ሸራተን አዲስ በሠራተኞቹ ላይ እንደፈለገው መሆን እንደማይችል ቦርዱ አስታወቀ

‹‹የሠራተኞች የሥራ ውል የተቋረጠው ከኢንዱስትሪ ሰላም ጋር በተገናኘ ነው›› የሸራተን አዲስ ጠበቃ

ሸራተን አዲስ ከሥራ ያሰናበታቸው 65 ነባር ሠራተኞችን በሚመለከት የአዲስ አበባ አስተዳደር አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ሸራተን አዲስ ገንዘብ ስላለው ብቻ በሠራተኞቹ ላይ እንደፈለገው መሆን እንደማይችል አስታወቀ፡፡

sheraton-addis-01ስድስት ሰዎች የሚሰየሙበት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሥራቸው የተሰናበቱ የሠራተኛ ማኅበር አመራሮች በቃለ መሀላ ያቀረቡትን አቤቱት ከተመለከተ በኋላ በሰጠው አስተያየት፣ ሸራተን አዲስ ዓለም አቀፍ ሆቴል እንደመሆኑ፣ ማንኛውም በሆቴሉ ውስጥና የሆቴሉን ስም ተከትሎ የሚደረግ ነገር ትኩረት እንደሚስብ አውቆ፣ ሠራተኞቹን በአግባቡና በጥሩ ሁኔታ መያዝ እንደነበረበት አሳስቧል፡፡

ቦርዱ ሆቴሉን በሚመለከት አስተያየቱን የሰጠው የሥራ ውላቸው የተቋረጠው የሆቴሉ ሠራተኛ ማኅበር አባላት፣ ቀደም ብለው ከሆቴሉ ጋር እያደረጉት የነበረው የኅብረት ስምምነት ድርድር በሌሎች ሠራተኞች እንዲቀጥል ለማድረግ፣ በሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞችን ለመወከል አለመቻላቸውን በመግለጽ በማመልከታቸው ምክንያት ያቀረቡትን አቤቱታ በመመልከት ነው፡፡

የሠራተኛ ማኅበር ተመራጭ በማንኛውም መንገድ ቢሆን የኅብረት ስምምነት እያደረገ ባለበት ሁኔታ ሊባረር የሚችልበት የሕግ አግባብ እንደሌለ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 26(2)ን በመጥቀስ ሠራተኞቹ ለቦርዱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ማኅበሩና ማኔጅመንቱ በኅብረት ስምምነት ዙሪያ ሊግባቡ ባለመቻላቸው፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ለቦርዱ አቤቱታ በማቅረቡ ምክንያት ቦርዱ ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ ከሥራ በተባረሩት የማኅበሩ አባላት ምትክ ሌሎች ሠራተኞች ተወክለው ድርድሩን እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ አጠናቀው እንዲቀርቡ ማለቱን ሠራተኞቹ በአቤቱታቸው አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን የተባረሩ ሠራተኞችን ለመወከል ወደ ሆቴሉ ግቢ መግባት ባለመቻላቸው፣ የቦርዱ ትዕዛዝ ሊፈጸም አለመቻሉንም አክለዋል፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞችም ከእነሱ ጋር ከታዩ የእነሱ ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥማቸው በማሰብ ሊያገኟቸው ባለመቻላቸው፣ የኅብረት ስምምነቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው የኅብረት ስምምነት ድርድሩ እንዲቀጥል ቦርዱ እንዲወስንላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 205 መሠረት በቃለ መሀላ የቀረበውን የሠራተኞቹን አቤቱታ የተመለከተው ቦርዱ፣ የሥራ ውል ተቋረጠ ማለት የመጨረሻ ውሳኔ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ሠራተኞቹ ከሥራቸው የተባረሩበት ሁኔታ ገና በየደረጃው የሚሰጥበት ውሳኔ እንዳለ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ከሥራ የተሰናበቱት የሠራተኛ ማኅበር አመራሮች ተመልሰው ከማኔጅመንቱ ጋር ድርድር ቢያደርጉ የሚገኘው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ እንደማያዳግት በመግለጽ፣ በአሠሪው በኩልም ግን ቅን ልቦና እንደሌለ መረዳቱን አስታውቋል፡፡

ቦርዱ ቀደም ብሎ በማኅበሩ አመራሮች በኩል ቀርቦለት ለነበረው አቤቱታ የሰጠው ትዕዛዝ ባለመፈጸሙ፣ በአዋጁ መሠረት አሥር ሺሕ ብር የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ ለሸራተን አዲስ አሥር ሺሕ ብር አሥር ሳንቲም እንደሆነ አውስቷል፡፡ ቦርዱ ሕግ ስለያዘው እንጂ የሆቴሉ አካሄድ ጥሩ አለመሆኑን በመግለጽ፣ እንደ አገር ግን በጣም ሊያስብበት እንደሚገባው በማስገንዘብ፣ በጉዳዩ ላይ ቦርዱ ቀደም ብሎ ትዕዛዝ የሰጠበት በመሆኑ፣ የአስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲያየው ደብዳቤ እንደሚጽፍ አስታውቋል፡፡ በሠራተኛ ማኅበርና በማኔጅመንቱ መካከል የሚደረገው የኅብረት ስምምነት መቀጠል ስላለበትና ግዴታም ስለሆነ፣ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለውና ደረጃውን ጠብቆ ወደ ሌሎች መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ሊደርስ እንደሚችልም አስረድቷል፡፡

የሸራተን አዲስ ማኔጅመንት ተወካይ ጠበቃ በሰጡት አስተያየት፣ በተባረሩት የማኅበሩ አባላት ምትክ ተወካዮች ቀርበው በኅብረት ስምምነቱ ላይ ቢደራደሩ ማኔጅመንቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርድሩ የሁለቱንም ወገን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን የገለጹት ተወካይ ጠበቃው በማኔጅመንቱ በኩል ችግር እንደሌለ ገልጸው፣ ሥራቸው የተቋረጠ ሠራተኞች ግን የተባረሩት የኢንዱስትሪ ሰላም በመንሳት በመሆኑ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ ተባራሪ ሠራተኞችም በየቀኑ ሆቴሉ ውስጥ መግባትና መውጣት እንዲችሉ መፍቀድ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ያቀረቡት ምክንያትም፣ ‹‹እነሱ ማለት የቆሰለ አውሬ ማለት ናቸው›› የሚል ሲሆን፣ ሆቴሉ ዓለም አቀፍ በመሆኑና የደኅንነት ፍርኃትም ስላለ፣ ቦርዱ ቀን ወስኖ በተወሰነው ቀን ብቻ ሊገናኙ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ የተቀየመ ሠራተኛ ሊፈጥር የሚችለው ነገር ስለማይታወቅ ጥንቃቄ ማድረግም ተገቢ መሆኑን ተወካይ ጠበቃው ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ ቀድሞ በሰጠው ውሳኔ ላይ በድጋሚ ቢወስን በሕግ እንደሚያስጠይቀው በመግለጽ፣ ድርድሩ ግን መቀጠል እንዳለበትና የአስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲያስቀጥለው ደብዳቤ እንደሚጽፍ በድጋሚ አስታውቋል፡፡ በቅንነት መደራደር እንዳለበት ሆቴሉን በማሳሰብ ከሥራ የታገዱት ነባር ሠራተኞችም ብዙ ዓመታት የሠሩበትና ክፉ ደጉን ያሳለፉበት ሆቴል በመሆኑ፣ የማይሆን ድርጊት ይፈጽማሉ በሚል ሆቴሉ ላይ ያደረው ሥጋት ተገቢ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኙና እንዲወከሉ የተጠየቁ ሠራተኞች ለቦርዱ ቀርበው እንዳስረዱት፣ ከሥራ የተባረሩት ሠራተኞች ለስድስት ወራት ሲከራከሩበት የነበረን ጉዳይ እነሱ መከራከር አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማኅበሩ ለዓመታት ሲሠራበት የነበረውንና ሲደራደርበት የቆየውን ጉዳይ በጥልቀት አያውቁትም፡፡ ሌላው ደግሞ እንኳን ከማኔጅመንቱ ጋር ሊደራደሩ ቀርቶ ሠራተኞቹ ከተባረሩ በኋላ፣ በማኔጅመንቱ ጠቅላላ ስብሰባ ተጠርቶ በሰጡት አስተያየት በተናጠል እየተጠሩ ዋና ሥራ አስኪያጁን ይቅርታ እንዲጠይቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ማኅበር ወክለው ቢደራደሩ ደግሞ የተባረሩት ሠራተኞች ዕጣ እንደሚደርሳቸው ማሰብ የሚጠይቅ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተባረሩ የሠራተኛ ማኅበሩ አመራሮች ለቦርዱ ባቀረቡት ቅሬታ፣ የሆቴሉ ማኔጅመንት ተወካይ ጠበቃ ‹‹የቆሰሉ አውሬዎች›› በማለት ሲሳደብ ቦርዱ ዝም ማለቱ ተገቢ አለመሆኑንና በዚህ ላይ ዕርምጃ ካልወሰደ መቼ ሊወስድ እንደሚችል ሲጠይቁ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ‹‹ነገሩን በማጥበብ ተመልከቱት›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Source: Ethiopian Reporter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.