትም በርካታ አባላትን ወደተለያዩ የገጠር ክፍሎች እንዲወጡና እንዲድኑ አስደረገ። በዛች ቀውጢ ወቅት በራሱ ላይ ሲደረግበት የነበረውን ክትትል ለማምለጥ እዛው አዲስ አበባ ከቦታ ቦታ በመቀያየር እየተንቀሳቀሰ እያለ በመጨረሻ በአምባሳደር ቲያትር አጠገብ ካለው በውቅቱ የኪዳነ በየነ ህንጻ እየተባለ ሲጠራ ከነበረው ህንጻ ከአንድ በሪሁን ማሪየ ከሚባል ጓዱ ጋራ ሲገቡ ሲከታተሉዋቸው በነበሩ የደርግ ገዳዮች ጓድ ማርየ ውዲያ ሲገደል ዶክተር ተስፋይ ቆሰለ። መቁሰሉን የተመለክቱ የደግር ገዳዮች እጅህን ስጥ ሲሉት ለፋሽስቶች እጄን አልሰጥም፣ ብሎ ደሙ እየፈሰሰ በሩጫ ደረጃዎቹን በመውጣት ከህንጻው 6ኛ ፎቅ ተወርውሮ በመሬት ላይ በመፈጥፈጥ መጋቢት 15 ቀን 1969 ዓ.ም. ተሰዋ።

ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ፣ ብዙ የማይናገር፣ አድማጭ፣ ሊታይ ሊታይ የማይል፣ ማንቱን በቀላሉ ልታውቀ የማትችል፣ አመራርን ራሱ አር አያ ሆኖ የሚሰጥ፣ ከራሱ በፊት የሚመራቸው የነበረ አባላትን የሚያስቀድም የተግባር ሰው መኖሩ ስለ ጓዶቹ የሚያውቀው የነበረውን ሚስጥር ላለመስጠት ወድ ህይወቱን ቤዛ ጓዶቹ የሰጠ ታላቅ ምሁርና ለኢትዮጵያ እጂግ በጣም ሲያስፈልጉዋት ከነበሩ በውቅቱ ከነበሩ ምሁራን አንዱ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ክበር ለጓድ ተስፋይና ላመኑበት ዓላማ ውድ ህይወታቸውን ለሰጡ ሰማዕታት በሙሉ!!!
በየነ ገብራይ፣ ደንማርክ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.