የክልሉ ኃላፊ በሱርማዎች ላይ ተፈፅሟል የተባለውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አስተባበሉ

12799055_10205978363479064_5243542462113344057_n

ሰሞኑን በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የሱርማ ብሄረሰብ አባላት በፖሊስ እስርና እንግልት እንደደረሰባቸው የሚያመለክቱ ፎቶዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲሰራጭ የሰነበተ ሲሆን የክልሉ መንግስት ጉዳዩን በስፋት ማጣራቱን ጠቁሞ የተባለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አለመፈፀሙን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በዞኑ ተፈፅሟል ተብሎ ሲናፈስ የነበረውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በተመለከተ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እስከ ስር አመራር ድረስ የዘለቀ ፍተሻና ግምገማ ማካሄዱን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የክልሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን፤ በተደረገው ማጣራትም መረጃው ትክክል አለመሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
“እንዲህ ያለውን ድርጊት የፈፀመ የፖሊስ አባል እንደሌለ አረጋግጠናል” ያሉት የክልሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ አርብቶ አደሮቹ ለስኳር ፕሮጀክት የመሬት ማስፋፊያ በሚል መሬታቸው መነጠቁን በመቃወማቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ ተፈፅሞባቸዋል የሚለውም ፈፅሞ ሃሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል። በዞኑ እየተሰራ ያለው የ“ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት” 85 በመቶ መጠናቀቁን በመግለፅም በአሁን ወቅት ምንም አይነት የመሬት ማስፋፋትም ሆነ የመሬት ጥያቄ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጀመር አርብቶ አደሩ ስለጉዳዩ ሰፊ ግንዛቤ እንዲይዝ መደረጉንና ለፋብሪካው ግብአት የሚሆን የአገዳ ልማት ላይ እንዲሰማራ መደረጉን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ እንደውም የመስኖም ሆነ የውሃ ተጠቃሚ ለመሆን ችሏል፤ በዚህም ህይወቱ እየተቀየረ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“የመከላከያ ኃይሉም ሆነ የክልሉ ልዩ ኃይል በተባለው ድርጊት ውስጥ አልተሳተፉም፣ የመሬት ጥያቄም አልተነሳም” ብለዋል ኃላፊዋ፡፡
የክልሉን ባለስልጣን በማናገር ይህንን ዘገባ የሰራው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ኃላፊዋን ድርጊቱ አልተፈጸመም በማለት የሚያስተባብሉ ከሆነ የተሰራጩት ፎቶግራፎች ከየት መጡ ወይም በምስሉ የሚታዩት ወታደሮች በክልሉ የተሰማሩ ስለመሆናቸው አልጠየቀም፡፡ባለስልጣኗ በደፈናው ጉዳዩን እንዲያስተባብሉ በአዲስ አድማስ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ከዘገባው መረዳት ይቻላል፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ