የኢሳት የሳምንቱ እንግዳ _ አቶ ሌንጮ ለታ (ግዜነው ደም መላሽ)

Lench Leta
ወደ ዋናው አርስት ከመግባቴ በፊት ለመንደርደሪያ የሚሆኑ ሁለት ነጥቦችን ላንሳ። በቅርቡ “አቤል ዋበላ” የተባለ ወንድም አራዳ ፍርድ ቤት የጏደኛውን የፍርድ ሂደት ለመከታተል በታደመመበት እርሱ ቃሊቲ በታሰረበት ወቅት  እጁን በካቴና ወደኋላ  አስሮ  ፣ ወለል ላይ እያንከባለለ ጀርባው እስኪቀደድ የገረፈውን  ፣  ሰብአዊ ክብሩን ገፎ   አካላዊና ስነ ልቦናዊ በደል የፈፀመበትን ግለሰብ አይቶት የተፈጠረበትን ስሜት “ገራፊዬን አየኹት” በሚል እርህስ ውብ አድርጎ ከትቦ አስነብቦን ነበር።ስሜቱን ለመረዳት እራስን አቤል ቦታ ላይ ማስቀመጥና ማሰብ ብቻ ነው የሚበቃው።ይህንን መሰል ከባድ ጉዳት ይቅርና በግዜአዊ  ግጭት ሀይለ ቃል የተለዋወጡትን ሰው በአጋጣሚ ፊት ለፊት መገጣጠም ስሜት የሚረብሽ ጉዳይ ነው ። አንድ እዚህ ግባ የማይባል ፍልጥ ደንቆሮ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ፀያፍ ቃላትን በአንተና በዘሮችላ ላይ እያዘነበ የቀጠቀጠህን ግለሰብ በአካል ማየት ይቅርና ስለሱ ሲወራ ብትሰማም ቁስልህ እንደ አዲስ ይጠዘጥዝኸልና ስሜቱን እረዳለሁኝ።

ዛሬ ደግሞ እኔ እንደ ኢትዮጵያዊ ሀገራችንን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ የሚበታትነውን ስርሀት ከዘረጉት ሦስት ቡድኖች የአንዱ መሪና የሀሳቡ ዋና አመንጪ የሆነውን፣ እንደ አማራነቴ ደግሞ አማራ በመሆናቸው እፃናትን፣ ፅንስ በሆዳቻው የያዙ እናቶችን፣ አረጋዊያንን በአጠቃላይ  በርካታ አማራ ወገኖችን  እንዲታረዱ፣ ከነ ሕይወታቸው ወደገደል እንዲወረወሩ ትዛዝ መስጠቱና ማስፈፀሙ  በበርካታ ወገኖች የሚታመነው ሌንጮ ለታን ኢሳት ላይ ዳግም አየሁት።በአረመኔው የኦነግ ቡድን  አረጋዊ አባትና እናታቸውን በግፍ ፣ በጠራራ ፀሀይ የተነጠቁ ልጆች፣ የሚወዷቸው ባሎቻቸው ፊትታቸው በስለት የታረዱባቸው ሚስቶች፣ የአብራክ ክፋይ፣ የአይን ማረፊያ፣ የነገ ተስፋቸውን ልጆቻቸውን እንደ እንስሳ አንገታቸውን ተቆልምመው የታረዱባቸው የአማራ ወላጆች  ይህንን እርኩስ ተግባር ፈፅሟል የተባለውን የኦነግ አበጋዝ ሌንጮ ለታን እንዲያዩና በሀዘን የቋሰለ ልባቸው (ልባችን) ዳግም እንዲመረቅዝ ተደረጎልና ስሜቱን ለሚጋሩ ወገኖች ዳግም መፅናናትና ብርታት እመኛለሁ።

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሁሌ የሚረብሹኝን የህሌና ጥያቄዎች ልሰንዝርና ወደተነሳሁበትጉዳይ እመለሳለሁ።ፖለቲካ ነክ ችግሮችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት እስከሌለ ድረስ ለነፃነት የሚደረግ የትጥቅ ትግል ይኖራል ። ይህንን በመሰለ ትግል ውስጥ ያልታጠቀው ሰላማዊ ዜጋ ላይ የሚፈፀም ወንጀል በመረጃ መደገፍ እስከቻለ ድረስ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚዳኝና የሚያስቀጣ ጉዳይ ነው። ይህንንም የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ተጠቅመውበታል።የኛ የኢትዮጵያዊያን ነገር ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ነው የማየው።አንድ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከባድ ወንጀል ፈፅሞል የሚባል የነፃነት ታጋይ መሪ ፣ ወይ ደግሞ የጨቋኝ ስርሀት አካል የነበረና ስርሀቱ ውስጥ በነበረው ስልጣን ተጠቅሞ ሕዝብ ሲበድልና ሀገር ሲዘርፍ ኖሮ በሆነ አጋጣሚ ስርሀቱን ከድቶ በአንዱ ምራባዊ ሀገር ጥገኝነት ከጠየቀ የሰራው ወንጀል ይደመሰስለትና የጀግና አቀባበል ተደርጎለት እናያለን። በዲያስፖራው ዘንድ በሚደረጉ ስብሰባዎች ፣ ሚዲያዎች ላይ ዋና ተጋባዥ ከመሆን አንስቶ እስከ መሪነት ቦታ ተሰጥቶቸው ታዝበናል። ለምሳሌ በመሰረቷቸውና በመሮቸው ቡድኖች ኢትዮጵያን ጎድተዋል፣ብዙ ኢትዮጵያዊን አስረዋል፣ገርፈዋል፣ገለዋል ዛሬ ላለንበት አጣብቂን ሁናቴ ዳርገውና በማለት ከሚነሱት ግለሰቦች መካካል መለሰ ዜናዊ ፣ ሌንጮ ለታና ኢሳያስ አፈወርቂ ግምባር ቀደሞቹ ይመስሉኛል።ከተወሰኑ ወራቶች በፊት ኢሳያስ አፍቂን የኢትይጵያ የነፃነት ታጋይ እስኪመስለን ድረስ በኢሳት ጋዜጠኞች ሞገስ ተሰጦት እንደነበር እናስታውሳለን። ይችን ሶስት ወር ደግሞ ሌንጮ ለታ ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶት ነው የሰነበተው። ከዚህ ተነስተን ስንገመም ምናልባት መለስ ዜናዊ ሞት ባይቀድመው ኖሮ የክብር እንግዳ ሆኖ የማናይበት አንዳች ምክንያት አይኖርም ነበር ማለት ይቻላል።ስለዚህ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ወንጀልና ወንጀለኛ ምን ማለት ይሆን? አንድ ሰው ይህንን አይነት ወንጀል ብፈፅም በመላው አለም በሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ዘንድ መገለል ይገጥመኛል፣ በግልም ሆን በቡድን ጥቃት ሊያደርሱብኝ ይችላሉ ፣ ተጋግዘውና መረጃ አሰባስበው ፍርድቤት ይገትሩኛል ብሎ ሊያሸማቅቀው የሚችለው እነዚህ አገር ያፈረሱና በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ከተደራደሩት ሰዎች ከፈፀሙብን ወንጀል የተለየ ምን አይነት ወንጀል ቢፈፅምብን ነዉ? ቀላል በማይባል ማሕበረሰብ ዘንድ በዚህ መልኩ የሚታወቁ ሰዎችን በመንከባከብስ ለባለተራ ባለስልጣናት የምናስተላልፈው መልክትስ ምንድን ነው? ይህንን በመሰለ አካሄድስ ወጀልን የሚፀየፍና ወንለኛን የሚዋጋ ትውልድ እንዴት ማፍራት ይቻላል? የሚሉትን መጠይቆች ለኢሳት ሰዎችም ሆና ለአምባቢ የህሌና ፍርድ እንዲሰጡ ጋብዤ ወደ ተነሳሁበት ዋና አጀንዳ እመለሳለሁ።

አቶ ሌንጮ ለታ ሰሞኑን ኢሳት እስቲዲዮ ተጋብዞ ከሲሳይ አጌና ጋር ያደረገው የፊት ለፊት ቆይታ በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ቢሆንም እኔ የታዘብኮቸውን አንድ አራት የሚሆኑ ነጥቦች እቃኛለሁ። ትኩርቴን ከሳቡት ሀሳቦች የመጀመሪያው የኦነግን የጫካ ቆይታ አስመልክቶ በተነሳ ጥያቄና በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ነው። ጥያቄው የነበረው  “ኦነግ በሕዝብ ብዛት አንፃር  ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኦሮሞን ሕዝብ እወክላለሁ የሚል ቡድን ነው ። ነገር ግን በቁጥር ሲታይ አናሳ ከሆነ ማሕበረሰብ የተውጣጣው ህውሃት ድል ሲቀናው ኦነግ ግን በትጥቅ ትግሉ ያስመዘገበው ይህ ነው የሚባል ፋይዳ የለም” የሚል ነበር። ከተሰጡት ማብራሪያ በከፊል  “ኦነግ በምስራቅ ያደርገው የነበረው የትጥቅ ትግል ሻብያና ወያኔ ሲያደርጉት ከነበረው ትግል የተለየ እንደነበር፤ የኦነግ ትጥቅ ትግሉ ከደርግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሱማሌዎችም ጋር ግጭት እንደነበርው ፣ ይህም የሆነው ሱማሌዎቹ ሐረርጌን፣ባሌን፣ሲዳሞን በሙሉ ጠቅልለው የሱማሌ አካል ለማድርግ እቅድ ስለነበራቸው እንደሆነ” ያስረዳል። በመቀጠልም ከሱማሌዎች ጋር የነበረውን ግጭት ለመፍታት በወቅቱ ፀረ ደርግ (ፀረ ኢትዮጵያ) ትግል ያደርጉ የነበሩ ለሱማሌው መንግስት እንደማያዋጣው መክረው እንዳቃታቸው ፤ሽምግልናው ላይም አንጋፋ የሻብያው አርክቴክቶች የነበሩት እነ እርመዳን ማሕመድ ኑርና ዑስማን ሳልህ ሲያድ ባሬን እንዳነጋገሩና ማሳመን እንዳልተቻለ ይገልፅልንና ሲያጠቃልል ፦

“ሱማሊያን እንድትወድም ያደረገ ያ ስህተት ነው ። መተባበር ከነበረባቸው ሀይሎች ጋር ሲጋጩ የነሱም ያቀዱት ሀሳብ  <<<ከሸፈባቸው>>> ። የኛንም ወደ ኋላ <<<እንዲጏተት (እንዲዘገይ)>>>”  አደረጉብን” ይለናል።

እዚህ ሀሳብ ላይ ሁለት ነገሮችን ማስተዋል እንችላለን። የመጀመሪያው እነዚህ ሶስት ሀይሎች (ሶማሌ፣ ሻብያ እና ኦነግ) በወቅቱ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የነበራቸው አቋም ተመሳሳይ ነበር። ይኸውም ኢትዮጵያን በታትኖ የየራሳቸውን ድርሻ መውሰድ። በሱማሌዎችና በኦነጎች መካከል የነበረው ግጭት ኢትዮጵያን ካፈረሱ በኋላ ፍራሹ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ሊፈጠር ይችላል በማለት ነበር። እዚህ ላይ ቆመን የሌንጮን “ሱማሊያን እንድትወድም ያደረገ ያ ስህተት ነው” የሚለውን የፀፀት ስሜት ስናይ ባይሳሳቱ ኖሮስ?  ብለን እንድናስብና የግለሰቡን ፊት ለፊት ከሚናገረው በስተጀርባ ያለውን ስሜቱን እንድንረዳ ያደርገናል።ሁለተኛው በስተመጨረሻ እንደዋዛ ጣል የተደረገችው “አጏተቱብን (አዘገዩብን) የምትለዋ ቃል ናት።ይህንን ሀሳብ ከቃላት ስንጠቃ አንፃር የሚወስዱ ወገኖች  እንዳሉ ብረዳም ለኔ እንደ ሌንጮ ያለ ፖለቲከኛ ቃላትን በዘፈቀደ ይገድፋሉ ብየአልወስድም።  ስለዚህ ሌንጮ “አዘገዩብን” የሚለን ምንድን ነው??  ብለን ብንፈትሽ “በእንጥልጥል” ያለው ወይም “የተጏተተው” ኦሮሞን እንገንጥል የሚለው ሀሳብ ሆኖ ነው የምናገኘው። እንደሚታዎቀው ትላንትም ሆነ ዛሬ የኦነግ አቋም ኦሮሞን መገንጠል ነው ።ዛሬ እሳቸው የሚመሩት ቡድን ደግሞ ቢያስ ከላይ “የኦሮሞ ሕዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄ በኢትዮጵያ ማህቀፍ ውስጥ ሆኖ <<ሕገ መንግስቱን እንዲተገበር በማድረግ>>> መፈታት ይቻላል” የሚል ይመስለኛል። ይህ ሆኖ ባለበት ዛሬ ላይ ቆሞ “ሱማሌዎቹ ትግላችንን “አጏተቱብን” ብሎ መብሰልሰል ምን አመጣው? ብሎ መጠየቅ ይገባል ለማለት ነው።

ሀሳቦቹ በተነሱበትን ቅደም ተከተል ለመተቸት ቀጣዩ ሀሳብ  በወቅቱ ኤርትራው ለመገንጠል ይታገል የነበረው አማፂ ሌሎችን የመገንጠል ሀሳባቸውን  እንዲቀይሩ ተፅእኖ ያደርግ ነበር የሚለው  ነጥብ ነው። ይህ ሀሳብ በአቶ ሌንጮ “በሻብያዎቹ አካባቢ የነበረው ስሜት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚል ነበር። ወያኔንም የመገንጠል አቋሙን ያስለወጠው ሻቢያ ነው”  በሚል ነው የተገለፀው።ይህ ሀሳብ እንግዲህ የዛሬውን በኤርትራ የሚደረገውን ትግል አዋጭነት ለማሳየት ታቅዶ የተወረወረ ሀሳብ ነው። ኢሳት እንደ ሚዲያ በኤርትራ በኩል ያለውን የትግል መስመር ደጋፊ እንደመሆኑና የግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር ልሳን እንደመሆኑ ነጥቡ እደሚነሳ የሚጠበቅ ነበር። ምናልባትም አቶ ሌንጮ “በአጋጣሚ አሜሪካ ለስራ ጉዳይ በሄዱበት” የኢሳት እንግዳ እንዲሆኑ የተፈለገበትም አንደኛ ምክንያት ይኸው ይመስላል።ከአቶ መለስ ጋር  እስከ ሕይዎት ፍፃሜያቸው ድረስ ግኑኝነት የነበራቸውና ይማከሩ እንደነበር የነገረን አቶ ሌንጮ መሳሪያና ቀለብ ይሰፍሩላቸው ከነበሩት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋርም ተመሳሳይ አገልግሎት አይሰጡም ለማለት አይቻልምና። ወደ ሀሳቡ ስንመለስ  ሻብያዎች በወቅቱ የሌሎችን ተገንጣዮችን አቋም ይቃወምም እንዲቀይሩ ያስገድዱም ነበር የሚለው ሀሳብ በሁለት ምክንያቶች እውነትነት ይኖረዋል። የመጀመሪያው ኤርትራ ዛሬ በምናውቃት መልኩ እንድትገነጠል በተቀሪዋ ኢትዮጵያ በኩል ሆኖ እውቅና የሚሰጥና የሚፈራረም አካል መኖርን ይጠይቃል። ሁሉም ከፈረሰ ከማን ጋር ተደራደርኩ ይባላል። ሁለተኛ ምክንያት የሚሆነው የግብፁን ጎራ ብንተወው ሻብያን ያስታጥቁ የነበሩ ምራባዊያን ደርግን መጣልና ኤርትራን ነፃ ማውጣትን እንጂ  የኢትዮጵያን መበታተን ይደግፋሉ ተብሎ አይጠበቅም።ስለዚህ ሁሉም እንገንጠል ካሉ የአለም ማሕበረሰብ ኤርትራን ጨምሮ ሁሉንም እውቅና ሊነሳቸው ይችላል። ይህንን ተራ ነገር ሻብያዎች ያጡታል ማለት አይቻልምና የሌሎችን መገንጠል ይቃወሙ ነበር የሚለው እውነታ አለው።ይህ ማለት ግን ዛሬም ተመሳሳይ አቋም አላቸው ወደሚል ድምዳሜ አያደርስም።ዛሬን ዛሬ ላይ ቆመን ነው የምንገመግመው።የኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ ለኤርትራ ምን ማለት ነው?  ፣ኤርትራ እንደነ ተስፋየ ገ/አብ አይነት ሰላዮችን አሰማራ እየሰራች ያለችው ስራ የኢትዮጵያን አንድነት ከሚፈልግ ወዳጅ ሀገር የሚጠበቅ ነው ወይ?  ለበርካታ አመታት ኤርትራ ውስጥ የመሸጉት አማፅያን ምን ምን ድሎችን አስመዘገቡ?  እና በርካታ መሰል መጠይቆችን እያነሳን የምናሰላስለው ጉዳይ ነው የሚሆነው።

ሶስተኛ የማነሳው ሀሳብ በሽግግር መንግስት ወቅት በህውሃትና በኦነግ መካከል በነበረው ድርድር የአቶ ሌንጮ ቡድን ይዞት ነበር የተባለውን አቋም ነው።እንደ ግለሰቡ አቀራረብ “በሽግግሩ ወቅት የስልጣን ድልድል በሚደረግበት ሰሀት እኛን ያስጨንቀንና ትኩረት ሰጥተን እንሰራው የነበረው የክልል አከላለል ጉዳይ እንጂ የስልጣን ሽሚያውን አልነበረም” ነው የተባለው።

በግሌ መለሰ ዜናዊ በስልጣን በቆየባቸው ግዜዎች ሁሉ አንድም ቦታ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለኢትዮጵያ ዘብ ቆሟል የሚል እምነት የለኝም። ስለዚህ ያደረጋቸውን ፀረ ኢትዮጵያ ድርጊቶች በኤርትራዊ ደሙ ነው ብየ ነው የማምነው።ነገር ግን በሽግግሩ ወቅት መለስ እንደ አንድ የትግራይ ሰው ኢትዮጵያዊ ሆኖ ነው ይደራደር የነበረው ከተባለ በኦነጉ ሌንጮ ለታ በፖለቲካ ተበልጦ እንደነበር ነው የምረዳው።ለዚህ አስተየት በሽግግሩ ወቅት “ኢትዮጵያን አፄ ምኒሊክ የመሰረቶት የመቶ አመት ታሪክ ብቻ ያላት ሀገር ናት” ተብሎ ይካሄድ የነበረው ፕሮፖጋንዳ ጠቀሜታነት የነበረው ለማን ነበር ብለን ማየት ብቻ በቂ ይሆናል። ከሶስት ሺህ በላይ ታሪክ ያላትን አገር ታሪኮን  ወደ መቶ ዝቅ እንዲል የተደረገው የትግል መሰረቱን ከጣልያን ቅኝ መገዛት ጋር ለሚያያይዘው ሻብያና  ዘፍጥረትን ከሚኒሊክ ንግስና ጋር ለሚጀምረው ኦነግ  ተብሎ እንጂ  ለትግራይ  አንዳች የሚጠቅመው ነገር ያለ አይመስለኝም። የትግሬ ታሪክ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር አብሮ ወደ ኋላ የሚለጠጥ ስለሆነ ይህንን መሰል የታሪክ አቀራረብ ህውሃቶች እንወክለዋለን ለሚሉት ማሕበረሰብ የሚዋጥ አይሆንምና ። ውጤቱንም  ስናይ ኤርትራ ሁለት ወደቦችን ይዛ እንድትገነጠል ሲሆን ፣ ኦነግም “ምኒሊክ በሀይል አስገብረውት ነው እንጅ ከመቶ አመት በፊት ኦሮሞ የሰፈረበት መሬት ነበር” በማለት ዛሬ “ኦሮሚያ”  ብለው የከለሉት የኢትዮጵያ ግዛት የኦሮሞ ሀገር ብቻ ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ ጥለዋል።

እዚጋ ህውሃት እንዴት በፖለቲካ ተበለጠ ይባላል? ስልጣኑን በሙሉ ጠቅልሎ በመውሰድ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በስልጣኑ ሙሉ ተጠቃሚ ሆኖል አይደል? የሚል ሀሳብ ሊነሳ ችላል።እውነት ነው።ለግዜው ስናየው እንደዛ ሊመስለን ይችላል ። ዛሬ ያለው ካትግራይ የበቀለው ቡድን አይኑን ጨፍኖ፣ ሕሌናውን ዘግቶ አይን ያወጣ ዘረፉ እያካሄደና በመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ግፍ እየፈፀመ ነው። ካባቶቹ ያልወረሰውን የጎንደርና የወሎ መሬት በማናለብኝነት እየቆረሰ ፣ ባለርስቶችን እያፈናቀለ፣ ዘር ማጥፋት ላይ ተሰማርቶል። እወክለዋለሁ ከሚለው ብሔር ውጭ ያሉት ብሔሮች ነገ ተጠናክረው እንዳይገዳደሩኝ በሚል ስሌ በሕዝቦች መካከል ጠላትነት እንዲነግስ፣እንዳይተባበሩ ፣እንዳይተማመኑ ሌት ተቀን እንደ ትል ሳያንቀላፋ እየታተረ ነው።መጠጊያና መደበቂያ እንዲያጡም የገዛ መሬታቸውን ለባእዳን አገራት እየሰጠና እየሸጠ ወዳጅ ለማፍራት እየተሮሮጠ ነው።ይህ ሁሉ ደረቅ ወንጀል ግን ግዜአዊ ነው።መጭውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድባብ ስንታዘብ ጉዳዩ በዚህ የሚቀጥል አይመስልም። ዛሬ ላይ የተደረሰበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንኮን ብናይ “ኦሮሚያ” የተባለውን ክልል ከህዉሃት ግልፅና ቀጥተኛ ከሆነ ዘረፋ የሚያስጥል ትልቅና ወሳኝ እርምጃ ተወስዶበታል። እንደምገምተው ከዚህ በኋላ እዛ መንደር የገዢዎች ወገን ነኝና ያሻኝን እዘርፋለሁ፣የተመኘሁትን መሬት ነባር ሕዝብና አፈናቅየ እሸጣለሁ ወይም ለዘሮቸ አከፋፍላለሁ፣ ያይኑ ቀለም ያላመረኝን አስራለሁና እገድላለሁ የሚል ድፍረት አይኖርም።”ኦሮሚያ” ከአሁን በኋላ በስርሀቱ ተማምነው ይቦርቁ ለነበሩ ግለሰቦች አስፈሪ ድባብ ያላትና የሰቀቀን ሕይዎት የሚገባት ክልል ወደ መሆን ተሸጋግራለች። ከኦሮሞ ውጭ ላሉ ሕዝቦች ቀድሞውንም ያው ነበርች ። ለዚህም የራሳቸው የህውሃቶቹ ሙሉ ድጋፍ ነበረበት ። “ማነህ ባለተራ ማነህ ባለሳምን” ነው ዛሬ።።ነገ ከነገወዲያ ደግሞ በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ክስተት እንደሚፈጠር ምንም ጥርጥር አይኖርም።

እንደኔ ዛሬ የህውሃትን ዘራፊ ቡድን በማህከላዊው ኢትዮጵያ የሚፈፅመውን ዝርፊያ በመሀል አዲስ አበባ ብቻ እንዲዎሰን ያስገደደውና “ልክ እንዲገባ” ያደረገው ድርጊት ቀደሞ ያልታሰበበትና በዘፈቀደ የተፈጠረ ነው የሚል ካለ እነ ሌንጮ ከሃያ አመት በፊት የቀረፁትን ሕገ መንግስት ምንነት ያልተረዳ ብቻ መሆን አለበት። የሆነውን በአጭሩ ለመቃኘት ሌንጮና ጎዶቹ በድል አጥቢያ የጥይት ድምፅ ሳያሰሙ የሽግግሩ ዋና ተዋናኝ እንዲሆኑ ተጋበዙ። ኤርትራ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ሁኔታ እንድትገነጠል ተባብረሩ። ለዚህ ውለታቸውም  በህልማቸው ሲያልሙት የኖሩትን የኢትዮጵያ መሬት ለራሳቻው ሕዝብ ብቻ በሚሆንበት መንገድ እንዲከልሉ ከሻብያ(መለስንም ይጨምራል)  ይሁንታን አገኙና ከለሉ። ህልማቸውን ተፈፃሚ ሊያደርግ የሚችል “ሕገ መንግስት” ቀርፀው እንዳገባባቸው አንዲትም የጥይት ድምፅ ሳያሰሙ ሹልክ ብለው ወጡ። በመጀመሪያቹ የስልጣን አመታት ህውሃት ሻብያን በኢትዮጵያ ሕዝብና ሀብት ላይ እንደልቡ እንዲቦርቅ ፈቅዶለት  እንደነበር ሁሉ ኦነግም ህውሃትን ያሻውን እንዲያደርግ ነበር ለቆለት የወጣው።ህውሃት በአንፃራዊነት አናሳ ቁጥር ካላው የተውጣጣ ወንጀለኛ ቡድን እንደመሆኑ አዲስ አበባን በቅርብ እርቀት ከቦ የሚገኘው የኦሮሞ ማሕበረሰብ አንድ ቀን በቃኸን ብሎ እንደሚነሳበት መገመቱ ቀላል ነበር።

እንደሚታወቀው የህውሃት የመጨረሻው ግቡ ከትግራይ ውጭ ያሉትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሀብትና ንብረት ዘርፎ “ታላቋን ትግራይ” መመስረት ነው። ይህ ደግሞ ዘር ማጥፋትን ጨምሮ በርካታ ደረቅ ወንጀሎችን መስራት የግድ እንደሚል እንኮን ፖለቲከኛው ሌንጮ ማንም የሚረዳው ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ላለፉት ሁለት አስት አመታት እንደታዘብው ህውሃት የነገዋ “ታላቋ ትግራይ ዘላቂ ሰላም” በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝች መካከል በሚፈጠር ዘላቂ ጠላትነት ላይ ነው ብሎ የሚያስብ ቡድን ነው። ለዚህም በተቀሩት የኢትዮያ ሕዝቦች መካከል ልዩነቶችን እያጎላና ሕዝብን ከሕዝብ እያናከሰ ወደ አንቀፅ 39 የሚወደውን መንገድ ጠረጋ አንዱና ዋናው የሂደቱ አካል ነውና የትግራይን መገንጠል የኦሮሞ ሀገርን ለመመስረት ለተነሱት ኦነጎች  በረከት ይዞ ዳግም እንደሚጋብዛቸው  ቀደም ብለው ቢተነብዩ የሚጠበቅ ነገር ነው።ስለዚህ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ያገኙትን ስልጣን ይዘው የግፉ አካል ከመሆን  ትላንት የሻብያዎቹ ገረድና ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆን የኢትዮጵያን ወደብ አሳልፎ የሰጠው ፣ ዛሬ ከባእድ ጎረቤት ሀገር ጋር አብሮ ድንበራችንን ቆርሶ ለመስጠት ጫፍ የደረሰው ፣ በአገርና በሕዝብ ላይ ለሚፈፅመው ክህደት አቻ የማይገኝለት፣ቅንታት ታህል ጥበብና ይሉኝታ ያልፈጠረበት፣ ሙትቻውን ህውሃት መንገዱን እንዲጠርግ ማድረግ። በመጨረሻም በሻብያ ተሸርቦ ኢትዮጵያን በዘርና በቋንቋ እንዲበታትን ተደርጎ የተተከለዉንና ሌንጮ “እኔ ነኝ ዋናው የሀሳቡ አመንጪው” ያለንን “ሕገ መንግስት” ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ይዋልን የምትል ውብ  “የዲሞክራሲ ጥያቄ” ይዞ መቅረብና ህልምን እውን ማድረግ ነው አላማው ። እየተሳካም ይመስላል።

በመጨረሻ የማነሳው በሌንጮ ቡድንም ሆነ በተቀሩት የኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባን አስመልክቶ እየተነሳ ስላለው ጉዳይ ይሆናል። እንደሚታወቀው “ማስተር ፕላኑን” ተከትሎ በኦሮሞ ማሕበረሰብ ዘድ የተደረገው ተቋውሞ ገዢው መንግስት ፕላኑን ሰርዠዋለሁ ካለ በኋላ ጥቄው እየተለጠጠ መጥቶል። በተቋውሞው ምክንያት የታሰሩ፣ አካላቸው የጎደለ፣ ንብረታቸው የወደመ እንዲሁም ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች በመኖራቸው ተጨማሪ ጥያቄች እንደሚነሱ የሚጠበቅ ነገር ነው።እንግዲህ ከላይ ከተዘረዘሩትንና ተመሳሳይ አግባብነት ከላቸው የዲሞክራሲ ጥያቄዎቻ ጎን ለጎን አንድ የሚገርምና መሰረተ ቢስ የሆነ ጥያቄ ከፊት መስመር ቀድሞና ደምቆ እየወጣ እንዳለ እያየን ነው። “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ትደረግ” የሚለው ጥያቄ። ይህ ጥያቄ አቶ ሌንጮ ዛሬ የሚመሩት ድርጅትን ጨምሮ በበርካታ ኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደ ዋና አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሎል።“ብረትን መቀጥቀት እንደጋለ” እንዲሉ አበው የኦሮሞ ሕዝብ ጭቆናና መገፉት ይብቃን ብሎ የወሰደው እርምጃ ህውሃትን አብረክርኮታልና ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም እንደ ሌንጮ ያሉ ብልጣ ብልጥ ፓለቲከኞች ሌላ ተጨማሪ የፓለቲካ ትርፍ ሊያገኙበት ድርድር ላይ ናቸው።የቅሚያና የዝርፊያ ዘመን ላይ ሆነንና ስለ ሀገር ታሪክ መተንተን፣የአባትን አጥቢያ መሻት ሰሚ ጆሮ ያጣበት ወቅት ሆነና ላለፉት 25 ዓመታት ሲደረግ የነበረው ዛሬም የማይሆንበት ነገር የለም።ሲጀመርም ዛሬ ያለውን ሕገ መንግስት የቀረፁትም ሆነ ለሕዝቦች የክልል አጥር ያበጁት በጂኦግራፊ የማይገናኙ (በመካከላቸው የድንበር ይገባኛል ችግር የሌለባቸው)፣ ዋና ጠላታችን የአማራ ሕዝብን ነው ብለው የተነሱና ጠላታቸንም ለማጥት እስከ አሁኖ ሰሀት ድረስ ጠንክረው እየሰሩ ያሉ ፣ መገንጠልን የትግላቸው ዋና ምሰሶ አድርገው የታገሉ ቡድኖች ናቸው።ለማንኛም ሀሳቡን ለማንሳት ያህል ኢትዮጵያን በዘር መቀራመት ከመጣ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የመአከላዊ የኢትዮጵያ ታሪክ በሰፊው የሚታወቅ በመሆኑ ያንን እዚህ ማንሳት ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል። ከላይ የጠቀስኩት የኢትዮጵያን ታሪክ ከአፄ ምኒሊክ የግዛት ማስመለስ ጋር የማስተሳሰሩ ዋናው ግብም ይኸዉ ነበር።ለማንኛውም አዲስ አበባ በቋንቋ ፣በባህል፣ነዋሪዎቾ ባላቸው ስነ ልቦና ፣በታሪክ ሲታይ የኦሮሞ ዞን የሚያደርጋት አንዳች ነገር የለም።ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ  ከ95 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ከተማ ፣የአፍሪካ ህብረት ዋና መዲና፣ የተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ ፣ኢትዮዽያ ውስጥ ዛሬ ካሉት ክልሎች ወደ 40 ፐርሰንት ከሚጠጉት ክልሎች በላይ የሕዝብ ቁጥርና ስብጥር ያላትን አዲስ አበባ የኦሮሞ አንድ ዞን ትሁን ብሎ ሀሳብ ማንሳት በራሱ አስቂኝና አሳፋሪም ነው።ቢሆንም ግን ይህ እንዳሆን ለመከላል የሚያስችል ጉልበት መፍጠር አልተቻለምና በቅንጅትን ወቅት ተነስቶ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ አዲስ አበባን “የኦሮሚያ” ዋና መቀመጫ እንድትሆን እንደተደረገ ሁሉ ዛሬም “የኦሮሚያ” አንድ ዞን ትሁን አትሁን የሚለው ጉዳይ በነዛው ቡድኖች እጅ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት አጣብቂኝ ሁናቴ እኔ እንደመፍትሄ የሚታየኝን ሀሳብ ላንሳና ሀሳቤን ልሰብስብ።ሁሉም ወገን እንደሚስማማበት ኢትዮጵያ ዛሬ አደጋ ላይ ናት። ዘርን መሰረት አድርጎ ለ25ዓመታት በተሰራው ፀያፍ ፕሮፖጋንዳ “እኛ”ና “እነሱ” የሚል አስተሳሰብ ተፈጥሮል ። ተጠንቶና ታስቦበት በሕዝቦች መካከል እንዲፈጠር በተደረገ ጥላቻ መተማመንና መተባበር እንዳይኖር ተደርጎል። የአብሮነቱን ታሪክን በማንቋሸስና በመበረዝ መቀራረብን ፣መተሳሰርን፣መፋቀርን ያመጣሉ የሚባሉ ሕዝባዊ ባህሎችና ልምዶችን ፣ የአብሮነት የትግል ውሎዎች፣ የወል የድል ባህላትን ትኩረት እንዳይሰጣቸው በማድረግ ለመጪው ትውልድ እንዳይተላለፋ ፣ እንዲከስም እየተደረገ ብሔራዊ ስሜት እንዲጠፋ ተደርጎልም እየተደረገም ነው።ይህንንም ተከትሎ ሀገራዊ አጀንዳ ይዘው የሚነሱ የፓለቲካ ቡድኖች በዋናነት በገዢው ፖርቲ አልፍ አልፎም ሰርገው በሚገቡ ብሔርተኞች በቀላሉ እንዲከስሙ ሲደረግ ዘርና ቋንቋን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ፖርቲዎች በአንፃራዊነት እየጎለበቱና ተፅእኖ ፈጣሪ እየሆን መምጣታቸውን እያየን ነው።ይህ መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው። እኔ በግል እስከማውቀው ድረስ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ብሔርን መሰረት አድርጎ ተቋቁሞ በገዢው ፓርቲ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት እንዲጠፋና አባላቱም ለሞትና ለእስራት የተዳረጉበት ፖርቲ ካለ የፕ/ር አስራቱ መአድ ብቻ ነው።

በኔ አመለካከት በመንግስ ሙሉ ድጋፍ የሚደረግለት ዘርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ብሔርተኝነት ባለበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ጎጣዊ አደረጃጀቱን መንግስ ቀጥተኛ ድጋፍ የማይሰጠው ሆኖ በዘር ላይ በተመሰረተ ፖርቲና በብሔራዊ ፖርቲ መካከል አቻ ትግል ቢደረግ አሸናፊነቱ የሚያመዝነው ወደ ዘርን መሰረት ወዳደረገው ፖርቲ ነው።ብሔራዊ ፖርቲዎች ሁሉን አሳታፊ በመሆናቸው ለሰርጎ ገቦች አመች ናቸውና ሚስጥራቸውን ለመጠበቅ ይቸገራሉ።በታሪካችንም የምናየው ይህንኑ ነው።ደርግ ብሔራዊ መንግስት ነበር።ታግለው የገፈተሩትና ዛሬ ሁለት መንግስት ያቋቋሙት ደግሞ ዘርና ቋንቋን መሰረት አድርገው የተደራጁ ቡድኖች ናቸው።ደርግ ለመውደቁ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱና ዋናው በመረጃ መበለጡ ነበር። በሁለቱም ወገን ትግሬዎችና ኦሮሞዎች በመኖራቸው የመረጃው ፍሰት ወደ ጎጣዊ ቡድን ያመዝናል።ተፈጥሮአዊም ነው። እንደሚታወቀው የደርጉ ቡድን የመጀመሪያውን ደም ያፈሰሰውና በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ አይንህን ላፈር የተባለው ጠቅላይ ሚ/ር አክሊሉ ሀብተ ወልድንና ጎዶቻቸውን በረሸነበት ወቅት ነው። ፕ/ር መስፍን ከአሻራ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለመጠየቅ ይህንን ጉዳይ አስመልክተው እንደገለፁት “የባለስልጣናቱን ጉዳይ እንዲዳኝ በተቋቋመው መርማሪ ኮሚሲዮኑ ዉስጥ ደርግ ባለስልጣናቱን እንዲረሽን ይገፋፉ ከነበሩት ግለሰቦች “መሰሪ” ብለው የጠቀሶቸው የኦነግ መስራቹ ባሮ ቱምሳና ሻብያ በረከተ አብ ወልደስላሴ” ነበሩበት። ጎጠኞቹ ይህንን መሰለ አሻጥር በመስራት ብሔራዊ ቡድን የነበረውን ደርግ እጁን በደም እንዲጨማለቅና ከሕዝብ እንዲነጠል አድርገው ወደ ጎጣቸው ኮበለሉ።ሌሎችንም ተመሳሳይ ክስተቶች ብንፈትሽ የተለዩ አሆኑም።

ስለዚህም “እኛ”ና “እነሱ” የሚለው አመለካከት ገዢ በሆነበትና የብሔራዊው (የአንደነቱ) ቡድን እየተዳከመ በመጣበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው ? የሚለውን ጉዳይ ስንመረምር “እሳትን በሳት” ወደሚል ጥግ እንደርሳለን።ሁሉም እንደሚስማማበት ዛሬ በኢትዮጵያ አንድ ብሔር ያለ እስከሚመስል ድርስ ተጠናክሮ የሚገኘውና መንግስትን እየተገዳደረ ያለው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነው።በሀገርም ሆነ በውጭ የሚገኙ ሚድያዎችን ተቆጣጥረው ያሉት የኦሮሞ ፖለቲከኞች ናቸው።በኢትዮጵያ ከሚገኙት ሕዝቦች ዉስጥ መበደሉ፣መገፋቱ ጎልቶ እተሰማ ያለውና የአለም አቀፍ እውቅና የተሰጠውም ይሄኛው ወገን ብቻ ነው ብል ማጋነን አይሆንም።እንደተቀሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች መገፋቱ ፣ መበደሉ እውነት ነውና ለመብቱ መታገሉ የሚደገፍና የሚመሰገን ሆኖ እያለ ብቻውን ጎልቶ መውጣቱ ግን ከኢትዮጵያ መፃሂ እድልና ከሌሎች ሕዝቦች እጣ ፋንታ ጋር ስንመረምረው አሉታዊነት ሊኖረውም ይችላል።

ህውሃት አናሳ ቁጥር ካለው ሕዝብ የተውጣጣ፣ ለኢትዮጵያ ፀር የሆነ ብሔርተኛ ቡድን ነው።ከኦሮሞ ፖለቲከኞችም አገራዊ አጀንዳ አንግበው ሳይሆን አዲስ አገር መመስረትን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ቀላል የማይባሉ ሀይሎች አሉ።በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሁለቱ ቡድኖች ብቻ እየጠነከሩ መምጣት ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለው ጭቆናና ግፍ በማንኛውም አካል የሚቀሰቀሱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ህውሃትን ባስደነበሩት ቁጥር እንቅስቃሴውን ለማፈን ድርድሩ በነዚህ ቡድኖች መካከልና ሁለቱ ቡድኖችን ብቻ በሚጠቅም ላይ ነው የሚሆነው። ይህን መሰል ክስተቶችን ደግሞ ደጋግመን ታዝበናል ። ለምሳሌ ከላይ እንደጠቀስኩት 97 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅ ሕብረ ብሔራዊ መሰረት የነበረው ቢሆንም እንዲኮላሽ የተደረገው በዋናነት በህውሃት የሀይል እርምጃ ሲሆን በወቅቱ ቅንጅትን “በነፍጠኝነት” ፈርጆ ትልግሉን ላለመደገፍ በኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች የተወሰደው አቋም ቀላል የማይባል ሚና ተጫዉቷል።ውጤቱም የሞተው ሞቶ የታሰረው ታስሮ አዲስ አበባን “የኦሮሞ” ዋና መቀመጫ አድርጎ ነው የተደመደመው።የሰሞኑንም እንቅስቃሴ ብንወስድም ኢሳትን ጨምሮ  በውጪ የሚገኘው ማህበረሰብ እንቅስቃሴዉን ከሰባዊ መብት አንፃር በማየት “ማስተር ፕላኑን”  ለማስቀረትና የኦሮሞ ወገኖችን ድምፅ ለማሰማት  ከፍተኛ አስተዋፅሆ አርጎ ነበር።”ማስተር ፕላኑ” በተሰረዘ ማግስት ግን ኦሮሞ ፖለቲከኞት አጀንዳውን ወደ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዞን መሆን አለባት”፣ “ኦሮሚያ የኦሮሞ ብቻ”  እንደሆነችና፣ ኦሮሚያ ዉስጥ የሚኖረው ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንደ ኬንያዊና ቻይናዊ ናቸው የሚሉ አግላይ ድምፆችና መግለጫዎች መሰማት ጀመሩ።ስለዚህ ይህንን መሰል ክስተት ሊገዳደርና ሊያሰቀር የሚችል ፣ሰፊ ዕራይ ያለው ነገር ግን ብሔርን መሰረት አድርጎ የተደራጀ ጠንካራ አካል መምጣት አለበት ብየ ነው የማምነው።ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ላይ ያለው  አሰላለፍ ይኸው በመሆኑ ጉዳዩን በብሔሮች መካከል እንደሚደረግ ገመድ ጉተታ አርጎ መውሰድ ይቻላል።ይህ ማለት ሳይዘገይ አዲሱና ጠንካራ ብሔርተኛ ቡድን ተቋቁሞ ፣ የመደራደር አቅም አጎልብቶ ገመዱን በተቃራኒው በኩል መጎተትና ወደ መሀል ማምጣት   (counter balance)  ማድረግ ይኖርበታል።ይህንን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ተመሳሳይ ሁኔታወች በተከሰቱ ቁጥር ዛሬ ተበታትነው ድምፃቸው የታፈኑ ሕዝቦች  ወደ ጠነከረው ሀይል መጎተታቸው ብቻ ሳይሆን ይህ ዛሬ ያለው ከፍተኛ የሀይል አለመመጣጠን የሚፈጥረው የስባት ፍጥነት(inertia) ሌሎችን ክፋኛየመጨፍለቅ አቅም ይኖረዋል።ይህንን እውነታ ሊታደግና እራሱንም ሆነ ሌሎችን ማዳን የሚችለው ብሔር ደግሞ አማራ ነው።የአማራ በብሔርተኝነት መሰባሰብና መደራጀት ግዜ ሊሰጠው የማገባ ጉዳይ ነው።

ቸር እንሰንብት!!!

E-mail

gizdemelash@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.